ጥቅምት 14 ቀን 1965 ዓ.ም የታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ የሌባ ተባባሪ የሆነ ታክሲ ነጂ ቅጣት እንደተላለፈበት የሚገልጽ ዘገባ ይዞ ወጥቶ ነበር፡፡
ታክሲ ነጂው የሌባ ተባባሪ በመሆኑ 300 ብር ተቀጣ
ቦርጋ ቦንገር የተባለው ግለሰብ በተከሰሰበት የሌብነት ወንጀል በሁለት ዓመት እንዲቀጣ የተጉለትና ቡልጋ አውራጃ ፍርድ ቤት ባለፈው ሳምንት ፈረደ፡፡
ተከሳሹ በርጋ ቦንገር በደብረ ብርሃን መስመር ወደ ሰሜን ከሚመጡትና ከአዲስ አበባ ከሚመላለሱት የጭነት መኪናዎች ላይ ሌሊት እየወጣ ጨውና ቡና፣ ልዩ ልዩ ዕቃዎች እየሰረቀ በማውረዱ በቀረበበት ክስ መሰረት ምርመራው ተጣርቶ አውራጃው ፍርድ ቤት ከደረሰ በኋላ ራሱ ከማመኑም በላይ ድርጊቱ በማስረጃ ስለተረጋገጠበት በሁለት ዓመት እስራት እንዲቀጣ ተፈርዶበታል፡፡
እንዲሁም ሁለተኛው ተከሳሽ አሰፋ ታደሰ የደብረ ብርሃን ታክሲ ነጂ፣ ቦርጋ ቦንገር ከመኪናዎቹ ላይ እየሰረቀ የሚያወርዳቸውን ዕቃዎች በታክሲው እየተቀበለ ተባባሪና የጥቅሙ ተካፋይ ነው ተብሎ በቀረበበት ክስ የተመሰከረበት ስለሆነ 300 ብር መቀጫ እንዲከፍል ተፈርዶበታል፡፡
ታክሲ ነጂው ቀን በህዝብ ፊት የህዝብ አገልጋይ እየመሰለ፣ ሌሊት ግን ከህብረተሰቡ ተቃራኒ ሌቦች ጋር ግንኙነት በማድረግ በፈጸመው ወንጀል ፍርድ ቤቱ ያዘነበት ሲሆን፣ ወደፊት ግን ከእንደዚህ ያለ መጥፎ ተግባር እንዲወገድ ማስጠንቀቂያ የተሰጠው መሆኑን የችሎቱ ሰብሳቢ ዳኛ አቶ እንግዳ ገብሬ ገልጸዋል፡፡
************************
ጥቅምት 19 ቀን 1965 ዓ.ም የታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ልጃቸው ያስቸገራቸው እናት ክስ መስርተው ፍርድ ቤት ቅጣት እንዲያስተላልፍላቸው መጠየቃቸውን የሚገልጽ ዘገባ አስነብቦ ነበር፡፡
ልጃቸውን የከሰሱት እናት በፍርድ ሸንጎ ይቀጣ ይላሉ
አንዲት የ40 አመት ሴት ከወለዱት 21 አመት የሆነውን አንድ ልጃቸውን አዲስ አበባ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በውንብድና ወንጀል ከሰው በፍርድ ሸንጎ ይቀጣልኝ ሲሉ አቤቱታ አቅርበዋል፡፡
በኮልፌ ቀበሌ ኗሪ የሆኑት እመት ከበደች ሐበሻ ለፍርድ ቤቱ ባሰሙት የአቤቱታ ቃል ልጃቸው ብርሃኑ ንጋቱ ስራም ቢይዝ አልሰራም በማለት ገንዘብ አምጪ እያለ የሚያስቸግራቸው መሆኑን ገልጸው፤ ወደ ትክክለኛ ማህበራዊ ኑሮ እንዲመለስ ፍርድ ቤቱ እርምጃ እንዲወሰድ አመልክተዋል፡፡
ልጃቸውን ከሰውት ከፍርድ ሸንጎ ያቀረቡት አዛውንት ወደ ፍርድ ቤቱ ችሎት ቀርበው፣ ካለሱ በቀር ወራሽ የሌላቸው መሆኑን በመተንተን ልጃቸው ፈቃዳቸውን የማይፈጽም፤ በየጊዜው ሊደበድባቸውና ራሱን ለመጉዳት ኮረንቲ ለመጨበጥ የሚሞክር፤ የተገዛለትን ልብስ እየሸጠ በውስጥ ልብስ ብቻ የሚመጣ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ተከሳሹ በበኩሉ ምንም አይነት ወንጀል የማይፈጽም መሆኑን ገልጾ፣ እናቱ ሊከሱትና እስከዚህ ሊጨክኑበት የበቁት፣ ወላጅ አባቱ ከሞቱ በኋላ አንድ ሌላ ሰው ወደው የአባቱን ሀብት ስለሚያባክኑ ስለሚቀናቀናቸው ከአዲሱ ባላቸው ጋር በመተባበር በየጊዜው እየከሰሱ የሚያሳስሩት መሆኑን አመልክቷል፡፡
ልጁ እንደሚለው ከሆነ እናቱና እንጀራ አባቱ በመተባበር እየተከታተሉ ልዩ ልዩ ወንጀል በመፈለግ እያሳሰሩ ሊያጠቁት ከመብቃታቸው በስተቀር እነሱ ከታገሱለትና የማይከታተሉት ከሆነ ምንም ሀብት ሳይፈልግ እነሱ ካልደረሱበት ላለመድረስ በሕግ ፊት የሚምል መሆኑን አስረድቷል፡፡
አዲስ ዘመን ሐምሌ 22/2012
የትናየት ፈሩ