አዲስ አበባ ኮንስትራክሽን እንደ አሸን የሚፈላበት በመባል በውጭ መገናኛ ብዙሃን ጭምር ይገለጻል። እንደ ሀገርም የኮንስትራክሽን ሥራዎች በኢትዮጵያ በስፋት ይካሄዳሉ። የኮንስትራክሽኑ ዘርፍ በሀገር ኢኮኖሚ ውስጥ ጉልህ ስፍራ እንዳለው ታሳቢ ተደርጎም ከፍተኛ መጠን ያለው በጀት የሚያዝለት።
ዘርፉ ከፍተኛ መጠን ያለው ሀብት የሚንቀሳቀስበት ሲሆን፣ ከሀገሪቱ በጀት 60 በመቶው አካባቢ የሚመደብለት መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያንቀሳቀስ ይጠበቃል።
በመሰረተ ልማትና የመሳሰሉት ግንባታ፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ ተጠቃሽ ነው። የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር አስመሮም ታደሰ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳሉት፤ የትምህርት እና የጤና የመሳሰሉትን ተቋማት እንዲሁም መሰረተ ልማቶችን የሚፈጥረው የኮንስትራክሽን ዘርፉ ነው። ለማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መሰረት የሚሆኑትን የግንባታ ፕሮጀክቶች ይፈጥራል። ለሀገር ወስጥ አጠቃላይ ምርት ዕድገት ከግብርና በመቀጠል አስተዋጽኦ በማድረግም ይታወቃል።
መሰረታዊ የልማት ዓላማዎችን በማሳካት የኢኮኖሚ ዕድገት መፍጠርም ሌላው ፋይዳው ነው። መሰረታዊ የኢኮኖሚ ዓላማዎቹ ከሚባሉት አንዱ ለአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት /ጂዲፒ/አስተዋጽኦ ማበርከት ነው። ለኢኮኖሚው ወሳኝ በሆኑት ገቢ መፍጠርና ገቢ ማከፋፈል ላይም ሚናው ከፍተኛ ነው። በሥራ ዕድል ፈጠራ ያስገኘውን ፋይዳ ኢንጂነር አስመሮም የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን የወጣውን መረጃ ዋቢ አርገው ሲያብራሩም፣ ዘርፉ በ2006 ዓ.ም ወደ 833 ሺ እንዲሁም በ2010 ወደ 2 ነጥብ 2 ሚሊየን የሥራ ዕድል ለዜጎች መፍጠሩን ያመለክታሉ።
ከሥራ ዕድል ጋር በተያያዘ ለዜጎች ከፍተኛ ገቢ ያስገኛል። ለሀገር ኢኮኖሚ ያለው አስተዋጽኦ ደግሞ እጅግ ግዙፍ ነው። ለምሳሌ በ2001 ብቻ 4 ነጥብ 03 በመቶ ነበር፤ በ2010 ለሀገር አጠቃላይ ምርት 19 ነጥብ 3 በመቶ አስተዋጽኦ አድርጓል። እጅግ ግዙፍ ዘርፍ ነው። በዚህ አስር ዓመት የኢኮኖሚውን ፍጥነት እየመራ ነው። ኮንስትራክሽን እና ሌላው አግሪጌት ኢኮኖሚውን ብንመለከተው አጠቃላይ ኢኮኖሚውን ሲመራ የነበረው / ዘ ግሮውዝ ድራይቨር/ ይህ ዘርፍ ነው ሲሉ ያብራራሉ።
በዘርፉ እጅግ በርካታ አነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት ይሳተፋሉ። በመሆኑም ዘርፉ ለሥራ ዕድል ፈጠራ /ለኢንተርፕሬነር/ መልካም አጋጣሚን ይፈጥራል። የውጭ ምንዛሬ ማመንጨት ሚናው ላይ ከተስተዋለው ውስንነት በስተቀር ኢትዮጵያ ውስጥ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ከነችግሮቹ ለአጠቃላይ የሀገር ዕድገትና ልማት የማይተካ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል። እነዚህ ቀጥተኛ አስተዋጽኦዎቹ ናቸው ይላሉ።
እንደ ኢንጂነሩ ገለጻ፤ ዘርፉ ቀጥተኛ ያልሆነ አስተዋጽኦም አለው። ኮንስትራክሽን ባለው የፊትና የኋልዮሽ ትስስር መሰረት ሌሎች ዘርፎች እንዲነቃቁ እንዲስፋፉ ያደርጋል። ለምሳሌ የኋልዮሽ ግንኙነቱን ብናይ ከ40 እስከ 60 በመቶው ግብአት ይጠቀማል፤ ስለዚህ አምራች ኢንዱስትሪውን አብሮ የሚያሳድግ ይሆናል። የፊት ግንኙነቱን ስንመለከት ደግሞ ኮንስትራክሽን መሰረተ ልማት አንዱ ውጤቱ ነው። መሰረተ ልማት ሲስፋፋ ከተሞች እና ኢኮኖሚው አብረው ይንቀሳቀሳሉ።
የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ሌሎች የሚጫ ወቱበትን ሜዳ የሚያመቻች መሆኑንም ያመለክታሉ። ሌሎች ዘርፎች ተጫዋቾቹን /ዘ አክተርስ/ን ያቀርባሉ። ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ግን ሌሎች ዘርፎች የሚጫወቱበትን ሜዳ ያመቻቻል ይላሉ።
ከከፍተኛ የሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር ተያይዞ ቀጥተኛ ባልሆነ መልኩም ብዙ የሥራ ዕድል ይፈጥራል። ይህን የሰው ኃይል ታሳቢ በማድረግ በርካታ ሱቆች፣ ቤት አከራዮች፣ ወዘተ ይፈጠራሉ። ዘርፉ ለእዚህ ሁሉ የሥራ ዕድል የሚፈጥር ነው። ስለዚህ ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ያልሆነ አስተዋጽኦዎቹን ስንመለከት የኮንስትራክሽን ዘርፍ ለሀገራችን ዕድገት ምናልባት የማይተካ ሚና እየተጫወተ ያለ ዘርፍ ነው ማለት ይቻላል።
ሌሎች የዘርፉ ባለድርሻዎች እንደሚገልጹትም የኮንስትራክሽን ዘርፉ በሀገር ኢኮኖሚ ውስጥ ጉልህ ስፍራ አለው። ከግብርና በመቀጠል ለአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት እስተዋጽኦ እያደረገ ነው። ይህን ሚናውን በሚገባ እንዲወጣ ግን ከተተበተበበት ሙስና መላቀቅ ይኖርበታል። ዘርፉ በኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች ማኔጅመንት በኩል ሰፊ ክፈተት አለበት፤ በዚህ የተነሳም ግንባታዎች በተያዘላቸው ጊዜ፣ በጀት እና ጥራት ሲጠናቀቁ አይስተዋልም። በባለሙያ መመራት፣ በቂ የውጭ ምንዛሬና የብድር አቅርቦትም ሊያገኝ ይገባል። መንግሥት እንደ ደንበኛም እንደ ሬጉላቶሪ ተቋም ራሱን አብቅቶ ዘርፉን መምራት ይኖርበታል።
የዘርፉን አቅም ሀገራችን በእውቀት ላይ በተመሰረተ መልኩ እየተጠቀመችበት ነው ሊባል ይቻላል? የሚል ጥያቄ ያቀረብንላቸው ኢንጂነር አስመሮም እንደሚናገሩት፤ ይህን በብዙ መንገድ ማየትን ይጠይቃል። አንዱ ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ተገቢውን ሀገራዊ ተልዕኮ እንዲወጣ ምን ማድረግ ያስፈልጋል? የሚለውን ማየትን ይጠይቃል። በመሰረታዊነት ሦስት ነገሮች ያስፈልጋሉ። አንዱ የታቀደ፣ ቀጣይነት ያለው፣ ተቋማዊ የሆነ የአቅም ግንባታ ሥራ ያስፈልጋል። ይህ መፈጸም ይኖርበታል። ሁለተኛው የማያወላዳ ሬጉላቶሪ ፍሬም ወርክ ነው። ሦስተኛው የፊሲካል ጉዳይ ነው፤ ዘርፉ ወደ 25 በመቶ የውጭ ምንዛሬ ይጠይቃል። ስለዚህ ምቹ የፊሲካል ፖሊሲ ይፈልጋል። በእነዚህ ሦስት እይታዎች ነው መለካት ያለበት።
ከአቅም ግንባታ አኳያ የመጀመሪያው ሆኖ የሚመጣው የሰለጠነና ስነ ምግባር የተላበሰ የሰው ኃይል ከመፍጠር አኳያ የተሠሩ ሥራዎች የሚለው ነው። ሌላው የኩባንያዎች ልማት ነው። ሌላው የአሠራር ስርዓት ሲሆን፣ ተወዳዳሪ ኩባንያዎች፣ የተሳለጠ የግብአት አቅርቦት እና የውጭ ምንዛሬ ግኝት ናቸው።
በእነዚህ ረገድም እጅግ ብዙ ሥራዎች መሠራታቸውን ኢንጂነሩ ይጠቅሳሉ። ከትምህርት ፖሊሲው አንስተን ስንመለከተው ለዘርፉ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ከፍተኛ መጠን ያለው የሰው ኃይል ስናፈራ ቆይተናል፤ ብዙ ውስንነቶች እንዳሉም ይታወቃል። ኢንዱስትሪው ውስጥ እየተንቀሳቀሰ ያለው የሰው ኃይል ብቃት በምዘና የተረጋገጠ ግን አይደለም ይላሉ።
ሌላውና ትልቁ ከማስፈጸም አቅም ጋር የተያያዘው ነው። ከመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ወዲህ ያለውን እንኳ ብናይ፣ ብዙ ሥራዎች ተሠርተዋል። ለአብነትም በ2006 የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ልማት ፖሊሲ ተዘጋጅቷል። ከዚያ በኋላ ይህ የኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች ማኔጅመንት ኢኒስቲትዩት ተቋቁሟል፣ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ የአቅም ግንባታ ፓኬጅ ተዘጋጅቷል፣ ዘርፉን የሚመራ የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ተቋቁሞም ነበር፤ አሁንም ከከተማ ልማት ጋር አለ። ትልልቅ የመንግሥት ኮርፖሬሽኖች መቋቋማቸው፣ ሌላው በቅርቡ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ተቆጣጣሪ ባለስልጣን መቋቋሙ ከተከናወኑት ተግባሮች መካከል ይገኙበታል። አሁን ደግሞ ዘርፉ በአጭር እይታ ከዚህ በዘለለ የ30 ዓመት ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቷል። እነዚህ በሙሉ ጥረቶቹን ያመለክታሉ።
እነዚህ ሁሉ በቂ እንዳልሆኑም በመጥቀስ፣ ከአቅም ግንባታም፣ ከሬጉላቶሪ ፍሬም ወርክም፣ ምቹ ፊሲካል ፖሊሲ ከመፍጠር አኳያ ብዙ ያልተሻገርናቸው ጋሬጣዎች አሉብን ይላሉ።
እንደሚታወቀው መንግሥት በሰው ኃይል ልማት ላይ አዲስ ፖሊሲ በማዘጋጀት በ70/30 እና በቴክኒክና ሙያ ተቋማት በኩል በርካታ የሰው ኃይል ልማት ሥራዎችን ለመሥራት ሞክሯል። ዘርፉ ግን ምሩቃኑን እያስገባቸው እንዳልሆነ ይጠቆማል። በዚህ የተነሳም ዘርፉ ከልማዳዊ አሠራር አሁን ሊወጣ አልቻለም እየተባለ ነው።
ዘርፉ በርካታ ችግሮች እንዳሉበት በኮንስትራክሽን ዘርፉ የሚሠሩት አርክቴክት አማኑኤል ተሾመም ይገልጻሉ። ለእሳቸው ግን የባሰው ችግር ዘርፉ በባለሙያ አለመመራቱ ነው። እንደ እሳቸው ገለጻ፤ የኮንስትራክሽን ዘርፉ ችግር በባለሙያ አለመመራቱ ነው። ይህም ከዕቃ አቅራቢ ይጀመራል ይላሉ። መሰረታዊው ነገር ድርጅቶቹ፣ ትምህርት ቤቶቹ፣ አሠሪ አካላቱ/መንግሥትም ሆነ የግሉ ዘርፍ/መመራት ያለባቸው በባለሙያ መሆኑን ጠቅሰው፣ የሚፈልገውን የሚያውቀው ባለሙያ መሆኑን ይገልጻሉ። ‹‹ብዙ ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ፣ ለእኔ መሰረታዊ ችግር ብዬ የማስቀምጠው ባለሙያን ማዕከል ያላደረገ/ፕሮፌሽናል ሴንተርድ አለመሆኑ/ መሆኑ ነው። ይህንን የቀየርን ቀን በዚህ ዘርፍ ትልቅ አብዮት/ሪቮሉሽን/መጣ ማለት ነው።›› ሲሉ ያስገነዝባሉ።
እንደ አርክቴክቱ ገለጻ፤ እንደ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን እንደ አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገሮች አርባናይዜሽን ገና ነው። እኛ እና ጎረቤት ሀገሮቻችን ከዓለም በከተማ ልማት በዝቀተኛ ደረጃ እንገኛለን። የኮንስትራክሽን ዘርፉ ዋናው የኢኮኖሚው እጅ መሆኑ ለቀጣዮቹ አስራ አምስትና ከዚያ በላይ ዓመታት ይቀጥላል።
በዚህ ውስጥ ውጤት አንጻራዊ ስለሆነ /ሪሌቲቭ ስለሆነ/ ከትምህርት ቤት በጥሩ ትምህርት የወጡ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ልምድ ያላቸው ልጆች የሚፈጠሩ ከሆነ ዘርፉ በዚህ ዘመን የነበሩ ሰዎች የሙቀት መጠን መለኪያ ቴርሞ ሜትር ሆኖ ያልፋል ብዬ አስባለሁ ይላሉ።
ከባለሙያ ጋር ተያይዘው የሚነሱት ተግዳሮቶች ብዙ መገለጫዎች መኖራቸውን የሚጠቅሱት ኢንጂነር አስመሮም፣የሙያ ብቃት ጉዳይን ያነሳሉ። ‹‹የሙያ ብቃት ስንል ማየት ያለብን ጉዳይ አለ። አንዱ የምሩቃን ፕሮፋይል ወይም ኮምፒታንስ ነው። አንድ ተመራቂ ተመርቆ ሲወጣ ሊያሟላቸው የሚጠበቁበት ጉዳዮች አሉ። ይህም የግራጁዌት ኮምፒተንስ ነው። ሁለተኛው የሙያ ብቃት /ፕሮፌሽናል ኮምፒተንስ/ ነው። እነዚህም ወደ ኢንዱስትሪው ከተቀላቀለ በኋላ ሊከውናቸው የሚገባ ብቃቶች ናቸው።
70/30 የሚባለው የትምህርት ፖሊሲ በእውቀት፣ በክህሎት እና በአመለካከት የታነጸ ባለሙያ ለማፍራት ውስንነቶች ነበሩበት የሚሉት ኢንጂነሩ፣ በአብዛኛው ቁጥር ላይ ያተኩራል ሲሉ ያብራራሉ። ችግሩ የትምህርት ማዕከላት ላይ ብቻ የተንጠለጠለ እንዳልሆነም ጠቅሰው፣ የኢንተርንሽፕ ጉዳይም እንዳለ፣ ተማሪዎች ወደ ኢንዱስትሪው ለኢንተርንሽፕ ሲላኩ ዘርፉ ሚናውን እንዳልተጫወተም ይጠቅሳሉ።
ሁለተኛው ምሩቃን ኢንዱስትሪው ውስጥ ከገቡ በኋላ ያለው መሆኑን ያመለክታሉ። መጀመሪያም ወደ ኢንዱስትሪው የማስገቢያ ነጥቡ ትክክል አይደለም። እኛ ሀገር የሙያ ምዘና ከነችግሩም ቢሆን መለስተኛ እና አነስተኛ ባለሙያዎች ሲኦሲ አለ። ለከፍተኛ ባለሙያዎች ግን ይህ የለም። በቀላሉ የትምህርት ማስረጃውን ያመጣል፤ የሥራ ልምድ ብሎ ከየቦታው አጽፎ ይቀርባል፤ ማስረጃው ወረቀት ላይ ያረፈ ነው። በምዘና አይደለም የብቃት ማረጋገጫ እየተሰጠ ያለው። ስለዚህ ችግሩ በምሩቁ ፕሮፋይል እንዲሁም በፕሮፌሽናል ፕሮፋይል ላይም አለ የሚሉት ኢንጂነሩ፣ ይህን ችግር ለመፍታት ይህ ኢኒስቲትዩት መሰረታዊ ሥራ እየሠራ መሆኑን ያመለክታሉ።
እንደ ዋና ሥራ አስኪያጁ ገለጻ፤ ኮንስትራክሽን ዘርፍ ውስጥ የሚሰማሩ የከፍተኛ ባለሙያዎች ማለትም አርክቴክቶች፣ ሁሉም ዓይነት መሀንዲሶች፣/የሲቪል፣ ኤሌክትሪካልና መካኒካል/ የፕሮጀክት፣ የቅየሳ ባለሙያዎች ሁሉ የሙያ ብቃት መጀመሪያ ኦኩፔሽናል ስታንዳርድ የሚባል የለንም፤ እሱ እየተዘጋጀ ነው። የሙያ በቃት ምዘናና ማረጋገጫ ስርዓት ዝርጋታም በዚህ ሁለትና ሦስት ወር ውስጥ ይጠናቀቃል። ስለዚህ በቀጣይ ወረቀት ላይ ከተመሰረተ የምዘና ስርዓት በግምገማ /አሰስመንት/ ላይ ወደ ተመሰረተው እንሸጋገራለን፤ በዚህም የባለሙያው ብቃት በምዘና ወደ ሚሸጋገርበት ስርዓት እንገባለን።
ይህም ኢንዱስትሪው ብቃቱ በተመዘነ ባለሙያ እንዲመራ ዕድል እንደሚፈጥር ጠቅሰው፣ የሰለጠነና ስነ ምግባር የተላበሰ ባለሙያ ከማፍራት አኳያ ተዋናዮቹ ብዙ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ የትምህርት ተቋማት፣ መንግሥት የሙያ ማህበራት፣ ኩባንያዎች ሁሉም ባለድርሻዎች የየራሳቸውን ድርሻ መጫወት ይጠበቅባቸዋል ይላሉ።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 21/2012
ኃይሉ ሣህለድንግል