የሕዝብ አደረጃጀቶች ወንጀልን ለመቀነስ በሚደረገው ጥረት አስተዋፅዖ እያደረጉ ነው

አዲስ አበባ፡- የሕዝብ አደረጃጀቶች ወንጀልን ለመቀነስ በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን አስተዋፅዖ እያደረጉ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ሰላም እና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ገለጸ፡፡ አዲስ የጫኝ እና አውራጅ መመሪያ ፀድቆ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ሰላም እና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ የሕዝብ አደረጃጀት ዘርፍ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍሬሕይወት በለጠ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በቢሮ የሚፈጠሩ የሕዝብ አደረጃጀቶች ወንጀልን ለመቀነስ እና ለመከላከል የበኩላቸውን አስተዋፅዖ እያበረከቱ ነው፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላም እና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ የተለያዩ የሕዝብ አደረጃጀቶች እንዳሉ የሚገልጹት ዳይሬክተሯ፤ የሰላም ሠራዊት፣ ጫኝ እና አውራጅ፣ የሰላም ክበባት፣ የሰላም ምክር ቤት፣ ጫማ አስዋቢ እና ተራ አስከባሪ በሚል የተደራጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

በሕዝብ አደረጃጀቶቹም ሰላምን ለማስፈን በግጭት አፈታት ዙሪያ እና የተለያዩ ደንቦችንና መመሪያዎችን የሚያስገነዝቡ ሥልጠናዎች እንደተሰጡም ጠቁመዋል። አደረጃጀቶቹም ሕገወጥ ተግባራትን ለመከላከል እና ሰላምን ለማረጋገጥ እንደሚሠሩም ገልጸዋል፡፡

የሕዝብ አደረጃጀቶቹም ከደንብ ማስከበር፣ ከፖሊስ እና ከቢሮው ጋር በጋራ በመሆን በትምህርት ቤቶች አካባቢ የሚከናወኑ አዋኪ ድርጊቶችን ለማስቀረት በኦፕሬሽን ሥራው ላይ መሳተፋቸውን አብራርተዋል። ሁሉም አደረጃጀቶችም ከቢሮው ጋር የሚገናኙበት እና ጥቆማ የሚሰጡበት አሠራር መኖሩን ገልጸዋል፡፡

በቢሮው የነፃ የጥቆማ መስጫ መስመር 8882 ጨለማን ተገን ተደርጎ የሚፈጸሙ ወንጀሎች፤ በጅምር ሕንፃዎች ውስጥ የሚፈጸሙ ወንጀሎች፤ ከሕገ ወጥ ግንባታ፤ ከመሬት ወረራ እና ማስፋፋት ጋር ተያይዞ በርካታ የስልክ ጥቆማዎች እንደሚደርሷቸውም ተናግረዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ፤ የሕዝብ አደረጃጀቶችን የሚቆጣጠሩ መመሪያዎች አሉ፡፡ ከዚህ በፊት ከጫኝ እና አውራጅ ጋር ተያይዞ በኅብረተሰቡ ዘንድ የክፍያ ቅሬታዎች ሲቀርቡ ቆይተዋል፡፡ ይህንንም ለመፍታት የጫኝና አውራጅ ማኅበራት ሕጋዊነት አገልግሎት አሰጣጥ እና የፀጥታና ደኅንነት ሁኔታ ለመከታተልና ለመቆጣጠር የወጣ መመሪያን በማዘጋጀት ከጫኝ እና አውራጅ ጋር ተያይዞ በአዲስ መልክ የማደራጀት ሥራ ተሠርቷል። በዚህም ዙሪያ ለኅብረተሰቡ የግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ተከናውኗል፡፡

በጫኝ እና አውራጅ አደረጃጀት ስር የነበሩ ግለሰቦች ሥርዓት አልበኝነት እና ባለንብረቱ የራሱ ንብረት እንዳያወርድ ሲከለከልበት የነበረውን አካሄድ ለማስተካከል መመሪያው የራሱ ሚና እንደሚኖረውም ጠቁመዋል፡፡

በአዲሱ የጫኝ እና አውራጅ አደረጃጀትም ግለሰቦቹ ሕጋዊ የሥራ ፈቃድ ያላቸው እና ግብር ከፋይ የሆኑ መሆናቸውንም ዳይሬክተሯ ገልጸዋል፡፡

መመሪያው የእቃ ዓይነቶች፣ የሚጠየቀው ዋጋ፣ የቦታ ርቀት አጠቃሎ የያዘ መሆኑን ጠቅሰው፤ ቢሮውም የመስክ የቁጥጥር ምልከታዎችን በየጊዜው ያደርጋል። በቢሮው ጥብቅ ኢንስፔክሽን ሥራ ከሕግ እና መመሪያ ውጭ ሲሠሩ የሚገኙ ማኅበራት ላይ ርምጃ እንደሚወስድም ተናግረዋል።

መክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን መጋቢት 27 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You