በግለሰብ ይሁን በገንቢዎች አይታ ብንመለከተው ግድብ ለተመሳሳይ ዓላማ የሚሠራ ነው። ግድብ የውሃ ፍሰት ማስተዳደር፣ መምራት እና መከለል ላይ በብዛት ያተኩራል። በሌላም በኩል ግድቦች 20 በመቶ የዓለም የኤሌክትሪክ ኃይል እና 88 በመቶ ታዳሽ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጩት የሀይድሮ ኤሌክትክ ኃይል ማመንጫዎች የተሠሩባቸው የተለያዩ ግድቦች አሉ። በዓለም ላይ 845 ሺ ግድቦች እንዳሉ ይገመታል። አንዳንዶቹ በጣም አስገራሚ ግድቦች ናቸው። ከነዚህ ውስጥ የተወሰኑትን እንመልከት።
ባለሦስት ጎኑ ጆርጅ ግድብ
ይህ ግድብ የተገነባው በቻይና ሳንዶፒንግ ያንጌዚ ወንዝ ላይ ነው። ይህ ግድብ አስገራሚ ያደረገው ነገር በቻይና ባለ ሦስት የጎን ግድቦች በዓለም ትልቁ የኃይል ማመንጫ ግድብ በመሆኑ ብቻ አይደለም፤ ለዓለም የኤሌክትሪክ ኃይል ምንጭ በመሆኑም ይታወቃል። የግድቡ ግንባታ የመጀመሪያ እቅድ እ.አ.አ. ከ1932 ጀምሮ ቢወጣም ግንባታው ግን እአአ እስከ 1994 መጨረሻ ድረስ አልተጀመረም ነበር። ግድቡ እአአ እስከ 2011 ሙሉ በሙሉ እንዲጠናቀቅ እቅድ ቢያዝም፣ ማሳካት አልተቻም። አንድ ነጥብ 24 ሚሊዮን ሰዎችን ወደ ሌላ አካባቢ በማስፈር እየተገነባ ይገኛል።
ታፑ ግድብ
በብራዚልና በፓራጓይ መካከል ፓራና ወንዝ ላይ የተገነባ ግድብ ነው። ይህን ግድብ አስገራሚ ያደረገው እ.ኤ.አ. በ2000 ላይ ከ90ሺ ጊጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨቱ ነው፤ በወቅቱ በኃይል ማመንጫ የመጀመሪያውን ረድፍ ተቆንጥጦ ነበር። ግድቡ ከ196 ሜትር በላይ ቁመት ያለው ሲሆን፣ ይህም የ65 ፎቅ ያህል ቁመት ማለት ነው። ግድቡ 380 ማማዎችም አሉት፤ ለግንባታውም 12 ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ኮንክሪት ጥቅም ላይ ውሏል።
ጉሪ ግድብ
በቦሎቪያ ስቴት ቬንዝዌላ ካሮኒ ወንዝ ላይ የተገነባ ግድብ ነው። ግድቡ ወደ ሰማይ ከፍ ያሉ ግድግዳዎችን እና ግዙፍ ጀነሬተሮች የተተከሉበት ሲሆን ፣ከውጭ ሲታይ የግንባታው ስነጥበብ ልዩ ውበት አለው። አርቲስት ካርሎስ ክሩዝ ዴዝ በግድብ ውስጥ ከተተከሉት ማሽን ክፍሎች ውስጥ በአንዱ አዕምሮን የሚያድሱ ሥዕሎች ሠርቷል። አሌጀንድሮ ኦቶሮ ደግሞ በአቅራቢያው አንድ ግዙፍ የሚሽከረከር ቅርፃቅርፅ ሠርቷል። ግድቡ በቀን 300 ሺህ በርሜል ዘይት የሚያወጣውን ኃይል ያመነጫል።
ግራንድ ኩሊ ግድብ
በአሜሪካ ዋሽንግተን ኮሎምብያ ወንዝ ላይ የተገነባ ግድብ ነው። ግዙፉ ግድብ በመባልም ይታወቃል። በግብፅ የሚገኙ ፒራሚዶችን በሙሉ መያዝ የሚችል እና አንድ ማይል ርዝመት እና 503 ሜትር ስፋት ያለው ነው። ከመሬት ወለል 115 ሜትር ከፍታ ያለው ይህ ግድብ ከፍታው በምዕራብ አፍሪካ ኒጀር ከሚገኘው የኒጋራ ፏፏቴ ከሁለት እጥፍ ይበልጣል። ግድቡም በሙዚቃ ታሪክ ውስጥ የማይረሳ ሚና መጫወቱ ይነገራል። የአሜሪካ የኃይል ድርጅት ኮሚሽነር ውዲ ጉትሬ ስለ ግድቡ እ.አ.አ በ1940ዎቹ መጀመሪያ ላይ የዘፈን ግጥሞች ፅፎ ነበር። ዘፈኖቹ ‹‹ሮል ኦን፣ ኮሎምቢያ ፣ ሮል ኦን›› እና “ግራንድ ኮሊ ግድብ” ተጠቃሽ ናቸው።
ሳይያኖ ሹሸንስካይ ግድብ
ካካስያ ሩስያ የንሲ ወንዝ ላይ የተገነባ ግድብ ነው። የሩሲያ የሳይያኖ-ሹሽንስካይ ግድብ ኤሌክትሪክ በማመንጨት ደረጃን ላይዝ ይችላል፤ በጥንካሬው ግን የሚደርስበት እንደሌለ ይነገራል። በሬክተር ስኬል ስምንት የተገመተ የመሬት መንቀጥቀጥን የመቋቋም ችሎታ ያለው ሲሆን፤ በዚህም በጊኒየስ መጽሐፍ ውስጥ የዓለም ሪኮርድ ሆኖ ተመዝግቧል። በእ.ኤ.አ. 2009 ላይ በተከሰተ ፍንዳታ የ 75 ሰዎች ሕይወት የጠፋ ሲሆን፣40 ቶን ዘይት ወደ ወንዙ መፍሰሱ ይታወሳል።
ክራንሶንያርስክ ግድብ
ግድቡ የተገነባው በዲቮንጎርስክ ሩስያ የንሲ ወንዝ ላይ ነው። ግድቡ የሩሲያ ጎረቤቶች ሳይፈቅዱ የተሠራ ነው። በአካባቢው ያለው የተለያየ ዓይነት እፅዋት እና ግድቡ በአካባቢው የአየር ንብረት ላይ ለውጦች እንዲታዩ አድርገዋል። ይህም አካባቢው ከወትሮው የበለጠ ሞቃታማ እና እርጥበት አዘል እንዲሆን ማድረግ ያስቻለ ሲሆን፣የሳይቤሪያን የበረዶ ሽፋን በመቀነስ ጥሩ የአየር ሁኔታ እንዲኖር እያደረገ መሆኑ ይገለጻል።
የአሸዋ ግድብ
ከእ.አ.አ 1995 ጀምሮ ኬንያ 500 የአሸዋ ግድብ የሠራች ሲሆን፤ ግድቦቹ 50 ሜትር ርዝመትና ከሁለት እስራ አራት ሜትር ከፍታ አላቸው። ግድቦቹ ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫነት ሳይሆን በርጥበታማ ወራት ዝናብን ለማቆር ጥቅም የሚሰጡ ናቸው።
ነገር ግን ግድቦቹ በዝናብ ወቅት የመቀበር ዕድል ይገጥማቸዋል። የዝናብ ውሃን ለማቆር ከዚህ በተሻለ መንገድ ግድብ መሥራት ይጠበቅባቸዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ
ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ እየገነባችው የምትገኘው ይህ ግድብ ግንባታው ሲጠናቀቅ በዓለም ሰባተኛ በአፍሪካ አንደኛ ደረጃን ይይዛል። ግድቡ ከአምስት ሺህ በላይ ሜጋ ዋት ያመነጫል። ለግንባታው በ2003 ዓ.ም 80 ቢሊዮን በላይ ወይም ከአራት ቢሊየን ብር በላይ የተያዘለት ሲሆን፣ ግንባታ ከተያዘለት ጊዜ የዘገየ እንደመሆኑ ወጪው እንደሚጨምር ይጠበቃል። በግንባታ ወቅት በብዙ ሺ ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የሥራ ዕድል እየፈጠረ ነው፤ ግንባታው ተጠናቆ ወደ ሥራ ሲገባ ደግሞ ለ15 ሺህ ያህል ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል።
ግድቡ 70 የሚደርሱ ደሴቶች የሚፈጠርበት እንደሚሆን በቅርቡ የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ። ለዓሣ ልማት፣ ለውሃ ላይ ትራንስፖርት፣ የአካባቢውን የአየር ፀባይና ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ ለማሻሻል ፋይደው ከፍተኛ መሆኑ እየተገለጸ ነው። ከአገራት /ሱዳን፣ጅቡቲ፣ ኬንያ../ የኢኮኖሚ ዕድገት ጋር ቀጥተኛ ትስስር ይኖረዋል።
የግድቡ ግንባታ በአሁኑ ወቅት 74 ነጥብ 5 ከመቶ የደረሰ ሲሆን፣ የመጀመሪያው የውሃ ሙሌትም በተሳካ ሁኔታ ተፈጽሞ 4 ነጥብ 9 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ መያዝ ተችሏል። በሚቀጥለው መጋቢት በሁለት ተርባይኖች ኤሌክትሪክ የማመንጨት ሙከራ የሚካሄድ ሲሆን፤ በሰኔ ወር ላይ ደግሞ ኤሌክትሪክ የማምረት ሥራው ይጀመራል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 21/2012
መርድ ክፍሉ