ከአስራ አንድ ጊዜ ወድቆ መነሳት በኋላ የተገኘ የስኬት መንገድ

ሸዋሮቢት አካባቢ ተወልዶ ያደገው የዛሬው የስኬት እንግዳችን በትምህርትና በሥራ ምክንያት ከትውልድ አካባቢው ርቆ በመጓዝ የተለያዩ የሕይወት ተሞክሮዎችን አግኝቷል። ከቦታ ቦታ መንቀሳቀሱ ከብዙ ሰዎች ጋር እንዲተዋወቅ፣ ከእነሱም ብዙ እንዲማር አስችሎታል።

ለመማር፣ ለመለወጥና ለማደግ ከነበረው ጉጉት የተነሳም ጥቂት የማይባሉ የንግድ ሃሳቦችን በማመንጨት በርካታ የራሱን ስራዎች ለመስራት ሙከራዎችን አድርጓል። ከብዙ ሙከራዎች በኋላም አዲስ የንግድ ሃሳብን ተግባራዊ በማድረግ ዛሬ ላይ ውጤታማ መሆን ችሏል።

የዛሬው ባለስኬት አቶ በላይ ሞርዴ ይባላል፤ የበላይ አትክልትና አስቤዛ ማዕከል መስራችና ባለቤት ነው። እሱ እንደሚለው፤ 11 የንግድ ሀሳቦችን ጀምሮ በአስራ አንዱም ሳይሳካላት በኪሳራ ወጥቷል። ሁሉም የንግድ ስራዎቹ / ቢዝነሶቹ / የከሰሩት በእሱ ስህተት እንደሆነ ያምናል። የዚህ ዋናው ምክንያት በወቅቱ የነበረው ጉዞ በስሌት ሳይሆን በስሜት፣ በጥናት ሳይሆን በፍላጎት፣ ከማይመጥነው ሰው ጠቃሚ ያልሆኑ ልምዶችን በመኮረጅ እና አስፈላጊ የሆኑ ጥናቶችን በተገቢው መንገድና በጊዜው ማከናወን አለመቻሉ ነበር። ይህም ለንግድ ሀሳቦቹ አለመሳካትና ለኪሳራ ዳርጎታል።

ይሁን እንጂ አቶ በላይ አስራ አንዱ የንግድ ሀሳቦች ላይ የፈጠረውን ስህተት በማረም አስራ ሁለተኛውን ንግድ ውጤታማና ስኬታማ ማድረግ ችሏል። ለዚህም በዋናነት አስፈላጊ የሆነውን የቢዝነስ ጥናት ጊዜ ወስዶ አካሂዷል። ጥናቱም አንድ ዓመት ተኩል ጊዜ የወሰደና ያለማቋረጥ ሌትና ቀን የተደከመበት ሲሆን፤ በጥናቱ መሰረት በላይ አትክልትና አስቤዛ ማዕከል የዛሬ ሰባት ዓመት ዕውን መሆን ችሏል። የአስር ዓመት የንግድ እቅድ የተሰራለትና አምስት ፕሮጀክቶችን በውስጡ ያካተተው በላይ አትክልትና አስቤዛ በአሁኑ ወቅት በስኬት ጎዳና እየተጓዘ ነው።

‹‹ለማንኛውም ሥራ ውጤታማነትና ስኬት አምስት የንግድ ሕጎች ወሳኝ ናቸው፡፡›› የሚለው አቶ በላይ፣ እሱ በእነዚህ ሕጎች መጠቀሙን ይናገራል። ሕጎቹ መፈለግ፣ መጀመር፣ ማመን፣ መጽናትና መተግበር መሆናቸውን ጠቅሶ፣ ከእነዚህ ውጭ ያለው ግብዓት ገንዘብን ጨምሮ ንግዱን ሊያግዙና ለያፋጥኑ ይችሉ እንደሆነ እንጂ መሰረት ሊሆኑ አይችሉም ይላል። እሱ እንደሚለው፤ ሰዎች አንገብጋቢ ጉዳያቸውን ነገ ዛሬ ሳይሉ መጀመር ይኖርባቸዋል። ለጀመሩትና ለፈለጉት ጉዳይ ደግሞ የተጠና የንግድ እቅድ ማዘጋጀትና በዓላማ ጸንቶ መቆም ያስፈልጋል፡፡

‹‹በአሁኑ ወቅት ያለው ኢኮኖሚያዊ ችግር በራሱ ሥራ ፈጥሮ ለመስራት አስገዳጅ ነው›› የሚለው አቶ በላይ፤ ወደ ንግዱ እንዲገባ ካደረጉት በርካታ ምክንያቶች አንዱ ሰዎች በየእለቱ የሚፈልጓቸውን የምግብ ሸቀጦች በቀላሉ ማግኘት አለመቻላቸው እንደሆነ አስረድቷል። አትክልትና የተለያዩ የምግብ ሸቀጦችን ለማቅረብ መነሳቴ ተገቢ ነው ይላል።

አቶ በላይ እንደሚለው፤ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ቢሩም በዚያው መጠን ችግሩን ለማለፍ የሚደረግ ሩጫ አለ። በዚህ ሩጫ ውስጥ ደግሞ የሰዎች የመጀመሪያውና የመጨረሻው መሰረታዊ ፍላጎት ምግብ ነው። በመሆኑም የምግብ ሸቀጦችን በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ላለው የማህበረሰብ ክፍል በቀላሉ የማድረስ ሥራ ምርጫው ሆኖም በላይ አትክልትና አስቤዛ ትኩረቱን በመሰረታዊ የምግብ ሸቀጦች ላይ በማድረግ ወደ ሥራው ገብቷል።

ይህ ሥራ ያልተነካና ብዙ ውጣ ውረድ ያለው ሲሆን፤ በተለይም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ካለው የማህበረሰብ ክፍል እንዲሁም በገጠር ካለው ገበሬ ጋር የማገናኘት ዕድሉ ሰፊ ነው። በመሆኑም ገበሬው በበጋ አቧራ ለብሶ በክረምት ከዝናብና ጭቃ ጋር ተጋፍቶ የሚያለማው የግብርና ምርት ሳይበላሽ በቶሎ ወደ ገበያ እንዲወጣ ምቹ ሁኔታን እየፈጠረ ይገኛል። በላይ አትክልትና አስቤዛ በዋናነት ሸማቹና አምራች እንዲሁም ገበሬው ዘንድ መድረስ የቻለ ማዕከል ነው።

ማዕከሉ በከተማ ውስጥ ያለውን የገበያ ክፍተት መሙላት ዋነኛ ዓላማው ሲሆን፤ ሸማቹ አትክልቶችን ጨምሮ መሰረታዊ የሆኑ የምግብ ሸቀጦችን በተለይም አትክልት ለመግዛት የሚወስድበትን ጊዜ፣ ጉልበትና ወጪ ለመቀነስ ያስችላል። ሌላው የገበሬውን ምርት በፍጥነት የሚረከበው እንዲሁም የገበያ መረጃ የሚሰጠው አካል ባለመኖሩ ገበያ አለ ወደተባለበት አካባቢ በመሄድ ይሸጣል። አልያም ነጋዴው በፈለገው ዋጋ ከማሳው ላይ ይወስዳል። ‹‹በዚህ ጊዜ ገበሬው የድካሙን ያህል ማግኘት አይችልም›› የሚለው አቶ በላይ፤ ማዕከሉ የተገነባው ይህን ችግር በመረዳት መፍትሔ ለማምጣት መሆኑን ተናግሯል።

ዕለት ዕለት ከሚፈለጉ የምግብ ሸቀጦች መካከል በተለይም እጅግ በጣም ጥንቃቄ የሚያስፈልገውና ከፍተኛ የመበላሸት ዕድል ያለው አትክልት ‹‹ከእርሻ ወደ ጉርሻ›› መሆን እንዳለበት ያስረዳው አቶ በላይ፤ ለዚህም ምርቱን በቀላሉ ከማሳው ወደ ገበያው ማምጣትና የተጠና የገበያ ስርዓት መዘርጋት የግድ ነው ይላል።

እሱ እንደሚለው፤ በላይ አትክልትና አስቤዛ ይህን በሚገባ አጥንቶ ወደ ሥራው መግባት በመቻሉ የበርካታ ሸማቾችን ፍላጎት እያረካ ነው። በአሁኑ ወቅትም ጥራት ያላቸውን ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ በስፋት እያቀረበ የሚገኘው በላይ አትክልትና አስቤዛ 75 ሺ ደንበኞችን ማፍራት ችሏል፡፡

ድርጅቱ ስራውን የአትክልት ምርቶችን ለማህበረሰቡ በማቅረብ የጀመረ ሲሆን፤ አሁን ደግሞ ከግብርና ምርቶች በተጨማሪ የፋብሪካ ምርቶችን፣ ደረቅ ቅመማ ቅመሞችን፣ የንጽህና መስጫ ግብዓቶችን እና አጠቃላይ ለሰው ልጆች አስፈላጊና መሰረታዊ የሆኑ ከ300 እስከ 500 የሚደርሱ የምርት አይነቶችን እያቀረበ ይገኛል። ይህም ቢዝነሱ በፍጥነት እንዲያድግና በርካታ ደንበኞች እንዲኖሩት አድርጎታል። የምርት መጠኑ በጥራትና በብዛት እንዲጨምርና የደንበኞቹ ቁጥርም በተመሳሳይ እንዲያድግ አርሶ አደሩ ላይ መስራት አዋጭና ተመራጭ እንደሆነ አቶ በላይ ይገልጻል፡፡

ለዚህም ጥናትና ምርምር በማድረግ የተለያዩ ድጋፎችን ለአርሶ አደሩ ያደርጋል። ለአርሶ አደሩ ሙያዊ የሆነ ስልጠና በመስጠት ግንዛቤ የማሳደግ ሥራ እየሰራ ነው። የጥናትና ምርምር ሥራውም ገበሬው በራሱ መሬት፣ ጉልበትና በሬዎች ሰፊ ምርት ማምረት የሚችልበትን መንገድ ማሳየት ያስችላል። ለዚህም ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በትብብር እየሰራ ሲሆን፤ በቀጣይም ድርጅቱ ከግብርና ሚኒስቴር በሚያገኘው የምስክር ወረቀት አማካኝነት ሙያዊ ስልጠና ይሰጣል። ስልጠናውም ገበሬው ምርታማነቱን በመጨመር በቀላሉ ማምረትና ውጤታማ የሚሆንበትን መንገድ ማሳየት የሚያስችል ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት በተለያዩ አካባቢዎች ከሚገኙና መቶ ከሚደርሱ አርሶ አደሮች ጋር የሚሰራው በላይ አትክልትና አስቤዛ፤ በተለይም ማዕከሉ ትኩረት ያደረገባቸውን ምርቶች ከሚያመርቱ ገበሬዎች ጋር በጋራ እንደሚሰራ አቶ በላይ ይገልጻል። ለአብነትም ቲማቲም ከመቂና ከአዋሽ አካባቢ እንዲሁም ከቆቃ፣ አዋሽ፣ ሸዋሮቢት፣ ጎንደር፣ አፋርና ሌሎች አካባቢዎች ደግሞ የሽንኩርት ምርት ያገኛል። ወቅታቸው ቢለያይም በእነዚህ አካባቢዎች ሽንኩርት በስፋት ይመረታል። ድንች ሆረታ፣ ሻሸመኔ፣ በአሰላና በዙሪያው የሚመረት ሲሆን፤ አልፎ አልፎ ደብረብርሃንና ጎጃም ይመረታል። በእነዚህ አካባቢዎች ለሚገኙ አርሶ አደሮች ማዕከሉ የአቅሙን ሁሉ በማድረግ አርሶ አደሩን ይደግፋል ሲል ያብራራል፡፡

ምርቱ ከመድረሱ አስቀድሞ ክትትል በማድረግ ምን አይነት ምርቶች በየትኞቹ አካባቢዎች መቼ ይደርሳሉ የሚለውን አስቀድሞ በማጥናት ዝግጅት ያደርጋል ያለው አቶ በላይ፤ ግዢውን የሚፈጽሙበት መንገድም የተለያየ እንደሆነ ይናገራል።

የድርጅቱ የገበያ ጥናት ቡድን በሚያደርገው ጥናት መሰረት በቀጥታ ከአርሶ አደሩ ገዝቶ ወደ አዲስ አበባ ማጓጓዝ አንዱ ሲሆን፤ አዲስ አበባ የደረሰውን ምርትም ከነጋዴው ይገዛል። ምክንያቱም የከተማው ሕዝብ ከፍተኛ መጠን ያለው የምግብ ሸቀጥ እንደሚፈልግ በጥናት ማረጋገጥ ችሏል። በላይ አትክልትና አስቤዛ ከአርሶ አደሩና ከነጋዴው የሰበሰበውን አጠቃላይ የምግብ ሸቀጥ በከተማ ውስጥ በሚገኙ አምስት የመሸጫ ሱቆች ለማህበረሰቡ እያቀረበ ይገኛል።

ማህበረሰቡ በእነዚህ አምስት የመሸጫ ሱቆች ለምግብነት የሚውሉ ማንኛውንም አይነት ሸቀጦች እስከ ምሽት 2፡30 ድረስ ማግኘት ይችላል ያለው አቶ በላይ፤ ሱቆቹ እንደ ሌሎች የገበያ ማእከሎች የቅንጦት ዕቃዎችን እንደማይዝም ይናገራል።

እሱ እንዳለው፤ ምርቶቹ ለምግብነትና ለንጽህና የሚውሉ ትኩስና ጥራት ያላቸው ከመሆናቸው ባለፈ በተመጣጣኝ ዋጋ የሚቀርቡ ናቸው። በላይ አትክልትና አስቤዛ ከሌሎች ገበያዎች ከሚለይበት አንዱ ደንበኛው ምርቶቹን በእጁ መንካት አይፈቀድለትም። ማንም ሰው አትክልቶችንና የታሽጉ ምግቦችን መመልከት ይፈቀድለታል ነገር ግን በእጁ መነካካት አይችልም። ዕቃውን መንካት የሚችሉት ሰራተኞች ብቻ ናቸው።

ለዚህም ዋናው ምክንያት አትክልቶች በእጅ ሲነካኩ የመበላሸት ዕድላቸው ከፍተኛ መሆኑ ነው። ይህም ሰዎች እጅ ላይ ያሉት ባክቴሪያዎች ምግቦቹ ላይ የመሆን ዕድላቸውን ለመቀነስ ነው። በመሆኑም በድርጅቱ የተመረጡ ሰራተኞች ደንበኛው የሚፈልገውን ዕቃ አዘጋጅቶ ያቀርባል። የምግብ ሸቀጦችን የሚነካው ሰራተኛም እንዲሁ ገንዘብ መንካት የለበትም። ገንዘብ ተቀባይ ለብቻ ነው፤ ብር የሚነካ ማንኛውም ሰራተኛ ዕቃዎችን አይነካም።

የከተማውን ሕዝብ ለማገልገል፣ ፍላጎቱን ለማሟላትና እየተጋ ያለው በላይ አትክልትና አስቤዛ፤ በቀጣይ ይህን መሰሉን የገበያ ማዕክል መስፋት እንዳለበት ያምናል። ከተማ ውስጥ ያለው ፍላጎት ምን ያህል እንደሆነ በጥናት ማረጋገጥ ችሏል። ፍላጎት በጊዜ የተለያየ ሲሆን፤ ለአብነትም በደሞዝ አካባቢና በበዓላት ወቅት ከፍተኛ ፍላጎት ሲኖር አልፎ አልፎ ከሚፈጠር አለመረጋጋት አገሪቷ ሰላም ስትሆን ፍላጎቱ ከፍ ያለ ነው። ከዚህ ውጭ ባሉት ወቅቶች መደበኛ የሆነ ፍላጎት አለ።

በላይ አትክልትና አስቤዛ 40 ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ እድል የፈጠረ ሲሆን፤ ሙሉ ወጪያቸውን ይችላል። 60 ያህሉ ደግሞ በጊዜያዊነት የሚሰሩ ሰራተኞች አሉት። አንድ ሰራተኛ ድርጅቱ ውስጥ ማገልገል የሚችለው ከሁለት እስከ አምስት ዓመት ብቻ ነው የሚለው አቶ በላይ፣ አንድ የድርጅቱ ሰራተኛ ከአምስት ዓመት በኋላ የራሱን ንግድ መክፈት እንደሚችልም ይገልጻል። ለዚህም ድርጅቱ በተለያዩ የንግድ አማራጮች ጥናት ማድረጉን ጠቅሶ፣ ሰራተኞች በፈለጉት መንገድ መሥራት እንዲችሉ የማማከር ሥራ እንደሚሰራም ይናገራል። ማንኛውም ሰራተኛ በድርጅቱ ሁለት ዓመት ማገልገል ግዴታው መሆኑንና ከአምስት ዓመት በላይ መቆየት እንደማይቻልም አቶ በላይ ይገልጻል።

እሳቸው እንዳሉት፤ በቋሚነት የሚሰሩ ሰራተኞች አምስት ዓመት ሲቆዩ ደምወዛቸው በአካውንታቸው ተቀማጭ ይደረጋል። እስከ አምስት ዓመት ወጪ ማድረግ አይችሉም። የዕለት ወጪያቸው ማለትም ምግብ፣ መጠለያ፣ መጓጓዣ፣ ልብስ፣ የንጽህና መጠበቂያ፣ የበዓል ወጪ በድርጅቱ ይሸፈናል። በስራ ላይ አደጋ ቢያጋጥማቸው የሕክምና ወጪያቸው በድርጅቱ ይሸፈናል።

አቶ በላይ ሰራተኞቹን አስመልክቶ እንዳብራራው፤ ሰራተኞቹ በቀን አራት ጊዜ ይመገባሉ፤ በየዕለቱ ለ20 ደቂቃ መረጃ፣ በሳምንት ሁለት ሰዓት ስልጠና ያገኛሉ፤ በአራት ወር አንድ ጊዜ ይዝናናሉ። በዚህ መልኩ አምስት ዓመት ከቆዩ በኋላ የተጠራቀመላቸውን ገንዘብና ያካበቱትን ሙያ፣ ዕውቀትና ልምድ ይዘው እንዲወጡና የራሳቸውን ድርጅት እንዲከፍቱ ይደረጋል። እስካሁን በዚህ መንገድ የወጡ ስምንት ግለሰቦች የራሳቸውን ድርጅት መክፈት ችለዋል፡፡

እንደ በላይ አትክልትና አስቤዛ አይነት ንግድ እንደ አገር በስፋት ያስፈልጋል የሚለው አቶ በላይ፤ ለዚህም በድርጅቱ አምስት ዓመታትን አስቆጥረው ከሚወጡ ሰራተኞች ብዙ ይጠበቃል ነው ያለው። ምክንያቱም የድርጅቱ ዓላማ በአገር ውስጥ ብቻ መገደብ አይደለም። ትኩስ የሆኑ የአገር ውስጥ ምርቶችን በተለይም አትክልቶችን የአገር ውስጥ ገበያን ካጠገቡ በኋላ በውጭ አገር ጭምር ተደራሽ ማድረግ ነው። ለዚህም ድርጅቱ ብቻውን የትም አይደርስምና የበላይ አትክልትና እስቤዛ ማዕከልን የመሰሉ ስራ ፈጣሪዎችን ማፍራት ነው። ስለዚህ አብዛኛው ሰው የድርጅቱን ሃሳብ እንዲከተል እያደረገ ነው፡፡

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥቅምት 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You