የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በየዓመቱ ከሚያከናውናቸው የሀገር ውስጥ ውድድሮች ውስጥ አንዱ የ30 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድር ነው። ፌዴሬሽኑ የ2017 ዓ/ም የውድድር መርሃግብሩን ከትናንት በስቲያ በቢሾፍቱ ከተማ በዚህ የጎዳና ላይ ውድድር የጀመረ ሲሆን ኢትዮ ኤሌክትሪክ አጠቃላይ የውድድሩ አሸናፊ ሆኗል።
ትልቅ ስም ያላቸው አትሌቶች ጭምር በተፎካከሩበት የሴቶች ውድድር ትግስት ግርማ ከፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ክለብ ቀዳሚ ሆና አጠናቃለች። ፅጌ ሃይለሥላሴ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ሁለተኛ፣ ሩቲ አጋና ሮዛ ደረጄ ከፌዴራል ማረሚያ ሦስተኛና አራተኛ ደረጃን ይዘው ፈፅመዋል። በወንዶች መካከል በተካሄደው ውድድር ደግሞ ሃይለማሪያም ኪሮስ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ቀዳሚ ሆኖ ሲያጠናቅቅ፣ አሰፋ መንግሥቱ በግል ሁለተኛ ሆኗል። ባየልኝ ተሻገርና አምባዬ ጎይቶም ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ሦስተኛና አራተኛ ሆነው ውድድሩን ጨርሰዋል።
በውጤቱ መሠረት ኢትዮ ኤሌክትሪክ በሴቶች በ22 ነጥብ 1ኛና የዋንጫ ተሸላሚ ሲሆን፣ ፌዴራል ማረሚያ በ24 ነጥብ 2ኛ፣ ኦሮሚያ ፖሊስ በ50 ነጥብ 3ኛ ደረጃን መያዝ ችለዋል። በወንዶችም ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ19 ነጥብ 1ኛ የዋንጫ ተሸላሚ ሲሆን ኦሮሚያ ፖሊስ በ40 ነጥብ 2ኛ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 76 ነጥብ 3ኛ ሆኖ አጠናቋል። በዚህም ኢትዮ ኤሌክትሪክ አጠቃላይ የውድድሩ አሸናፊ የሆነበትን ዋንጫ ወስዷል።
በወንዶች ቬትራን ከ50 ዓመት በላይ በተካሄደው ውድድር ገዛኸኝ ገብሬ አሸናፊ ሲሆን ስዩም ደበሌ ሁለተኛ፣ ደረጄ ገመቹ ደግሞ ሦስተኛ ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል። በተመሳሳይ በቬትራን ሴቶች ከ50 ዓመት በታች አበሩ ዘውዴ አሸናፊ ስትሆን አዳነች ተስፋዬና እህተብርሃን አዳሙ ሁለተኛና ሦስተኛ ሆነው ማጠናቀቅ ችለዋል።
ከ1ኛ-3ኛ ያጠናቀቁ አትሌቶች የወርቅ፣ የብር እና የነሐስ ሜዳልያ የተሸለሙ ሲሆን እንደየደረጃቸው ከ40 ሺ እስከ 18ሺ ብርም ተበርክቶላቸዋል፡፡ ከ4-8 ያጠናቀቁ አትሌቶችም እንደየደረጃቸው ከ16ሺህ እስከ 8 ሺህ ብር ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ ከ1-6 ባለው ደረጃ ያጠናቀቁ የቬትራን አትሌቶችም ከ6ሺህ ብር እስከ 500 ብር እንደየደረጃቸው የገንዘብ ሽልማት አግኝተዋል፡፡
የውድድሩ ዓላማ ለክልልና ከተማ አስተዳደር ክለቦች፣ ተቋማትና የግል ተወዳዳሪ አትሌቶች የውድድር ዕድል ለመፍጠርና ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት እንዲሁም አትሌቶችን በሽልማት ለማበረታት መሆኑን ፌዴሬሽኑ ገልጿል፡፡
የውድድሩ ተሳታፊዎች ክልሎች፣ ክለቦች፣ እና በግል ተመዝግበው የሚወዳደሩ አትሌቶች እና አንጋፋ አትሌቶች ሲሆኑ በዘንድሮው ውድድር ላይ ሦስት ክልል አንድ ከተማ አስተዳደር፣ አስራ አምስት ክለቦች፣ አንጋፋ (ቬትራን) አትሌቶች እና በግል ተመዝግበው የሚወዳደሩ አትሌቶች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ 385 ወንድ ፣ 137 ሴት አትሌቶች በአጠቃላይ 522 አትሌቶች ተፎካካሪ ሆነዋል፡፡ ይህም ካለፈው ውድድር አንፃር በ 59 አትሌቶች የዘንድሮ ውድድር ተሳትፎው የበለጠ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
ይህ የ 30 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በ2001 ዓ.ም. በአዳማ ከተማ የመጀመሪያውን ውድድር በ115 ወንድ እና 28 ሴት በድምሩ 143 አትሌቶችን በማሳተፍ የተጀመረ ሲሆን፣ ለ10 ተከታታይ ዓመታት እስከ 2003 ዓ.ም. ድረስ በአዳማ ከተማ ሲካሄድ ቆይቶ እስከ 2010 ዓ.ም. ድረስ ውድድሩ ተቋርጦ በድጋሚ 7ኛውን እና 9ኛውን ውድድር በቢሾፍቱ ከተማ ሲደረግ 6ኛው ውድድር በ2012 በፊዴሬሽኑ የውድድር መርሃ ግብር ለማካሄድ በእቅድ ተይዞ በኮቪድ-19 ወረርሽን ምክንያት ተሰርዟል፡፡ ለ8ኛ ጊዜ ሊካሄድ የነበረው ውድድርም በሥራ መደራረብ ምክንያት ሳይካሄድ መቅረቱን ከፌዴሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ ዘንድሮ ግን ‹‹11ኛው የ30 ኪሎ ሜትር የጐዳና ላይ ሩጫ›› በሚል ስያሜ በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በቢሾፍቱ ከተማ በስኬት ተካሂዷል፡፡
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ህዳር 3/2017 ዓ.ም