የቴክኖሎጂ ዕድገት ሲባል ቅድሚያ አዕምሮ ላይ የሚመጣው የኤሌክትሮኒክስ ኢንዱስትሪው ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በግንባታው ዘርፍም አዳዲስ ፈጠራዎች በመምጣት ላይ ናቸው። ይህም ዘርፉን በፈጠራው ረገድ ቀዳሚ እየሆነ እንዲመጣ እያረገው ይገኛል።
በአሁኑ ወቅት የግንባታው ኢንዱስትሪ የሰለጠነ የሰው ኃይል፣አዲስ ዘላቂ የሆነ ህግ፣ የቴክኖሎጂና የሶፍትዌር ዕድገት ለውጥ አለመኖር እንዲሁም የቀጣይ የዘርፉ አቅጣጫ አለመታወቅ ፈተና እንደሆኑበት መረጃዎች ያመለክታሉ። እንዲያም ሆኖ ግን በሮቦት በመታገዝ የሚሠራው 3ዲ የቤት ህትመት ቴክኖሎጂ በፍጥነት ማደግ ዘርፉን በመታደግ ላይ ይገኛል። በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት ደግሞ የግንባታውን ዘርፍ አንድ ደረጃ የሚያሳድጉ አዲስና የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎች ተፈጥረዋል። ከእነዚህ የግንባታ ቴክሎጂዎች የተወሰኑትን ይዘን ቀርበናል።
ኤል. ዲ. ኤ. አር
ኤል. ዲ. ኤ. አር ወይም ለብርሃን መለያ መሳሪያ ምስጋና ይግባውና በዚህ ቴክኖሎጂ አማካይነት የግንባታ እቃዎችን ለመቃኘት፣ የሥራ አካባቢን ለመቆጣጠርና የ3ዲ ምስሎችን በቀላሉ ለማምረት ይቻላል። ቴክኖሎጂው በግንባታ ቦታዎች ሰዎች ተራርቀው እንዲሠሩና በሥራ ላይ ሊፈጠር የሚችለውን ጉዳት በመቀነስ በኩልም አስተዋፅኦ ያደርጋል። የዚህ ቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪ በአሜሪካ ሁለተኛው አደገኛ ሥራ ተብሎ ይነገራል። ኤል.. ዲ ኤ. አር በተወሰኑ ሁኔታዎች ላይ የመሥራት አቅሙ ውስን ነው። ኤል.. ዲ ኤ. አር በከባድ አቧራማ ፣ በዝናብ፣ በበረዶና በጭጋግ ቦታዎች የሚሰጠው አገልግሎት ግን አነስተኛ ነው።
ሂማኖይድ ላቦርስ
አብዛኛዎቹ በሰው ኃይል የሚሠሩ ኢንዱስትሪዎች ችግር እየገጠማቸው ላለው የሰው ኃይል እጥረት ምላሽ ለመስጠት የጃፓን ተመራማሪዎች ‹‹ኤች አር ደብሊው 5ፒ›› የተሰኘውን ሃርድዌር ሮቦት ሠርተዋል። ሮቦቱ መሰረታዊ የተባሉ የጉልበት ሥራዎችን ማከናወን ይችላል። የሮቦት ሠራተኞቹ የተወሰነ አውቶሜትድ የሆነ ማሽን የተገጠመላቸው ሲሆን፣ ለመንቀሳቀሻነትም ጎማ መሰል መንሸራተቻ ተዘጋጅቶላቸዋል። ሮቦቶቹ ሰው ሊሠራቸው የሚችላቸውን ሥራዎች መተካት ችለዋል።
የሮቦቶቹ መፈጠር በአንድ በኩል አደገኛ ሥራዎችን ለማከናወንና ሠራተኞችን ከጉዳትና ከአደጋ ለመከላከል የሚረዳ ቢሆንም፣ የጉልበት ሠራተኞችን ከሥራ ውጪ ሊያደርግ ይችላል የሚል ስጋት አሳድሯል። ለዚህም የኢንዱስትሪ አመራሮች ቀደም ሲል የሠራተኞች እጥረት ባጋጠማቸው መስኮች ሠራተኞችን በማሰልጠን ለማቆየት ሰፊ እንቅስቃሴ ጀምረዋል።
ድሮን
በግንባታው ኢንዱስትሪ ውስጥ ከሚጠበቁት የቴክኖሎጂ ዕድገቶች መካከል የድሮን ቴክኖሎጂ በጣም ታዋቂ ሊሆን ይችላል። እ.ኤ.አ. በ2017 የሥራ ቦታዎች ላይ የድሮን አጠቃቀም በአንድ ዓመት ውስጥ በ239 በመቶ አድጓል። የኮንስትራክሽን ድሮኖች ሠራተኛን ለመቆጣጠር፣ የሥራ ዕቃዎች እንዳይሰረቁ ለመከታተል እንዲሁም የሥራ ቦታን ደህንነት ለማስጠበቅ ጥቅም ላይ ይውላሉ። በሌላም በኩል የካርታ ሥራዎች ላይ ወጣ ገባ መሬቶች ላይ ልኬት ለማወቅ ያገለግላሉ።
ስማርት ጫማ
ሌላ ተለባሽ የቴክኖሎጂ ዕድገት ስማርት ጫማ ሲሆን፣ የሠራተኛን ድካም ለመለካት፣ በአደጋ ጊዜ የመጀመሪያ ምላሾችን ለመስጠት እና ሠራተኞችን ከተሽከርካሪ አደጋዎች ለመከላከል ያስችላል። ስማርት ጫማዎቹ በሠራተኛው ዕርምጃዎች በሚመነጭ ኃይል የሚሠሩ ሲሆን፣ ሠራተኞች ወደ ጣቢያው ሲገቡ ወዲያውኑ ለይተው የሚያሳውቁ እና ለጣቢያ አስተዳዳሪዎች በተንቀሳቃሽ መሣሪያዎች ላይ ሥራዎችን ለማሠራት የሚያስችሏቸው ቴክኖሎጂ የተገጠሙላቸው ናቸው። ስማርት ጫማዎቹ በግንባታ ጣቢያዎች ላይ ብቻ ሳይሆን በወታደራዊ መከላከያ እና የመጀመሪያ ምላሽ ሰጭ አካባቢዎች በመጪዎቹ ዓመታት ሊስፋፉ ይችላሉ።
ስማርት መሠረተ ልማት
የመቆጣጠሪያ መዋቅር ማለትም በሄክሳጎንና በጂኦ ሲስተም የተሠሩ የግንባታ ሥራዎችን ጥንካሬና ድክመት ለመለየትና ለሰው ዓይን ሳቢ ለማድረግ ቴክኖሎጂዎች ጥቅም ላይ ይውላሉ። እነዚህ መቆጣጣሪዎች የመፈጠራቸው ዋነኛ ጥቅም የግንባታ መዋቅር ችግሮችን ቀደም ብሎ ለማወቅ ነው። ይህም የግንባታ ጣቢያው ባለቤት በጣቢያው አደገኛ ብልሽቶች ከመከሰታቸው በፊት አስፈላጊውን ጥገና ለማከናወን የሚያስችሉ የግንባታ ሠራተኞችን እንዲያመጣ ያስችለዋል። በግንባታ ወቅት በሠራተኞች ላይ ሊከሰት የሚችል ናዳን እና የመሳሰሉትን አደጋዎች ተጋላጭነትን በመቀነስ የሠራተኞቹን የጥንቃቄ አስተማማኝነት ለመገምገም ሊያገለግል ይችላል።
ቨርችዋል አጉሜንትድ ሪያሊቲ
የአየር ኃይልና የመንገደኞች አውሮፕላን አብራሪዎች ምስለ በረራ በመጠቀም ትምህርት እንደሚሰጡ ሁሉ፣ ይህ ዓይነቱ ስልጠና በአሁኑ ወቅት ደግሞ ለመሳሪያ ኦፕሬተር ስልጠና ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል። ምናባዊ የእውነታ ስልጠና ከቪዲዮ ወይም ከስርዓተ-ትምህርቱ የበለጠ ሳቢ ነው። የበለጠ ትክክለኛ እና አጓጊ የዝግጅት አቀራረብ ስለሚኖረው አንድ ግለሰብ የተማረበትን ደረጃ የበለጠ እንዲያውቅ ያስችለዋል። በቨርችዋል ሪያሊቲ የመሣሪያ ኦፕሬተሮች ስልጠና በተፈጥሮ አደጋ ወቅት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ መሳሪያዎችን የሚጠቀም ሲሆን፣ በዚህም በጣም አደገኛ የሚባሉ ሥራዎችን እንዲያካሄዱ ያስችላቸዋል።
ቨርችዋል ሪያሊቲ የዲጂታል ልምድን የሚጠይቅ ሲሆን፣ ተጨባጭ እውነታ በእውነተኛ-ዓለም ሁኔታ ውስጥ የሚተገበርበት ነው። በቨርችዋል ሪያሊቲ አማካኝነት ሠራተኞች ሌንሶችን ወይም በካሜራ የታሸገ ተንቀሳቃሽ መሣሪያን በመጠቀም ጣቢያ ላይ እያሉ እንቅስቃሴዎችን ማየት ይችላሉ። ይህ ማለት አንድ ሥራ ተቋራጭ ቤቱ ሆኖ በግንባታው ቦታ ላይ የሚሠሩ እንቅስቃሴዎችን መመልከት ይችላል ማለት ነው፤ የፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ዲዛይኖችን በመጠቀም የእቅድ ማሻሻያዎችን ሊያደርግ ያስችለዋል። በቨርችዋል ሪያሊቲ ቴክኖሎጂ በበለጠ ትክክለኛ የሕንፃ ግንባታ ዕቅድ እንዲኖር የ2 ዲ አምሳያዎችን በ 3 ዲ ዕቅድ ላይ ለማመንጨት አስችሏል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 21/2012
መርድ ክፍሉ