ተናፋቂዋ ባለ ቅኔ

“መቼ ነው?

ዛሬ ነው? ነገ ነው?

ድምጿን የምንሰማው?”

የእርሷን ሙዚቃ ያጣጣሙ ሁሉ ዘወትር የሚሉት ይህንን ነው። ብዙዎች ያንን መረዋ ድምጽ፣ የአዕዋፍ ዝማሬ የመሰለውን ዜማ ለመስማት ናፍቀዋል። እንደ ሰሊሆም ወንዝ ልብን የሚያረሰርሱትን፣ እንደ ዓባይ ጅረት ፈሰው የማያልቁት የግጥም ቅኔዎቿ በጆሮ ሲንቆረቆሩ ለማድመጥ፣ በልብ የቋመጡ እጅግ በርካታ የሙዚቃ አፍቃሪያን ናቸው። ጂጂ ወዴት ናት? ጂጂ የት ነሽ? የስንቱን የሙዚቃ ጥም ቆርጠሽ፣ የኢትዮጵያን ሙዚቃ በዓለም አደባባይ ከፍ አድርገሽ ስታበቂ፤ አንቺ ፀሐይ ወዴት ገባሽ?…

“ፀሐይ ውጪ ውጪ

ፀሐይ ውጪ ውጪ

ደማቅ ብርሃንሽን

ለምድሪቷ ስጪ”

በመድረክና በሌላው ወዲህ ብትታይም፤ እስካሁን አልበሟን ለመጨረሻ ጊዜ የለቀቀችው በ2002ዓ.ም ነበር። ድንገት የውሃ ሽታ ስትሆን፣ በመሃል ለዓመታት ዝምታ ሰፍኖ ነበር። በዚህ ዝምታ ውስጥ ተጨንቆ የመፈለጋት አነበረም። ምክንያቱም፤ ዕለት ዕለት የምናስታውሳቸው ብዙ ዕውቅ ድምጻውያን፣ ድምጻቸውን አጥፍተው ለሁለትና ለሦስት ዓመታት ያህል ይሰወራሉ። መሰወራቸው የሽሽት ሳይሆን፣ ያስለመዱትን ወይንም ከዚያ በላይ የሆነ ሥራ ይዞ ለመምጣት እንደ ሱባኤ ባለ የጥበብ ዋሻ ስለሚገቡ ነው። ጂጂ የግሏን ሰባት አልበሞች ስታከታትል፣ ከአንዱ ወደ ሌላ ለመምጣት ቢበዛ ከ3 ዓመታት በላይ ዘግይታ አታውቅም ነበር።

የሙዚቃ አፍቃሪና አድናቂዎቿም ሦስትና አራት ዓመታት ቢጠባበቋትም ብቅ ሳትል ቀረች። እንዲያ ባለው የሃሳብ ተስፋ፤ ከአሁን አሁን፣ ከዓመት ዓመት ትመጣለች እያለ ደጅ ደጇን ቢያማትርም እስካሁንም የለችም። አንዳንዶችም “እጅጋየሁን ያያችሁ” ቀሪውም “አላየንም ባካችሁ” ተባብለው ያፈላልጓት ጀመሩ። እርሷም እንዲህ ነኝ፣ እንዲያ ነኝ ሳትል በዝምታ ዝም ብላ ብቻ ጠፋች። ጂጂ ይህን ያህል ጊዜ፣ በደህናዋ ለእነዚህ ሁሉ ዓመታት ከሙዚቃ ርቃ ልትኖር በፍጹም አይቻላትምና ደህና ባትሆን ነው ብለው ጠረጠሩ።

“ፀሐይ” አንቺ ፀሐይ…በ1989ዓ.ም ይህንን የመጀመሪያ አልበሟን ካስደመጠችበት ጊዜ አንስቶ፣ እልፎች በሙዚቃ ሥራዎቿ ፍቅር ወደቁ። ከዚያን ጊዜ አንስቶ ዛሬም ድረስ እርሷን ከማንም ጋር ማነጻጸር የማይፈልጉም ብዙ ናቸው። በልባቸው ዙፋን ላይ ያነገሷትን ንግሥት ሽረው ቦታውን በሌላ ለመተካት አልተቻላቸውም። ከሙዚቃ ርቃ፣ ከዓይን ተሰውራ ጠፍታ ከቀረች ብዙ ዓመታት ቢቆጠሩም፤ ትመጣለች፣ ዳግም ዙፋኑን ታድሰዋለች ብለው ይጠብቋታል። ፀሐይ በአመሻሹ ጀንበር ትጠልቅ ይሆናል፣ በምሽቱ ጭለማ ውስጥም ብቅ ብላ አትታይ ይሆናል፣ ክረምትም ይሁን በጋ፤ ሌቱ ሲነጋጋ በማለዳው ናፍቆ የሚጠብቃት ግን ብዙ ነው። በማለዳዋ ጀንበር ዝናብ አሊያም ደመና ቢሆን፤ አረፋፍዳ በረፋዱ ወይንም ከቀትር ላይ ብቅ ማለቷ አይቀርም ሲል አሁንም በተስፋ ይጠባበቃታል።

እጅጋየሁ ሽባባውን ያበቀለች የአገው ምድር፣ የቻግኒዋ ስጋዲስ የምትለው ምን ይሆን…ዳግም እርሷን ለመመልከት እንደምን ላትናፍቅ ኖሯል። “ውሃ አጃሪ… ውሃ ኩሉ…” እያደመጠች መብሰልሰሏ አይቀርም። የጂጂና የቻግኒ ትውውቅ በ1975ዓ.ም የጥቅምት ወር ላይ ይጀምራል። በዚሁ ዓመት፣ በዚሁ ወር ላይ ተወልዳ፤ ከእናቷ ጡት በፊት በአፏ የማገቸውና ወደ ውስጧ የገባው የመጀመሪያው ነገር የቻግኒ አየር ነው። ከውስጧ የተነፈሰችው የመጀሪያው ነገርም ይሄው እስትንፋስ የሆናትን አየር ነው። የሰው ልጅ በትውልድ ሀገሩ ፍቅር የሚወድቀው፣ ከእትብቱ መቀበር በላይ ወደውስጡ ባስገባት እስትንፋሱ ነው። ጂጂና ቻግኒም ከዚህም በላይ የሚመስል ውስጣዊ ትስስር አላቸው።

ሀሁ…አቡጊዳ…ጥበብ…ሄውዞ…ልጅነት በቻግኒ ከሁሉም ስፍራ ቦረቀችበት። ከመንደር ጓደኞቿ ጋር ተያይዛ፣ አስኳላን ፍለጋ ወደ ትምህርት ቤት ትሮጣለች። ከወዲህ ለአቡነ ዘ ሰማያት ስተከንፍ ከሰንበት ቤተ ክህነት ትደርሳለች። በዚያው ፍጥነት ጂጂ ዳዊት እስከመድገም ተጋች። የምትኖረው ኢትዮጵያዊነትና ጥበብ ከሚነፍስበት ቤተሰብ ጋር ነውና ኢትዮጵያዊውን ጥበብ ትቦርቅበት ነበር። ከእናት እስከ እህትና ሌሎችም የቤተሰቡ አባላት ከአንገታቸው የጥበብን ማህተብ ያሰሩ ናቸው። መላው ቤተሰቡ ተሰብስቦ የሚመለከተው የጂጂን ትርዒት ነው። ትዘፍናለች፣ በእስክስታ ትውረገረጋለች። ግጥም ታነባለች፣ ትሸልልና ትፎክራለች። “ኦቴሎ” የተሰኘውን የሼክስፒርን ቲያትር፣ ሁሉንም ገጸ ባህሪያት እየሆነች ትተውንላቸዋለች። ሁሉ ነገር የሚሆንላትና የሚያምርባት ፍልቅልቅ ጸአዳ ልጅ የሰጣቸውን አምላክ እያመሠገኑ፣ በሳቅ በስሜት ይመለከቷታል፡፡

የ15 ዓመት እንቦቅላ ሳለች፤ ደህና ሁኚ ቻግኒ ስትል በልብ እንባ ተሰናብታት አዲስ አበባ ገባች። ለጂጂ ግን የአዲስ አበባ እቅፍም ቢሆን የሚጎረብጥ የሚቀዘቅዝ አነበረም። የአዲስ አበባዋን ሴንት ሜሪ ትምህርት ቤት ስትቀላቀል የሙዚቃ ፍቅሯ ያነሆልላት ጀመረ። በዚሁ ምክንያት የትምህርቷን ነገር ወደጎን ብላ፣ ደብተር አንጠልጥሎ መሄዱም ጠፋት። ቀሪ እያበዛች ብታስቸግር መክረው ዘክረው አልሆን ቢላቸው ከትምህርት ቤቱ ተባረረች። የሙዚቃ ፍቅሯ ምን ቢያንሰፈስፋት፣ ያለ ትምህርት መጓዙን አልወደደችውምና እንደገና የማታ ትምህርት ጀመረች። አሁንም ግን ብዙም ሳትዘልቅበት ሌላ አጋጣሚ ተፈጠረ። በመሃል ባገኘችው አንድ አጋጣሚ ለቤተሰቦቿ እንኳን ሳትናገር ሾልካ ኬንያ ገባች።

በቃላት የምታሽሞነሙናትን ኢትዮጵያን ጥላ የኬንያን ምድር ስትረግጥ ጂጂ ያኔም ገና ልጅ ነበረች። ልጅነቷ ግን እንደ ትልቅ ሰው ከመኖር አላገዳትም ነበር። እዚያ ከደረሰች በኋላ ካደረገቻቸው ነገሮች አንደኛው አዲስ አበባ ላይ ያቆመችውን ትምህርቷን መቀጠል ነበር። ቢሆንም ግን፤ እንድትጀምረው እንጂ እንድትጨርሰው ያልወደደ ይመስል አሁንም አልሆንልሽ አላት። ውስጧ ያለው ጉራማይሌ ጥበብ እንደ እንቦሳ እየዘለለ አላስቆም አላስቀምጥ አላት። ለዚህ ለሚቦርቅባት የሙዚቃ ፍቅር አውጥታና አውርዳ በስተመጨረሻ አንድ የሙዚቃ ባንድ ልታቋቁምለት ቻለች። ኬንያ ላይ ከምታውቃቸው ኢትዮጵያውያን ሙዚቀኞችን አሰባስባ፣ ሌላ ሁለት የታንዛኒያ እና የዛየር ሙዚቀኞቹን አክላ “ባቲ” የሚል ባንድ አቋቋመች። የባንዱ ዋነኛ የሙዚቃ አደባባይም “ቦውሊንግ ግሪን” የተሰኘው ሆቴል ነበር። በሆቴሉ ውስጥ የሙዚቃ ሥራዎቻቸውን ማቅረብ ሲጀመሩ፣ ተወዳጅና ዝነኛ እየሆኑ ሄዱ። በምትጀምራቸው አስደሳች ጉዞዎች መካከል መሰናክል የማያጣት ጂጂ እዚህም ፊቷ ተደነቀረ።

“ባንዱን የሠራሁት እኔ ነኝ። …እኛ ዓለማችን ሙዚቃ ነበር። እነርሱ ግን የፖለቲካ መጠቀሚያ ሊያደርጉት ፈለጉ” ስትል ከውጪ ዓይናቸውን ባንዱ ላይ ጥለው የነበሩ ሰዎች እንደነበሩ ትናገራለች። በዚህ ዓይነት ሁኔታ ለመቀጠል አስፈላጊ አነበረምና ባንዱ ሥራውን አቁሞ፣ አባላቱም ተበታተኑ። ከባንዱ መፍረስ በኋላም የሙዚቃ ፍቅሯ ለመፍረስ ቀርቶ ለመሸራረፍ እንኳን አልቃጣውም። እናም አንድ የካሴት ሥራ ለመሥራት ወሰነች። ለካሴቱ የሚሆኑ ሙዚቃዎቿን አሰናድታ ስታበቃ አቀናብርልሻለሁ ላላት የሙዚቃ ባለሙያ ገንዘቧን ቆጥራ አስረከበችው። አቀናባሪው ግን ብሯን ከበላ በኋላ የገባበት ጠፋ። ብታፈላልገውም ሰውየው የውሃ ሽታ ሆኖ ቀረ። ይህን ጊዜ ግን ሀገርን ያስመኛል፤ ማን እንደ ሀገር ብላ ወዲያው ወደ እናት ሀገሯ ተመለሰች። ፀሐይ…ፀሐይ…ብርሃን የምትረጭ የማለዳ ፀሐይ፣ እያሳሳቀች ልብን የምታቃጥል የቀትር ፀሐይ…ጂጂና “ፀሐይ” የተሰኘችው የበኩር አልበሟ እንዲህ ተያያዙ።

ጂጂንና የኢትዮጵያን የሙዚቃ አድማጭ ያገናኘችው “ፀሐይ” የተሰኘችው የበኩር አልበሟ ነበረች። ማልዳ የወጣችው የጠዋት ፀሐይ፣ ጅማሬዋ ለጂጂ የቀትር ወላፈን ነበር። ኋላ ልብ አርስ መሆኑ ላይቀር፤ መውጫዋ ቁር ሀሩር ሆነ። እጅጋየሁ ሽባባው የአሁኑን ዓይነት የራሷ የሆነውን የሙዚቃ ጥበብ ያገኘችው ገና ከዚህ አልበም መውጣት በፊት ነበር። እናም የምናውቃቸውን እኚያን ግጥሞቿን ጽፋ፣ ራሷ ዜማዎቹን ደርሳ በማለዳው ወደ ሙዚቃው ኢንዱስትሪ ጉዞ ጀመረች። ከዚህም ቤት ከዚያም ቤት እያንኳኳች ደጆች ብትልም፤ አቤት ብሎ የሚከፍት አነበረም፤ ተኝተው አሊያም ለመክፈት ፈርተዋል። ስለዚሁ ጉዳይም በአንድ ወቅት ለያኔው “ኢትዮጵ” መጽሄት ስትገልጸው “…ምን ያልገጠመኝ ነገር አለ…ያልረገጥኩት የሙዚቃ ደጃፍ የለም። ኦኦ! ይቅር ይቅር” ትላለች። ይሄ እንግልት የገጠማት ወዶና ፈቅዶ አልበሟን የሚያሳትምላትን በማጣት ነበር። ምክንያቱ ደግሞ፤ አስቀድመው ሥራዎቿን ለማድመጥ የሚቀጥሯት አሳታሚዎች በሙሉ፣ ሙዚቃዎቿን ከሰሙት በኋላ ወጣ ያሉና አዲስ ዓይነት በመሆናቸው፣ ብንከስርስ የሚል ፍርሃት ይወራቸዋል። ባልተለመደ ዓይነት የአዘፋፈን ስልት የሠራቻቸው በመሆናቸው አድማጭም አይኖረውም የሚል ጥርጣሬ፣ አንዳንዶቹም እርግጠኛ ሆኑ። አዲስ ፊትና አዲስ ነገር ቢጣፍጥም አይዋጥልንምና በዚሁ ምክንያት ጂጂ በፀሐይ ተንገላታች፡፡

አያልፉት የለምና በስተመጨረሻ ሌቱም ነጋ። የቀን ጨለማ ተገፈፈ። የማለዳ ጀንበርም ትክክለኛዋን የጠዋት ፀሐይ አገኘች። ለለማ ድማሙ ምሥጋና ይግባና ዕድሜ ልኳን የማትረሳውን መልካም ሥራ ሠራላት። ለማ ኦርጋኒስት ነበር። ጂጂ አግኝታ ሙዚቃዎቿን ካስደመጠችው በኋላ ሊሠራላት ተስማማ። ከዚህ በኋላ ቀን ሳይሉ ማታ፣ በሌት በማዕልት፣ በብርድ በሙቀቱ ለአንድ ዓመት ሙሉ ትግላቸው ለፀሐይ ሆነ። የብዙዎቹን ፍርሀት ሰብሮ፣ አሬጅመንቱን ጭምር ጥንቅቅ አድርጎ ሠራው። “ኦ! እንዴት ለፍቷል መሰለህ” ትላለች ጂጂ የለማን ልፋት እያስታወሰች። “በዚህ ሥራ ከኔ በላይ የደከመው ለማ ነው። በጣም ባለውለታዬ ነው” ስትልም ውለታውን በልባዊ ምሥጋና ታወሳለታለች።

ጂጂ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ የተገለጠችበት ወቅት ቀድሞ ከነበረው ትውልድ፣ አንድ ሙዚቃዊ ሽግግር የተካሄደበት ነበር። ቀድሞ የነበረው የሙዚቃ ባንድ ዘመን፤ በ1980ዎቹ መጨረሻ አክትሞ፣ 90ዎቹ በአንዲት ጠባብ ስቱዲዮ ውስጥ የመታጎር ነበር። ያም ሆኖ ግን፤ የዘመን ክስተት ለመሆን የቻሉ ሙዚቀኞች የተገኙበት ነው። ከእነዚህ ክስተቶችም አንዷ እጅጋየሁ ሽባባው ናት። ጂጂም በፀሐይ ስትጀምር፣ ከዚሁ ጠባብ ስቱዲዮ ውስጥ ተቀምጣ ነበር። ምንም እንኳን ከለማ ጋር ሆነው ለሁለት እየታገሉ የነበረ ቢሆንም፤ በነጋዴዎቹ በኩል የነበረው ፍርሃትና ሽሽት ግን እንደነበረው ነበር። “ሕዝቡ የስክስታ ዘፈን እንጂ አንቺ እንደምትዘፍኚው ያለ ዘፈን አይፈልግም። አይቀበልሽም” እያሏትም፤ እርሷ ግን ጥርሷን ነክሳ “እንቢ!” አለች፡፡

እናም አንድ መላ ዘየደችና በጊዜው አሉ የተባሉ የሙዚቃ ጠበብት ከያሉበት ወደ ስቱዲዮው በማምጣት ማስደመጥና ማስገምገም ጀመረች። የሚያውቁ ግን በሥራዋ መደነቃቸው አልቀረም። እንዲህ ቢሆን ባሏቸው ሃሳቦች ላይ ማስተካከያ እያደረገች፣ በስተመጨረሻም የጂጂ ፀሐይ በኤሌክትራ ሙዚቃ ቤት ቦግ! አለች።

“ደማቅ ሆነሽ ትወጪያለሽ የኔ ፀሐይ

እናፍቃለሁ እኔ አንቺን ላይ” እንዳለችውም ፀሐይ ወጣች።

እጅጋየሁ ሽባባው(ጂጂ) አንድ ነገር ብቻ አነበረችም። አንዷ ጂጂ በብዙ ጥበብ ውስጥ አድራለች። ለምሳሌ፤ በ1987ዓ.ም በተሠራ “የጊዜያችን ሰዎች” በሚል ፊልም ውስጥ ተውና ነበር። ከዚያ በኋላም “የሞት ፍቅር” በተሰኘ ሌላ ፊልም ውስጥ ሠርታለች። በዚህ ፊልም መሥራት ብቻ ሳይሆን፤ በ1988ዓ.ም በተካሄደው በፊልሙ የምረቃ ዝግጅት ላይ በምርጥ ተዋናይት ዘርፍ አሸናፊ ነበረች። ከፊልም ሥራዎቿ ባሻገር በብሔራዊ ቲያትር ቤት በትርፍ ጊዜ(በፍሪላንስ) ተቀጥራ ትሠራ ነበር። ታዲያ እዚህ ስትሠራ በአንደኛው የበዓል ዝግጅት፣ የፊልም ባለሙያና መምህሩን ብርሃኑ ሽብሩን ጋበዘችው። ብርሃኑም በኋላ ላይ ያስገረመውን ነገር አጫውቶት ነበር። “በርካታ ሰዎች በታደሙበት ዝግጅት ላይ ድምጻውያኑ ወደ መድረክ የሚወጡት በአጋፋሪው እየተዋወቁና እየተወደሱ ነበር። በመሃከል ጂጂ መድረኩ ላይ ወጥታ “ፀሐይ” የሚለውን ሥራዋን አቀረበች። የወጣችው ስሟ ሳይጠራ ነበርና እኔም ስለገረመኝ ለምንድነው ስል ጠየቅኋት” ይላል ብርሃኑ የሆነውን አስታውሶ። በሰዓቱ ጂጂ የሰጠችው ምላሽም እንዲህ የሚል ነበር “ታዋቂ ስላልሆንኩ ስሜን አይጠሩም። ያለ አጋፋሪ ነው መድረክ ላይ የምወጣው፡፡”

“ፀሐይ” የተሰኘችውን አልበሟን ከለቀቀች በኋላ፣ ጂጂ ሙዚቃውን ለአድማጭ ጆሮ ትታ ወደ አሜሪካ አቀናች። እንደ ጥላ በሄደችበት ሁሉ የሚከተላት የሙዚቃ ፍቅሯ ግን አብሯት አሜሪካም ዘለቀ። በዚያ በነበራት የሙዚቃ እንቅስቃሴ ነበር ጂጂ በብዙዎች የምትወደስ ዓለም አቀፍ ሙዚቀኛ ለመሆን የበቃችው። ትልቁ CNN በቴሌቪዥን መስኮቱ ብቅ አድርጎ “New talented Ethiopian singer Gigi” ሲል አስተዋወቃት። ከዚያን በኋላ የሚያቆማት አነበረም። በእኛው ሙዚቃ የእርሷን ታላቅነት ሲነግሩን፣ ይሄኔ ፀሐይን ፍለጋ ተረባረብን። ገና ያኔ ታላቅነቷን አውቀን ሙዚቃዋን ማጣጣም ጀመርን።

ፀሐይ በ1989ዓ.ም፣ ዋን ኢትዮጵያ በ1990ዓ.ም፣ ጉራማይሌ(ጂጂ) 1993ዓ.ም፣ ኢሉምኔትድ በ1993ዓ.ም፣ አቢሲኒያ 1995ዓ.ም፣ ሰምና ወርቅ በ1998ዓ.ም፣ ምስጋና በ2002ዓ.ም ያሳተመቻቸው ሰባቱ የአልበም ሥራዎቿ ናቸው። ከሰባቱ በተጨማሪ ከፋንታሁን ሸዋንቆጨው ጋር ተጣምራ የሠራችውን ሌላ አንድ አልበም ሲታከልበት ደግሞ ስምንት ሆነው እናገኛቸዋለን።

ታዲያ በእነዚህ የጂጂ ሙዚቃዎች ያቡ ጥፍት ያላለ፣ በቅኔዎቿ ያልተማረከ ማን አለ? ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ በጻፈው፣ መምህርና ገጣሚው ፈቃደ አዘዘ (ዶ/ር) ለተማሪዎቻቸው እንዲህ አሉ፤ “ዛሬ እንቅልፍ ሳይወስደኝ ነው ያደርኩት” ተማሪዎቻቸውም ለምን? በማለት ይጠይቃሉ። “ፍቅር እየራበኝ እያለች የምትዘፍን ልጅ እጅግ እየደነቀችኝ ደጋግሜ ስሰማት ነው ያደርኩት። …በኢትዮጵያ ውስጥ ከ26 ዓመት በኋላ በሙዚቃ ነፍሴን የገዛችው ይህቺ ድምጻዊት ናት” ብለው ተናገሩ። ፕሮፌሰር ሃይሌ ገሪማ ደግሞ ተናገሩላታ፤ “አሁን ባለው ትውልድ ውስጥ አንድ ነበልባል ትውልድ ብቅ ብሏል። እነዚህም እጅጋየሁ ሽባባውና ቴዲ አፍሮ ናቸው፡፡” እንኳንስ ሰው፤ በበረሃው እንደ አቦሸማኔ የሚገሰግሰው ዓባይ፣ የሰው ልጅን ክብር የገለጠው ዓድዋ በተናገሩት። የእውነትም ትናገር ዓድዋ!…ጂጂ ግን የታለች፤ የት ናት?

ከምትወደው ጥበብ ርቆ መተንፈሱን እንደምን ቻለችበት! ከልጅነት እስከ ዕውቀት፣ ከቻግኒ እስከ አሜሪካን ግዛት፣ ለዘመናት ዳናዋን ሲከተል የኖረው ጥበብም ድክም አለው መሰል። በሀገረ አሜሪካ ብቸኝነት ከልቧ ሸምቆ፣ ከብዙሃኑ ርቃ፣ ከሰው ተነጥላ፣ የውስጧን ከውስጧ ጋር ዝም ብቻ። ያ የሚስረቀረቀው ድምጽዋ፣ ጣፋጭ አንደበቷ ብዙ መናገር ሰለችው። እንደምን ያለው ህመም እንደሆን አልለይሽ ብሏት አለች። ምናልባት ፍቅር እርቧት ይሆን? የጠማት ውሃ ሳይሆን ሰው፣ የሰው ትንፋሽ ይሆን? ማን ያውቃል… ማንስ ተረድቷታል…ውስጧ ግን ዛሬም ሀገሯን፣ ዛሬም የሀገሯን ልጆች ይናፍቃል። ከአንድ ዓመት በፊት ቤተሰቦቿ እንደምትመጣ ገልጸው የነበረ ቢሆንም፤ እሷ ግን ይኼው ዛሬም አልተመለከትናትም። ያ የራበን የጠማን ድምጽዋን ዳግም ልንሰማው አልቻልንም። ግን መቼ ይሆን የምንሰማው?

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን እሁድ መጋቢት 21 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You