የሌማት ትሩፋት በክልሉ ዓሣን የማምረት ሥራ እያለማመደ ነው

ሐረር፡- በክልሉ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የሌማት ትሩፋት ቀደም ሲል የአካባቢው ነዋሪ ያልለመደውን ዓሣ የማምረት ሥራ እያስተዋወቀ መሆኑን የሐረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሮዛ ዑመር አስታወቁ፡፡

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሯ ከትናንት በስቲያ በክልሉ የልማት ሥራዎችን እየጎበኙ ላሉ ጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ፤ እንደክልል የሌማት ትሩፋት ይፋ ከተደረገ ወዲህ በከተማም በገጠርም የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛል፡፡ በዋናነትም የወተት፣ የማር፣ የዶሮ እና የዓሣ መንደሮችን በመለየት ሰዎች እንደየዝንባሌያቸውና እንደየአካባቢው ሁኔታ በሌማት ትሩፋት መርሐ-ግብሩ በንቃት እንዲሳተፉ ተደርጓል፡፡

በክልሉ ገጠራማ አካባቢዎች በተለይም ዓሣን የመመገብና የማርባት ልምድ እንዳልነበር ያስታወሱት ወይዘሮ ሮዛ፤ ከሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመነጋገር ለአካባቢው ምቹ የሆኑ የዓሳ ዝርያዎችን ማርባት እንደተቻለ ጠቅሰዋል፡፡

የአካባቢው ነዋሪዎች ለአትክልትና ፍራፍሬ በሚያቁሯቸው የውሃ ጉድጓዶች ውስጥ ዓሣን እንዲያረቡ እየተደረገ እንደሆነ ገልጸው፤ ክልሉ የሌማት ትሩፋት ሥራው ወደ ኅብረተሰቡ እንዲሰርጽና ግንዛቤው እንዲያድግም መጀመሪያ በራሱ ወጪ የማስተዋወቅ ሥራ መሥራቱን ተናግረዋል፡፡

በዶሮ መንደር የሴቶች ተሳትፎ እንዲጎላ ለእያንዳንዱ እማወራ 25 ጫጩቶችን ማከፋፈል እንደተቻለም አመልክተው፤ ይህ ሲደረግ ሁለት ነገሮች ታስበው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በአንድ በኩል ሴቶች የራሳቸውን ገቢ እንዲያመነጩ ያለመ ሲሆን በሌላ በኩል የኑሮ ውድነቱንም ለማረጋጋት እንደሚጠቅም አስረድተዋል፡፡

የብድር አቅርቦት በማመቻቸት ከዩኒቨርሲቲ የተመረቁ ወጣቶችም በከፍተኛ አቅም ወደ ዶሮ መንደር እንዲገቡ በመደረጉ የከተማው ነዋሪ ምርቱን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ አስችሏል ብለዋል፡፡ በወተት መንደር የሚመረተው ምርት ተቀነባብሮ ለተለያየ አገልግሎት እንዲያውል ባለሀብቶችን የማሳተፍ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል፡፡

ሐረሪ ክልል የቆዳ ስፋቱ ትንሽ ነው ያሉት ወይዘሮ ሮዛ፤ ይህን አነስተኛ የመሬት ሀብት አብቃቅቶ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የበጋ መስኖንም የሌማት ትሩፋት አካል በማድረግ እየተሠራ እንደሆነ አመላክተዋል። በተለይም የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን በትንሽ መሬት ላይ ደጋግሞ የማምረት ሥራ እየተከናወነ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ቀደም ሲል ሽንኩርት፣ ድንች እና ቲማቲምን የመሳሰሉ ምርቶች ከአዲስ አበባ እና ሻሸመኔ እየመጡ ይሸጡ እንደነበር ጠቅሰው፤ በአሁኑ ጊዜ ምርቱን በአካባቢው በማምረት በሰንበት ገበያ ለከተማው ማኅበረሰብ ማቅረብ እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡ በዚህም ከመቶ ብር በላይ የነበረውን የአንድ ኪሎ ሽንኩርት ዋጋ ሃምሳና ስልሳ ብር ማውረድ ተችሏል ነው ያሉት፡፡

ከማምረት እስከ መሸጥ ባለው የሥራ ሠንሠለትም ለበርካታ ሰዎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን ጠቁመው፤ ከዩኒቨርሲቲ የተመረቁ ወጣቶች የመንግሥትን ሥራ ከመጠበቅ የራሳቸውን እንዲፈጥሩ ሥልጠናዎች ተሰጥቷቸዋል ብለዋል፡፡

ፈጣን ምግቦችን እያዘጋጁ የሚሸጡ ወጣቶችም ከኮሪዶር ልማቱ እና ከከተማው ውበት ጋር በሚጣጣም መልኩ ሥራቸውን እንዲያከናውኑ እየተደረገ ስለመሆኑ ጠቅሰዋል፡፡

በኮሪዶር ልማቱ ጥቅም ላይ የዋሉ የመብራት ምሰሶዎችም በአካባቢው ወጣቶች እንዲመረቱ መደረጉን ተናግረዋል፡፡ በሁሉም ዘርፍ ባሉ ጅምር ሥራዎች የታየውን አበረታች ውጤት አጠናክሮ ለማስቀጠል በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ ወይዘሮ ሮዛ ተናግረዋል፡፡

ኢያሱ መሰለ

አዲስ ዘመን መጋቢት 27 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You