የውጤት ማሽቆልቆል ተግዳሮቶች

የትምህርት ጉዳይ የማያንኳኳው ቤት፣ የማይመለከተው አካል የለም፡፡ ወላጆች ልጆቻቸውን ለማስተማር እና ከፍተኛ ደረጃ ላይ ለማድረስ ይጥራሉ፡፡ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች በቀለም ትምህርት ታንጸውና በሥነ-ምግባር ተኮትኩተው እንዲወጡ ይሠራሉ፡፡

ሆኖም አሁንም የትምህርት ጥራት ችግር ፈተና ሆኗል፡፡ በኢትዮጵያ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የፖሊሲና የትምህርት ፍኖተ ካርታ ሥርዓት ማሻሻያዎች ተደርገዋል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት ለረጅም ጊዜ የቆየው የተማሪዎች የፈተና አስተዳደር ሥርዓት ለውጥ ተደርጓል፡፡

የፈተና አስተዳደር ለውጡ ከዚህ ቀደም በ10ኛ ክፍል ይሰጥ የነበረውን የሀገር አቀፍ ፈተና በማስቀረት፤ የ12ተኛ ክፍል ዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ተማሪዎችን ወደ አንድ ማዕከል በማምጣት በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንዲወስዱ ተደርጓል፡፡ ሆኖም አሁንም የትምህርት ጥራትና የፈተና ውጤት ጉዳይ አነጋጋሪ እየሆነ ነው፡፡

የፈተና አስተዳደር ለውጡ ከተካሄደ በኋላ የ12ተኛ ክፍል ተማሪዎች ውጤት እጅጉን አሽቆልቁሎ እና ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ ተማሪዎች ቁጥር አነስተኛ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰው ሀብት ልማት ሥራ ስምሪት፣ ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የ2016 የትምህርት ሚኒስቴርን አፈጻጸም በገመገመበት ወቅት የ12ተኛ ክፍል ተማሪዎች ብሔራዊ ፈተና ውጤት ማሽቆልቆል መንስኤ ጥናት ተደርጎ እንዲቀርብ መጠየቁ ይታወሳል፡፡

የትምህርት ሚኒስቴርም የተማሪዎች ውጤት ማሽቆልቆልን አስመልክቶ መንስኤውን የሚዳስስ ጥናት በገለልተኛ አካል እንዲጠና በማድረግ ሰሞኑን ለቋሚ ኮሚቴው አቅርቧል፡፡ ቋሚ ኮሚቴውም የጥናቱን ሪፖርት በማዳመጥ በጉዳዩ ላይ ውይይት አድርጓል። ጥናቱን ያቀረቡት በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ፕሮግራምና ጥራት ማሻሻያ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዮሐንስ ዎጋሶ (ዶ/ር)፤ ጥናቱ ከዚህ ቀደም በትምህርት ዘርፍ እንደሀገር የተደረጉ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ተማሪዎች የነበራቸውን ውጤት በንጽጽር አቅርቧል ይላሉ፡፡

በጥናቱ ላይ የትምህርት ቤት አመራሮች፣ ተማሪዎች፣ መምህራን፣ ወላጆች ያካተተ ሲሆን የትግራይ ክልልን ሳይጨምር በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ የመንግሥትና የግል ትምህርት ቤቶች ተደራሽ ማድረጉን ጠቅሰዋል ፡፡

በጥናቱ መሠረትም የ8ተኛ ክፍል የተማሪዎች ውጤት 50 በመቶ የሚያመጡ ተማሪዎች ውጤት እየቀነሰ መምጣቱን ያሳያል፡፡ ጥናቱ 50 በመቶ ውጤት የሚያመጡ ተማሪዎች ውጤት በእጅጉ መቀነሱን እና ይህ ውጤት በክልሎች ላይ በስፋት እንደሚታይ ተገልጿል፡፡

በጥናቱ ከተመላከቱ ግኝቶች የፈተና አስተዳደር ለውጥ ድንገት መደረጉ በአብዛኛው ተማሪዎች ዘንድ ለቦታው አዲስ መሆን የፈጠረባቸው የሥነ-ልቦና ጫና እንደ ምክንያትነት ተነስቷል፡፡ በትምህርት ቤቶች ውስጥ የተማሪዎች እና የመምህራን ጥምረት አነስተኛ መሆን ሌላኛው ሲሆን በክፍል ውስጥ የሚማሩ ተማሪዎች ቁጥር መብዛት የማስተማር ሥነ-ዘዴው ላይ ጫና ማሳደሩን ጥናቱ አመላክቷል፡፡

ሌላኛው ተከታታይነት የሌለው የምዘና ሥርዓት፣ ፍኖተ ካርታው የሚሸፍነው የትምህርት ዘርፍ በርካታ መሆን፣ ተማሪዎች አንድ የትምህርት ዓይነት ሳይጨርሱ ወደ ሌላኛው ክፍል መሸጋገር፣ የትምህርት ቀናት መሸራረፍ፣ የመምህራን ተነሳሽነት ማነስ በጥናቱ ላይ የቀረቡ ችግሮች መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡

ጥናቱ ለተማሪዎች ውጤት ማሽቆልቆል የመፍትሔ ሀሳቦችንም አስቀምጧል፡፡ ለተማሪዎች ልዩ የማካካሻ የማጠናከሪያ ትምህርት በንቅናቄ ደረጃ መስጠት፣ በገጠር የሚገኙ የአርሶ አደርና የአርብቶ አደር አካባቢዎች ላይ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች በልዩ ሁኔታ መመልከት፣ የትምህርት አመራር አቅምን ግንባታ ላይ ትኩረት መስጠት እንደ መፍትሔ የተቀመጡ ሃሳቦች መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴውም ከጥናቱ በመነሳት ተከታታይ ጥናቶች በየክልሉ በጥልቀት እንዲደረግ፣ የመምህራን የማስተማር አቅምን ማሳደግ እንደሚገባና የመምህራንን ሕይወት ማሻሻል እንደሚገባ፣ የሚገነቡ ትምህርት ቤቶች ከቁጥር ባሻገር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ጨምሮ ያላቸው ጥራት እንዲፈተሽ እንዲሁም ወላጆች ለልጆቻቸው ትምህርት ጉዳይ ድርሻ እንዳላቸው ተጠቁሟል፡፡

የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ከቋሚ ኮሚቴው ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽም በፈተና አስተዳደር ሥርዓት ከትምህርት ጥራት ጋር በተያያዘ የነበሩ ችግሮች በይፋ የታዩበት ነው፡፡ ከፈተና ስርቆት ጋር በተያያዘም ይሠሩ የነበሩ ኢ-ሞራላዊ ድርጊቶች በዚህ የፈተና አስተዳደር እንዲቋረጡ መደረጋቸው አንዱ የውጤት ማሽቆልቆል መንስኤ መሆኑን ገልጸዋል። በፈተና ስርቆት የሚሳተፉት ተማሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ወላጆች፣ መምህራን፣ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች መሆኑን ተናግረዋል። ይህንን ችግር መቅረፍ የወላጆች እና የሁሉም ማኅበረሰብ ኃላፊነት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የመምህራንን ሕይወት ማሻሻል ተገቢ መሆኑን ያነሱት ፕሮፌሰሩ፤ ለዚህም የመምህራን ባንክን ለማቋቋም በሂደት ላይ ነው፡፡ ይህም መምህራን ሕይወታቸውን ለማሻሻል የሚረዳ ነው፡፡ የባንኩ ምስረታም በቀጣዩ ዓመት ተግባራዊ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ የትምህርት ጥራት ችግር መኖሩን ያነሱት ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ አገልግሎት የተሰኘ አዲስ አሠራር በ2019 ዓ.ም እንደሚጀመር ገልጸዋል፡፡ ይህም ተማሪዎች ከመመረቃቸው አንድ ዓመት አስቀድመው ወደ ተለያዩ ቦታዎች በመሄድ ለአንድ ዓመት ያክል በማስተማር ኅብረተሰባቸውን እንዲያገለግሉ የሚያስችል መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን መጋቢት 27 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You