የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ውድድር በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ከታህሳስ 3 ቀን 1980 ዓ·ም ጀምሮ ለ15 ቀናት እዚህ አዲስ አበባ እና አስመራ በተካሄደበት ወቅት የነበረው የሕዝብ ስሜት ከጣራ በላይ ሆኖ ያለፈ መሆኑ በወቅቱ በሰፊው ተዘግቧል።
በሁለት ምድብ ተከፍሎ በስድስት ቡድኖች መካከል ሲካሄድ በነበረው፤ የዓለምን ዓይንና ጆሮ ቀስፎ በመያዝ እስካሁን አቻ ያልተገኘለት ውድድር ሲካሄድ በነበረበት ወቅት ዜጎች ይህንን ሀገራዊና ብሄራዊ ስሜታቸውን በተለያዩ ሚዲያዎች ሲገልፁ የነበረ ሲሆን፤ አንዱና ዋንኛው ደግሞ በዚህ ጋዜጣ ላይ ሲፃፉ የነበሩት ግጥሞች ናቸው።
ባለፈው ሳምንት በጨዋታው ፍፃሜ የኢትዮጵያ እና የዚምባቡዌ ብሄራዊ ቡድኖች ለዋንጫ በሚፋለሙበት (ታህሳስ 22) ወቅት ከፍልሚያው በፊት፤ በዋዜማው፣ ዋንጫውን ከማግኘታችን አስቀድሞ ልናገኝ እንደሚገባ በመተንበይ፣ “የእኛ ይሁን!” በሚል ርእስ የተገጠሙ ስንኞችን ማቅረባችን ይታወሰል።
ዛሬ ደግሞ ተንባይ ግጥሞቹ ተሳክቶላቸው ዋንጫውን ካገኘን በኋላ የተቋጠሩ ስንኞችን ይዘን ቀርበናል። እነዚህን ግጥሞች ከሌላው ለየት የሚያደረጋቸው ለድል ያበቁንን ተጫዋቾች ለታሪክ ምስክርነት ይበቁ፤ ውለታቸው አይረሳ፤ ድላቸው ይዘከር ዘንድ በውስጣቸው በዝርዝር መያዛቸው ነው። እኛም፣ የታሪክ አካል ነንና ይህንኑ ታሪክ ለአሁኑ ትውልድ ማስተላለፉ ላይ ልንሠራ የሚገባ መሆኑ ላይ በማመን፣ ያንን በወርቅ የተፃፈ የሀገራችንን የእግር ኳስ ታሪክ ለትውልድ ልናሻግረው ወደድን።
ብሄራዊ ቡድናችን ለዋንጫ ሽሚያ የደረሰው ከአዲስ አበባ ምድብ ከታንዛኒያና ከዛንዚባር ጋር 1 ለ 1 ተለያይቶ፤ ኬንያን 2 ለ 1 አሸንፎ፤ የምድቡን ማጣሪያ በሁለተኛነት ካለፈ በኋላ በአስመራ ምድብ አንደኛ ሆኖ ያለፈውን ዩጋንዳን 3ለ0 በሆነ ውጤት አሸንፎ መሆኑ በወቅቱ ተዘግቦ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል።
ኢትዮጵያ ይህንን የምስራቅና የመካከለኛው አፍሪካ)ሴካፋ) ጨዋታ ስታዘጋጅ ይህ የመጀመሪያዋ መሆኑ፤ ብሄራዊ ቡድናችንም ለዋንጫ ሽሚያ ሲደርስና ይህንን ዋንጫ ሲያገኝም የመጀመሪያው መሆኑ በዚያው ወቅት ሰፋ ያለ የሚዲያ ሽፋን ያገኙ ዘገባዎች ነበሩ።
በተረፈ ትዝታውን ለአንባቢያን ግጥሞቹን ወደ ማስታወስ እንሂድ።
የቅኔ ስጦታ ለባለውለታ
የዝምባቡዌ አጥቂዎች ግብ እያንዣበበ
የጥቃት ግድግዳው በራችን ተካበ።
ወገኖችህ ሁሉ ድል እንደ ጠማቸው፤
አደባባይ ወጥተው ሲቃ ሲይዛቸው፤
ልበሙሉ ጀግና አንተነህ ዳኛቸው።
በገና ዋዜማ በገና ጨዋታ፤
አሲላዬ ሲሉ እነሙሉጌታ፤
ሜዳውን በሙሉ አየነው ቃኘነው፤
ዓይናችን ልባችን ካማኑኤል ጋር ነው።
ደገስገስ እያለ ሲጨነቅ ወገኔ፤
ጨለማ ገፋፊው በቀለ ብርሃኔ።
23 ዓመታት እንደማያልፍ የለም
ገና አሁን ዘንድሮ ሆነልን ሙሉአለም።
ጥቃት የማይወደው ወገንህ በሙሉ፤
ገብረመድህን ኃይሌ ይሉሀል አምበሉ።
አቦ ዝም በሉ ደስ ብሎናል እኛ!
መንግሥቱና ነጋሽ ጌቱና ሰለሞን የኛ አስራት አዱኛ።
ሀቁን እንመስክር ባህላችን ነውና፤
በኳስም ታጋይ ነው የዚምባቡዌ ጀግና!
ትናንትም እነመንጌን እንዴት ተሰማቸው!
ይድነቃቸውንስ መሬት ቀለላቸው!
(አበባው ይግዛው)
እንኳን ደስ አለን
(ጽጌ አብረሃም፣ ጀነራል ዊንጌት ትምህርት ቤት፤ አዲስ አበባ)
ኳስ አዬ ኳስ ድቡልቡል
አንዴም ልብ ስትሰቅል
ስታሰጥም በሃሳብ ማእበል
ስታስፈነጥዝ በደስታ በርካታ
አየ · · · የእግር ኳስ ጨዋታ · · ·
የሰሞኑ የልባችን ትርታ · · ·
- · · የኳስ ቅብብል ጭውውት
አንዱ ሲያቀብል ሌላው ሲይዛት
- · · አቤት ሲያስደስት
በጭንቀት በሀሳብ መዋለል
የሞት ሽረት ትግል · · ·
ጨዋታ · · · የኳስ ቅብብል
መሸነፍን መቀበል ተስኖን
ከኳሷ ጋር ዓይናችንን አንከራተን
ግባችን ተስፋ ቆርጦ
በጨዋታ ዓለም ማሸነፍ መሸነፍ ስላለ
መቸም ምንም አይደለ
ኦ · · · እንዴት ሊሆን
ጭራሽ ለመቀበል አቅቶን
ኳስ ድቡልቡልነቷን ስተን
የተጫዋቾቻችን ድካም እየታሰበን
ኢትዮጵያ የዋንጫ ባለቤት መሆን
ማጣቱ ቆጭቶን · · ·
ጎንበስ በኀዘን በንዴት
አየ · · · በአቻ ልታልቅ ትንሽ ሲቀራት
እ· · · እ· · · አይንን መፈታተን
ግብ · · · ግብ የመጨረሻ ገባችልን
ዳኘ ዳኘን · · ·
ኦ! · · · ሆ · · · እንኳን ደስ አለን
ከልብ በላይ ፈነጠዝን
አሻሩን · · · አስደሰቱን
አስደሰቱን · · · አሻሩን
እንኳን ደስ አለን · · ·
ዋንጫዋ ገባች በእጃችን።
(አዲስ ዘመን ፣ ታህሳስ 22 ቀን 1980 ዓ.ም)
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ህዳር 3/2017 ዓ.ም