መጽሐፈ ሔሮዳተስ ወይስ መጽሐፍ ቅዱስ?
“እግዚአብሔር ሰማይና ምድርን ከፈጠረ በኋላ ስለውሃው (የተፈጠሩት ፍጥረታት ውሃ ስለሚያስፈልጋቸው ማለታቸው ነው) ግዮን ብሎ አንደኛው የኢትዮጵያን ዓባይን ውሃ ነው እንዲፈስ ያደረገው። ይህም ዓለምን ሁሉ እየዞረ ያጠጣል ይላል። ዓለምን ሁሉ ከሚያጠጣው ከዚህ ውሃ ኢትዮጵያ አለመጠቀሟ ግን ለብዙዎች ስብራትና ውድቀት ነበር። ብዙ የኢትዮጵያ ልጆች ለስደት ተዳርገዋል። አሁን ግን ዘመን መጣ፣ ጊዜው ደረሰ፣ እግዚአብሔር ብሎ በራሷ በኢትዮጵያ ልጆች ተገነባ፣ የመጀመሪያውም ውሃ ተሞላ። ትልቅ ደስታ ነው የሆነልን” ወይዘሮ ደብሬ ታዬ የተባሉ የባህር ዳር ከተማ ነዋሪ የታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያውን ዙር የውሃ ሙሌት በሰሙበት ወቅት በስፍራው ተገኝታ ለነበረችው የአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ ዘጋቢ የተናገሩት ነው።
እርግጥ ነው ወይዘሮዋ እንዳሉት የዓባይን ወንዝ ምንነትና የማንነት በተመለከተ ሁለት ጥንታዊ የጽሑፍ ማስረጃዎች በመጽሐፍ ውስጥ ተሰነድው ይገኛሉ። አንዱ የታሪክ አባት በመባል የሚታወቀው የግሪካዊው የታሪክ ሊቅ የሄሮዳተስ መጽሐፍ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ በእግዚአብሔር መንፈስ መሪነት የተጻፈው ታላቁ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። ሄሮዳተስ “ግብፅ የናይል ስጦታ ናት” ሲል ታላቁ መጽሐፍ ደግሞ “የሁለተኛውም ወንዝ ስም ግዮን ነው እርሱም የኢትዮጵያን ምድር ሁሉ ይከብባል” ይላል።
ተፈጥሯዊ መልክዓ ምድራዊ ስሪቱን ስናጠናም ከሰማንያ ስድስት በመቶ በላይ የሚሆነው የዓባይ አካል መገኛው ኢትዮጵያ ውስጥ መሆኑን እናረጋግጣለን። እናም እንግዲህ የኢትዮጵያን ምድር ሁሉ የሚከበው ዓባይ አብዛኛው አካሉ የኢትዮጵያ ቢሆንም ወደ በረሃም ሄዶ ደረቅ ምድርን ያለመልማልና ለግብፅም “ስጦታ” ሆኗል ቢባል ከእውነታው ጋር የሚስማማ እንጅ የሚጣላ አይደለም። ታዲያ ይህን እውነት ታላቋ ባቢሎን፣ ኃያሉ የፐርሽያ ኢምፓየር፣ ህንድ፣ ግሪክ፣ ታላቁ የሮማን ኢምፓየርና ኃያሉ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ግዛተ አጼም ቢሆን ማንም ሊለውጠው አይችልም። ምክንያቱም ከሄሮዳተስም በላይ ታላላቆች ሊቀይሩት የማይችሉት የታላቁ መጽሐፍ ህያው ማስረጃ፣ ኃያላን ሊለውጡት የማይቻላቸው የኃያሉ እግዚአብሄር ኃያል ቃል አለበትና! ለዘመናት የኃያላን ቅኝ ግዛት የነበረችው ታላቋ አሜሪካም ብትሆን ይህንን ህያው እውነት የምትቀይርበት ምንም ኃይል የላትም! ምክንያቱም ዓባይ መነሻውም መድረሻውም ገነት እየተባለች የምትጠራው ውቢቷ ሃገራችን ኢትዮጵያ ናትና።
ከገነት የሚወጣውና ገነትን የሚያጠጣው ታላቁ ወንዝ ዓባይ ገና ሲፈጠር ጀምሮ የኢትዮጵያን ምድር ሁሉ እንዲከብብ ተደርጎ ነውና የተፈጠረው። እውነተኛ ስሙም ምድሯን ሁሉ እየዞረ እንዲያረስርሳትና እንዲያለመልማት የተፈጠረላት እናቱ ኢትዮጵያ የምትጠቀምበት ግዮን ነው። እናም ግብፃውያን የትናንቱን ግሪካዊው የታሪክ ፀሐፊ ሄሮዳተስን ሰምተው “ግብፅ የናይል ስጦታ ናት” ቢሉም ግዮን ግን የኢትዮጵያን ምድር ሁሉ የሚከብ የሕይወት አጥር፣ ከፍጡሩ ከሄሮዳተስ ሳይሆን ከሄሮዳተስ ፈጣሪ ከጥንት የተሰጣት መተኪያ የሌለው ውድ ስጦታዋ እንደሆነ ይዘነጋሉ ወይንም አውቀው ይክዳሉ።
ዓባይ፡– ከኢትዮጵያ ለግብፅ የተሰጠ ስጦታ
ዓባይ ከጥንት ሲፈጠር ጀምሮ ምድሯን ሁሉ ከብቦ ኢትዮጵያን እንዲያለመልም፤ እርሷኑ ምድራዊ ገነት እንዲያደርግ የተፈጠረ ቢሆንም ለዘመናት ሲሆን፤ የኖረው ግን ሌላ ነው። በዕድልም ይሁን በሌላ ባልታወቀ ምክንያት እስከአሁን ኢትዮጵያዊው ዓባይ ድረስ ዘመኑን ሁሉ ሲመግብ የኖረው እትብቱ የተገኘባትን ኢትዮጵያን ሳይሆን ሄሮዳተስ “ትንቢት” የተናገረላትን በሰው ላይ ብቻ ሳይሆን በፈጣሪው ላይም የታበየውን ፈርኦን አብቃይዋን ግብፅን ነው። እናም ዓባይ ለዘመናት ለግብፅ ምግቧም መጠጧም፣ እርሻዋም ኢንዱስትሪዋም፣ እራቷም መብራቷም ሆኖላት ኖሯል። በዓባይ ግድብ ላይ በገነባችው የአስዋን ግድብ ብቻ በዓመት እስከ 2100 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ታመነጫለች። በዚህም የህዝቧን የኃይል ፍላጎት በከተማ መቶ በመቶ በገጠር ከ90 በመቶ በላይ አሟልታለች። ከኤሌክትሪክ ኃይሉ በተጨማሪ በግድቡ ውሃ በመጠቀም መጠነ ሰፊ የመስኖ እርሻ ልማት ታከናውናለች። ዓመቱን ሙሉ ከፍተኛ ምርት ታመርታለች፤ ከራሷ አልፋም የግብርና ምርቶችንና
የኤሌክትሪክ ኃይል ወደ ውጭ በመላክ ከፍተኛ ገቢ ታገኝበታለች። ይህ ሁሉ ሲሆን፤ ግን ውሃውን ብቻ ሳይሆን አፈሩንም የምታገኘው ከታላቁ የዓለማችን ወንዝ ከኢትዮጵያዊው ዓባይ ነው።
የሚገርመው ግን ይህ ሁሉ መሆኑ አይደለም። ኢትዮጵያም የምድሯ ሲሳይ ዓባይ ከእርሷ በላይ ለግብፅ ሲሳይ በመሆኑ አንድም ቀን ከፍቷት አያውቅም፤ ግብፅ በመጠቀሟ ለምን ተጠቀመች የሚል ክፉ የቅናት መንፈስ አድሮባት አያውቅም። እንዲያውም ከአብራኳ በወጣ ሲሳይ እንደ ግብፅ ዓይነት በተፈጥሮው የተጎዳ ደረቅ ሃገር በመጠቀማቸው ስልጣኔን ከዓለም ቀድማ አጣጥማ ጥበቧንና ስልጣኔዋን ለቀሪው ዓለምም ያካፈለችው ታላቋ ኢትዮጵያ ደስ ይላታል። ማወቅ፣ መሰልጠን፣ ታላቅ መሆን ማለት ከራስ አልፎ ለሌሎች መኖር እውነተኛ ደስታ የሚገኘው ከ “ስጦታ” መሆኑን ስልጡኖቹ የኢትዮጵያ ህዝቦች ያውቁታልና!
ስጦታን ይዞታ ያደረገችው ግብፅ ኢትዮጵያውያን ቢበዛ እንኳን “ዓባይ፣ ዓባይ የአገር ለምለም፣ የአገር ሲሳይ፣ ያላገሩ ዘምሮ፣ ያለቅኝት ከርክሮ፣ ዓባይ ያላገሩ ኑሮ” እያሉ ሲሳያቸውን ከሃገሩ ውጪ በመኖሩ መገረማቸውን በቅኔ እየተቀኙ ወደ ቤቱ እስኪመለስ በትዕግስት ይጠብቁታል፣ በፍቅር ይዘምሩለታል እንጅ ሃገሩን ትቶ ግብፅን በመጥቀሙ ዓባይን ፈጽሞ አይጠሉትም። ምክንያቱም “ለሁሉም ጊዜ አለው” የሚለውን ጠቢቡን ቃል ትርጉም ጠንቅቀው የሚያውቁት አርቆ አሳቢዎቹ ኢትዮጵያውን ጊዜው ሲደርስ ዓባይም “ለሃገሩ እንደሚዘምር፣ በሃገሩ እንደሚያድር፣ ለሰው ሃገር የሆነውን ለሃገሩም ሲሳይ” መሆኑ እንደማይቀር አስቀድሞ ምስጢሩ ገብቷቸዋልና! እናም ከዘመናት በኋላ ጊዜው ሲደርስ እናት ኢትዮጵያ የአምላኳ ስጦታ የሆነውን ሲሳይዋን ዓባይን “ውዴ እስከ መቼ ድረስ ግንድ ይዞ ይዞራል እየተባለ ይተረትባሃል፣ እስከመቼስ ዓባይ ማደሪያ የለው ትባላለህ?” ከእንግዲህስ እስኪ ዙረቱ እንኳን ባይቀር በቤትህ እንኳን እደር፣ እናትህ ትፈልግሀለች” አለችው። ለዚህም በሀገሩ ላይ ሆኖ መገኛ ማህጸኑን እናቱን ኢትዮጵያን የሚያገለግልበት የክብር ማደሪያ የዙፋኑ መቀመጫ የሚሆን የግዮን ቤተ መንግሥት ልትገነባለት ወሰነች። በውሳኔዋ መሰረትም ኢትዮጵያ መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም የታላቁ የኢትዮጵያ ወንዝ የግዮን የሃገሩ ማደሪያ ቤተ መንግሥት ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ አስቀመጠች።
እነሆ በእናቱ ቤት አድሮ፣ በሰው ሃገር ብቻ ሳይሆን በሃገሩ ላይም ኖሮ፣ እንደ ግብፅ ሁሉ ለኢትዮጵያም ሲሳይ ለመሆን እትብቱ በተቀበረባት፣ ምድሯን ሁሉ ከብቦ በሚኖርባት በርስት ምድሩ ኢትዮጵያና በኢትዮጵያውን የግዮን የክብር ማደሪያ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እየተገነባ ይገኛል። ግድቡ ብዙ ውጣ ውረዶች አልፎ ዛሬ ላይ 72 በመቶ ግንባታውን አጠናቆ ከአራት ወራት በፊት መጋቢት 24 ቀን 2012 ዓ.ም ዘጠነኛ ዓመቱን በድምቀት አክብሯል። ታዲያ የሚገርመው እውነትም ከገነት የሚፈልቅ፣ ተዝቆ የማያልቅ የእግዚአብሔር ስጦታ በመሆኑ ባለማለቁ ነው እንጅ ዓባይን በብቸኝነት መጥምጣ ስትበላው የኖረችው ግብፅ ኢትዮጵያ በዓባይ ውሃ እንዳትጠቀም ቀንደኛ ተቃዋሚ ሆና መቅረቧ ነው። እናም ስጦታ ይዞታ የመሰላት ነውረኛዋ ግብፅ፣ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ተጸንሶ ከተወለደበት ጊዜ ጀምሮ አድጎ ተጠናቆ ለእርሷም የሚሰጠውን ጥቅም ለኢትዮጵያ እናቱም መስጠት እንዳይጀምር የምትፈልገው ግብፅ፣ ግድቡ እንዳይጠናቀቅና ዓባይ ለኢትዮጵያ መጥቀም እንዳይችል ሁሉ እያደረገች ትገኛለች።
እስከመጨረሻው እውነትን የተከተለው የኢትዮጵያ መንገድ
እናት ኢትዮጵያም ምንም እንኳን በልጇ መጠቀም ማንም ምድራዊ ኃይል የማይከለክላት ተፈጥሯዊ መብቷ ቢሆንም በኖረው የብዙ ሺህ ዘመናት የዳበረ የእኩልነትና ፍትሐዊነት ዕሴቷ በግድቡ ምክንያት ግብፅ ሊፈጠረብኝ ይችላል የምትለውን ማንኛውንም ስጋት በቅንነት ተቀብሎ ለማየትና በእርግጥ ችግር የሚፈጥር ሆኖ ከተገኘም ተገቢውን መፍትሔ ለማበጀት ከመጀመሪያው በሯን ክፍት አድርጋ እየሠራች ትገኛለች። በእርግጥ ቀድሞውንም ቢሆን ግብፅ አልጠግብ ባይነት ምቀኝነቷ ያንገበግባታል እንጅ ኢትዮጵያ አንጡራ ሲሳይዋን ዓባይን “በቤትህ እደር” ስትል ወደ ግብፅም ሆነ ወደ ሌሎች የታችኛው ተፋሰስ ሃገራት መሄድ የለብህም፤ እኔን ብቻ እንጅ እነርሱንም አትጥቀም ማለቷ አይደለም። እንዲያውም
ከዓባይ በሚገኘው ሲሳይ ሌሎችንም ለመጥቀም፣ በተለይ ደግሞ ግብፅን በየዓመቱ ከሚደርስባት በደለል መሞላትና በጎርፍ መጥለቅለቅ ስጋትና ጥፋት ሊያድን የሚችል ዓለም አቀፍ ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ ንድፍና ስልትን በመከተል ነው ግድቡን እየገነባች ያለችው።
በውሃ ኃይልና ግድብ ግንባታ ምህንድስና ትልቅ ስምና ዝናን ያተረፉ፤ ከምትተማመንባቸው ምዕራባውያን ሃገራት የተመረጡ፣ በዘርፉ አንቱ የተባሉ የፈረንሳይ፣ ደችና ጀርመን ዓለም አቀፍ አጥኝ ድርጅቶች ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከሳሿን ግብፅን ጨምሮ በአንድም የታችኛው ተፋሰስ ሃገር ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት እንደማያስከትል አረጋግጠዋል። እንዲያውም ለእርሷና ለሌሎች የተፋሰሱ የግርጌ ሃገራትም ከላይ በተገለጸው መልኩ ትልቅ ጥቅም ያለው መሆኑን ወራትን የፈጀ ጥናት አድርገው በአደባባይ መስክረዋል።
ድብቁ የግብፅ ጭንቀት፡- ሙሊቱ የሚያመነጨው “ኃይል”
በዚህች ምድር ላይ ከውሃ የበለጠ ሀብት የለም። ውሃ ዓይነተኛው የህይወት ምግብ እንደመሆኑ መጠን በዚህች ምድር ላይ የሚኖሩ ህይወት ያላቸው ፍጥረታት ተክሎች፣ እንስሳትና ሰው በሕይወት እንዲኖሩ አስችሏል። የሚተነፈስ አየር በሌለበት በህይወት መኖር እንደማይቻል ሁሉ ውሃ በሌለበትም እንዲሁ የሰው ልጅ ከጥቂት ቀናት
በላይ በህይወት መቆየት አይችልም።
ይሁን እንጂ እንደ ግሎባል ሪሰርች ፀሐፊው እዮሃኪም ሃጎፒያን ከሆነ በዓለም አቀፍ የሙቀት መጨመር፣ እየተስፋፋ በመጣው ድርቅ እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመጣው የውኃ ብክለት ምክንያት ከዓመት ዓመት ቁጥሩ እያሻቀበ ለሚሄደው የዓለም ህዝብ የበቂ ንጹሕ ውሃ አቅርቦት እጥረት በዚህ ዘመን እጅግ አስጨናቂ ከሆኑ የሰው ልጆች ፈተናዎች መካከል አንዱ ሆኗል። እ.ኤ.አ. በ 2015 የግብርና ምርት በመጨመሩ ምክንያት በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የውኃ ፍላጎት በ17 በመቶ ሊጨምር ችሏል። በተመሳሳይ በአውሮፓውኑ 2025 በመላው ዓለም እየጨመረ በሚሄደው የዓለም ህዝብ ቁጥር ምክንያት የውኃ ፍጆታ ፍላጎትን በ 40 በመቶ ሊያሳድገው እንደሚችል ተተንብዮአል። በመሆኑም ይላሉ ፀሐፊው፤ “በሃያኛው ክፍለ ዘመን ነዳጅ ወሳኙን ሚና ሲጫወት እንደቆየው ሁሉ በሃያ እደኛው ክፍለ ዘመን ደግሞ ውሃ እጅግ በጣም ውዱ የዓለማችን የተፈጥሮ ሀብት ይሆናል።”
ይህን ግምት ውስጥ በማስገባት ከዓመታት በፊት የተባበሩት መንግሥታት ንፁሑ የመጠጥ ውሃ ማግኘት ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብት መሆኑን ደንግጓል። የግሎባል ሪሰርቹ እዮሃኪም ሃጎፒያን እንደሚሉት ከሆነ በዓለም ላይ እስከ ዛሬ ድረስ በተደረጉ ጦርነቶች ከሞቱት ሰዎች ይልቅ በአሁኑ ሰዓት በውሃ ወለድ በሽታዎች ምክንያት እየሞተ ያለው የህዝብ ቁጥር ይበልጣል። ከንጹሕ ውሃ እጥረት ጋር በተያያዘ በዓለም ላይ በያንዳንዷ ሰዓት 240 ሕፃናት ይሞታሉ። በንጽሕና ጉድለት ሳቢያ በየዓመቱ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሕፃናት በኮሌራና በታይፎይድ በሽታዎች ይሞታሉ። እነኝህ የማይታመኑ የሚመስሉ አሳዛኝና አስደንጋጭ ሐቆች በምድር ላይ በህይወት ለመቆየት የንጹሕ ውሃ አቅርቦት ምን ያህል ወሳኝና አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑን ያረጋግጣሉ።
እናም ቀጣዩን የዓለም የኃይል ሚዛን የሚወስነው የውሃ ሀብትና አጠቃቀሙ ይሆናል። እንግዲህ የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ “ወዳጃችን” ግብፅን ዕረፍት የነሳት ይህ ሐቅ ለመሆኑ ጥርጥር የለውም። አልሆንላት ብሎ እንጂ እንኳንስ አድጋ በልጽጋ ኃያል ሆና ማየት ኢትዮጵያ የምትባል ሃገር ከነጭራሹ ባትኖር ደስ የሚላት እንደ ንጉሦቿ እንደነ ፈርኦን ልቧ በድንቁርና የደነደነው እቡይዋ ግብፅ ግድቡን በተመለከተ እውነቱን መቀበል ያቃታት ለዚህ ነው። “ግብፅ ዓባይን ያለ ስጋት ለመጠቀም ኢትዮጵያን ወርራ ህዝቦቿን ወደ እስልምና እምነት መቀየር አለባት። ይህ የማይቻል ከሆነም ሃገሪቱን በመንግሥት አልባነትና ባለመረጋጋት ውስጥ እንድትቆይ ማድረግ ይኖርባታል” የሚለው በአንድ ወቅት የግብፅ ፈርኦን አማካሪ የነበረው የዋርነር ሙዚንገር ምክር ለዚህ ዓይነተኛ ማሳያ ነው። ግብፆች የሚያስቡት እንግዲህ እስከዚህ ነው።
ዓባይን በተመለከተ አሁንም ድረስ ግብፅ የምትከተለው ፖሊሲም በዚሁ አረመኔያዊ ምክር ላይ የተመሰረተ መሆኑን ዓለም ይታዘበዋል። እናም በክፉ መካሪዋ ሃሳብ የጸናችው ግብፅ “ሌባ እንደ ራሱ፣ አመንዝራ እንደ ነፍሱ” እንዲሉ “ኢትዮጵያ የዓባይን ውሃ ገድባ ልታጠፋኝ ነው” የሚል የምቀኝነት ክሷን አጠናክራ የቀጠለችበት ከህዳሴ ግድብ ግንባታ ጀርባ ያለው ተደበቀው ፍርሐቷ ከዚህ አስተሳሰቧ የሚቀዳ ነው። የሚያሳስባት የግድቡ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ሳይሆን ኢትዮጵያ በውሃ ሀብቷ መጠቀም ስትጀምር በቀጣይ የምትፈጥረው ሃገራዊ ኃይልነት ነው።
ቀጣዩ የዓለማችን የኃይል ሚዛን ማስጠበቂያ ውሃ መሆኑን እሷ ብቻ የምታውቀው ይመስል ግብፅ የምትጨነቀው “እንግዲህ ኢትዮጵያ የውሃ ሀብቷን መጠቀም ከጀመረች በአፍሪካም ሆነ በዓለም ላይ ተገዳዳሪ ኃይል ሆና መምጣቷ ነው” የሚለው ግብፅን የሚያስጨንቀው እውነተኛ ምክንያት። ግብፅ ሆይ ጭንቀትሽ ይገባናል። ነገር ግን ብልህ አንች ብቻ አይደለሽም፤ ውሃ ኃይል መሆኑን እኛም እናውቃለን። ለዚያም ነው የውሃ ሀብታችንን መጠቀም የጀመርነው። እናም ግብፅ ሆይ ሺህ ጉድጓድ ብትቆፍሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እንዳሉት ግድባችንን ከመሙላት የሚያግደንም ማንም ምድራዊ ኃይል የለም! ለዚያም ነው የሞላነው! የኃያልነት ጉዟችንንም ጀምረናል፤ እንቀጥላለንም። ደጉ ነገር ግን ኃይላችንን የምንጠቀመው፤ ኃያል መሆንም የምንፈልገው አንች እንደምታስቢው ለጥፋት አይደለም። የእኛ ኃያልነት ሌላውን በማጥፋት ላይ የተመሰረተ አይደለም፤ በማልማት እንጂ።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 22/2012
ይበል ካሳ