የመዲናዋ የማዘጋጃ ቤት አገልግሎቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል እያሳየ ነው

አዲስ አበባ፡- የአዲስ አበባ ከተማን በመዲናዋ በሚሰጡ የማዘጋጃ ቤት አገልግሎቶች መሻሻል እያሳዩና ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን የከተማዋ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ወንድሙ ሴታ ገለጹ፡፡

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ በማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ዙሪያ ውይይትና ግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ትናንት ሲካሄድ እንደገለጹት፤ በማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች የሚሰጡትን የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ፣ የእሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን፣ የፅዳት አስተዳደር፣ የኤሌክትሪክ አገልግሎቶችን እያስተባበረ ይገኛል።

በዚህም የከተማዋን እድገት የሚመጥን ዘመናዊ አገልግሎት በማቅረብ ፅዱ፣ ከአደጋ ስጋት ነፃ የሆነች ከተማ ለመፍጠር የሚያስችሉ ሥራዎች መከናወናቸውን አብራርተዋል።

መንግሥት በሚያከናውናቸው የልማት ሥራዎች ውስጥ የሕዝቡና የባለድርሻ አካላት ሚና ከፍተኛ መሆኑን አስታውሰው፤ በከተማዋ የተሠራው የኮሪዶር ልማት ሥራም አንዱ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አገልግሎቶች በላቀ ደረጃ ለማቅረብና በተሟላ ሁኔታ ለመፈጸም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸው እንዲወጡ ጠቁመው፤ የሚሰጡ አገልግሎቶችን በተሟላ መልኩ ዲጂታል በማድረግ ኅብረተሰቡ አገልግሎት ለማግኘት የሚደርስበትን እንግልት ለመቅረፍ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

በከተማዋ ከነበሩ ችግሮች ዋነኛው ደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ተጠቃሽ መሆኑን አንስተው፤ በተሠራው ሥራ ከተማዋ የፅዳት ተምሳሌት እየሆነች መሆኑን አመልክተው፤ በዚህም በከተማዋ ሕጻናት እንደልብ የሚቦርቁባት፤ ወጣቶች ጊዜ የሚያሳልፉባቸው በርካታ ፕሮጀክቶች መሠራታቸውን ዋና ሥራ አስኪያጁ አመላክተዋል፡፡

የአደጋና ስጋት እንዲሁም የከተማዋን ሰላም ከማስጠበቅ አንጻር ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን ጠቅሰው፤ የመልሶ ማልማት ሥራዎችም የአደጋ ተጋላጭነትን በመቀነስ በኩል ትልቅ ውጤት አስገኝተዋል፡፡ የአደጋ ስጋት ምንጭ የነበሩ የወንዝ ዳርቻ አካባቢዎች ለምተው የነዋሪዎች መዝናኛ መሆን መቻላቸውንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የልማት ሥራዎችን ለማዘመንና አቅዶ ለመተግበር የሲቪል ምዝገባ መረጃዎች ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ጠቁመው፤ ይህን መረጃ በተሟላ መልኩ ለማደራጀት ብሔራዊ መታወቂያ ምዝገባ ማካሄድን ጨምሮ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት እየተሠራ ነው፡፡ በጥቅሉ ሲታይ በመዲናዋ በሚሰጡ የማዘጋጃ ቤት አገልግሎቶች መሻሻል እያሳዩና ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።

ለመጣው ውጤት የኅብረተሰቡ ተሳትፎ ትልቅ በመሆኑ በቀጣይም የሚሠሩ ሥራዎች የተሟሉና ዘላቂነት ያላቸው እንዲሆኑ ኅብረተሰቡ ተሳትፎውን መቀጠል እንደሚኖርበት አመላክተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የመሠረተ ልማትና የማዘጋጃ ቤታዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አሕመድ አብዱራህማን (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች በከተማዋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻሉ መምጣታቸውን ጠቁመዋል፡፡

በተለይም ቋሚ ኮሚቴው በየወቅቱ በሚያካሂደው ክትትልና ድጋፍ የታዩ ጠንካራና ውጤታማ ሥራዎች በሕዝብ ተሳትፎ ተጠናክረው የሚገባቸው በመሆኑ፤ ይህን መሰል የምክክር መድረክ የሚኖረው አስተዋፅዖ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን መጋቢት 27 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You