ሰንበቴ በሚከፍሉት ባለ ትዳሮች ንግግር ተነሳስተው የምዕመኑን ሳቅና ጨዋታውን አደበዘዙት። ከቅዳሴ ውጪ ሁሉም ፊቱን ክንብንቡ ውስጥ ቀብሮ የተዘከረውን መክፈልት ይቀምሳል። አባ አጥላውም ከመክፈልቱ ጋር ነገር ያላምጣሉ። “ሥጋና ደሙን አልፈትት እንጂ እኔኮ ቄስ ማለት ነኝ፤ ታዲያ እንዴት ገላዬን ታረክሳለች?” እያሉ ይንገበገባሉ።
ባሻጋሪ የተቀመጡት ሽጉልቴና እማሙ አባ አጥላውን እያዩ አፋቸውን በነጠላ ሸፍነው ይንሾካሾካሉ። “በምን ተጣሉ ይባላል አንቺዬ?” ስትል ሽጉልቴ እማሙን ጠየቀቻት። “ከሚስታቸው መቀነት ላይ ተባይ አገኙና የትኛው መናጢ ደረሰብሽ? ብለው ነው አሉ” በማለት እማሙ ከንፈሮቿን ሸሽተው ሃጫ በረዶ የመሰሉ ጥርሶቿ ብቅ እያሉ መለሰች።
ሽጉልቴ “የመናጢ መሆኑን ደግሞ በምን አወቁ?” ብላ ሌላ ጥያቄ አስከተለች። ያለፋታ ሲልሰኝ ነው ያደረው፤ መናጢ ምን ደም ኖሮት ይጠግባል? ሲደፈጥጡት ልምሽሽ ነው፤ ደህና ሰውነት ቢያገኝ ኖሮ ጥንቡሽ ነበር የሚለው ይላሉ አሉ” እያለች ታስረዳ ያዘች። ሽጉልቴ የሰማችው የድሮ ታሪክ ታወሳትና ማረብረቢያ እንዲሆናቸው አቀበለቻት። “እቴጌ ጣይቱ እቃ ሲወድቅባቸው ይሁን ወሬ ሲደናገራቸው “ወንድዬ ድረስ” ማለት ይቀናቸዋል። በዚህ ጠባያቸው ግራ የተጋቡት ዓፄ ምኒልክም በጌምድር የሚኖሩ የቀድሞ አራተኛ ባላቸውን አስጠሯቸው። “ነገ ድረስ በቆማጣ ፈረስ” የተባሉት ሰውዬም ቤተ መንግሥት እንደደረሱ ንጉሡ የጎሪጥ እያይዋቸው ላይናቸው አልሞላ ቢሏቸው ጊዜ “ጣይቱ የምትምልብህ ወንድዬ ማለት አንተ ነህ?” አሏቸው ።
ወንድዬም የዋዛ አልነበሩም። “አዎ ጌታዬ! ጣይቱኮ እንዳው ባል አይወጣላትም” ሲሉ በወርቅ የተለበጠ ውስጠ/ወይራ ንግግር ጣሉባቸው” በማለት ስታጫውታት አባ አጥላውንና ባለቤታቸውን እታጉን እየተመለከቱ ይታገላቸው የነበረውን ሳቃቸውን ለቀቁት።
ቄስ ልንገረው ቆመው ሲያጨበጭቡ መስኩን የሞላው ምዕመን ጆሮውን ወደ ዓውደ ምሕረቱ ላከ። “የድሮ ሰዎች ቆንጆ ሲያዩ “ይህችን ቆንጆ አየሃት?” ሳይሆን “ይህን እህል አየኸው?” ነበር የሚሉት።
“ሰውና አቁማዳ በእህል ነው” እንዲሉ ገበታ ንጉሥ ነውና የሞተ እህል በመሐላችን ሾመን ቂም ይዘን መቅረብ ስለማይገባን ቀን ሲከዳን ቀን የሚያወጡን፣ የቀያችን አድባር ዋሳችን ተጣልተዋልና ሽማግሌዎች መላ ወዲህ በሉ?” አሉ ወደአባ አጥላውና ወደ ወይዘሮ እታጉ እየጠቆሙ።
ቄስ ልንገረው መቀነት ላይ በተገኘ ተባይ ሰበብ እንደተጣሉ ሲሰሙ “እሥራኤላውያንን በስደታቸው ጊዜ የወረደባቸው ተባይ ነው ወይስ የውሽማ?” ብለው ቢጠይቋቸው በወደዱ፤ ዳሩ ምን ይሆናል፤ አሁን በሚያገለግሉበት ደብር ዋስ ሆነው ያስቀጠሯቸው እሳቸው ናቸው።
አባ አጥላው ከጭልፊት እንዳመለጠች ጫጩት ጭብጥ ብለው ከተቀመጡበት ተነሱና ሀገር ፍረደኝ፤ ድፍን ጮርቃ መንደር
“በዳልቻ በሬ ሂድ ሂድ ብሎ፣
ቆርቆሮ አለበሰው ሣሩን ወዲያ ብሎ።”
ሲል ያወደሰኝ ምሳሌ በመሆኔ እንደሆነ አይካድም፤ ታዲያ እንዲህ ከሆነ ለምን ተደፈርኩ? እሷስ ግድ የለም ትባልግ፤ እንዴት ሌላው ክብሩን ይዘነጋል? አሉና በሽመላቸው መሬቱን ደሰቁት።
አባ አጥላው ደርሰው ራሳቸውን መካብ ይወዳሉ። ቀጠሉና “ያፈረሰ ቄስ አይቀድስም የሸሸ ንጉሥ አይነግሥም ብዬ ሀገሬንና ደብሬን ለመጠበቅ ከሞቀ ቤቴ ወጥቼ በዱር በገደሉ ተዋድቄ ነበር፤ ጀግናው አርበኛ በላይ ዘለቀ የከፋ ጦርነት ውስጥ ከምንገባ ብንተው ይሻላል ብሎኝ እንጂ። ያም ሆነ ይህ ሀገር ፍረደኝ” ብለው እግራቸውን አጥፈውበት ወደነበረው ጠፍጣፋ ድንጋይ ተመለሱ። የነፍስ አባታቸው ቄስ ልንገረው ሲፈሩ ሲቸሩ ስማቸውን ጠሩና “የመይቴ መቀነት ላይ ተባይ አየሁ ብለው ከወንድ እንደሄዱ የጠረጠሩ የመነኩሴ ደበሎ ላይ ተባይ ቢያገኙ ምን ሊሉ ኖሯል?” በማለት አስታመው ጠየቋቸው።
አባ አጥላው እምር ብለው ተነሱና “ወዴት ወዴት?” አሉ ተቆጥተው። “እንደሱ ነዋ” አሉ ቄሱ መልሰው። “ከቤታችን ዓባይ ከመደባችን ተባይ በዘራችን አያውቀንም” አሉ አባ አጥላው በመጀነን። ይህን ጊዜ አንድ ሽማግሌ ከዘራቸውን ተደግፈው ቆሙና ለሕዝቡ ሰላምታ ከሰጡ በኋላ በጉዳዩ ዙሪያ ሃሳባቸውን ሰነዘሩ። “እኛ በእድሜያችንም በልምዳችንም የተማርነው በሰንበት የተለቀለቀ ቤትና መረን የለቀቀ ትውልድ ተባይ እንደሚያፈራ ነው፤ ያልኩትም ሐቅ ሆነና የሚያከብሩትን ሰንበት በመሻር መሰለኝ ቤቱ ተባይ አፍርቶ ድምፃቸው ተሰምቶ የማያውቁ ጥንዶች የተስካር ብቅል ሆኑ። ተባይ እንቅልፍ ቢነሳቸው ዳፋው ለኛም ተረፈና ይኸው በማለዳው የነገር ደመና ተጭኖን እንንቆራጠጣለን።
ጎበዝ የግለሰብ ተባይ ላገርም ይተርፋል፤ አለመደማመጥ፣ አለመነጋገርና አለመግባባት የሚሉ ተባዮች እስከመለያየት ያደርሳሉ። መክረውና ዘክረው ሀገር ያሳድራሉ ያልናቸው እነዚህ ሰዎች ምክንያታቸውን በግልጽ ተነጋግረው ቢሆን ኖሮ ባልታዘብናቸው ነበር፤ ዳሩ ምን ይሆናል ሁሉም በየግል ክብራቸው ታጠሩና አልሞከሩትም፤ ይህ ማለት ግን አሁን አትጀምሩትም ማለቴ አይደለም። ለጸብ የነጋ ጀንበር ለፍቅር አይመሽምና ይቅር ተባባሉ ልጆቼ” አሉ ሽማግሌው አባ አጥላውንና ወይዘሮ እታጉን እጅ ለእጅ አጨባብጠው።
ወይዘሮ እታጉ “ሽበትዎ ይባረክ አባቴ፤ የዓርብ ውሃ ስቀዳ አላደርስ አለኝና አመድ ሆኖ ሳየው አላስችልሽ ቢለኝ በሰንበት ለቅልቄው ነው ለዚህ ያበቃን” አሉ እንባቸውን እየጠረጉ። አባ አጥላው ከባለቤታቸው እግር ስር ተንበረከኩና “የኔ እንባ ይፍሰስ አካሌ፤ የሰው ተባይ መስሎኝ ቅናት አመል ቢነሳኝ እንጂ ኃዘንሽን መቼ ፈቅጄ? እኔን ሃፍረት ያጉብጠኝ፤ አንቺማ ምን አጠፋሽ? በዳዩ እኔው ሆኜ ሳለ ባደባባይ ከሰስኩሽ፤ ማሪኝ ገበናዬ” አሉ አባ አጥላው እንባቸው ጣምራ ጣምራ እየወረደ።
ሀብታሙ ባንታየሁ
አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 26 ቀን 2017 ዓ.ም