ሩሲያ በዩክሬን የተደረገውን ሄሊኮፕተር የመጥለፍ ሙከራ አከሸፍኩ አለች

ዩክሬን የሩሲያን “ሚ-8 ኤምቲፒአር -1” የውግያ ሄሊኮፕተር ለመጥለፍ ያደረገችው ሙከራ መክሸፉ ተሰማ፡፡ የሀገሪቱ የስለላ ድርጅት አባላት ሩሲያዊው አብራሪ ሄሊኮፕተሩን ለዩክሬን እንዲያስረክብ ከዛም 750 ሺ ዶላር እንደሚከፍሉት ሲያግባቡ ተደርሶባቸዋል፡፡

አብራሪው የደህንነት ሰዎቹ በቴሌግራም እንዳነጋገሩት፣ የተጠየቀውን የሚፈጽም ከሆነ ከሚከፈለው ገንዘብ ባለፈ የቼክ ሪፐብሊክ ፓስፖርት ተዘጋጅቶለት ከሀገር እንደሚያስወጡት ቃል እንደገቡለት ተናግሯል፡፡

ከዚህ ባለፈም “ሰርጌይ” በሚል የቴሌግራም ስም ሲያወራው የነበረው የዩክሬን የስለላ ድርጅት አባል አብራሪው ሄሊኮፕተሯን ወደ ዩክሬን ይዞ ከማምራቱ በፊት ባልደረቦቹን መመርዝ እንዳለበት እንደነገረው ገልጿል፡፡

ለዚህም በማንኛውም ፋርማሲ ውስጥ ሊገዙ የሚችሉ ንጥረ ነገሮችን ያካተተ ገዳይ ድብልቅ በምግብ ውስጥ የሚጨምርበትን መመሪያም እንደተላከለት ይፋ አድርጓል፡፡

ሄሊኮፕተሩን ወደ ዩክሬን የሚወስድበትን ሂደት በተመለከተ በተሰጠው መመሪያም በቅድሚያ ወደ ቱርክ እንዲያቀና ከዛም ሞልዶቫ እና ፖላንድን አቋርጦ ዩክሬን ሲደርስ ለእርሱ እና ለቤተሰቦቹ የቼክ ሪፐብሊክ ፓስፖርት እና 750 ሺህ ዶላር እንደሚዘጋጅለት ተመላክቷል፡፡

የሩሲያ የፌዴራል ደህንነት አገልግሎት (ኤፍኤስቢ) ከአብራሪው የደረሰውን ጥቆማ ተከትሎ ሄሊኮፕተሩን ለመውሰድ የሚደረገውን ጥረት እስከ መጨረሻው ለማየት ወስኖ ከዩክሬናዊው ሰላይ ጋር ውስብስብ የሆነ የማጥመድ ጨዋታ ሲያደርግ እንደነበር ነው የተሰማው፡፡

ከደህንነት ተቋሙ ጋር በመነጋገር አብራሪው ሄሊኮፕተሩን ወደ ዩክሬን ለማምጣት መስማማቱን ተከትሎ የሚያርፍበትን ቦታ ካርታ እና ቀን የሚያመላክት መመሪያ ተልኮለታል፡፡

ሂደቱን እስከመጨረሻው የተከታተለው የሩስያ ደህንነት አገልግሎት በተጠቀሰው ቦታ ሄሊኮፕተሩን ለመቀበል ሲጠባበቁ በነበሩ የዩክሬን ወታደሮች እና የስለላ አባላት ላይ የሚሳይል ጥቃት መፈጸሙን ገልጿል።

በተጨማሪም ሰላዮቹ የሩስያ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮችን በመርዝ እና በተለያዩ መንገዶች ለመግደል ከብሪታንያ እና ሌሎች ምዕራባውያን የስለላ ድርጅቶች ጋር አብረው እንደሚሠሩ እንደተደረሰበት የሩሲያ የደህንነት አገልግሎት አስታውቋል፡፡

መሰል ጥረቶቹ አብራሪዎቹን በገንዘብ በማባባል ፣ በማስፈራራት እና ሌሎችም ዘዴዎችን በመጠቀም የሚጠየቁትን የሚያደርጉ ከሆነ አብራሪዎቹን እና ቤተሰቦቻቸውን ወደ ፈለጓቸው የውጭ ሀገራት በመውሰድ ኑሯቸውን መመስረት የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንደሚችሉ እስከማስማማት ይደርሳል ተብሏል፡፡

አርቲ እንደዘገበው የተለያዩ የውግያ ሄሊኮፕተሮችን እና አውሮፕላኖችን ለመጥለፍ የዩክሬን ሰላዮች የሩሲያ ጦር አብራሪዎችን ለመደለል የሚያደርጉት ጥረት አሁንም ቀጥለዋል። ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ኤፍኤስቢ የሩሲያ አብራሪ “ቲዩ-22ኤም3” የተባለ ኒዩክሌር መሸከም የሚችል የጦር አውሮፕላን ወደ ዩክሬን እንዲበር ለማሳመን በኪቭ የተደረገውን ተመሳሳይ ያልተሳካ ሙከራ ማክሸፉ ተዘግቧል፡፡

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ህዳር 3/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You