የኃይማኖት አባትና የነፃነት አርበኛው ሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ በፋሺስት ኢጣሊያ ወታደሮች በጥይት ተደብድበው ሰማዕትነትን የተቀበሉት ከ83 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም ነበር።
አቡነ ጴጥሮስ በ1875 ዓ.ም በሰላሌ አውራጃ ፍቼ አካባቢ ተወለዱ። ከልጅነታቸው አንስቶ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ስርዓተ ያደጉት አቡኑ፣ በደብረ ሊባኖስ ገዳም ከንባብ እስከ ቅኔ ያሉትን ትምህርቶች ተከታትለው በአጭር ጊዜ ውስጥ አጠናቀዋል። ቀጥሎም በጎጃም ዋሸራ ቅኔ ተምረዋል። ወደ ጎንደር አቅንተውም ዜማን ጠንቅቀዋል። በኋላም ወደ ወሎ ተጉዘው የመጽሐፍት ትርጓሜ ትምህርቶችን ከተማሩ በኋላ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ተዘዋውረው አስተምረዋል። በአገልግሎት ከቆዩ በኋላ 1921 ዓ.ም ከግብፅ እስክንድርያ መንበረ ማርቆስ ቤተ-ክርስቲያን መዓረገ-ጵጵስና ተቀብለው ‹‹አቡነ ጴጥሮስ ጳጳስ ዘምሥራቀ ኢትዮጵያ ተላዌ አሰሩ ለአቡነ ኢየሱስ ሞዓ›› ተብለው በመንዝና ወሎ ሐገረ ስብከት ተሾሙ።
አቡነ ጴጥሮስ በመንዝና ወሎ ሐገረ ስብከት ከተሾሙ ከሰባት ዓመታት በኋላ በ1928 ዓ.ም ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ወረረች። አቡነ ጴጥሮስም ወራሪው የኢጣሊያ ጦር በኢትዮጵያውያን ላይ የሚያደርሰውን ግፍ ተመልክተው ከአርበኞች ጋር በመሰለፍ አርበኞችን ያበረታቱና መደገፍ ጀመሩ።
ኢትዮጵያውያን አርበኞች ኃይላቸውን አሰባስበው በአዲስ አበባ የሚገኘውን የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ሠራዊት ለመውጋት በወሰኑበት ወቅት አቡኑ የአርበኞቹን ኅብረት ለመባረክና ሞራላቸውን ለማጠንከር ወደ አዲስ አበባ ሄደው ነበር። በወቅቱ በነበረው የመረጃ እጥረትና የቅንጅት ጉድለት ምክንያት የታሰበው ጥቃት ባይሳካም “የመጣሁበትን ሳልፈፅም ወደኋላ አልመለስም፤ ብችል በአዲስ አበባም ጠላት በኢትዮጵያውያን ላይ እያደረሰ ስላለው ጉዳት ሕዝቡን በማትጋት በጠላት ላይ እንዲነሳ አደርገዋለሁ፤ ካልሆነም እዚሁ እሞታለሁ” በማለት ሕዝቡ ለፋሺስት እንዳይገዛና አስተዳደሩንም እንዳይቀበል ያስተምሩ ጀመር።
ይሁን እንጂ ጠላት በመላ ከተማው ያሰማራቸው በርካታ ባንዳዎች ችግር ፈጠሩባቸው። በዚህም ምክንያት ጳጳሱ እንዳሰቡት ሊንቀሳቀሱ ባለመቻላቸው በወቅቱ የኢጣሊያ እንደራሴ ለነበሩት ለራስ ኃይሉ እጃቸውን ሰጡ። ራስ ኃይሉም ለፋሺስቱ አስተዳደር የበላይ ለነበረው ለሮዶልፎ ግራዚያኒ አሳልፈው ሰጧቸውና የፋሺስት ጦር ቤተ መንግሥት ውስጥ አስገብቶ አሠራቸው።
ከዚያም ጳጳሱ የኢጣሊያን ገናናነት አምነው እንዲሁም የንጉሥ ኢማኑኤልንና የቤኒቶ ሙሶሎኒን ገዢነት ተቀብለው በሐይማኖታዊ ተልዕኳቸው እንዲሰብኩ ተጠየቁ። እርሳቸው ግን “የኢጣሊያን ገዢነት የተቀበላችሁ ሁሉ አወግዛችኋለሁ! የኢጣሊያን ገዢነት ከተቀበለ እንኳን ሰው ምድሯ የተረገመች ትሁን!” አሉ። እንዲፈፅሙ የተጠየቁትን ፍርጥም ብለው “እምቢ!” ያሉት አቡነ ጴጥሮስ ወደ ችሎት ቀረቡ። ለፍርድ የተሰየሙት ሦስት ዳኞችም ጳጳሱ በጥይት ተደብድበው እንዲገደሉ ፈረዱ።
የቀረበባቸውም ወንጀል ‘ሕዝብ ቀስቅሰዋል፣ ራስዎም አምፀዋል፣ ሌሎችንም አንዲያምፁ አድርገዋል›› የሚል ነበር። ዳኛውም ‹‹ካህናቱም ሆኑ የቤተ ከህነት ባለሥልጣኖች ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ቂርሎስም የኢጣሊያንን መንግሥት ገዢነት አምነው አሜን ብለው ሲቀበሉ እርስዎ ለምን ዐመፁ፣ ለምን ብቻዎን አፈንጋጭ ሆኑ?›› ሲል ጠየቃቸው። አቡነ ጴጥሮስም ‹‹አቡነ ቄርሎስ ግብፃዊ ናቸው፣ ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የሚገዳቸው ነገር የለም። እኔ ግን ኢትዮጵያዊ ነኝ። ሐላፊነትም ያለብኝ የቤተ ከርስቲያን አባት ነኝ። ስለዚህ ስለ ሀገሬና ስለ ቤተ ከርስቲያኔ እቆረቆራለሁ። ከዚህ በቀር ለእናንተ ችሎት የማቀርበው ነገር የለኝም። ለፈጣረዬ ብቻ የምናገረውን እናገራለሁ። እኔን ለመግደል እንደወሰናችሁ አውቃለሁ። ስለዚህ በእኔ ላይ የፈለጋችሁትን አድርጉ። ግን ተከታዮቼን አትንኩ›› አሉ።
ይህንንም ብለው በጥይት ተደብድበው ሲገደሉ እንዲያይ ተጋብዞ ለተሰበሰበው ሕዝብ የሚከተለውን ሕያው መልእከት አስተላለፉ።
‹‹አረማዊ የሆነው የፋሺስት መንግሥት ቤተክርስቲያንን ለማቃጠል፣ ሕዝበ ክርስቲያንን ለመግደል፣ ሃይማኖትን ለማጥፋት፣ ታሪካችንን ለማበላሸት የመጣ ነው እንጂ በጎ ለመሥራት እውነተኛ ፍርድ ለመስጠት ስላልመጣ ለዚህ ለግፈኛ አትገዙ።››
ወዲያውም ስምንት ወታደሮች በስተጀርባቸው ሃያ ርምጃ ርቀው ተንበርክከው በተጠንቀቅ ቆሙ። ወዲያው አዛዡ “ተኩስ” በማለት ትእዛዝ ሲሰጥ ስምንቱም ቢተኩሱባቸውም በስምንት ጥይት ሳይሞቱ ቀሩ። መሞታቸውንና አለመሞታቸውን ለማረጋገጥ ዶክተር ተጠራ። ዶክተሩም እንዳልሞቱ አረጋገጠ። ከዚያም ሌላ ወታደር በሦስት የሽጉጥ ጥይት ራስ ቅላቸውን መትቶ ገደላቸው። የብፁዕነታቸው አስክሬን ማንም እንዳይወስደው በአስቸኳይ ከአዲስ አበባ ውጭ ማንም በማያውቀው ቦታ በምሥጢር እንዲቀበር ተደረገ። በዚያች ሌሊት በአዲስ አበባ ውስጥ በየቤቱ ለቅሶና ዋይታ ሆነ። የእርሳቸው መስዋዕትነት የኢትዮጵያውያንን ጀግኖች እልህ አፋፋመው። የሰማዕቱን የአቡነ ጴጥሮስን ጀግንነትና ጽናት ስንቅ ያደረጉ ኢትዮጵያውያንም በፅኑ ትግላቸው ፋሺስትን አንበርክከው የኢትዮጵያን ነፃነት አስመለሱ።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 22/2012
የትናየት ፈሩ