እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ እርሳቸው በሚፈልጉት ንድፍ ያሰሩት ቪላ አልፋ የተሰኘው ቤታቸው ከስዕላቸው በተጨማሪ እጅግ የተጠበቡበት እንደሆነ ይነገራል፡፡ ቤቱ የኢትዮጵያዊ ቅርስ የሚመስል አሻራ እንዲያርፍበት ጽኑ ፍላጎት እንደነበራቸውም ይገለጻል፡፡
ህንጻውን ሲያስገነቡ በርካታ ዓመታትን የፈጀባቸው መሆኑ የሚነገርለት ይህ ቪላ አልፋ 22 የተለያዩ ክፍሎች እንዳሉት ይታወቃል። መኖሪያቸው ባለ አንድ ፎቅ ነው። የኢትዮጵያውያን የጥበብ አሻራ የሚንጸባረቅበት ይህ ግቢ ሀገራዊ ዕሴቶችን አቀናጅቶም ይዟል። እያንዳንዱ ነገር ቦታ ቦታውን ሲይዝ በደመነፍስ ሳይሆን በምክንያት ነው፡፡ ሁሉም ነገር ለእርሳቸው ትርጉም እንዳለው ነው የሚገለጸው፡፡
ለአብነት ያህል የግቢው ዋና መግቢያ በር
የሐረር ግምብ መግቢያ እና የፋሲል ግንብን አሰራር ጥበብ አዋህዶ የተሰራ ነው። ለዚህ ታላቅ የጥበብ ግቢ «አልፋ» የሚል ስያሜ የሰጡት በትምህርታቸው ጎበዝ ስለነበሩ መምህሮቻቸው «አልፋ ፕላስ» እያሉ ይጠሯቸው ስለነበረ ያንን በማስታወስ መሆኑን ነው የተናገሩት።
ደራሲና ጋዜጠኛ በዓሉ ግርማ በ1961 ዓ.ም በመነን መጽሔት «የቪላ አልፋ አዲሱ መልክ» በሚል ርዕስ አንድ ጽሁፍ ማቅረቡ ይታወሳል፤ በዛ ጽሁፉም እንደጠቀሰው፤ ሰዓሊው ቪላ አልፋን ለመገንባታቸው ዋና ምክንያታቸው የሠራኋቸው ሥዕሎች በተሠሩበት አካባቢ እንዲታዩ ለማድረግ ስለፈለጉ ነው፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊ ሠዓሊ እንዴት እንደሚኖር ለማሳየትና ከዚህም አልፎ ከሀገራችን የታሪክ ቅርስ ጋር ለማስተዋወቅም አስበው እንደሆነ ነው ጋዜጠኛና ደራሲ በዓሉ ግርማ በመጽሄቱ ላይ የገለጸው።
ቪላ አልፋ የተሰራው አንድ ሺህ ሜትር ካሬ ላይ ነው። የተገነባውም በአሥር ዓመት ፕላን መሠረት ሲሆን፣ ቤቱን ለመሥራት ከሚሸጧቸው ሥዕሎች ዋጋ አንድ ሦስተኛውን ለዚህ ፕላን ቆጥበው እንደነበር ይነገራል። ነገር ግን የቆጠቡት ገንዘብ ስላልበቃቸው ከአዲስ አበባ ባንክ ብድር መውሰዳቸው ተጠቅሷል። ቤቱን የሰሩት የአፄ ፋሲልን ግንብ አስመስለው ነው፡፡ ለዚህ ምክንያታቸው ደግሞ
ስለ አፄ ፋሲል ግንብ ያላቸውን አድናቆት ለመግለጽና ይህ የጥንት ቅርስ ተሻሽሎ ለዘመናይ ኑሮ ለመዋል መቻሉን ለማሳወቅ ነው።
ሦስቱ መስኮቶች ሦስት አይነት ቀለማት የተቀቡበት ምክንያት የፀሐይዋን ዕለታዊ ጉዞ ተከትለው እንዲያንጸባርቁ ለማድረግ ነው። የቤቱ ክፍሎች አሰያየስም የራሳቸው ምክንያት ያላቸው ሲሆን፣ ሃምሳ አራት ሥዕሎች ባንድ ጊዜ ለማሳየት እንዲቻል ታስቦ የተደረገ እንደሆነም ይነገራል፡፡ የጋራጁም ስፋትና ቀለም ያለ ምክንያት አለመደረጉ የሚነገር ሲሆን፣ ሁለት መኪናዎች እንዲይዝ ከመሆኑም በላይ የጋራጁ ቀለም ከመኪናዎቹ ቀለም ጋር ተዋህዶ ኅብረትን ለመፍጠር እንዲችል ታስቦ መሆኑ ነው የሚገለጸው፡፡
አዲስ ዘመን ሐምሌ 21/2012
አስቴር ኤልያስ