‹‹አዋጁ እንደከዚህ ቀደሙ ዝም ተብሎ የመንግሥት ሠራተኛ የሚል ስም ይዞ መቀጠል የማያስችል ነው›› -ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ

ከሰሞኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበለትን የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች ረቂቅ አዋጅ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል:: ከአዋጁ ዓላማዎች መካከል የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የተሰጣቸውን ኃላፊነት፣ ተግባርና ተልዕኮ በአግባቡ እንዲወጡ የሚል ተጠቃሽ ነው፤ በተጨማሪም ብዙሃነትና አካታችነትን ያገናዘበ እንደሆነ ይነገራል::

ከዚህ አኳያ አዲስ ዘመንም በሕዝብ ተወካዮች ምከክር ቤት የሰው ሃብት ልማት ሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር)ን የዛሬው ወቅታዊ እንግዳ ያደረጋቸውን ሲሆን፣ ከአዋጁ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ጥያቄዎችን በማንሳት የሰጡትን ማብራሪያ እንደሚከተለው አጠናቅሯል::

አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ የጸደቀው የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች አዋጅ የመሻሻሉ ዋና ዓላማ ምንድን ነው?

ነገሪ (ዶ/ር)፡– በኢትዮጵያ በእስካሁኑ ጉዞ የተለያዩ መንግሥታት እንደነበሩ የሚታወቅ ነው፣ ሁሉም የየራሳቸው አደረጃጀት እንደነበራቸው ይታወቃል:: ነገር ግን በሀገር ደረጃ መንግሥት መንግሥት ሆኖ ቢሮክራሲውን ከዘረጋ ጊዜ ጀምሮ ብዙ ክፍተቶች ይታዩ ነበር:: ያንን ክፍተት ደግሞ በማጥናትና በመለየት አንድ ውሳኔ ላይ መድረስ የግድ ነበር:: በተለይም በቅርብ ጊዜ ስራ ላይ የነበረውን 1064/2010 የፌዴራል ሰራተኞች አዋጅን ማሻሻል አስፈላጊ ሆኗል::

የቀድሞውን የተካው አዲሱ አዋጅ ነባሩን መሰረት አድርጎ የተሻሻለ ነው:: በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ የደረሰችበትን ደረጃ በምናይበት ጊዜ የፐብሊክ ሰርቪሱን ወይም የፐብሊክ ሴክተሩን የአገልግሎት አሰጣጥን አስመልክቶ ጥናቶች ተካሂደው ነበር:: ጥናቱን የሰሩት የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽንና የሚመለከታቸው የክልልና የፌዴራል አካላት ናቸው::

ጥናቱን ያጠኑ አካላት፤ ረቂቁን ሲያቀርቡልን የተረዳነው በመንግሥት አስተዳደር ውስጥ ትልቅ ችግር መኖሩን ነው፤ ይህ ማለት በመንግሥት ሠራተኞች አገልግሎት አሰጣጥ ትልቅ ችግር እንዳለና በአገልግሎት አሰጣጡ የሕዝብ እርካታ አለመኖሩን አመላካች ነው:: በተጨማሪም ከጊዜ ወደጊዜ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትም ሆነ ፍጥነትም እንደሌለው ማጤን ተችሏል::

ከዚህም በላይ የስነምግባር ችግር እንደሚስተዋልና ይህ ደግሞ የሚያስከትለው ጉዳት በተገልጋዩ ላይ ብቻ ሳይሆን በሀገር ላይም ጭምር እንደሚሆን መረዳት ተቸሏል:: እነዚህ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች የመንግሥት መስታወት ናቸው ተብለው የሚታሰቡ ቢሆንም በፐብሊክ ሰርቪሱ ላይ ጥራት ያለው አገልግሎት ካለመኖሩም በተጨማሪ ያለእጅ መንሻና ማጉላላት አገልግሎት የማይሰጥባቸው በመሆናቸው ሕዝቡ እያደር ቅሬታ ውስጥ የሚገባ መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው:: ምክንያቱም በኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት ዓመታት ያለ እጅ መንሻ አገልግሎት ማግኘት አይቻልም ተብሎ የተደመደመበት ሁኔታ ተፈጥረዋል::

በሌላ በኩል በጥናቱ የተለዩት ምቹ የሥራ ቦታ፣ የዘመነ ቴክኖሎጂ የሌለበት የሲቪል ሰርቪስ መኖሩን ነው:: ከአደረጃጀት አንጻር እንዲሁ ሲታይ በአንድ መስሪያ ቤት ውስጥ መዋቅሩ የሚሸከመው ብዙ የሰው ኃይልን ነው፤ ብዙ የሰው ኃይል ሲሸከም ደግሞ የሚያገኘው ጥቅም አናሳ ነው:: በብዛታቸው መጠን አገልግሎቱ የሚያረካ አይደለም::

የተወሰኑት ይሰራሉ:: ሌሎቹ ግን የተወሰኑ ሠራተኞች በሰሩት ትከሻ ላይ ተንጠላጥለው የሚኖሩ ናቸው:: የሚለፋው ሰራተኛ ጥቂት ሲሆን፣ የሚያገኘው ጥቅምም በጣም አናሳ ነው:: ስለዚህ አንደኛ ከአደራጃጀት አንጻር የመንግሥት ሴክተር በጣም ሰፊ ነው:: የሠራተኛው ቁጥር ሀገሪቷ ከምትሸከመውና አገልግሎቱ ከሚፈልገው በላይ የበዛ ነው::

ይህ የሆነው እንዴት ነው ቢባል ከላይ በሕግ የሚመራ፣ የሚወስን፣ በበላይነት ስራን በአግባቡ የሚመዝንና ለዚህ ስራ ደግሞ ይህን ያህል ሰው ያስፈልጋል የሚል ማዕከላዊ የሆነ የሕግ ማሕቀፍ ባለመኖሩ ነው:: የተለያዩ ተቋማት መዋቅራቸውን ሰርተው ያመጣሉ፤ ከዚያም ያጸድቃሉ:: ይህ አይነቱ አሰራር እስከ ወረዳ ድረስ ሲታይ በጣም ሰፊ በዚያ ላይ ደግሞ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ችግር ያለው ነው::

ሌላው ከሠራተኛ ጥቅማጥቅም ጋር በተያያዘ ሲሆን፣ የሠራተኛው ደመወዝም ሆነ በየጊዜው ይጨመርለት የነበረው እርከን የቆመበት ሁኔታ ተፈጥሯል:: ጥቅማጥቅም የተባለውም በነበረበት የሚሄድ፣ የሠራተኛ ተነሳሽነት የሌለበት ሲሆን፤ የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ያመጣው ነገር ቢኖር የሲቪል ሰርቪስ ሴክተሩ ውጤታማ እንዳይሆን ነው::

አንድ ሀገር እንደሀገር መቆም የሚችለው ደግሞ ተቋማት በአግባቡ ሲገነቡ ነው:: የመንግሥት ተቋማት በሚፈለገው ደረጃ ከተገነቡና ብቁ ከሆኑ፣ ግልጸኝነትና ተጠያቂነት ላይ የተመሰረተ አገልግሎት የሚሰጡ ከሆነ ያ ሀገር አንዳንድ ጊዜ የፖለቲካ አመራሩ ማለትም ራሱ መንግሥት በማይኖርበት ጊዜ እንኳ ተቋማቱ ራሳቸው የመቀጠል እድል ይኖራቸዋል:: ከዚህ ጋር ተያይዞ በርከት ያሉ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል፤ መንግሥት ሳይኖራቸው አንድ ሁለት ዓመት የቀጠሉ ሀገሮች አሉ:: ስለዚህ አሁን ባለበት መቀጠል ስለሌበት በጥናት የተለየው እነዚህን የሚፈታ መፍትሔ በማስፈለጉ በጥናት ለመለየት ተሞክሯል::

በሌላ በኩል በጥናቱ ከተለየው ውስጥ የብዝሃነትና ያካታችነት ችግርም መኖሩ ነው:: በመሆኑም የጠቅስኳቸውን ዋና ዋና ችግሮችን ለመፍታት መፍትሔው ምንድን ነው በሚል በመጀመሪያ እንዲወጣ የተደረገው ፖሊሲ ነው:: በፊት የነበረው አዋጅ ፖሊሲን መሰረት ያደረገ አልነበረም:: ስለሆነም አሁን ጥናት ላይ የተደገፈ ፖሊሲ ከተቀረጸ በኋላ እሱንም ፖሊሲ መሰረት አድርጎ ደግሞ አዋጅ መውጣት እንዳለበት ታወቀ::

ይህ አዋጅ በአንድ በኩል የሀገራችን ሲቪል ሰርቪስ የነበረበትን አጥንቶ ዛሬ እንደ ሀገር የኢትዮጵያ ሕዝብ ምን ያህል እየጨመረ እንደሆነ፣ የተቋማት ብዛት ምን ያህል እየጨመረ እንደሆነ፣ ሕዝባችን ምን አይነት አገልግሎት እንደሚፈልግ፣ የአገልግሎት ሁኔታ ምን አይነት ችግር እንዳለበት ካጠኑ በኋላ ፖሊሲውን መሰረት አድርጎ ደግሞ አዋጅ ከዚያም በቀጣይ የሚጸድቁ ደንቦች ይኖራሉ:: መመሪያውም ከሲቪል ሰርቪስ ተዘጋጅቷል:: ይህ አዋጅ ዋና ያስፈለገበት ምክንያት ኢትዮጵያ ያለባትን ችግር ሊፈታ የሚችል እንዲሆን ነው::

የአዋጁ ዓላማ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ወይም ደግሞ የፌዴራልም ሆነ የክልል ሠራተኛ የራሱ ችግር ስላለበት ይህን ሴከተር መቀየር በማስፈለጉ ነው፤ መቀየር ካልቻልን ግን እንደ ሀገር የተጀመረው ሪፎርም ከግቡ መድረስ አይችልም:: እንደ ሀገር በኢኮኖሚው፣ በማኅበራዊውም ሆነ በፖለቲካው ትልልቅ ሪፎርም እየተካሄደ ነው::

በጸጥታውም ሆነ በሚሊታሪ እንዲሁም በደህንነቱ ዙሪያ ባለፉት አምስትና ስድስት ዓመታት በርካታ ሪፎርሞች እየተካሔዱ ናቸው:: እነዚህ ትልልቅ ለውጦች ውጤታማ ሊሆኑ የሚችሉት በጣም ግዙፍ የሆነው የሲቪል ሰርቪስ ሴክተር ሪፎርም ተደርጎ ውጤታማ አገልግሎት ሲሰጥ ነው:: አዲሲቷ ኢትዮጵያ ልትፈጠር የምትችለው በዚህ መልክ ነ::

አዋጁ የሠራተኛውን ጥቅማጥቅም ያካተተ ነው፤ ተወዳድረው የተሻለ የሚሰሩ ሠራተኞች የተሻለ ነገር የሚያገኙበትን ሁኔታ አስቀምጧል:: አዋጁ እንደከዚህ ቀደሙ ዝም ተብሎ የመንግሥት ሠራተኛ የሚል ስም ይዞ መቀጠል የማያስችል ነው:: የተዘጋጀውም ይህን ታሳቢ በማድረግ ነው::

አዲስ ዘመን፡- ነጻ እና ገለልተኛ ሲቪል ሰርቪስ ሲባል የሚገለጸው እንዴት ነው?

ነገሪ (ዶ/ር)፡- ወደዚህ ከመምጣታችን በፊት የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር ፖሊሲ የሚል አለ፣ ይህ አዋጁ የሚተገበርበት የመንግሥት አገልግሎት ሰነድ ሪፎርም ፍኖተ ካርታ ነው:: ፖሊሲው የያዘው ትልቅ ጉዳይ ነው:: ዋና ዋና ምሰሶ የሚባሉት ምንድን ናቸው ከተባለ ከሠራተኛ ምልመላ ቅጥር ጀምሮ ከዚህ ቀደም የነበረው ብቃትን መሰረት ያደረገ አልነበረም የሚል ነው:: ብቃት ሲባል ከሌሎች ጋር ሲወዳደር የተሻለ የሚፈጽም እና ያንን ስራ ለመስራት ከሌሎች ጋር ሲወዳደር የተሻለ መፈጸም የሚችል መሆን ማለት ነው:: ከዚህ ቀደም በዚህ ላይ ትኩረት አይደረግም ነበር::

በሌላ በኩል ቀደም ሲል የነበረው አካሄድ፤ አንድ ሰው መቀጠር የሚችለው ሰው ሲኖረው ወይም ባለስልጣን የሆነ ሰው ሲያውቅ ነው ተብሎ ይታሰባል:: ብዙዎች፣ የመንግሥት መስሪያ ቤት ለመቀጠር ገንዘብ የለኝም እስከማለትም የደረሱበት ሁኔታ ተፈጥሮ እንደነበር ያወራሉ:: አሁን ይህንን የሚያስቀር ብቃትን መሰረት ያደረገ ሲቪል ሰርቪስ እንዲገነባ ነው የተመቻቸው:: ይህ ብቃት የተባለው መመዘኛ ደግሞ አሁን ስራ ላይ ያሉትንና ለወደፊትም የሚቀጠሩትን የሚጨምር ነው::

ይህ ማለት በአሁኑ ሰዓት ስራ ላይ ያሉት ከስራቸው ጋር በተያያዘ ስልጠና ይሰጣቸዋል፤ ይፈተናሉ:: ያንን በብቃት የሚያልፉ ከሆነ ይቀጥላሉ:: አንድ ሰራተኛ በዓመት ሁለት ጊዜ ከሚፈለገው ውጤት በታች የሚያመጣ ከሆነ ሠራተኛ ሆኖ መቀጠል አይችልም::

ሌላው አንድ ሰው የመንግሥት ሠራተኛ ሆኖ ለመቀጠር ዲግሪና ከዚያ በላይ ስለያዘ ብቻ መቀጠር አይችልም:: ለመቀጠር ፈተና ተሰጥቶት ብቁ መሆን ሲችል ነው:: ስለዚህ በብቃት ላይ የተመሰረተ ውድድር አለ ማለት ነው:: ይህ በብቃት ላይ የተመሰረተ ውድድር መኖሩ የሚያስገኘው ውጤት ዘመድ ስለሌለኝ ወይም ገንዘብ ስለሌለኝ መቀጠር አልቻልኩም የሚለውን ቅሬታ የሚያስወግድ መሆኑ ነው:: ከዚህ አኳያ ሥርዓቶች ይዘረጋሉ::

ሌላው ነጻ እና ገለልተኛ መሆን አለበት:: ሲቪል ሰርቪሱ እያነሳቸው ያለው ዋና ዋና ጉዳዮችን ነው:: ዋና ዋና ይዘቶች ምንድን ናቸው ከተባለ ነጻ እና ገለልተኛ ሲቪል ሰርቪስ ማለት የፖለቲካ ፓርቲ አባል ስለሆነ የፈለገውን ያደርጋል ማለት አለመሆኑን የሚያሳውቅ ነው:: ይህ ካነሳችሁት ጥያቄ ጋር የሚሔድ መልስ ነው:: የፖለቲካ ፓርቲ ቅጥር ላይ ገብቶ እንደፈለገ እንዳያደርግ፣ ወይም ደግሞ በሃይማኖት እንዲሁም በዝምድና እና ሌላ ሰው በመሃል ገብቶ ተጽዕኖ እንዳይፈጥር የሚከላከል ድንበር ይበጅለታል ማለት::

ሰዎች የሲቪል ሰርቪስ ሠራተኛ ሆነው ከተቀጠሩ በኋላ የፓርቲ አባልም ሆኑ አልሆኑ ጉዳዩ እሱ አይደለም:: ምክንያቱም ነጻ እና ገለልተኛ ሲቪል ሰርቪስ መገንባት ማለት በዴሞክራሲ በምትመራ ሀገር ውስጥ ፓርቲዎች ለምርጫ ይወዳደራሉ፤ አንዱ ፓርቲ በሌላው በሚሸነፍበት ጊዜ ገዥው ፓርቲ ወይም በሌላ አባባል መንግሥት ሲሸነፍ የሚመጣው አዲስ አሸናፊ ፓርቲ ጋር ሲቪል ሰርቪሱ አብሮ መሄድ የሚችል መሆን አለበት ማለት ነው:: ይህ መሆን የሚችለው ነጻ እና ገለልተኛ ሲሆን ነው ማለት ነው::

ስለዚህም አሁን የሚገነባው ይህን የሚያረጋገጥ ሥርዓት ነው:: ሲቪል ሰርቪሱ የኢትዮጵያን ሕዝብ ያለምንም ልዩነት እንዲሁም ያለማንም ጣልቃ ገብነት እንዲሁም ያለማንም ተጽዕኖ ማገልገል መቻል አለበት:: በሌላ በኩል ደግሞ ከሃይማኖት፣ ብሔርና ፖለቲካ ተጽዕኖ ነጻ ሆነው ማገልገል መቻል አለባቸው:: እንዲህ ሲሆን ሲቪል ሰርቪሱን ብቁ፣ ነጻና ገለልተኛ ያደርጋል:: ነጻና ገለልተኛነት ሊኖር የሚችለው ደግሞ ግልጽኝነትና ተጠያቂነት ሲኖር ብቻ ነው::

አዲስ ዘመን፡- ረቂቅ አዋጁ ካሰፈራቸው ጉዳዮች መካከል፤ አንድ ኃላፊ አንድን ሰራተኛ እንደፈለገው ከአንዱ የስራ መደብ ወደሌላ የስራ መደብ ሊያዛውረው እንደሚችል ነው፤ ይህ ግን ሰራተኛው ላይ ጫና የሚፈጥር ነው ይባላል፤ ይህን እንዴት ይገልጹታል?

ነገሪ (ዶ/ር)፡– የሠራተኞች ስምሪትን በተመለከተ አንድ ሠራተኛ ብቁ ነው ተብሎ ከተመደበ በኋላ በስራ ላይ ያለም ይሁን አዲስ ሠራተኛ፤ በመጀመሪያ የመጣው ረቂቅ አዋጁ፤ አንድ ኃላፊ አንድ መደብ ላይ ያለውን ሠራተኛ ወደ ሌላ አዛውሮ ማሰራት ከፈለገ ይመድባል የሚል ነው:: ኃላፊው ከመደበው በኋላ ሠራተኛው የተመደበበትን መደብ ካልፈለገ ደግሞ በራሱ ፈቃድ ስራ እንደለቀቀቀ ይቆጠራል ይላል::

በእኛ በኩል ይህን ስናስተውል የታየን ነገር ቢኖር ይህ አካሔድ እድሉ ለኃላፊው ብቻ የሚሰጥ ከሆነ በኃላፊዎች ዘንድም ችግር ሊኖር ይችላልና ጉዳዩ ይበልጥ መጤን አለበት ወደሚለው መጣን:: ምክንያቱም አንዳንድ የስራ ኃላፊዎች ሠራተኛውን ለመጉዳትና ተጽዕኖ ለመፍጠር ሊጠቀሙበት ከፈለጉ ምቹ ሁኔታ እንዳይፈጠርላቸውና የሠራተኛው መብት እንዳይገደብ በሚል ቋሚ ኮሚቴው በዚህ ሃሳብ እንዳይቀጥል ያደረገው ነገር አለ::

ይኸውም ለምሳሌ በዚህ አዋጅ ውስጥ የስራ አመራር ጉባኤ የሚል አለ:: ወይም ደግሞ በአንዳንድ ተቋማት ውስጥ የተቋም ማኔጅመንት የሚባል አለ:: በመሆኑም ከአንዱ መደብ ወደሌላው መደብ አንድ ኃላፊ ብቻ እንደፈለገው የሚያነሳና የሚያስቀምጥ ሆኖ ረቂቁ ላይ እንደተቀመጠው ቢጸድቅ ኖሮ እንደተባለው ስጋት ነበረው:: ነገር ግን እኛ ይህን አሻሽለን ያደረግነው ነገር፤ አንድ የመንግሥት መስሪያ ቤት ኃላፊ አንድን ሠራተኛ ከአንድ መደብ ወደሌላ መደብ አዛውሮ ማሰራት የሚቻለው በስራ አመራር ጉባኤው ወይም ደግሞ በማኔጅመንቱ ከታመነበት ብቻ ነው:: ይህ ያሻሻለው ምንድን ነው ከተባለ የአንድ ሰው ስልጣን የነበረውን የቡድን እንዲሆን ማድረጉ ላይ ነው:: ስለዚህ ቡድኑ ሁሉ ደግሞ አንድን ሰው ለመጉዳት ይተባበራል ብለን አናምንም::

በሌላ በኩል ደግሞ ሠራተኛው ወደሌላ መደብ መዛወሩን ካልተቀበለ በራሱ ፈቃድ እንደለቀቀ ይቆጠራል የሚለው ላይ የተደረገው የሠራተኛውም ምክንያት መደመጥ ስላለበት ያለበቂ ምክንያት መሆን የለበትም በሚል አስተካክለናል:: ስለዚህ በሐሰትና በጫና ከአንድ መደብ ወደ መደብ አይዛወርም ማለት ነው:: ሠራተኛው ስራውንም ያለበቂ ነገር አይለቅም:: ምክንያቱም አሳማኝ ምክንያቱን ስለሚያስቀምጥ የሠራተኛውን መብት ያስጠብቅለታል:: እንዲህ አይነት ጥያቄ ያነሱ አካላት ያዩት ረቂቁን በመሆኑ ነው፤ የተሻሻለ ነገር መኖሩ ግንዛቤ ውስጥ መግባት አለበት::

ለምሳሌ ረቂቅ አዋጁ ላይ ከአንዱ ወደሌላው አዛውሮ ማሰራት ላይ አንዲት ነፍሰጡር ሴት ትሰራበት የነበረው የስራ መደብ በእርግዝናዋ ጊዜ ለጤናዋ ጥሩ ካልሆነ በእርሷ ፍላጎት ወደሌላ መደብ ማዛወር ይቻላል ይላሉ:: ይሁንና ወደስራዋ የምትመልስበትን አይጠቅስም:: እኛ ያደረግነው በጊዜያዊነት የሚል እንዲጨመር ነው:: ምክንያቱም ከወሊድ በኋላ ወደ መጀመሪያ መደቧ መመለስ ስላለባት ማለት ነው:: እዚያው ባለችበት ትሁን በሚል ያለአግባብ ጫና እንዳይፈጠር የተደረገ ማሻሻል ነው:: ስለሆነም በዚህ ላይ ምንም ስጋት አይኖርም::

አዲስ ዘመን፡- አዋጁ ግልጸኝነትንና ተጠያቂነት የሚመልሰው እንዴት ነው?

ነገሪ (ዶ/ር)፡– አዋጁ ግልጸኝነትንና ተጠያቂነትን የሚለስው አንድ የመንግሥት ሥራ ኃላፊ የፈለገውን ማድረግ አይችልም:: ምክንያቱም ስራዎች የሚሰሩት ግልጽ በሆነ መንገድ ነው:: ቴክኖሎጂ እንዲጠቀሙ ያበረታታል:: ይህ ደግሞ ለሁሉም ግልጽ እንዲሆን የሚያደርግ ነው:: በሌላ በኩል ደግሞ የተጠያቂነት ማሕቀፍም ተቀምጧል:: አንድ ኃላፊ ኃላፊነቱን ያለአግባብ በመጠቀም አንድ ሠራተኛ ላይ ጉዳት የሚያደርስ ከሆነ የሚጠየቅበት ሥርዓት ተቀምጧል:: ለሰራተኛውም በተመሳሳይ ተቀምጧል::

ከዚያም ባለፈ እንደተቋምም አንዳንድ ተቋማት መረብ ዘርግተው ጉዳት የሚያደርሱ ካሉ እና የሚወራባቸው ችግር ካለ ያንን ተቋም ቡድን በማደራጀት እንዲጠና እና የጥናቱ ውጤት እንዲቀርብ ይደረጋል:: በተለይም ችግር አለበት እየተባለ የሚነገርለት ተቋም ለተጠሪ ተቋሙ ይቀርባል:: ችግሩ ደግሞ የሚኒስቴር መስሪያ ቤት ከሆነ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲቀርብ ይደረጋል:: በዚህም መሰረት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ እንዲወስንበት ያደርጋል:: ስለዚህ የተጠያቂነት አሰራር ስላለ ምንም እንዳሻው በሩን ዘግቶ የፈለገውን ማድረግ አይችልም::

አዲስ ዘመን፡- ከአካታችነትና ብዝሃነት ጋር በተያያዘ በተለይ አንቀጽ 71 ላይ የሰፈረውን አስመልክተው አንዳንዶች ረቂቅ አዋጁ በአንድ በኩል ብቁ የሆነ ሠራተኛ የሚፈልግ ይመስላል፤ በሌላ በኩል ደግሞ የብሔር ተዋጽኦን ያካትታል:: ይህም ኮታ የሚመስል ነገር ስላለው ይጋጫል ይላሉና እዚህ ላይ ምን ይላሉ?

ነገሪ (ዶ/ር)፡- ትክክል ነው፤ እንዲህ አይነት ጥያቄ ተነስቷል:: ይህን ጥያቄ የሚያነሱ አካላት ከግንዛቤ እጥረት የጠየቁ ናቸው ባይ ነኝ:: አንደኛ በረቂቅ አዋጁ ውስጥ ኮታ የሚባል ነገር የለም:: አንዳንድ ጥያቄዎችን በማይበት ጊዜ በምክር ቤት አባላት ዘንድም ሲነሳ ነበርና የጥያቄዎቹ መነሻ ወይም ምንጫቸው የፖለቲካ ፍላጎትን የያዘ ነው እላለሁ::

አንዳንድ የተፎካካሪ ፓርቲ አባላትም ሊሆኑ ይችላሉ የሚያነሱት ጥያቄ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ነው:: አንድን የማኅበረሰብ ክፍል የወከሉ በመምሰል አዋጁ ያንን የማኅበረሰብ ክፍል ሊገፋ የወጣ ነው ብለው የደመደሙ ናቸው:: የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መድረክ ለሕዝብ ክፍት ስለሆነ ያቺን እድል ለመጠቀም በማሰብ የሚናገሩት ነው:: የፖለቲካ ትርፍ ነው ብለው የሚያስቡትን ለማግኘት የተደረገ ጥረት ነው እንጂ የተባለው የኮታ ጉዳይ አይደለም::

አዋጁ የወጣው በፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ውስጥ ያለውን አንድን ማኅብረሰብ ለመግፋትም ሆነ በሌላ የመተካት አይደለም:: ዓላማውን ግልጽ ለማድረግ ያህል ኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን ድረስ ከእኩልነት ጋር በተያያዘ ትልቅ ችግር እንደነበር ይታወቃል:: የመጣንበት ሥርዓት ራሱ አንዱን አቅፎ ሌላውን የሚገፋ በመሆኑ አካታች አልነበረም::

ይህ ደግሞ በመንግሥት ሥርዓት ውስጥ የገባ ነው:: ሥርዓቱ ቢቀየር እንኳ በአንዳንድ ሰው አዕምሮ ውስጥ ሥርዓቱ እስካሁን አልተቀየረም:: በዚያ ምክንያት ደግሞ አንዳንድ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ከማዕከላዊ መንግሥቱ ራሳቸውን አግልለውና ዳር አስቀምጠው ቆይተዋል::

በኢህአዴግ ጊዜ የተጠየቀው የእኩልነት ጥያቄ ነው:: ኢህአዴግም የራሱ ችግር ነበረው:: አንዱን አቅፎ ሌላውን ክልል የገፋበት ሁኔታ ነበር:: አሁን ከለውጡ ወዲህ ደግሞ በስም ደረጃ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያውያን ከጫፍ እስከ ጫፍ ሀገራቸውን መምራት ይችላሉ ብሎ ማንም የትም ቢወለድና የትኛውንም ቋንቋ ቢናገር እና የትኛውም ባህል ቢኖረው በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የሚያምንና በሰላማዊ መንገድ የሚታገል ሀገር መምራት ይችላል፤ መምረጥና መመረጥም ይችላል:: ይህንን ደግሞ በተግባር ማሳየት አለብን::

በተመሳሳይ ሁኔታ በፌዴራል መንግሥት ተቋማት ውስጥ ሚናቸው መታየት አለበት:: ኢትዮጵያን የሚመስል ሲቪል ሰርቪስ መገንባት አስፈላጊ ነው:: ስለዚህ በአዋጁ ክፍል ዘጠኝ አንቀጽ 71 ላይ ያለው ሁሉ አቀፍ ብዝሃነት፣ አካታችነት እና ተጨማሪ የድጋፍ እርምጃ አፈፃፀም ሲባል እዚህ ውስጥ ያለው ብሔር ብቻ አይደለም::

እንዲያውም አንቀጽ 71 ንዑስ አንቀጽ አንድ ላይ ኢትዮጵያን የሚመስል የመንግሥት ሠራተኞች ስብጥር መኖሩን በማረጋገጥ የብሔር ብሔረሰቦች፣ የአካል ጉዳተኞች፣ የፆታ ተዋጽኦ የመሳሰሉትን ብዙሃነት እና አካታችነትን ያገናዘበ የመንግሥት አገልግሎት እና አስተዳደር ሥርዓት ተግባራዊ መደረግ አለበት ይላል:: ታድያ ይህ አባባል የሚጎዳው ማንን ነው?

እንዲያውም ከዚህ ቀደም ከፌዴራል መንግሥት መስሪያ ቤት ውስጥ የማይታዩ በተለያየ የሀገሪቱ ጫፍ የሚገኙ ብሔሮች ያሉት ነገር ቢኖር፤ ‹ከዚህ በፊት መንግሥት የሚጠይቀን ልጆቻችንን ለጦርነት ሲፈልጋቸው ስጡን ወታደር ይሁኑልን በማለት ነበር:: እነርሱም ወይ ይሞታሉ፤ ወይም ደግሞ አካለ ስንኩል ሆነው ይመለሳሉ:: አሁን ግን የሀገር ባለቤት አድርጎ መንግሥት እኛን ቀርቦ እያወያየየን ነው::›› በማለት ሃሳባቸውን እየገለጹ ነው:: ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያ ሰላም የሚያመጣ ነው::

በሁሉም ጫፍ አካታችነትን ማረጋገጥ ማለት የተገለለ ማኅበረሰብ የለም ማለት ነው:: ይህን እኩልነት ማየት የማይፈልጉ ‹እኛ የተመረጥን ነን፤ እኛ ወርቅ ነን፤ በሚል ሌላውን ሕዝብ እንደ ሕዝብ ማየት የሚያስችል አመለካከት የሌላቸው አካላት ናቸው አሁን የተቸገሩት እንጂ ሁሉም ኢትዮጵያዊ መሳተፍ አለበት ማለት ክፋቱ ምኑ ላይ እንደሆነ አልታየኝም:: ብቃት ደግሞ ሲታሰብ ከብቃት ጋር አብሮ የሚወለድ ሰው አይኖርምና በሁሉም የዓለም ክፍል ያለ ሁሉም ብሔር ከብቃት ጋር አልተወለደም:: ነገር ግን ሰው ከተወለደ በኋላ እድል ከተሰጠው የመማር ብቃት አለው::

ስለዚህ ይህ አዋጅ አንቀጽ 74 ላይ በአግባቡ ተንትኖ ያስቀምጠዋል:: እንዲያም ሆኖ እድል መስጠት ማለት ብቃትና ውድድር አይኖሩም ማለት አይደለም:: ማነሳሳትና ማበረታታት ያስፈልጋል:: ምክንያቱም በኢትዮጵያ ውስጥ 17 የሚሆኑ ብሔር፣ ብሔረሰቦች በፌዴራል ተቋም ውስጥ አንድም ሠራተኛ የሌላቸው የሚል የጥናት ውጤት ቀርቧል:: እነዚህን አካላት በትምህርትና መሰል ተግባራት አካትተን ቢሆን ኖሮ አሁን ላይ የተገኘውን የጥናት ውጤት ባላየን ነበር:: ታድያ ጉዳዩ የኮታ ሆነ ያሉ አካላት በእነርሱ እይታ እነዚህ ብሔር ብሔረሰቦች ኢትዮጵያዊ አይደሉም ማለት ነው?

የፓርላማ አባል ምንም እንኳ ከአንድ ብሔር ተወክሎ በቦታው ቢገኝም የሚወክለው ኢትዮጵያውያንን እስከሆነ ድረስ ይህ ጉዳይ ሊሰማው ይገባል:: አንዳንዶች የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ መሰረት ተደርጎ የተረቀቀን አዋጅ ጭራሽ የሚያነሱት ጥያቄ ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የማይገናኝ መሆኑና በአሜሪካ ካሉ ታላላቅ እንደማይክሮሶፍት አይነት ኩባንያዎች ጋር እያነጻጸሩ ለማብራራት መሞከር ደግሞ የበለጠ ትዝብት ውስጥ የሚከትና ጉዳዩን ለማጣጣል እንደመሞከር የሚቆጠር ነው:: ከዚያም በላይ የራስን ቤት እንደማፍረስ የሚቆጠር ነገር አይኖርም:: በጥቅሉ ግን አሁን ያለንበት የዴሞክራሲ ሥርዓት ውስጥ እንደመሆኑ ሰው በተረዳው ልክ ሊናገር ይችላል፤ ትክክለኛውን ማስገንዘብ ደግሞ የሚጠበቅ ይሆናል::

አዲስ ዘመን፡- ረቂቅ አዋጁ ላይ የመንግሥት ሠራተኛ ማለት በፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤት በቋሚነት ተቀጥሮ የሚሠራ ሰው ነው ይላል፤ ሆኖም የማይጨምራቸው አሉ ብሎ ይዘረዝራል፤ ከዘረዘራቸው ውጪ ያሉ ሌሎች የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ጉዳይስ የሚታየው እንዴት ነው?

ነገሪ (ዶ/ር)፡- በልዩ ሁኔታ የማያካትታቸው አሉ:: በግልጽ ያስቀመጣቸው ደግሞ በዝርዝር አሉ:: ነገር ግን ከሲቪል ሰርቪሱ መተዳደሪያ ደንብ ውጪ ሠራተኞችን የሚያስተዳድሩ ተቋማት አሉ:: ወይም በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ወይም ደግሞ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ደንብ ማለት ነው:: በክልል ሆነ በከተማ አስተዳደር ደረጃ እንደዚህ አይነት ተቋማት አሉ:: አዋጁ እነዚህን በተመለከተ ያስቀመጠው ነገር አለ:: የመንግሥት ተቋማት ሆነው በልዩ ሁኔታ እንዲተዳደሩ የሚገባቸው አሉ::

ከዚህ በፊት እኔ ልዩ ነኝ በሚል መዋቅር ሰርተው ያጸድቁ ነበር፤ አሁን ግን ይህ አዋጅ የሚለው፤ ተቋማት ልዩ ባህሪ እንዳላቸው በጥናት ላይ የተመሰረተ ውሳኔ የሚሰጣቸው ማለትም ሠራተኛውን ለማስተዳደር ነጻነት የሚሰጣቸው አንድ ሀገራዊ ተቋም መኖር አለበት፤ ያ ሀገራዊ ተቋም ደግሞ በአዋጁ አንቀጽ 17 ላይ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቦርድ ሰብሳቢነት የሜሪት እና የደመወዝ ቦርድ ስለመቋቋም ይገልጻል፤ የዚህ ቦርድ ኃላፊነት ደግሞ በአንቀጽ 18 ላይ ተቀምጧል:: ቦርዱ በመጨረሻ ደግሞ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ሕግ ሆኖ እንዲወጣ አቅርቦ ያጸድቃል::

ስለዚህ እስካሁንም ሆነ ወደፊት በራሳቸው በመተዳደሪያ መቀጠል የሚፈልጉ ተቋማት ከሌላው በምን ምክንያት ተለዩ? ስራቸውስ በምን ምክንያት ነው የተለየው? በዚህ አዋጅ ውስጥ ከቆዩ የሚደርስባቸው ጉዳት ምንድን ነው? የሚለው ታይቶና ተጠንቶ ውሳኔ ይሰጣል:: ለምሳሌ ያህል የሚዲያ ተቋማትን ይህ አዋጅ የሚነካ አይደለም::

ምክንያቱም የሚዲያ ተቋማት በራሳቸው የሚተዳደሩና ገቢያቸውን ራሳቸው የሚያመነጩ በመሆናቸው ነው:: ነገር ግን የሚነካቸውም ቢሆኑ ቋሚ ኮሚቴ ይህን አይቶ የጨመረው አንቀጽ 18 ንዑስ አንቀጽ ዘጠኝ፣ አስር እና አስራ አንድ አዳዲስ የተጨመሩ አንቀጾች ናቸው:: በተለይ ንዑስ አንቀጽ አስር ላይ የሚለው ቦርዱ፣ የሰው ኃይል አስተዳደርን በሚመለከት ለሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የተሰጠው ኃላፊነት በውክልና ለተቋማት ሊሰጥ ይችላል የሚል ነው:: ምክንያቱም በአዋጁ ለሲቪል ሰርቪስ የተሰጠው ኃላፊነት አለ::

ከዚህ ኃላፊነቱን ወስዶ ለተቋማት ሊሰጥ ይችላል ማለት ከተጠና በኋላ ለሚገባቸው ተቋማት ለምሳሌ ለፌዴራል ፍርድ ቤቶች ሠራተኛ ከሲቪል ሰርቪስ ውጪ በምትፈልገው አስተዳደር ብሎ ይሰጣል ማለት ነው:: ስለዚህ እነሱ ደግሞ የነበረውን ደንብ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አምጥተው እንዲሻሻል በማድረግ አዋጁን በመጥቀስ በአዋጁና በተሰጠው ውክልና መሰረት ደንቡ ተዘጋጅቷል በማለት በዚያ ይቀጥላሉ ማለት ነው::

እንዲያም ሆኖ ውክልና እስኪሰጣቸው ድረስ መጠበቅ የማያስችል መስሪያ ቤቶች በመኖራቸው እነርሱ ልዩ በሆነ ጉዳይ የሚታዩ ይሆናሉ:: በሽግግር ድንጋጌ ውስጥ በልዩ ሁኔታ ይተዳደሩ የነበሩ አዲስ ሕግ እስኪወጣ ድረስ ይቀጥላሉ የሚል አንቀጽ 157 ላይ አለ:: ይህ የሚሆነው ከሀገር ጥቅም አንጻር እንጂ አንድን ኃላፊ ለማስደሰት ሌላውን ደግሞ ለማሳዘን ተብሎ አይደለም::

ይህን አዋጅ አንዳንድ አካላት ለሆነ ትርጉም ሰጥተው ለማዛባት እንደሚሞክሩት አይነት አይደለም:: ልዩ ባህሪ ያላቸውም ተቋማት ልዩ ባህሪ እንዳላቸው ታምኖበት የተሻለ የስራ አካባቢና ጥቅማጥቅም እንዲያገኙ ተደርገው ብቃት ኖሯቸው ለሀገር እንዲሰሩ ይደረጋል::

ቀደም ሲል የመንግሥት ሠራተኛ የደመወዝ ጭማሪ ሳይደረግለት ብዙ ጊዜ ይቆያል:: አበል ራሱ አንዴ ከተተከለ ለብዙ ጊዜ እንደሚቆይ የሚታወቅ ነው:: ይህ አዋጅ ግን ግልጽ አድርጎ ያስቀመጠው አንደኛ በየአራት ዓመቱ የደመወዝ ጭማሪ ዝቅተኛ የደመወዝ እርከን ብሎ ነው:: የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት በየሁለት ዓመቱ አበልንም ጥቅማጥቅምንም በተመለከተ እንደየኑሮ ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ የሚገባ ጥናት አካሒዶ አቅርቦ እንዲጸድቅ ይህ አዋጅ ያስገድዳል::

አዲስ ዘመን፡- በረቂቅ አዋጁ ላይ አንድ ሠራተኛ ተደጋጋሚ ፈተና ወስዶ ብቁ ካልሆነ የሁለት ዓመት ደመወዝ ወስዶ እንደሚሰናበት ያስቀምጣል፤ የሚወስደው ብር ግን ቢያንስ ከ12 ሺ በታች መሆን የለበትም ይላል፤ ይህ ማለት የአንድ ሠራተኛ ደመወዝ ስንት ቢሆን ነው?

ነገሪ (ዶ/ር)፡- እሱን ቀይረነዋል፤ ማለትም ተስተካክሏል:: ይህ ውሳኔ በሚወሰንበት ጊዜ ባለው ዝቅተኛ የደመወዝ እርከን ተሰልቶ ይሰጠዋል ወደሚል ተቀይሯል:: ሠራተኛው ጡረታ ደረጃ ላይ ከደረሰ ጡረታው ይጠበቅለታል:: ለምሳሌ በ2017 በጀት ዓመት የሚሰናበት ሠራተኛ በአሁኑ ሰዓት ዝቅተኛ ደመወዝ የሚባለው አራት ሺ 700 ብር አካባቢ ነው፤ እሱ ተባዝቶ የሚሰጥ ይሆናል የሚል ነው:: ነገር ግን በዚህ ሒደት ብዙ ይሰናበታል የሚል ሐሳብ የለንም፤ ምክንያቱ ስልጠናም ድጋፍ ይኖራል:: ከዚህ በላይ የሚሆን ከሆነ ግን የሚሰናበት ይሆናል::

አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ::

ነገሪ (ዶ/ር)፡– እኔም አመሰግናለሁ::

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You