በአርሲ ዞን የሚከናወኑ የግብርና ሥራዎች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ተስፋ ሰጪ ናቸው

ሌሙና ብልብሎ፡- በአርሲ ዞን በሌሙ ብልብሎ ወረዳ የሚከናወኑ የግብርና ሥራዎች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ለሚደረገው ጥረት ስኬት ተስፋ ሰጪ መሆናቸው ተገለጸ። በወረዳው በመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት አዘጋጅነት የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የመስክ ጉብኝት እየተደረገ ነው።

በጉብኝቱ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ደኤታ አቶ ከበደ ዴሲሳ እንደገለጹት፣ መንግሥት ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ብሎም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በርካታ ጥረቶች እያደረገ ነው።

በተለይ የሌማት ትሩፋት ከከተማ እስከ ገጠር ትልቅ የሥራ ባሕል መፍጠሩን፣ ሕዝቡ ማሳውን ተግቶ በማልማት ከራሱ አልፎ ለገበያ የሚቀርብ ምርት እያመረተ መሆኑን አስታውቀዋል። የሕዝቡን የአመጋገብ ሥርዓት ከማሻሻል ባሻገር  ሀገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት ጉልህ ድርሻ እያበረከተ ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት የአርሲ ዞን በወተትና ወተት ተዋጽኦዎችን ራስን ከመቻል አልፎ ለመሐል ገበያ ማቅረብ ፤ ከውጭ ሲገባ የነበረውን የቢራ ገብስ በሀገር ውስጥ ማምረት ችሏል ይህም ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲው ትክክለኛ እና ውጤታማ መሆኑ ትልቅ ማሳያ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ቡናና፣ ወርቅ፣ የቅባት እህሎችንና ሌሎች ምርቶችን ወደ ውጭ የምትልክ ሀገር መጀመሪያውኑ የገብስ ቢራን ከውጭ ለማስገባት መገደድ እንዳልነበረባት አመልክተዋል።

የአርሲ ዞን ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ገና መሐመድ በበኩላቸው እንደገለጹት፣ በንድሮው ዓመት በዞኑ በአጠቃላይ ከ930ሺህ ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኗል ፤ ከዚህም 29 ማሊዮን ኩንታል ምርት ይጠበቃል።

በዋናነት የመንግሥት የትኩረት አቅጣጫ የሆነው የሰንዴ ምርት በ451 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን 16 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ጠቅሰው፤ ከውጭ ሲገባ የነበረውን የቢራ ገብስ ለማስቀረት 177ሺህ ሄክታር መሬት የቢራ ገብስ በመዝራት 6.9 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ አስታውቀወል።

አርሶ አደሩ በክላስተር የቢራ ገብስ እያመረተ በጥሩ ዋጋ ለገበያ ከማቅረብ በዘለለ የቢራ ገብስ ዘር በማባዛት እየሸጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

አርሶ አደር ግርማ ከበደ፣ የቢራ ገብ በክላስተር በማምረት ኑሮአቸውን ካሻሻሉት አርሶ አደሮች አንዱ ናቸው ፤ በክላስተር ከሚለማው የብራ ገብስ ከአንድ ሄክታር

መሬት 50 ኩንታል ምርት እንደሚገኝ ተናግረዋል። የቢራ ገቢስም ለምግብ ከሚውለው ገብስ ዋጋው ከፍ ስለሚል ኑሮአቸውንም እየቀየረ መሆኑን ገልጸዋል።

በተመሳሳይ መልኩ የሌሙ ብልብሎ ወተት አምራች ማሕበር ሰብሳቢ አቶ ሙሉጌታ ቱፋም፤ አርሲ እምቅ የወተት ሀብት ቢኖረውም ቀደም ሲል በገበያ እጦት ምክንያት ተጠቃሚ አለመሆኑን ጠቁመዋል።

አሁን ላይ ማሕበር በመቋቋሙ ከእርሶ አደሮች ጥራት ያለውን ወተት አንድ ሊትር በ45 ብር እየተረከበ በቀጥታ ለአዲስ አበባ ገቤ እየቀረበ መሆኑን አመልክተው ፤ ማሕበሩ የተቋቋመው ገና ሶስት ወር ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ አስር ሚሊዮን ብር ካፒታልና 642 አባላት እንዳሉት አስታውቀዋል።

አርሶ አደር ደበሌ ቱራ የማሕበሩ አባል ናቸው ፤ ከዚህ ቀደም ለግል ፍጆታ ከመጠቀም ውጭ ወተት ለገበያ እንደማያቀርቡ ገልጸው፤ አሁን ግን በቀን 72 ሊትር ወተት ለማሕበሩ እያቀረቡ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የሚዲያ ባለሙያዎቹ የአርሲ ዞን ሌሙና ብልብሎ ወረዳ ግብርና ሥራዎችን በተለይ የከብት እርባታና በቢራ ገብስ

የለማውን ማሳ ጎብኝተዋል።

ዋቅሹም ፍቃዱ

አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You