ወጣትነት መማር፣ ሥራ ዓለም ውስጥ መግባት፣ ትዳር መመስረት ፣ ልጅ መውለድ እያለ ወደ ጎልማሳነት ያመራል። ይህ በየትኛውም ዓለም ያለ ወጣት የሚሸጋገርበት ሂደት ቢሆንም፤ ይህን ሂደት በትክክል ለማለፍ ግን በተለይ በአሁኑ ወቅት እንደ እኛ ባሉ ሀገሮች ዕድለኛ መሆንን እየጠየቀ ነው።
ወጣት በሀይሉ አንዳርጌ ተወልዶ ያደገው አዲስ አበባ ቢሆንም የልጅነት ህይወቱን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነው ያሳለፈው።የቤተሰቦቹ ቤት ጠባብና ምቹ ባለመሆንዋ ምክንያት አንዳንዴ ጎረቤት እየሄዱ ማደር ግዴታው እንደነበር ያስታውሳል።የመኖሪያ ቤትን ችግር መጋፈጥ ገና በጨቅላ እድሜው ነው።
በኮከበ ጽባህ የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ያጠናቀቀ ሲሆን፣ ከአዲስ ኮሌጅ በአውቶ ሜካኒክ ዲፕሎማ ይዟል።ረጅም ጊዜውን ያሳለፈው ግን በተማረበት የሙያ መስክ በመስራት ሳይሆን በታክሲ ረዳትነት ነው።ረዳትነቱ ግን መንጃ ፈቃድ ለማውጣት ነገሮች አቅልሎለታል። መንጃ ፈቃድ እንዲህ እንዳሁኑ በሚፈልጉት ደረጃ ማግኘት የሚቻልበት ወቅት ስላልነበር የታክሲ ሹፌር ሊያደርገው የሚችለውን ፈቃድ ለማግኘት ሶስት ዓመታትን ጠብቋል።
በሁለተኛ መንጃ ፈቃድ ሰፋ ያለ ሥራ መስራት እንደማይቻል የተረዳው በሀይሉ፣ሶስተኛ መንጃ ፈቃድ ለማውጣት ይነሳሳል።ይሁንና ፈቃዱን ለማውጣት ቀናትን እየተጠባበቀ ባለበት ወቅት የእጅ ስብራት ገጠመው።ይህም ችግር የመንጃ ፈቃድ ማውጣቱን ለአንድ ዓመት እንዲያራዝም አስገደደው። እነዚህ ሁኔታዎች በተፈጠሩበት ወቅት በሀይሉ በአንዲት ጠባብ ቤት በደባልነት ይኖር ነበር።
ዓመቱ አለፈና ሦስተኛ መንጃ ፈቃድ አውጥቶ የተመኘውን ታክሲ ማሽከርከር ጀመረ። በዚህም ከደባልነት ወጥቶ አነስተኛ ቤት በሁለት መቶ ብር ተከራየ። የቤቱ አከራይ የበሀይሉን ወጣትነት አይተው እንደ ልጃቸው ቢያቀርቡትም ማምሸቱን ግን አልወደዱለትም። በነጋ በጠባ ቁጥር ለምን አመሸህ ማለታቸው እያሰለቸው መጣ። አከራዩ ማታ ከ ሁለት ሰዓት በኋላ የግቢያቸውንም በር መቆለፍ ጀመሩ። እነዚህ የአከራዩ እርምጃዎች በሀይሉን ለስድስት ወር ከኖረበት ቤት እንዲለቅ አስገደዱት።
አሁንም ወደ ፈረንሳይ ጉራራ ተራራ አካባቢ ሌላ ቤት ተከራየ፤ቤቱ ያለበት አካባቢ በወቅቱ የለማ አልነበረም፤ትንሽ ከጨለመ ጅብ ይመጣል።ጫካና ቋጥኝ ስለሚበዛው ከዓለም ተለይቶ እንደመኖር ይቆጥረው ጀመር።ይሁንና አማራጭ ስላልነበረው መኖር ጀመረ።
የታክሲ ሥራ ሌሊት መነሳትን ይጠይቃል። ከጅብ ጋር እየተጋሉ መስራትን ለመደ። ነገር ግን ሥራ በሚወጣበት በአንዱ ሌሊት ዘረፋ ተፈጸመበት።በዚህም ምክንያት አሁንም አካባቢውን ለመልቀቅ ተገደደ።
በመቀጠል የገባበት ቤት ቧንቧ፣ መብራትና ሽንት ቤት በአከራዮቹ ፈቃድ የሚወሰንበት ነው። ‹‹የእነርሱ መኝታ ቤት የእኔ ሳሎን ነው፤ የእኔ ሳሎን የእነርሱ መኝታ ቤት ነው። ንግግር እንኳ ይሰማል። አሰራሩ እንደ አሁኑ የጋራ መኖሪያ ቤት እርስ በእርሱ የተሳሰረ ነበር።›› ይላል።
ቦታው ብዙም ሰው ያልነበረበት በመሆኑ የሚገባ ውንና የሚወጣውን ሰው የሚያይ ባለመኖሩ ቤቶች ይዘረፉበታል።‹‹ከአንድም ሁለት ጊዜ በሌሊት ሥራ ስሄድ ተዘርፌያለሁ። ማንም የማንንም አያይም። ግቢው የተጠናከረ አልነበረም። በጊዜው ከአውሬ ለመጠለል እንጂ የተመቸ ቤት ነው ለማለት አያስደፍርም›› ሲል ያብራራል።
አንድ ሰው ቤትን የሚያህል ነገር ሳይኖረው በተከራይነት በተለይ የወጣትነት ዘመንን በከንቱ ማሳለፍን ወጣት በሀይሉ ሲያስበው እጅግ በጣም ይዘገንነዋል። ሰው ቤት ካለው በቤቱ ያለችውን አብስሎ ይኖራል። ቤት ከሌለው እንደሚፈልገው ሆኖ መኖር ያዳግተዋል ይላል።
የጋራ መኖሪያ ቤት በ2005 ዓ.ም ቢመዘገብም እስከ አሁን ቤት አላገኘም።በዚህ የተነሳም ቤት አገኛለሁ የሚለው ተስፋው ስለተሟጠጠ ቁጠባውን መክፈል ያቆማል። ከተከራይነት ለመውጣት ጠንክሮ መስራት እንዳለበት በማመኑ ከታክሲ ሹፌርነት ወደ አንበሳ አውቶቡስ አሽከርካሪነት ከዚያም በአልያንስ አውቶቡስ አሽከርካሪነት እንዲሁም የአገር አቋራጭ መኪናዎችን በመንዳት 14 ዓመት ያሳልፋል።
ዱሮ ሰዎች ከተማሩ ሥራ ያገኛሉ፤በመማራቸው ብቻ ሥራ የሚመደቡ ነበሩ የሚለው ወጣት በሀይሉ፣ዛሬ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ተመርቆ የሥራ ማመልከቻ ይዞ ሲንከራተት እንደሚታይ ይገልጻል።ዱሮ ለሥራም ሆነ መኖሪያ ቤት ለማግኘት ምቹ ነበር።በአሁኑ ወቅት ምንም አይነት ሥራ ቢኖር ቤት ማግኘት ከባድ ሆኗል ይላል።
ወጣት በሀይሉ ለፍቶ ባገኘው ገንዘብ ጣፎ አካባቢ ቤት መስራቱን ይጠቅሳል። ይሁንና ከኪራይ ቤት ለመገላገል ብሎ ቆጥቦ በሰራው ቤት እንዳይኖር ደንቃራ ተፈጥሮበታል። አንዳንዴ የሚያጋጥመው አለመረጋጋት በሰራው ቤት ውስጥ ለመኖር እንዳይችል ያደረገው በሀይሉ፣ መገናኛ አካባቢ ቤት ተከራይቶ በመኖር ላይ ይገኛል።
አንዳንዱ ወጣት ጎጆ ለመቀለሻ የምትሆን ትንሽ ቦታ ሲያጣ ሌሎቹ መሬትን እንደ ወረቀት ቀዳደው ይቀራመቱታል ያለው ወጣት በሀይሉ፣ይህ አላንስ ብሎ በአሁኑ ወቅት በተለይ በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ተፈጥሮ በነበረው ሁከት ሰው ስንት ደክሞ የሰራውን ቤት በማፍረስ እና በማቃጠል ላይ በተሰማሩ ህገወጦች በተፈጠረው ድርጊት ማዘኑን ያመለክታል።
ሰዎች ብሔር ስሌት ላይ ተለጥፈው መሬት በምሪት እና በዕጣ ማግኘት ቀርቶ በዝምድና በብሄር ሆኗል ያለው ወጣቱ፣ የሰራውን ቤት ስም ለማዞር ሁለት ዓመት እንደጠበቀ ይናገራል።በፍጥነት ውል እንደሚፈርሙለት ቢነግሩትም፣ገንዘባቸውን ከተቀበሉ በኋላ ግን ቃላቸውን ማጠፋቸውን ያስታውሳል።
ማንኛውም ሰው ሰርቶ የፈለገው ቦታ የመኖር መብቱ ሊከበር እንደሚገባም ይናገራል። ኢትዮጵያ በተወሳሰቡ ችግሮች ተተብትባለች። ህዝቡ ከምን ጊዜውም በላይ አሁን መተሳሰብ እንዳለበት ይጠቅሳል። መንግሥት የህዳሴው ግድብ ጉዳይ፣ በዓለም የተከሰተው በሽታ ወደ አገር ምግባቱ እና የውስጥ አርበኛ ነኝ ባይ እየፈተነው መሆኑን በማስታወስ፤ ሁሉም መተባበር እና ኃላፊነቱን መወጣት እንደሚኖርበት ያመለክታል።
ካልሆነ ግን በቤት ብቻ ሳይሆን በሥራ እና በአጠቃላይ በወጣቶች እየታጣ ያለው ዕድል ከቀጠለ፤ አደጋው ከባድ በመሆኑ ሁሉም ግዴታውን ሊወጣ እንደሚገባም ይናገራል። ትውልዱ ዕድሉን ማስተካከል እንዳለበት፤ በብሔርተኝነት ላይ ያለውን አስተሳሰብ መለወጥ እና ሙስናን መታገል የግድ መሆኑን በማብራራት ሀሳቡን ያጠቃልላል። ቸር ሰንብቱ!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 21/2012
መርድ ክፍሉ