ለመላ የእስልምና እምነት ተከታዮች እንኳን ለ1446ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል በሰላም አደረሳችሁ! ይህ በሃይማኖታዊ እንዲሁም በባህላዊ እሴቶች ጭምር የሚከበር ታላቅ በዓል ላለፈው አንድ ወር የተደረገ የሮመዳን ፆምን ተከትሎ የሚከበር ነው።
ፆሙ የእምነቱ አስተምሕሮ በሚያዘው መሠረት ተካሂዷል። ባለፉት የፆም ወቅቶች እርስ በርስ በመደጋገፍ፣ በመረዳዳትና በአንድነት ሲካሄድ እንደቆየ ሁሉ በበዓሉ እለትም ከረመዳን ቀጥሎ በሚመጡ ጊዜያትም እንዲሁ መልካምነትና ደግነት የበለጠ የሚተገበርበት እንደሚሆን የእምነቱ አባቶች አስገንዝበዋል። በዓሉ ሲከበር የተቸገሩ ወገኖችን መርዳት ከአለው ማጋራት እንደሚጠበቅም አስታውቀዋል።
የኢድ አል ፈጥር በዓል በልዩ ልዩ የእስልምና እምነት ሥነሥርዓቶች የሚከበር ከመሆኑ በተጨማሪ በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖረው ሙስሊሙ ኅብረተሰብም ከእምነቱ አስተምሕሮ ጋር የጠበቀ ቁርኝት ባላቸው ባህላዊ እሴቶቹ ጭምር በዓሉን በደማቅ ሥነሥርዓት ሲያከብር ኖሯል፤ እያከበረም ይገኛል፡፡
በዓሉ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስልጤ ዞን በስልጤ ማኅበረሰብ ዘንድ ከሃይማኖታዊ ሥነሥርዓቱ ጎን ለጎን የስልጤ ማኅበረሰብ ለዘመናት ጠብቆ ባቆያቸው ባህላዊ እሴቶች በድምቀት ይከበራል።
የስልጤ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ይርዳው ናስር (ዶክተር) እንዳሉት፤ የኢድ አልፈጥር በዓል በዋናነት በስግደትና እርድ በመፈጸም የሚከበር ሲሆን፣ የተለያዩ ባህላዊ ሥርዓቶችም ይካሄዱበታል። አብዛኞቹ በእዚህ በዓል ወቅት የሚንፀባረቁ ባህላዊ እሴቶች በመጠያየቅ፣ በመተሳሰብ፣ በመዘያየርና በዓልን አብሮ በማሳለፍ ላይ የተመሠረቱ ናቸው፡፡
ማኅበረሰቡ በዓሉን በተለይ በስግደት ወቅት በአብዛኛው የስልጤን ባህላዊ አልባሳት በመልበስ ያከብረዋል። ከስግደት መልስ ደግሞ ዝየራ ይካሄዳል፡፡
ወጣቶች በአንዳንድ አካባቢዎች ወደ ከተማ በመሄድ ባህላዊ ጨዋታዎች ያካሂዳሉ፤ በአካባቢያቸውም ይዝናናሉ፤ በዚህም ለበዓሉ ተጨማሪ ልዩ ድምቀት ይሰጡታል። እንደ አረፋ በዓልም ባይሆን በርካታ ሙስሊም የብሔረሰቡ አባላት ከተለያዩ አካባቢዎች ቤተሰቦቻቸው ወደአሉበት ስልጤ ዞን እንደሚሄዱ ጠቁመዋል።
ኢድ አል ፈጥር በስልጤኛ ‹‹ሮሪ ፍቼ›› ትልቁ ፍቼ በመባል እንደሚታወቅም ይርዳው (ዶ/ር) ይገልጻሉ። እንደ እሳቸው ማብራሪያ፤ ማኅበረሰቡ በዓሉን ሲያከብር ለባህላዊ ክዋኔዎች ትኩረት ይሰጣል። ከእነዚህ ባህላዊ ሥነሥርዓቶች አንዱ ዝየራ ነው። በዚህ በዓል ዝየራ በስፋት ይካሄዳል፡፡
ኅብረተሰቡ ወደ እናት፣ አባት፣ ታላቅ ወንድምና ወደመሳሰሉት በመሄድ እነዚህን የኅብረተሰብ ክፍሎች ይዘይራል። እናትና አባት በተለየ መልኩ የሚጠየቁበትና የሚዘየሩበት ለትልልቅ ሰዎችም ስጦታ የሚሰጥበት ነው።
አንዳንዶቹ እናት አባቶቻቸው ሩቅ ቦታ ሊሆኑ ይችላሉ፤ እነሱን ሊዘይሩ ይሄዳሉ ወይም ታላቅ ወንድማቸውንም ሊዘይሩ ራቅ ብለው ሊሄዱ ይችላሉ። ይህ ዝየራ ብዙ ጊዜ ለመጠያየቅና ዝምድናን ለማጠናከር ተብሎ የሚፈጸም ነው። እነዚህ ሥርዓቶች በአብዛኛው ኢድ ላይ ይከናወናሉ።
አባቶችም እንዲሁ መልካም ምኞት የመግለጽ ኃላፊነት አለባቸው። ልጆቻቸው፣ የቅርብ ዘመዶቻቸው፣ አማቾቻቸው መጥተው ሲጠይቋቸው፣ ስጦታ ሲያቀርቡላቸው ይመርቋቸዋል። በሄዱበት ሁሉ ፈጣሪ የተመኙትን እንዲያሳካላቸው፣ የሰገዱት ሰላት፣ ፆማቸው በፈጣሪ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው ፈጣሪያቸውን ይጠይቃሉ፤ በዚህም ለልጆቻቸው ተስፋ ይሰጣሉ፤ መልካም ምኞታቸውን ይገልጻሉ።
ለተጎዱና መረዳት ላለባቸው፣ ለአቅመ ደካማ ወገኖች ርዳታ በማድረግ በዓሉን ተደስተው እንዲያሳልፉ ማድረግም ሌላው በበዓሉ ወቅት የሚታይ የማኅበረሰቡ የቆየ እሴት መሆኑን ይርዳው (ዶ/ር) ይገልጻሉ። ብሔረሰቡ ይህን የመረዳዳት ባህል በየዓመቱ በዚህ ወቅትም ያካሂዳል። ካለው ሀብቱና ንብረቱ እያወጣ የተቸገሩ ሰዎችን ይረዳል ሲሉ ያብራራሉ። ዘካ የሚባለውን በመፈጸምም በተሻለ መልኩ እርስ በርስ የመረዳዳትና የመደጋገፍ ሁኔታ የሚፈጠርበትም ነው።
መረዳዳቱ ከዚህም ከፍ ሊል እንደሚችል ኃላፊው ያመለክታሉ። በተለይ ሀብቱ ያላቸው ዕለታዊ መደጋገፉ እንዳለ ሆኖ፣ ከትንንሽ የመረዳዳት ሁኔታ ከፍ ባለ መልኩ ከድህነት ማውጣት የሚያስችል ሥራ ሊሠሩ እንደሚችልም ይርዳው (ዶ/ር) ጠቁመዋል።
በመረዳዳቱ ሂደት ሙሉ ለሙሉ ከችግር እንዲወጡ የሚያደርጉ አንዳንድ አካባቢዎች አሉ ሲሉም ጠቅሰው፣ በእንዲህ አይነቱ የመረዳዳት ሂደት ድህነትን ከስሩ ለመንቀል የሚሠራበት ሁኔታ እንደሚታይም ጠቅሰዋል። አንዳንዶች ሱቅ፣ ወይም ሻይ ቡና መሥሪያ ብር፣ መኪና ገዝተው እስከመስጠት የሚደርሱ እንዳሉም አመልክተዋል።
መተጫጨት ሌላው በበዓሉ ወቅት በስፋት የሚፈጸም ባህላዊ እሴት ነው። በተለይ ወጣቶች ለዝየራ ሲሉ በተለያዩ ቤቶች በሚፈጽሙት ባህላዊ ሥርዓት ወቅት የመተያየት የመተሳሰብ ሁኔታ ይፈጠራል። በዚህ ሂደት መፈላለግና ዝምድናችንን እናጠናክር የሚል ነገር ይመጣል ሲሉ ይገልጻሉ።
በዚህ ባህላዊ ጨዋታና ዝየራ ወቅት የተፈጠረው መግባባት እስከ መተጫጨት ሊደርስ ይችላል፤ እምነቱ በሚፈቅደው መልኩም የኒካ ሥርዓት ሊከናወን የሚችልበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል ያብራራሉ። የጋብቻው ሥርዓት በበዓሉ ወቅትም ከበዓሉ በኋላም ሊፈጸም እንደሚችልም ጠቁመዋል።
‹‹ቤተሰብ ጋብቻው ቶሎ እንዲፈጸም ይፈልጋል፤ በተለይ ለበዓሉ ብለው ከሌላ ቦታ የመጡ ከሆኑ በመጡበት አጋጣሚ አጭተውም ኒካ አስረው ይዘዋት ሊሄዱም ይችላሉ ሲሉ ያብራራሉ። በሌላም ጊዜ ተመልሰው መጥተው ጋብቻውን ሊፈጽሙ የሚችሉበት ሁኔታ እንዳለ ጠቅሰው፣ ዋናው ግን መተጫጨቱ የሚፈጸምበት አንዱ ወቅት ይህ የኢድ አል ፈጥር በዓል ነው ሲሉ አብራርተዋል።
የሃይማኖቱ ተከታዮች በዚህ በዓል ወቅት የየራሳቸው የሥራ ድርሻ እንዳላቸውም ኃላፊው ጠቁመዋል። አባቶች እርድ ያከናወናሉ፤ ለልጆች አልባሳትን ይገዛሉ ሲሉም ይገልጻሉ።
እናቶች ለእዚህ በዓል የሚሆኑ ነገሮችን አስቀድመው ሲያዘጋጁ ይቆያሉ፤ እንደ አተካኖ ያሉ ለበዓሉ አከባበር ድምቀት የሚሰጡ ባህላዊ ምግቦችን፣ የስልጤ ባህላዊ መጠጦችን /ቃሪቦ፣ ሻሜታ/ እንዲሁም ቅመማ ቅመሞችን ያዘጋጃሉ። ለበዓሉ ድምቀት የሚሰጡ የቤት ውስጥ ዝግጅቶችን እንዲሁ ያካሂዳሉ፡፡
በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ ደግሞ እናቶች ለበዓሉ ሲሉ የቅቤ ዕቁብ እንደሚገቡም ጠቅሰው፣ ለእዚህም ኡጁ የሚባል ሥርዓት አለ፤ በየወሩ ቅቤ እያጠራቀሙ ለሁሉም እንዲደርስ ያደርጋሉ፤ ለበዓሉ የሚያስፈልገውን ቅቤም በእዚህ መልኩ ዝግጁ ያደርጋሉ ይላሉ።
የስልጤ ማኅበረሰብ ከሌሎች ብሔረሰቦች እንዲሁም ከሌሎች እምነት ተከታዮች ጋር ጠንካራ መስተጋብር እንዳለው ጠቅሰው፣ በዚህ በዓል ወቅት ደግሞ ይህ መስተጋብር ጎልቶ እንደሚታይ ተናግረዋል።
እሳቸው እንዳብራሩት፤ በስልጤ ባህል በዚህ በዓል ወቅት ጎረቤትን ጨምሮ ሁሉም እኩል ተደስቶ እንዲውል ይፈለጋል። የየትኛውም እምነት ተከታይ ቢሆን መረዳት ካለበት ይረዳል። ማኅበረሰቡ ይህን እንደ ግዴታ ይመለከተዋል።
በአጠቃላይ ከጎረቤት የሌላ እምነት ተከታዮች ጋር አብሮ በመብላት በመጠጣት በመዘያየር በዓሉ ይከበራል። ለእነዚህ የእምነት ተከታዮች ሃይማኖታቸው የሚፈቅደው ምግብ ይቀርብላቸዋል።
ይህ ባህል ዱሮም የነበረ፣ ወደፊትም የሚቀጥል ይሆናል፤ እምነቱም መጠያያቅና መዘየርን ያዛል። ይህም ትልቁ ምንዳ የሚገኝበት ተብሎ ይታሰባል፤ ዝምድናን ማስቀጠል የሚቻልበት እንደሆነም የሚታወቀው ሲሉ አብራርተዋል።
ባህላዊ እሴቱ በተለይ ለጎረቤት ደግሞ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ አስታውቀው፣ ከየትኛውም በፊት ጎረቤት ይቀድማል ሲሉ የእምነቱ አስተምሕሮም የብሔረሰቡም ባህላዊ እሴቶች ያስገነዝባሉ። በእምነቱም በባህሉም በማኅበረሰቡም እንዲሁም በሌሎች እምነቶችም ቢሆን ለመጠያየቅ ለመዘያየር ትልቅ ስፍራ ይሰጣል። የሌሎች እምነት ተከታዮችም እንዲሁ ሙስሊሞቹ ቤት በመሄድ እንደሚዘይሩም ተናግረዋል። በዚህም እንኳ አደረሳችሁ የሚል መልዕክት ያስተላልፋሉ።
ይርዳው (ዶ/ር) እንዳብራሩት፤ እነዚህ የብሔረሰቡና የእምነቱ እሴቶች በሚገባ እንዲጠበቁ እንዲሁም ይበልጥ እንዲጎልበቱ እየተሠራ ይገኛል። በእዚህ በኩል የስልጤ የሀገር ሽማግሌዎች ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ናቸው።
የሀገር ሽማግሌዎቹ ምክር ቤት አላቸው። ምክር ቤቱ /አንዱ አደረጃጀት አምስት ሽማግሌዎችን ይይዛል/ እነዚህ ባህሎች እንዲጠናከሩ እንዳይጠፉ ከቀበሌ አንስቶ እስከ ዞን ድረስ አደረጃጀቶች ተፈጥረውለት ይሠራል። ሽማግሎቹ በምክር ቤታቸው በኩል የስልጤ ማኅበረሰብ የያዘውን የመደጋገፍ እሴት በአጠቃላይ ያሉትን እሴቶች አጠናክሮ እንዲቀጥል እሴቶቹ በመጤ ባህሎች እንዳይበረዙ ለማድረግ ይሠራሉ።
በተጨማሪም እኛም እንደ ባህልና ቱሪዝም ከወራቤ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን በእነዚህ እሴቶች ላይ ጥናቶችን እየሠራን ግንዛቤ እንፈጥራለን ሲሉ ኃላፊው ጠቅሰው፤ ከሀገር ሽማግሌዎችም ከማኅበረሰቡ ጋር በተያያዘ ጥናቶች እንደሚሠሩም አመልክተዋል።
‹‹ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል። ከዚህ በተጨማሪም በየዓመቱ በዓላቱ ሲከበሩ እኛ ከማኅበረሰቡ ጋር በመሆን የምናሳውቅበትና መረጃ በመያዝ የምንሰንድባቸው ሁኔታች አሉ›› ሲሉም አብራርተዋል።
በዓሉ በየዓመቱ የሚከናወን እንደመሆኑና በባህላዊ ሥርዓቶችም ደምቆ የሚከበር በመሆኑ ባህሉ በዚያው ልክ በማኅበረሰቡ ዘንድ በጉጉት ይጠበቃል፤ የስልጤ ባህል ከእምነቱ አስተምሕሮ ጋር አብሮ የሚሄድ መሆኑም ማኅበረሰቡ በዚያ ልክ ባህሉን ይበልጥ እንዲያውቀው እንዲጠቀምበት ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።
እሳቸው እንዳሉት፤ በእዚህ ላይ በተከናወኑ ተግባሮች እስከ አሁን አንዳንድ ጉድለቶች ሊኖሩ ቢችሉም፣ የቴክኖሎጂ ዘመንና ሌሎች ችግሮች ጫና ቢያደርሱም ወጣቶች የስልጤን ባህል እሴት ይዘው እንዲዘልቁ በማድረግ በኩል ጥሩ ተሠርቷል።
እሴቱ ስልጤ ዞን ላይ ብቻ ያለ አይደለም፤ በመላ ሀገሪቱ በሚኖሩ ስልጤዎች ዘንድም ያለ ነው። ስልጤዎች ከየትኛውም ማኅበረሰብ ጋር ተዋደው ተግባብተው የሌላውንም ማኅበረሰብ ቋንቋ አክብረው ይኖራሉ። ይህ ደግሞ የማኅበረሰቡ እሴት ውጤት ነው።
ማኅበረሰቡ በጣም በሰላም ውስጥ ያለ መሆኑንም ጠቅሰው፣ ይህን ሰላሙን ጠበቆ እንዲቆይ ያስቻሉት ደግሞ እነዚህ እሴቶቹ ናቸው ተብሎ በጽኑ እንደሚታመንም ተናግረዋል።
እሳቸው እንዳስታወቁት፤ ከዞኑ አጐራባች ክልሎች ዞኖች ማኅበረሰቦች ጋርም ጭምር በሰላም አብሮ ይኖራል። ለምሳሌ ዞኑ ከሚዋሰናቸው ክልሎች መካከል የኦሮሚያ ክልል አንዱ ነው፡፤ ከዚህ ክልል ሕዝብ ጋር ተግባብቶ ይኖራል፤ አንድም ቀን ኮሽታ ተሰምቶ አያውቅም። ከጉራጌ፣ ከማረቆና ከአላባ ማኅበረሰቦች ጋርም እንዲሁ በየጊዜው በመቀራረብ ውይይት ይደረጋል፤ በዚህም ከጎረቤት ማኅበረሰብ ጋር ግጭት እንዳይፈጠር በሰላም ለመኖር እንዲቻል ይሠራል።
‹‹ለእዚህም በኛ በኩል ከአጎራባች ዞኖች ጋር መድረኮችን እየፈጠርንም እንሠራለን›› ሲሉም አስታውቀው፣ በዚህም እነሱም የሚያነሷቸው ችግሮች ካሉ እኛም ጋ የሚነሱ ችግሮች ካሉ ለመፍታት ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል። በእዚህና በመሳሰሉት መንገዶች በመሥራት የስልጤ ባህላዊ እሴቶች እንዲጠበቁ እንዲለሙ ይደረጋል።
እነዚህ የብሔረሰቡ ባህላዊ እሴቶች እንዲተዋወቁ፣ እንዲጎበኙ እንዲሸጡ በማድረግ በኩል እየተሠራ መሆኑንም ይርዳው (ዶ/ር) ጠቁመዋል። ከእነዚህም አንዱ ለቱሪዝም የሚሆኑ ባህላዊ እሴቶች የትኞቹ ናቸው የሚለው የልየታ ሥራ መሠራቱንም ተናግረዋል። በዚህ ላይ በመመስረት እሴቶቹን ለማስተዋወቅና በዩኔስኮ ለማስመዝገብም ከክልሉ መንግሥት ጋር በመነጋገር እየተሠራ ነው ሲሉ ያብራራሉ።
በተለይ የሴቶች አረፋ መዘያየር፣ ከኢድ አል ፈጥር በኋላ በማኅበረሰቡ ዘንድ በሚከበረው በትንሹ ኢድ የሚካሄዱ ሥነ ሥርዓቶችን ለመለየት መሠራቱን ገልጸዋል። በእስልምና እምነት ሁለት በዓላት እንዳሉ ጠቅሰው፣ በስልጤ ማኅበረሰብ ግን ሌላ ተጨማሪ ብሔረሰቡ የሚያከብረው ባህላዊ በዓል /ኢድ/ እንዳለውም ጠቁመዋል።
እሳቸው እንዳብራሩት፤ ይህ በዓል ‹‹ቃሊ ፍቼ›› ይባላል። በስልጤዎች ዘንድ ዋናው የኢድ በዓል በተከበረ ማግስት ፆም ይገባል፤ ይህ ፆም የሸዋል ፆም ይባላል። ፆሙ ለስድስት ቀናት የሚቆይ ነው። ሌሎች በወር ውስጥ በፈለጋቸው ጊዜ ስድስት ቀናቱን ሊፆሙ ይችላሉ።
ስልጤዎች ይህን የስድስት ቀን ጾም የሚፈቱበት በዓል ነው ‹‹ቃሊ ፍቺ›› ወይም ትንሹ ኢድ የሚባለው ያሉት ኃላፊው፣ በእዚህ የፍቺ ወቅት ሰዎች ይዘያየራሉ። ስልጤዎች አባትና ልጅን ይዘይራሉ፣ እናትንና አባትን ይካድማሉ ሲሉ አስታውቀዋል።
ሌሎች በዓሎች ከአረፋ ጋር በተያያዘ በሴቶች አረፋ በዓል ላይ ከተለያዩ የኢትዮጵያና የውጭ ሀገሮች የሚመጡ ስልጤዎች ወራቤ ላይ እንደሚገናኙም ገልጸዋል። በዚህ ወቅት ከዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች የተውጣጡ ልጃገረዶችና ወንዶች በዓሉን በማስመልከት በከተማ የተለያዩ አካባቢዎች ጭፈራዎችን እንደሚያሳዩ፣ ቤቶችን በስልጤ ባህላዊ ቀለሞች የማስዋብ፣ ሥራዎች እንደሚሠሩም ተናግረዋል። እነዚህን ሥነሥርዓቶች ለይተን መዝግበን የማስተዋወቅ ሥራ እየሠራን ነው ሲሉ ኃላፊው አመልክተዋል።
ኃይሉ ሣሕለድንግል
አዲስ ዘመን እሁድ መጋቢት 21 ቀን 2017 ዓ.ም