ቱሪዝምን ከዘመኑ ጋር የሚያራምደው ረቂቅ ፖሊሲ

ኢትዮጵያ በርካታ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሠራሽ የቱሪዝም ሀብቶች ያላት ሀገር ናት፡፡ እነዚህን ሀብቶች በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችልና ዘመኑን የዋጀ ፖሊሲ አስፈላጊ ግብዓት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ነባሩ የቱሪዝም ፖሊሲ ከ10 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ በመሆኑ ፖሊሲውን ወቅታዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን ያገናዘበ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ከዚህ አንጻር የቱሪዝም ሚኒስቴር አዲስ ፖሊሲ በማዘጋጀት በተሻሻለው ረቂቅ ፖሊሲ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል፡፡ በቱሪዝም ሚኒስቴር የፖሊሲ አማካሪ የዚህዓለም ሲሳይ (ዶ/ር) እንደሚናገሩት፤ በ2001 ዓ.ም የወጣው ነባሩ የቱሪዝም ፖሊሲ ላለፉት 16 ዓመታት ቆይቷል፡፡ ነገር ግን አንድ ፖሊሲ ከአምስት እስከ 10 ዓመታት ባሉት ጊዜያት መከለስ አለበት፡፡

ነባሩ ፖሊሲ ከወጣ በኋላ እስካሁን ባሉት ዓመታት በርካታ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ለውጦች ተከስተዋል፡፡ ከእነዚህ ለውጦች አንጻር ሲታይ ፖሊሲው እነዚህን ለውጦች ያገናዘበ አይደለም፡፡ የቱሪዝም ፖሊሲውን ከ10 ዓመቱ የልማት እቅድ ጋር እንዲጣጣም ለማድረግ ነባሩን ፖሊሲ መከለስ እንዳስፈለገ ይገልጻሉ።

‹‹በዋናነት ቱሪዝም በመንግሥት ትኩረት ከተሰጣቸው ከአምስቱ ቁልፍ የኢኮኖሚ ዘርፎች መካከል አንዱ ነው፡፡ ይህን የመንግሥት እይታ ሊመጥን በሚችል መንገድ ፖሊሲውን መከለስ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ፖሊሲውን ማሻሻል አስፈልጓል›› ይላሉ፡፡ በተጨማሪም የዲጂታል ቴክኖሎጂን መጠቀም የቱሪዝም ሥራዎችን ለማስተዋወቅ፣ ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እና የቱሪስት መዳረሻዎችን ለማስፋፋት ሲባል ፖሊሲውን ማሻሻል እንዳስፈለገም ያስረዳሉ፡፡

የዚህዓለም (ዶ/ር) እንደሚገልፁት፤ ነባሩ ፖሊሲ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ያካተተ አልነበረም፤ ረቂቅ ፖሊሲው ፀድቆ ወደ ተግባር ሲገባ የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ አይነተኛ አስተዋፅዖ እንደሚኖረው በመግለጽ፤ ቱሪዝም ለሀገር ውስጥ ምርት እድገት የሚኖረውን አስተዋፅዖ ያሳድገዋል፤ በዘርፉ ሰፊ የሥራ ዕድልና ዘላቂ ገቢ እንዲፈጥርም ያደርጋል፡፡ የኢትዮጵያን ገጽታ በተሻለ መልኩ በዓለም መድረክ ለማስተዋወቅ ያስችላል፡፡

የታላቅ ኢትዮጵያ አስጎብኚ ድርጅቶች ማኅበር የቦርድ አባል አቶ ናሆም አድማሱ በበኩላቸው፤ ‹‹ነባሩ ፖሊሲ ከ10 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል ይባል እንጂ በውስጡ የያዘው ነገር በንጉሡ ዘመን ከነበረው ነገር ተጨምቆ የወጣ ነው›› ይላሉ፡፡

‹‹አሁን ለሦስተኛ ጊዜ የተዘጋጀው ረቂቅ ፖሊሲ ኢትዮጵያ ተግባራዊ ሳታደርግ አስቀምጣቸው የነበሩ ጉዳዮችን የሚዳስስ ነው፡፡ ለበርካታ ጉዳዮች ትኩረት የሚሰጥ በመሆኑ ሀገሪቱን በዓለም ተወዳዳሪ የሚያደርግ፤ በአገልግሎት፣ በባለሙያ ብቃት፤ በመዳረሻ ልማት እና በዘላቂ የቱሪዝም ልማት ግቦች ላይ ኢትዮጵያ ትክክለኛውን ቦታ እንድታገኝ ያስችላል ተብሎ ታሰባል›› ነው ያሉት፡፡

‹‹እንደማኅበር ባለፉት ዓመታት ስንታገልባቸው የቆዩ ጉዳዮች ነበሩ›› የሚሉት አቶ ናሆም፤ ኢንዱስትሪው በባለሙያ እንዲመራና፤ ፈቃድ ለማውጣት የሚያስፈልጉት መስፈርቶችን በማመጣጠን ለመሥራት የሚያስችሉ ጉዳዮች በአዲሱ ረቂቅ ፖሊሲ እንደተካተቱ ይገልጻሉ፡፡

‹‹በረቂቂ ፖሊሲው እንደ ጤና፣ ቱሪዝም እና የቅርሶች ጥበቃ ያሉ ጉዳዮች የተካተቱ ቢሆንም፤ የሀገር በቀል እውቀት ግን አልተጠቀሰም፡፡ ቀደም ሲል የሀገር በቀል እውቀት ጉዳይ በአዋጅ ደረጃ ሲጠበቅ የነበረ ቢሆንም፤ ከዘመናዊነት ጋር ተያይዞ እንዳይካተት የተደረገበት ሁኔታ አለ፡፡ ያንን መልሶ ወደ አዋጅ ማካተት ያስፈልጋል›› ይላሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት የቱሪዝም ዘርፉ ኢኮኖሚውን ከሚያንቀሳቅሱ ዘርፎች አንዱ እንደመሆኑ ነባሩን ፖሊሲ መከለስ አስፈላጊ እንደሆነ የሚናገሩት ደግሞ የሲዳማ ክልል የባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊና የቱሪዝም ዘርፍ ኃላፊ አቶ አበበ ማሪሞ ናቸው፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፣ አዲሱ ፖሊሲ ከዚህ ቀደም ተበታትኖ የነበረውን ሀብት ወደ አንድ ለማምጣት ያስችላል። ጊዜውን የዋጀ የቱሪዝም ግብይት ስልት እንዲኖር የአገልግሎት ሰጭ ተቋማት ልዩ ትኩረት እንደተሰጣቸው አቶ አበበ ይገልጻሉ፡፡

ረቂቅ መመሪያው ጥሩ የቱሪዝም እድገት ካላቸው ከተርኪዬ፣ ኬንያ፣ ፈረንሳይ እና ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮ በመውሰድ መዘጋጀቱ በቀጣይ ዘርፉ ለሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት ከፍተኛ ሚና እንዲኖረው እንደሚያስችል ይናገራሉ፡፡

የትግራይ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኃይላይ በየነ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ ረቂቅ ፖሊሲው በአጠቃላይ በቱሪዝም ዘርፍ በክልልም ሆነ በሀገር ደረጃ በቱሪዝም ማኅበረሰቡ ሲነሱ ለነበሩ ጥያቄዎች ወሳኝ መልስ ይዞ የመጣ ነው፡፡ ‹‹ከአወቃቀር፣ ከኢንቨስትመንት ማበረታቻዎች፣ ከጥራት፣ ከአገልግሎት አሰጣጥ፤ ከቴክኖሎጂ እና ከቱሪዝም ባንክ ጋር ተያይዞ ሲነሱ ለቆዩ ጉዳዮች ምላሽ የሚሰጥ ነው›› ይላሉ፡፡

ዓመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን መጋቢት 27 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You