እነሆ ክረምቱ ተጋመሰ፤ አገራችንም ምድሯ አረንጓዴ ለበሰ። በሰሜንም ይሁን በደቡብ አሊያም በምዕራብ እና በምስራቅ ክረምቱ ያረሰረሰው መሬት በምላሹ የአካባቢውን ገጽታ በበጋ ከምናውቀው የተለየ አድርጎታል። በዘፈኖቻችን የምናውቃት ለምለሚቷ ኢትዮጵያም እንደዘፈኑ የምትታየው እንዲህ በክረምት ብቻ ከሆነ ዓመታት ነጉደዋል። ደኖቿ መንምነው፤ ምንጮቿ ነጥፈው፤ ሃይቋቿ ደርቀው በነበር ከቀሩ ሶስት እና አራት አስርት ዓመታት አለፉ።
የደኖች መመናመን በአየር ንብረት ላይ ባሳረፈው አሉታዊ ጫና እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ታዳጊ አገራት እየከፈሉት ያለው ዋጋ ከአዕምሮ በላይ ነው። ከዚህ ችግር ለመውጣትም ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታን ከጀመረች ጥቂት ዓመታት ተቆጥረዋል። አፍሪካን ወክላም የአየር ንብረት ጠበቃ በመሆን በዓለም አቀፍ መድረኮች ተሟግታ ፍሬያማ ውጤትን አስመዝግባለች። ይህ አንድ አገርንና ህዝብን የሚያኮራ ተግባር ነው። በሌላ በኩል ደግሞ የራስን የውስጥ ስራ
መስራት ሌላ የአገር መሪዎችን አገር ወዳድ ዜጎች ግዴታ ነው።
ከዚህ አንጻር በክረምት ወራት ችግኞችን በመትከል በበጋ ወራት ተንከባክቦ የተራቆተውን የአገሪቷን መሬት ደን ማድረግ የሚጠበቅ ተግባር ነው። ቀደም ባሉት ዓመታት በተናጠል በበረቱ ክልሎች ብቻ ይከናወን የነበረው የአካባቢ ጥበቃ ስራ አሁን ላይ አገር አቀፍ ንቅናቄ ሆኖ በየዓመቱ ቢሊዮን ችግኞችን መትከል ባህል እየሆነ መጥቷል። ይህ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ጥረት በመሆኑ ምስጋና የሚቸረው ነው።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአረንጓዴ አሻራ አረንጓዴ ተጋድሎ ዘንድሮ ሁለተኛ ዓመቱን አስቆጥሯል። ባለፈው ዓመት በአራት ቢሊዮን ችግኝ መትከል የተቋጨው የአረንጓዴ አሻራ ተጋድሎ፤ ዘንድሮም በአምስት ቢሊዮን ችግኝ ለመድገም ስራው ከተጀመረ አንድ ወር ተኩል ደፍኗል። ዘንድሮ በሦስት ወራት ውስጥ አምስት ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ውጥን ተይዞ በአንድ ወር ተኩል ውስጥ ብቻ አራት ነጥብ አንድ ቢሊየኑን መትከል ተችሏል። ይህ አረንጓዴዋን ኢትዮጵያ
ለሚናፍቅ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ትልቅ የምስራች ነው። ለዚህ ግብ መሳካት ሌት ተቀን ለደከሙ ሁሉ
ምስጋና ይገባቸዋል።“የአረንጓዴ አሻራን ጉዳይ እንደ ሁለተኛ ሳይሆን እንደ ዋነኛ ጉዳያችን መመልክት አለብን” የሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በኢትዮጵያ አረንጓዴ መሆን ብቻ የሚኩራሩና የሚያቆሙ እንዳልሆነ ከሰሞኑ በነበረ አንድ መድረክ ላይ ይፋ አድርገዋል። አገራዊ ልምዳችንን ወደ ጁቡቲ፣ ኬኒያ፣ ኤርትራ እና ሌሎችም የጎረቤት ሀገራት ማዳረስ እንዳለብን አመልክተዋል። ለዚህም እንዲረዳ ጎረቤቶቻችንንም ታሳቢ ያደረገ የችግኝ ማፍላት ዝግጅት ማድረግ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ራዕይ እውን የሚሆነው በእርሳቸው ጥረት ብቻ ሳይሆን በየደረጃው ያለ ኢትዮጵያዊ ሁሉ
በተለይም የዘርፉ ተዋኒያን የሚጠበቅባቸውን ማድረግና አገራቸውን፤ ሃላፊነት እንደሚሰማው ጎረቤት ደግሞ ጎረቤቶቻችን የበጎ ተሞክሮዎቻችን ተቋዳሽ ማድረግ ይገባናል።