አንድ ሰው ከገጠር ወደ ከተማ እንጂ፤ ከከተማ ወደ ገጠር ሄዶ ለመኖር ሆነ ለመሥራት ሲያስብ ብዙም የተለመደ አይደለም፡፡ በተለይ ደግሞ ብዙ መሠረተ ልማቶች ወደ አልተሟሉባቸው እንደ የሀገሪቱ ገጠራማ ክፍል ሲሆን፣ ነገሩ ከባድ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ራሄል ሕሩይ፣ የገጠሩን የተፈጥሮ ስጦታ እንጂ የመሠረተ ልማቱን ጉድለት አልተመለከተችም፡፡
ምንም እንኳን ትውልድና እድገቷ ለአፍሪካም ለኢትዮጵያም መዲና በሆነችው አዲስ አበባ ከተማ ቢሆንም፤ የሰነቀችው ራዕይ ወደ ገጠር እንድትመለከት አደረጋት፡፡ ራዕይዋን ለመከተል በመወሰኗም ለበርካታ እናቶች በጓሯቸው ሰርተው የሚለወጡበትን እድል ልትፈጠር ችላለች፡፡
ለካፋ እና ቤንቺ ሻኮ አካባቢዎች አዲስ የሥራ ባሕልን በመፍጠር አምስት ሺህ ሴቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ በር ከፋች ናት፡፡ እስካሁን በሠራቸው ሥራም ከሀገር ውስጥ አልፋ በአፍሪካ ደረጃ ተሸላሚ ከመሆን የዘለለ በተለያዩ የሥራ ውድድሮች ዳኛ በመሆን፤ በአንዳንድ መንግሥታዊ ተቋማት ዓመታዊ እቅድ ዝግጅት ላይ በማማከር ለመሳተፍ ችላለች፡፡
ወይዘሮ ራሄል፣ የዳማሴን እሴንሻል ኦይል ድርጅት መሥራችና ኃላፊ ስትሆን፣ ድርጅቷ የሚሰራው በካፋ እና ቤንቺ ሻኮ ዞኖች፤ እናቶች እና ወጣቶች በጓሯቸው የተለያዩ ቅመማ ቅመሞች እንዲያመርቱ የተለያዩ ከዘር አንስቶ በሌሎች ነገሮች ይረዳል፡፡ ምርቱ ከተመረተ በኋላ መልሶ ከአርሶ አደሮቹ በመግዛት ለገበያ የማቅረብ ሥራ ይሠራል፡፡
የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን የተማረችው በአዲስ አበባ ከተማ ሕይወት ብርሃን ትምህርት ቤት ነው፡፡ የከፍተኛ ትምህርቷን በፋርማሲ የሙያ ዘርፍ ተምራ ከፍተኛ ባለሙያ እስከመሆን ድረስ ሠርታለች፡፡ አሁን እየሠራች ባለችው የቅመማቅመም እና የግብርና ዘርፍ ውጤታማ ለመሆን መንገድ እንዲሆናት በተለያዩ ጊዜያት ስልጠና ከመውሰድ ያለፈ “በአግሪ ቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን” ሁለተኛ ዲግሪዋን ተምራለች፡፡
ትዳር መስርታ ሶስት ልጆችን ያፈራች ሲሆን፣ ባለቤቷ በሞት ስለተለያት ልጆቹን የማሳደግ ኃላፊነት በእርሷ ላይ ሊወድቅ ችሏል፡፡ ከልጆቿ በተጨማሪ እናቷን፣ አክስቷን እና የአክስቷን ልጆች የምታስተዳድረው እርሷ ናት። ልጆቿ እና ቤተሰቦቿ የሚኖሩት አዲስ አበባ ስለሆነ፤ አብዛኛው ጊዜ በሥራ ምክንያት ለረጅም ጊዜያት ክልል ከተሞች ስለምትቆይ ላይገናኙ የሚችሉበት አጋጣሚ መኖሩን ትገልጻለች፡፡
ወይዘሮ ራሄል፣ ወደ ቅመማ ቅመም ልማት ሥራ የገባችው፤ ከባሕላዊ መድኃኒቶች እና የውበት መጠበቂያዎች ጋር ተያይዞ ለሚታዩ ክፍተቶች የመፍትሔ አካል ለመሆን በማሰብ ነበር፡፡ “የባሕላዊ መድኃኒቶቻችን ብዙ ጊዜ በዘልማድ ይደረጋሉ እንጂ በሥነ ሥርዓት አላስቀመጥናቸውም፤ ለሌላው ዓለም እንዲደርሱ አልሠራንባቸውም፡፡” ስትል ትናገራለች፡፡
እያደገች ስትመጣ የባሕላዊ መድኃኒቶች በስም ደረጃ ብቻ የምንጠቀማቸው ብቻ ሳይሆን፤ በስፋት ተመርቶ ለዓለም ቢሰጥና ቢለማመደው የሚል እሳቤ አደረባት፡፡ ከፍ እያለች ስትመጣ ባሕላዊ የውበት መጠበቂያዎች ላይ መሥራት የበለጠ ፍላጎቷ እየሆነ ስለመጣ አቅጣጫዋን ወደዚህ ዘርፍ አዞረች፡፡ ይህ ፍላጎቷ የመመረቂያ ጽሑፏን በውበት መጠበቂያ ዙሪያ እንድትሰራ ተጽእኖ ያሳደረባት እንደሆነም ታመለክታለች፡፡
ወይዘሮ ራሄል፣ የመመረቂያ ጽሑፏን የሰራችው በወይባ ጢስ ላይ ነው፡፡ ወይባ ከውበት መጠበቂያነት ያለፈ፤ ለጤና ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑን በመጥቀስ፤ 12 ዓይነት ዝርያ ስላለው እሱን አምርቶ በመሸጥ በኢኮኖሚ ረገድም ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻል ትናገራለች፡፡
“እነዚህን ነገሮች በሥነ ውበት መጠበቂያዎች ምርምር ላይ ለመሥራት ቀድሜ ባስብም፤ ምርምር ላይ መሥራት ብር እና እውቅና ስለሚፈልግ ጊዜ የሚፈጅ ነው። ስለዚህ መዓዛማ ዘይቶች የሚባሉ በባሕር ዛፍ፣ በጠጅ ሳር የሚሰሩ ስላሉ እነሱን ለማምረት አሰብኩ። ከእነሱም ጋር ተያይዞ የተለያዩ የውበት መጠበቂያዎች ለማምረት ስነሳ ጥሬ እቃ አጠረኝ፡፡” ትላለች፡፡
ዳማሴን ድርጅት በ2006 ዓ.ም የውበት መጠበቂያዎችን ማምረት አላማው አድርጎ ቢመሰረትም በጥሬ እቃ እጥረት ምክንያት፤ የውበት መጠበቂያ ጥሬ እቃዎችን በቋሚነት ለገበያ ለማቅረብ ነው ወደ ግብርናው ዘርፍ ሊገባ የቻለው፡፡
“ቡና ላይ ልሠራ ብዬ ብመጣ እንደ ሀገር ከዚህ በፊት የተሰራ ነገር ስላለ አልቸገርም፡፡ የተለያዩ ቡና አቅራቢ ማህበሮች ስላሉ ከእነሱ ጋር ልሠራ እችላለሁ፡፡ ነገር ግን ቅመማ ቅመም ላይ የተሰራ ነገር ባለመኖሩ የተስተካከለ ነገር ስላልነበረ ቀጣይነት ባለው መልኩ ጥሬ እቃ አቅራቢዎቹን በማፈላለግ ረገድ አደራጅቶ የመሥራቱ ነገር የኔ ሆነ፡፡ “ስትል ትናገራለች፡፡
ከግብርና ምርምር ጋር መሥራት ብትጀምርም፤ ግብዓቶቹን ማግኘት ቀጣይነት ያለው እና ቋሚ ጥያቄ እንደመሆኑ፤ አምርቶ ጥሬ እቃ የሚያቀርብላትን ወደማፈላለግ ገባች፡፡ ካፋና አካባቢው ሄዳ ለመሥራት ምክንያት የሆናት በብዝሀ ሕይወት የሚሰራ ድርጅት በአካባቢው ያሉ ደኖች የአካባቢውን ነዋሪ ተጠቃሚ እንዲያደርግ እና ቀጣይነት እንዲኖረው ፕሮጀክት ይዞ ነበረና፤ እርሷ ጥሬ እቃ አቅራቢ ስለምትፈልግ ፕሮጀክቱን እንደትይዝ ተደረገ፡፡
ነገር ግን አብዛኞቹ ምርቶች ከጫካ የወጡ ባለመሆናቸው አመቺ አልነበረም፡፡ ምክንያቱም ጥራታቸው ተመሳሳይ አይደለም፡፡ ጫካ ውስጥ ያለ ነገር የሕዝብ ከመሆኑ አልፎ የእንስሳት እና የዱር እንስሳቱም ፍላጎት አለው፡፡ ሌላው ነገር በቀጣይነት ለማቅረብም ብዛት የለውም፡፡
“ስለዚህ የራሴን መሬት ወስጄ ላልማ የሚለውን ሃሳብ ሳስብ ተቀባይነት ማግኘቱ ትንሽ ስለሚከብድ፤ ማህበረሰብ ውስጥ ስመለከት በጉልህ ያዩት ትርፍ ነገር መሬት ነው፡፡ እንደ ከተማ ልጅ አንድ ሺህ ካሬ እንጂ አንድ፣ ግማሽ እና እስከ 10 ሄክታር ድረስ ጓሮ ያለው ሰው አይቼ አላውቀወም፡፡ እነዚህ መሬቶች ቢገጣጠሙ ትልቅ መሬት ይወጣቸዋል፤ ሰዎቹንም ወደ ሥራ ማሳተፍ ይቻላል የሚል ሃሳብ ላይ ደረስኩ፡፡” ስትል ትናገራለች፡፡
“እነሱ በዚህ ሁኔታ ከሰሩ ደግሞ ለእኔ አቅራቢ ስለሚሆኑኝ እኔው በራሴ አቅራቢ ፈጠርኩ ማለት ነው፡፡ ሰዎቹ ዘንድ ምንድነው የሚጎድለው የሚለውን ስመለከት እውቀት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር እና በማህበር መደራጀት ያሉ ክፍተቶች መሆናቸውን ተመለከትኩ፡፡ ሥራውን ለመሥራት ደግሞ በማህበር ተደራጅተው በተቋም ደረጃ ማቋቋም ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ከመንግሥት እና ሊያግዙኝ ከሚችሉ አካላት ጋር ደረጃ በደረጃ እያናገርኳቸው ለመሥራት ቻልኩ፡፡” ትላለች፡፡
ወደ ሥራው ስትገባ የነበሩትን 20 አርሶ አደሮች ብቻ ማሳተፍ የቻለች ቢሆንም፤ አሁን ካፋ ዞን ላይ አምስት ሺህ ሴት አርሶ አደሮች በማሳተፍ እየሠራች ነው፡፡ ከዚያም ባለፈ በአንድ ዞን ብቻ ሳትገደብ ወደ ቤንቺ ሻኮ ዞን ተሻግራ እየሰራች ትገኛለች፡፡ የሥራ ቦታዋን ከማስፋፋት እና የተሳታፊ አምራቾችን ቁጥር ከመጨመር በተጨማሪ ምርቶቹ የሚቀርቡበት ትላልቅ ገበያዎችን በማፈላለግ ረገድም እየሰራች ነው፡፡
የቅመማ ቅመም ምርቶቹን በሥርዓት አምርቶ ለዓለም የማስተዋወቅ ተግባር በተወሰነ መልኩ የተሳካላት ይመስላል፡፡ አሁን ላይ ለሁለት ሀገራት በተወሰነ መልኩ የቅመም ምርቶቹን እያቀረበች ይገኛል፡፡ በቀጣይ ምርቶቿን በስፋት እያመረተች ባልተቋረጠ መልኩ ለተለያዩ ሀገራት ለመላክ፣ ምርት መጨመር ላይ እና ገበያ የማፈላለግ ሥራ ላይ እየሠራች እንደሆነ ትናገራለች፡፡
“ከሴቶች ጋር እንድሠራ ያደረገኝ ምክንያት ካፋ ዞን ስመጣ፤ የራሴን የእርሻ መሬት ማግኘት ባለመቻሌ እንደ አማራጭ የወሰድኩት የሌሎቹን የእርሻ መሬት መጠቀም ነው፡፡ ወንዶቹን ሳናግር ሥራው ገና ሙከራ ላይ ስለነበር እምነት ኖሯቸው ከዚህ በፊት የለመዱትን የሰብል ዓይነት ትተው ከኔ ጋር ቅመማ ቅመም ላይ በጋራ ለመሥራት ባለመፈለጋቸው ሌላ አማራጭ ስመለከት ሰፋፊ ጓሮ እንዳለ አስተዋልኩ፡፡ ጓሮውን ደግሞ የሚያስተዳድሩት ሴቶች ናቸው፡፡” ትላለች፡፡
“ለምሳሌ ለ10 ሴቶች ግማሽ ሄክታር መሬት ቢኖራቸው ስንደምረው አምስት ሄክታር ይሆናል። በዚህ ሁኔታ በርካታ ሴቶች በተሳተፉ ቁጥር ሄክታሩ እየጨመረ ይመጣል፡፡ ሴቶቹም እዛው ቤታቸውን እና ልጆቻቸውን እየተንከባከቡ በጓሯቸው በመሥራት ገንዘብ ከሚያስገኘው ሥራ ላይ ሌላ መሳተፍ ተጨማሪ እድል ሆነ ማለት ነው፡፡” ስትል ታስረዳለች፡፡
ምንም እንኳን የተመረተውን ምርት መልሳ ከአርሶ አደሮቹ ገዝታ የምትረከብ ቢሆንም፤ አርሶ አደሮቹን ከማደራጀት አንስታ፣ ከዘር መረጣ እስከ ችግኝ ማቅረብ እና ወደ እርሻ ገብታ አተካከሉን እስከ ማሳየት ድረስ ትሰራለች፡፡ በዚህ ካምፓኒው የግል ይሁን፣ ግብረሰናይ ድርጅት ይሁን፣ የመንግሥት ይሁን ለብዙ ሰው ግራ ያጋባል ትላለች፡፡
በአሁኑ ወቅት ከሁለት ሺህ ሄክታር መሬት በላይ የደረሰች ሲሆን፣ በካፋ ዞን በአምስት ወረዳዎች በቤንች ሻኮ ዞን ሁለት ወረዳዎች ላይ እየሠራች ነው፡፡ ቅመማ ቅመም ተያያዥነት ያለው እንደ መሆኑ 15 ዓይነት ቅመሞችን ነው እያመረተች ያለችው፡፡
“ሽሮ እንኳን ብንወስድ የሚፈጨው ነጭ ሽንኩርት፣ ቀይ ሽንኩርት፣ ዝንጅብል ፣ ኮረሪማ ፣ ነጫ አዝሙድ እና ሌሎች ቅመሞች ገብተውበት ነው፡፡ ስለዚህ ቅመም አንድ ሰብል ብቻ ስላልሆነ አንዱ ቅመም ካንዱ ጋር አብሮ መሆን ስላለበት የተለያዩ ዓይነት ቅመሞችን ነው የምናመርተው። ለዚህ ደግሞ የታወቁ ዝርያዎች ከምርምር ተቋማት መምጣት ይኖርባቸዋል፡፡ በዚህ ረገድም የምርምር ተቋማት ቋሚ አጋሮቼ ናቸው፡፡” ትላለች፡፡
እናቶች የራሳቸው የሆነ ባሕላዊ እውቀት አላቸው የምትለው ወይዘሮ ራሄል፤” ካፋ ላይ ይሄን እውቀታቸውን ለመጠቀም እናቶችን ከየቀበሌው ሰብስበን ለቅመምነት ከሚሆኑ የቅጠል ዝርያዎች የትኛው ይሻላል ብለን አስመረጥናቸዋል ትላለች፡፡ እነርሱ የመረጡትን ደግሞ አባዝተን አምጥተን መርጠው ወስደው እንዲተክሉ አድርገናል፡፡ አሁን ካፋ አብዛኛዎቹ ሴቶች ጓሮ ሮዝመሪ፣ ኮሰረት፣ ዝንጅብል እና ሎሚናታ አለ፡፡” ስትል ትገልጻለች
በምርምር እና የማህበረሰቡን ባሕላዊ እውቀት ተጠቅማ የምታገኛቸውን የቅመማ ቅመም ዝርያዎች በሰፊው በተመሳሳይ ደረጃ እንዲኖሩ ለማድረግ ችግኝ ጣቢያዎችን አቋቁማ ዝርያዎች ላይ ትሰራለች፡፡ እስካሁን ወደ ስድስት የሚደርሱ የችግኝ ጣቢያዎች አቋቁማለች፡፡
“አሁን ሴቶቹም ሥራውን ስለለመዱ ችግኝ ሲያፈሉ አንዳቸው ለአንዳቸው ያከፋፍላሉ፡፡ መንግሥት በሚገርም ሁኔታ ከእኛ ገዝቶ ያከፋፍላል፡፡ ከዚህ በፊት የአካባቢው ኮሮሪማ ተወዳጅ አልነበረም፡፡ በዝርያ ረገድ በሠራነው ሥራ አሁን ላይ ‘እስፔሻሊቲ’ ተብሎ መሸጥ ጀምሯል፡፡” ትላለች፡፡
ወይዘሮ ራሄል፣ የከተማው ድምቀት ሳይጎትታት የሄደችለት ዓላማ በጊዜ ሂደት አብቦ ከራሷ አልፋ ለሌሎች እንድትደርስ አድርጓታል፡፡ በዚህም እስካሁን ባሰየችው የሥራ ውጤት በአህጉር ደረጃ በውጤታማ ገበሬ ሴቶች ዘርፍ ተሸላሚ የሆነች ሲሆን፣ እንደ ሀገር ሥራ ፈጣሪ ተብላ ለመሸለም በቅታለች፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ እስካሁን ባሳለፈችው መንገድ ተመስርታ አማካሪ እና ዳኛ ሆና ለመሥራት ተመራጭ ሆና በመገኘቷ እድሉን ማግኘት ችላለች፡፡ ሁለት ጊዜ በሥራ ፈጠራ ውድድሮች ላይ በዳኝነት ተሳትፋለች። ከዚህ በተጨማሪ ቡና እና ሻይ ባለሥልጣን ዓመታዊ እቅድ ሲያዘጋጅ በቅመማ ቅመም ዘርፍ እስከ ማማከር ደርሳለች፡፡
ቀጣይ እቅዷ ደንበኞች በሚፈልጉት መልኩ ለበርካታ ሀገራት የቅመማ ቅመም ምርቶችን ማቅረብ እና በዘርፉ ምርምሮችን ወደ ማድረግ መዛወር መሆኑን የምትገልጸው ወይዘሮ ራሄል፣ በመጨረሻም የገንዘብ ተቋማት ብድር በማመቻቸት ረገድ ትብብር ቢያደርጉ ስትል ጥሪዋን አቅርባለች፡፡
አመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን ህዳር 3/2017 ዓ.ም