እንደው እነዚህ ፈላስፎች የሚሉት ነገር አያልቅባቸው! ስለስንት ነገር ስንቱን ብለዋል መሰላችሁ! ስንቱስ እነሱ በሚያነሷቸው ሃሳቦች ተፅእኖ ስር ወድቋል?! ስንቱስ እነሱ በሚያነሷቸው ጥያቄዎች ተወዘጋግቧል?! ያው ምን ይባላል….ቤቱ ይቁጠረው ነው እንጂ! እኔም ተፅእኖ ስር ከወደቁት እና ከተወዘጋገቡት አንዱ አይደለሁ?…ኧረ ነኝ…እጅ ወደላይ!…አምኛለሁ!
ለዚህም ነው ለፅሁፌ መግቢያ ትሆነኝ ዘንድ በማለት የፈረንሳዊውን ፈላስፋ ቦነት (Bonnet) ምሳሌ ለመጠቀም የወሰንኩት። “አንድ ከእምነ በረድ የተሰራች የሴት ቅርፅ ያላት ሀውልት ነበረች። እናም ይህቺ ሀውልት ከማሽተት ክህሎት በመጀመር በተለያየ ጊዜ የተቀሩትን የመቅመስ፣ የመዳሰስ፣ የመስማት እና የማየት ክህሎቶች ሲሰጧት ጊዜ ሀውልትዋ ሀውልትነትዋን እርግፍ አድርጋ ትታ ነፍስ ዘራች፤ ነፍስ ከመዝራትም አልፋ ሃሳቦች እንዲሁም ስሜቶችን ማፍለቅ እና ማገናዘብም ጀመረች።”
ቦነት ይህን ምሳሌ ለመስጠት ምን አነሳሳው።ብትሉኝ! መልሴ ስለ አንድ ነገር የሚኖረን ግንዛቤ ከየት እንደሚጀምር በቀላሉ ለማስረዳት ስለፈለገ ይሆናል የሚል ነው። እናም ምሳሌው በአጭሩ ሲብራራ ለነገሮች የሚኖረን ምልከታ፣ ግንዛቤ፣ መረዳት እና ውሳኔ የሚመነጨው በስሜት ሕዋሳቶቻችን በኩል በሚገባው ወይም በሚመጣው መረጃ (sensation) ነው። እንዲሁም ይህ በስሜት ሕዋሳቶቻችን በኩል የሚገባው መረጃ አእምሮኣችንን (ማለትም አስተሳሰባችንን እና ባህርያችንን) የመቅረፅ ብቃት አለው የሚል ድምዳሜ ላይ ይረግጣል።
ውድ አንባብያን!.. የቦነት ሀውልት ታሪክን በልባችሁ ያዙና ቀጥሎ ስለምነግራችሁ ልብወለድ ታሪክ ለደቂቃ አስቡበት! ነገሩ እንዲህ ነው…አንድ ሰውዬ ነበረ። ይህም ሰው ምንም አይነት ጉዳት ያልደረሰበት ጤነኛ አንጎልም የነበረው ነው። [ልብ በሉ አንጎል ነው አእምሮ አይደለም]። አምስቱም የስሜት ሕዋሳቶቹም ጤነኛና በአግባቡ የሚሰሩ ነበሩ። ከእለታት አንድ ቀን ግን ይህ ሰው የአይን ብርሃኑን ያጣል። ምንም እንኳን የማየት ክህሎቱን ቢያጣም በሱ ፈንታ የተቀሩትን አራቱን የስሜት ሕዋሳቶቹን ክህሎት አሟጦ በመጠቀም መኖሩን ግን ቀጠለ። ይቺ ዓለም መቼስ ፍትሃዊነት ብሎ ነገር አልፈጠረባትም፤ የማየት ክህሎቱ አልበቃ ብሏት ብዙም ሳትቆይ የመስማት ክህሎቱንም ትነጥቀዋለች። ምስኪኑ ሰውየም ብዙም ሳያማርር አሜን ብሎ ተቀብሎ የተቀሩት የስሜት ሕዋሳቶቹ ላይ ጥገኛ በመሆን መኖሩን ቀጠለ።
ይሁን እንጂ ዓለም ሁለቱን የወሰደቻቸውን የስሜት ሕዋሳቶቹ አልበቃት አለ መሰለኝ በጊዜ ሂደት ተራ በተራ የተቀሩት ሶስቱ (የመዳሰስ፣ የማሽተት፣ የመቅመስ) ክህሎቶቹ በመጨረሻም የማስታወስ ችሎታውን ሳይቀር ወሰደችበት። ይህ ሰው ይች ዓለም ሳትወስድበት የቀረው አንድ ነገር ቢኖር የመናገር ችሎታውን ብቻ ነበር። ነገር ግን ይሄ ሰውዬ ምን ያውራ? ስላለፈ ህይወቱ አያወራ ነገር የማስታወስ ችሎታው ጠፍቷል፤ ስለ አሁን አያወራ ነገር አሁንን በተመለከተ ወደ አንጎሉ የሚሄድ መረጃ የለውም። እናም ውድ አንባብያን ምን አሰባችሁ? የዚህ ሰውዬ ህይወት ምን ሊመስል ይችላል ብላችሁ ታስባላችሁ? ይህ ሰውዬ እና የቦነት ሀውልት ይለያያሉ ወይስ ይመሳሰላሉ? በደንብ አስቡበትና መልሱን ለራሳቸሁ መልሱ።
የቦነት ምሳሌ እና የሰውየውን ልብ ወለድ ታሪክ የጠቀስኩት በስሜት ሕዋሳት በኩል ወደ አንጎላችን የሚገባው መረጃ ጠቀሜታ በቀይ እስክርቢቶ ላሰምርበት ስለፈለኩኝ እንጂ የመፈላሰፍ ወይም ልብ ወለድ ታሪክ የመፃፍ ፍላጎት አሳድሮብኝ አይደለም። ሊሰመርበት ይገባል ብዬ ያሰብኩት ሀሳብ ላይ ካሰመርኩ ዘንዳ አሁን እፅፍበታለሁ ብዬ ወደ ተነሳሁበት የአንጎል መረጃ ፍሰት እና አወቃቀር ሂደት ፅንሰ ሀሳብ ልግባ።
ይህ ሃሳብ በንድፈ ሃሳብነት ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሳይንሱ ማህበረሰብ ብቅ ያለው በሳይኮሎጂስት፣ ኦክፔሽናል ቴራፒስት እና የኒሮ ሳይንስ ተመራማሪ የነበረችው ጄን አይሪስ (ፒ,ኤች.ዲ) እ.ኤ.አ 1950ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ነበር። ዶ/ር አይሪስ ሃሳብዋን ወደ ንድፈ ሃሳብነት ለማሳደግ ለተከታታይ ሶስት አስርት ዓመታት በዚሁ ርእሰ ጉዳይ ላይ ጥናት አድርጋለች። በመጨረሻም በእንግሊዘኛው ‘’sensory integration’’ በማለት ሰየመችው።
ንድፈ ሃሳቡ የሚያውጠነጥነው አንጎላችን ከሁሉም የስሜት ሕዋሳት በአንድ ጊዜ የሚመጣለትን ለመቁጠር አዳጋች በሆነ መልኩ ብዛት ያለው መረጃ ፍሰቱን ጠብቆ እንዲሄድ የሚያደርግበት ሥርዓት ምንድን ነው።ይህን ብዛት ያለውን መረጃ አንጎላችን እንዴት ያዋቅረዋል።የአወቃቀር ሥርዓቱ ሲዛባስ እኛ ላይ የሚያስከትላቸው ጉዳቶች ምን ምን ናቸው።በዚህ ሥርዓት መዛባት ምክንያት የሚመጡ ችግሮችስ ሕክምናቸው ምንድን ነው።የሚሉት ጥያቄዎች ላይ ነው።
ውድ አንባብያን!……ከላይ የሰውየው ታሪክ ላይ ከአምስቱም የስሜት ሕዋሳት የሚመጣ መረጃ ላይ ብቻ ያተኮርኩት አብዛኛው ሰው በተለምዶ አምስት የስሜት ህዋሳት በሚል ስለሚያውቃቸው ነው። ነገር ግን ቀጥሎ ከማስተዋውቃቹህ ሁለት ተጨማሪ የስሜት ሕዋሳት ጋር በጠቅላላም ከሰባት የስሜት ሕዋሳት የሚመጣ መረጃ አንፃር በማየት ከላይ ያሉትን ሶስት ጥያቄዎችን በማብራርያ እመልሳለሁ።
ከሁለት ተጨማሪ የስሜት ሕዋሳት አንደኛው ቨስቲቡላር (vestibular) የሚባል ሲሆን በሁለቱም ጆሮዎቻችን የውስጠኛው ክፍል ይገኛል። የዚህ የስሜት ህዋስ የስራ ድርሻ አካላዊ ሚዛን መጠበቅ እና አካላችን ያለበት አቅጣጫ ከመሬት ስበት፣ ከአየር ግፊት እና ከመሳሰሉት ከባቢያዊ ሃይሎች አንፃር ወደ አንጎል መረጃ መላክ ነው።
ሁለተኛው ፕሮፕርዮሰብቲቭ (proprioceptive) የሚባለው የስሜት ሕዋስ ሲሆን የሚገኘውም በአጥንት መገጣጠሚያ ውስጥ ነው። የስራ ድርሻውም ጡንቻዎች የሚኮማተሩበት እና የሚለጠጡበት እንዲሁም በአጥንት መገጣጠሚያ ውስጥ የሚፈጠር የመታጠፍ እና የመታመቅን ክስተት በመከታተል ለአንጎል ስለ አካላችን አቀማመጥ እና አቋም መረጃ መላክ ነው።
ከላይ የጠቀስኳቸው ሁለቱ የስሜት ሕዋሳት “የቅርብ’’ (Near senses) እየተባሉ የሚጠሩ ሲሆን ይህም ስያሜ የተሰጣቸው በአካላችን ውስጥ ስለሚገኙ እና ለአንጎል የሚልኩት መረጃ ስለ አካላችን ብቻ ስለሆነ ነው። በተቃራኒው አምስቱ የስሜት ሕዋሳት ለአንጎል የሚልኩት መረጃ በከባቢያችን ስላሉ ነገሮች ወይም ሁኔታዎች ብቻ ስለሆነ ‘’የሩቅ’’ (Far senses) በሚል ስያሜ ይጠራሉ። የአንጎል መረጃ ፍሰት እና አወቃቀር ሂደት ራሱን የቻለ የአንጎል ውስጥ ጅማቶች / ነርቮች ተግባቦት ሂደት (Neurological/Neural communication) ሲሆን አንጎል በሰባቱም የስሜት ሕዋሳት በኩል ከባቢያችንን እና አካላችንን በሚመለከት የሚመጡለትን ስፍር ቁጥር የሌላቸውን መረጃዎች አግባብ ባለው መልኩ በማቀናጀት ከባቢያችን ውስጥ ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር አካላችንን ካለምንም እክል እንድንጠቀምበትና ባህሪያችንን እንድንገራበት የሚረዳን የአንጎላችን አሰራር ሥርዓት ነው።
ውድ የስነልቦና አምድ ተከታታዮች፣ መቼም ስለአንጎል አሰራ ዘርዝሮ መጨረስ ከባድ እንደሆነ እንገነዘባለን። ነገር ግን ከዛሬው ርዕሰ ጉዳያችን አንጻር አንጎላችን ይህን መረጃ በሥርዓቱ የሚያፈስበት እና የሚያዋቅርበት አሰራርን በተመለከተ ቀጣዩን ክፍል ሳምንት ይዤላሁ እቀርባለሁ። ቸር ሰንብቱ።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 24/2012
ሒሳቡ ሓድጉ
(ክሊኒካል ሳይኮሎጂስት)