ከቃሊቲ ማሰልጠኛ አደባባይ ተነስቶ ከቱሉ ዲምቱው የአዲስ አዳማ የፍጥነት መንገድ ጋር ይጋጠ ማል፡፡ ከቃሊቲ ወደ ምስራቁና ደቡቡ የሀገሪቱ ክፍል ለመውጣትና ለመግባት ሲያጋጥም የቆየውን የትራፊክ መጨናነቅ እንደሚያሻሽለውም ታምኖበታል፡፡ የአሪቱን ገቢና ወጪ ንግድ በማሳለጥ ረገድም ፋይዳው የጎላ እንደሚሆን ይጠበቃል- የቃሊቲ ቱሉ ዲምቱ የመንገድ ፕሮጀክት፡፡
የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ እያሱ ሰለሞን ፕሮጀክቱ በመጋቢት ወር 2009 ዓ.ም ነው የተጀመረው፡፡የመንገድ ፕሮጀክቱ 11 ኪሎ ሜትር ርዝመትና 50 ሜትር የጎን ስፋት ያለው ሲሆን፣ 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ተመድቦለት ግንባታው እየተከናወነ ይገኛል፡፡ ፕሮጀክቱን በተያዘለት የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅም እየተሰራ ነው፡፡ግንባታውንም የቻይናው ኮሚዩኒኬሽን ኮንስትራክሽን ኩባንያ /cccc/ በሥራ ተቋራጭነት እንዲሁም ኢንጂነር ዘውዴ በአማካሪ ድርጅትነት የማማከርና የቁጥጥር ሥራውን ያከናውናሉ፡፡
እንደ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ግንባታው ሶስት ዋና ዋና ማሳለጫዎችን ያካተተ ነው፡፡ የመጀመሪያው የፕሮጀክቱ መነሻ የሆነው የቃሊቲ ማሰልጠኛ አደባባይ ማሳለጫ ድልድይ ሲሆን፣ይህም 40 ሜትር ርዝመት ያለውና ከሳሪስ የሚመጣውን ትራፊክ ተቀብሎ ወደ ቃሊቲ ማሻገር የሚያስችል ነው፡፡ ከስር ያለው ነባሩ የቃሊቲ አደባባይ ደግሞ ወደ ሳሪስ አቦና ኃይሌ ጋርመንት አደባባይ የሚጓዙ ተሽከርካሪዎችን ያስተላልፋል፡፡
ሁለተኛው ማሳለጫ በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘው የጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል አካባቢ የሚገኘው ሲሆን ከአትሌት ደራርቱ ትምህርት ቤት ወደ አቃቂ ከተማ የሚወስድ ይሆናል፡፡ ድልድዩ 90 ሜትር ርዝመት እንዲኖረውም ተደርጎ እየተሰራ ይገኛል፡፡ ሶስተኛው ማሳለጫ ደግሞ ቀደም ሲል ጋሪ ድልድይ ተብሎ የሚጠራውና አቃቂ አካባቢ የሚገኘው ነው፣ይህም 20 ሜትር ስፋትና 50 ሜትር ርዝመት እንዲኖረው ተደርጎ እየተሰራ ነው፡፡ እስካሁን ባለው ሂደትም የመንገድ ፕሮጀክቱ አፈፃፀም እስከ ሰኔ 2012 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ 62 ከመቶ ደርሷል፡፡
ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ የመንገድ መሰረተ ልማቶችን ለማስፋፋት ጥረት እየተደረገ ያለው አዲስ አበባ ቀድማ የለማች ከተማ ሆና ባለችበት ሁኔታ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በመንገድ ግንባታ ሂደት ላይ በተደጋጋሚ የወሰን ማስከበር ችግሮች ሲያጋጥሙ እንደሚስተዋል ጠቅሰው፣በዚህም ፕሮጀክት የወሰን ማስከበር ችግር አጋጥሟል ይላሉ። ከመንገድ ፕሮጀክቱ ባህሪ አንፃርና እስከ 50 ሜትር የሚደርስ ስፋት እንዳለው አመልክተው፣ይህን ወሰን ጠብቆ ለመሄድ ሲባል የሚነሱ ቤቶች በመኖራቸው የወሰን ማስከበር ችግሮች ማጋጠማቸውን ያብራራሉ፡፡
የከተማ አስተዳደሩ የበላይ አመራር የቅርብ ክትትል እና ድጋፍ የሚደረግበት የመንገድ ፕሮጀክቱ ፣ከሚመለከታቸው የከተማ አስተዳደሩ አስፈፃሚ ተቋማት ጋር ቅንጅት በመፍጠር አጋጥመው የነበሩ የወሰን ማስከበር ችግሮችን ለመፍታት መቻሉንም ይገልጻሉ፡፡
ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ መንገዱ የከተማዋ ከፍተኛ ወጪና ገቢ ንግድ እንቅስቃሴዎች የሚከናወኑበትና ተሽከርካሪዎች ከፍተኛ ምልልስ የሚያደርጉበት ከወደብ የሚመጡ መኪናዎችም የሚገቡበት አቅጣጫ መሆኑን ጠቅሰው፣ በግንባታው ሂደትም ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ የሚታይበት መስመር መሆኑን ያመለክታሉ። የትራፊክ እንቅስ ቃሴው ብዙም ሳይስተጓጎል የግንባታውም እንቅስቃሴ ሳይቋረጥ ለማስቀጠል በሚደረገው ሂደት ውስጥ የተወሰኑ የትራፊክ ፍሰት ጫናዎች ሲፈጠሩ መቆየታ ቸውንም ይናገራሉ፡፡
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ከሚመለከታቸው የከተማ አስተዳደሩ አስፈፃሚ አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት ያጋጠሙት ችግሮች ተፈተዋል፡፡ የወሰን ማስከበር ችግሮቹ ከተፈቱ በኋላም አሁን ባለው ሁኔታ አንደኛውን የመንገዱን ክፍል አስፓልት በማንጠፍ የትራፊክ እንቅስቃሴው የተሻለ እንዲሆን ለማድረግ ጥረት ተደርጓል፡፡ የቀሩ ሥራዎችንም በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ሰርቶ ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል፡፡
በዚህ የመንገድ ፕሮጀክት በአሁኑ ወቅት የቤዝ ኮርስ፣ሰብ ቤዝና የአስፓልት ሥራዎችን ጨምሮ የድልድይ ግንባታዎች እየተከናወኑ ናቸው፡፡ አጠቃላይ ሥራዎች ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የበላይ አመራሮች፣ በከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባና በሚመለከታቸው አካላት እንዲሁም በቴክኒክ ባለሙያዎች የቅርብ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገለት የሚገኝ ፕሮጀክት በመሆኑ አሁን በጥሩ አፈፃፀም ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
የቃሊቲ ቀለበት መንገድ አደባባይ ቱሉ ዲምቱ ፍጥነት መንገድ ከደቡብና ምስራቅ ኢትዮጵያ አቅጣጫ ወደ አዲስ አበባ ተሽከርካሪዎችን የሚያስገባ ትልቅ ኮሪደር ከመሆኑ አኳያ ግንባታው ሲጠናቀቅ የትራፊክ እንቅስቃሴውን በማሻሻል ረገድ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው የሚጠበቅ እንደመሆኑ አሁንም ግንባታውን አፋጥኖ ለትራፊክ ክፍት ማድረግ ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ሐምሌ 21/2012
አስናቀ ፀጋዬ