የበርካታ ሙያዎች ባለቤትና የጥበብ ሰው የነበሩት አዝማሪው፣ ባለቅኔው፣ ቀራፂው ሰዓሊው፣ ነጋዴው፣ መኪና አሽከርካሪው፣ መካኒኩና ፖለቲከኛው ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ የተወለዱት ከ143 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሐምሌ 20 ቀን 1869 ዓ.ም. ነበር።
ነጋድራስ ተሰማ ከአባታቸው ከአቶ እሸቴ ጉቤ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ወለተየስ ሐብቱ ሐምሌ 20 ቀን 1869 ዓ.ም ምንጃር ውስጥ ቀርሾ አጥር በተባለ ስፍራ ተወለዱ። የራስ መኮንን ጭፍራ የሆኑት አባታቸው መሰንቆ ተጫዋችም ነበሩ። አፄ ምኒልክ በ1879 ዓ.ም. ሀረርን ከውጭ ወራሪዎች ተከላክለው ከተማዋን ለመቆጣጠር በሚል የጦር አለቆቻቸውን ይዘው ወደ ሥፍራው በሄዱ ጊዜ ልዑል ራስ መኰንን በቡልጋና አካባቢዋ የሚገኙ የሠራዊት አባላትን ይዘው ተጓዙ:: ራስ መኮንን ወደ ሐረር በዘመቱበት ወቅት እርሳቸውን ተከትለው ወደ ሐረር የዘመቱት አቶ እሸቴ ኑሯቸውን በዚያው በሐረር አድርገው ሳለ ሕይወታቸው አለፈ።
ተሰማ የአባታቸውን ህልፈት ተከትሎ ወደ አዲስ አበባ መጡ። ታዳጊው ተሰማ ገና በልጅነታቸው በስዕል ችሎታቸው ተደናቂ መሆን ቻሉ። ለሙዚቃም የተለየ ፍቅር ነበራቸው። የሙዚቃ ፍቅር ያደረባቸው ከአባታቸው እንደሆነ ይገመታል። ሙሴ አርኖልድ ሆልስ የተባለ ጀርመናዊ በአዲስ አበባ የነበረውን ቆይታ ጨርሶ ወደ ሀገሩ ለመመለስ ለስንብት ወደ ዳግማዊ አጤ ምኒልክ ዘንድ ሲቀርብ ለንጉሰ ነገሥቱ አንድ ጥያቄ አቀረበላቸው። ሦስት ኢትዮጵያውያን ወጣቶችን ወደ ጀርመን ወስዶ በማስተማር ወደ ኢትዮጵያ ሊመልሳቸው እንደሚፈልግ ገለጸ። ንጉሰ ነገሥቱም የተሰማን የስዕል ችሎታና ቀራፂነት አስተውለው ነበርና “ያ ተሰማ እሸቴ እጁ ብልህ ስለሆነ መኪና መንዳትና መጠገን እንዲማር እርሱም ይሂድ” አሉ። በዚህ መንገድ ተሰማ ወደ ጀርመን አቅንተው ለሁለት ዓመታት መኪና መንዳትና መጠገን ተማሩ።
በጀርመን ቆይታቸው ትምህርታቸውን ከመከታተል ጎን ለጎን 17 የዘለሰኛና የመዲና ዘፈኖቹን በሸክላ ላይ አስቀርጸዋል። በዚህም በሸክላ ላይ ሙዚቃን በማስቀረጽ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ለመሆን በቅተዋል። ሙዚቃዎቹን ላስቀረጹበትም 17ሺ የጀርመን ማርክ ተከፍሏቸዋል። ከጀርመን መልስ የቤተ-መንግሥት መኪናዎች ኃላፊ ሆኑ። በርካታ ኢትዮጵያውያንንም መኪና ማሽከርከር አስተማሩ።
ነጋድራስ ከሙዚቃ ችሎታቸው በተጨማሪ በግጥም ችሎታቸውም የተደነቁ ነበሩ። ግጥሞቻቸው የሰምና የወርቅ ፍችዎች ያሏቸው፤ ጠንካራ መልዕክት የሚያስተላልፉና በአፃፃፍ ስልታቸው የተዋጣላቸው ስለመሆናቸው ታላላቅ ገጣሚያንና የጥበብ ሰዎች መስክረውላቸዋል። ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድኅን ‹‹ነጋድራስ ተሰማ የአማርኛን ውበትና ውስጠ ምስጢር በተሰጥኦ የተካኑ፣ የቋንቋውን ብልት ተንትነው የበለቱ፣ ሰዋሰውስ የሸዋ ሰው የሚያሰኙ ነበሩ›› በማለት አድናቆታቸውን ገልጸውላቸዋል። የነጋድራስ ተሰማ ግጥሞች ወቅታዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በመዳሰስ ትችት የማቅረብ ባህሪ ይንፀባረቅባቸዋል።
በዳግማዊ አፄ ምኒልክ፣ በልጅ ኢያሱ፣ በንግሥት ዘውዲቱና በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥታት የኖሩት ነጋድራስ ተሰማ በልጅ ኢያሱ ዘመን ጉልህ ፖለቲካዊ ተሣትፎ አድርገዋል። ለልጅ ኢያሱም የተለየ አክብሮት ነበራቸው። አብዛኛው በአዲስ አበባ ከተማ የነበረው የመሐል አገሩ መኳንንት ልጅ ኢያሱን ከሥልጣን ለማውረድ በተሰለፈ ጊዜ ሁሉ ነጋድራስ ተሰማ ግን የልጅ ኢያሱ ታማኝ ባለሟል ሆነው እስከ መጨረሻው ድረስ ዘልቀዋል። በልጅ ኢያሱ የአስተዳደር ዘመንም ሰይድ ባዝራ ከተባለ ግለሰብ ጋር በመሆን ከብት ወደ ውጭ አገራት እየላኩ በምትኩ ወደአገር ውስጥ የጦር መሳሪያ በማስመጣት የንግድ ስራ ላይ ተሰማርተው ነበር። ልጅ ኢያሱ ከዙፋን ሲወርዱም የልጅ ኢያሱ ወዳጆችና ደጋፊዎች ለግዞትና ለእንግልት ተዳረጉ። ነጋድራስ ተሰማም ጅማ ውስጥ በግዞት ተቀምጠው ቆዩ። ከግዞት በተጨማሪም ብዙ ንብረቶቻቸው ተወርሰውባቸው ነበር። ሳይወረስ የቀረው አዲስ አበባ ከተማ ራስ መኮንን ድልድይ ፒያሳ አካባቢ የሚገኘው ቤታቸው ብቻ ነበር። በጉምሩክ መሥሪያ ቤትና በአንድ ግሪካዊ ነጋዴ ቤት ያስቀመጡት 300ሺ ብር የሚያወጣ ጠመንጃና ጥይትም ሳይመለስላቸው ቀርቷል። በአባ ጅፋር ግቢ በግዞት ሰባት ዓመታትን ካሳለፉ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ።
በጣሊያን ወረራ ወቅት የፋሺስት አስተዳደር ከንጉሰ ነገሥቱ ጋር የተጣሉ ሰዎችን ማስጠጋት ጀምሮ ስለነበር ነጋድራስ ተሰማ የተወረሰው ቤታቸው ተመልሶላቸው አከራዩት። ይሁን እንጂ ቤታቸውን የተከራዩት ጣሊያኖች ለነጮች እንጂ ለጥቁሮች ቦታ ስላልነበራቸው ነጋድራስ ተሰማ ከዕለታት አንድ ቀን ምግብ ለመብላት ወዳከራዩት የራሳቸው ቤት ሲገቡ በጥቁርነታቸው መገለል ደረሰባቸው።
ፋሺስት ኢጣሊያ ተሸንፎ ንጉሰ ነገሥቱ አዲስ አበባ ሲገቡ ነጋድራስ ተሰማ ‹‹ከፋሺስት ኢጣሊያ ጋር ተባብረው መስራታቸውን እናውቃለን›› የሚሉ ከሳሾች በዙና ወሊሶ አካባቢ ለስድስት ዓመታት በግዞት እንዲቆዩ ተደረገ። ከግዞት እንደተፈቱም የሻሸመኔ የእንጨት ፋብሪካና የቲማቲም ድልህ ፋብሪካ ዳይሬክተር ሆነው ተሾሙ። በወንጂ ስኳር ፋብሪካ ሸንኮራ አገዳ መትከል የጀመሩት እርሳቸው ነበሩ። አገራቸው በግብርና ዘርፍ ታዋቂ እንድትሆንና የውጭ አገራት ጎብኚዎችን ዓይን እንድትስብም ጥረት ያደርጉ ነበር። በሶደሬ፣ በወንጂ፣ በወሊሶ፣ ፍልውሃና በቦኮ እንፋሎት ላይ ያከናወኗቸው ተግባራት ተጠቃሽ ናቸው።
የበርካታ ሙያዎች ባለቤት የነበሩት ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ አደርኛ፣ ጀርመንኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ጣሊያንኛና አረብኛ ቋንቋዎችን ይናገሩ ነበር። መጀመሪያ ያገቡት ወይዘሮ ፀሐይወርቅ አንዳርጌን ነበር። በኋላ ግን የመጀመሪያ ትዳራቸውን አፍርሰው ወይዘሮ ሙላቷ ገብረሥላሴን አግብተዋል። ከትዳራቸውም ሰባት ልጆችን አፍርተዋል። ከልጆቻቸው መካከል አራቱ የተወለዱት በግዞት ላይ ሳሉ ነው። ከልጆቻቸውም አንደኛው ታዋቂው የስፖርት ሰው አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ናቸው።
ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ልጃቸው መቶ አለቃ ኤልያስ ተሰማ በአውሮፕላን አደጋ መሞቱን መስማታቸው በፈጠረባቸው ድንጋጤ ለአምስት አመታት በጸና ታመው በህክምና ሲረዱ ከቆዩ በኋላ ጥቅምት 3 ቀን 1957 ዓ.ም አርፈዋል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 22/2012