ባሳለፍነው ሳምንት በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ከሆኑት ከአቶ ታደሰ ከበበ ጋር ባደረግነው ቆይታ ሚኒስቴሩ በቀጣይ አስር ዓመት ውስጥ ምን ያህል ቤቶችን በመገንባት የቤት ፈላጊውን ችግር ለማቃለል እንዳቀደ ማስነበባችን ይታወቃል።በይደር ያቆየነው ጉዳይ ደግሞ ቤቶቹ የሚገነቡባቸው ቦታዎች፣ ማን እንደሚገነባቸውና የቤት ግንባታው ስለሚከተለው ቅይጥ የቤት ልማት መርሃግብር መሆኑም የሚታወስ ሲሆን፣ ይህንንም እንደሚከተለው አሰናድተን አቅርበነዋል፡፡
በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ ታደሰ ከበበ፣ ይገነባሉ ተብለው በእቅድ የተያዙ ቤቶች ግንባታ የሚካሄደው በመሃል ከተማ መሆኑን ያመለክታሉ።ግንባታቸውም በጣም ቦታ ቆጣቢ የሆነ አሰራርን እንደሚከተል ነው የሚያስረዱት።
እርሳቸው እንደሚሉት፤ የሚከተሉት ስልት ቅይጥ የሆነ መንገድን ነው፤ እንዲህም ሲባል ደሃውም ሀብታሙም እንዲሁም መካከለኛ ገቢ ያለውም ሁሉም የሚሆነው አንድ ላይ ነው። እንደ ከዚህ በፊቱ አንደኛው አካል ብቻ ከከተማ መሃል ተነቅሎ ዳር ላይ ተወስዶ ሌሎቹ ወደመሃል ከተማ አይመጡም።
እንደሚታወቀው፤ በአዲስ አበባ መሬት ብርቅ ነው።እሱን በአግባቡ ለመጠቀም እዛ ያለውን ነዋሪ መልሶ ማልማት ደግሞ ግዴታ ነው።መልሶ ልማቱ ነባር ነዋሪዎችን ቅድሚያ ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ ነው የሚሰራው። በቅዲሚያ የልማቱ ግንባታ ተጠቃሚ የሚሆኑት እነሱ ናቸው።
ሌላው ደግሞ ከተሞቹን ማስተዋል ቢቻል አንዳንድ ቦታ ላይ ባዶ ናቸው። ህንጻዎች ይገነባሉ፤ ከተገነቡ በኋላ ግን ነዋሪ የላቸውም። በተለይ መሃል ከተማ ላይ ከተስተዋለ ቤቶቹ ባዶ ናቸው።ሰው ወደውጭ አገር በመሄዱ መሃል ከተማዋ ባዶ ናት። ስለዚህ ቅይጥ የቤት ልማት መርሃግብር ነው የሚካሄደው። በተጨማሪም ደግሞ ቢዝነሱም ሆነ ኑሮው እዛው እንዲሆን ይፈለጋል። ከተቻለ በአንድ ህንጻ ላይ ካልተቻለ ደግሞ ህንጻዎቹ ጎን ለጎን ተሰርተው ቅይጥ መርሃግብርን እንከተላለን። ግለሰቦች ቤት ሲገነቡ የተወሰነ ቤቶችን ለመኖሪያ እንዲያደርጉም ድጋፍ እናደርጋለን ይላሉ፡፡
ኃላፊው፣ ቤቶቹ የሚገነቡት በመልሶ ማልማት ስልት እንደሆነ ነው የሚናገሩት። በተቻለ መጠን ህገ ወጥ ቤቶች እንዳይኖሩም መጠንቀቅ የግድ እንደሚል ተናግረዋል።
እርሳቸው እንደሚያስረዱት፤ ሌላው የትኩረት አቅጣጫ አድርገው የወሰዱት የፋይናንስና የመሬት ጉዳይ ሲሆን፣ እዚህ ላይ በትኩረት ይሰራል። እንዲህም ሲባል የፋይናንስ ምንጩ የተለያየና በርከት ያለ መሆን አለበት።ይህን 4 ነጥብ 4 ሚሊዮን ቤት ለመገንባት አንድ የፋይናንስ ተቋም ብቻ ሊወጣው አይችልም።ስለዚህ በተቻለ መጠን የመንግስትን ድጋፍ አድርጎ ሌሎች ባንኮች በፋይናንስ ሥርዓት ውስጥ መግባት አለባቸው።
የግል ባንኮችም በተቻለ አቅም እዛ ውስጥ መግባት ይጠበቅባቸዋል።ስለሆነም ለዚህ ጉዳይ በመንቀሳቀስ ላይ ያሉ የግል ባንኮች ውስጥ ለምሳሌ የጎህ ቤቶች ባንክ እየጀመረ ነው።ይህ ባንክ ቤቶች ላይ ብቻ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ባንክ ነው።በዚሁ ሌሎቹም ቤት ልማቱ ላይ በማተኮር ቢሰሩ ተመራጭ ነው።ሌላው ቀርቶ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትም በየገጠሩ ያሉ ትንንሽ ከተሞች ላይ መስራት የሚያስችላቸው በመሆኑ ስራው በቤት ልማቱ ላይ ከብሄራዊ ባንክ ጋር ብዙ ጥረት ማድረግን ይፈልጋል።
አቶ ታደሰ፣ ሌላው ጉዳይ ደግሞ ግንባታ የሚያጓትቱ ብዙ ነገሮች አሉ ይላሉ፤ ስለዚህም ይህን ችግር ለመፍታት የቴክኖሎጂ አጠቃቀማችንን ማዘመን አለብን።ለዚህ ሁሉ ዋና ራዕይንማስተካከል ነው።ራዕይ ካልተስታካከለ ቤቶችን መገንባት አይቻልም ይላሉ።
‹‹በአስር ዓመት ውስጥ የመጀመሪያ የሆነው ራዕያችንና በደንብ መታወቅ ያለበት ለሁሉም ዜጎች ተደራሽ የሆነ የመኖሪያ ቤት አቅርቦትን ማረጋገጥ ነው፤ እንዲህ ሲባል ዜጋው አንድም ከተማ አንድም ገጠር ነው የሚኖረውና እያንዳንዳቸው ትንንሽ ከተሞች በፕላን ተመርተው ቤቶችን መገንባት አለባቸው የሚል ስትራቴጂ አለ›› ብለዋል። ‹‹ስለዚህ በገጠርም በከተማም ደሃም ሀብታምም እያንዳንዱ ዜጋ መኖሪያ ቤት ማግኘትና ተደራሽ መሆን አለበት።ለዚህ ደግሞ ቅንጅታዊ አሰራር ተከትለን ለሁሉም ዜጎቻችን የመኖሪያ ቤቶችን ተደራሽ እናደርጋለን ማለት ነው›› ሲሉ ያብራራሉ።
እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ በእስር ዓመት እቅድ ውስጥ የከተሜነት ደረጃ ተብሎ የተቀመጠው 35 በመቶ አሃዝ መነሻ ያደረገው መካከለኛ ገቢ ያላቸው ተብለው የተቀመጡትን ከተሞች ነው። በከተሜነት ደረጃ 35 በመቶ እንደርሳለን ስንል የከተሜነት ደረጃችንን ከፍ ለማድረግ መካከለኛ ገቢ ወዳላቸው ከተሞች ደረጃ መጓዝ ይጠበቅብናል። በእርግጥ መካከለኛ ገቢ ሲባል በራሱ በአራት ደረጃ የሚከፈል መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል፡፡
‹‹የእኛ የአስር ዓመት እቅ ዳችን የተዘጋጀው መካከለኛ ከፍተኛ ለተባለው ደረጃ ነው። ይህ ማለት ከፍተኛ መካከለኛ ገቢ እንደማለት ነው። እንደ ሚታወሰው የመጀመሪያ የእድገ ትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዝቅተኛ መካከለኛ ገቢ ነበር የሚለው። አሁን ግን ከፍተኛ መካከለኛ ገቢ ለመግባት ነው እቅዱ የተሰራው። ስለዚህ በከተሜነት ደረጃ ላንደርስ እንችላለን። በገቢ ደረጃ ግን መካከለኛ ገቢ ወደላቸው ደረጃ እንገባለን ተብሎ ነው የታቀደው›› ይላሉ።
በቤቶቹ ግንባታ የመንግስት ሚና እየቀነሰ ይሄዳል በሚል አካሄድ በመሆኑ በግንባታው ከውስጥም ከውጪም የግል ባለሀብቶች በስፋት ሊሳተፉበት ይገባል።የሚሳተፉባቸው በርካታ መንገዶችም አሉ። በግሉ ዘርፍ ሲታይ በሪል ስቴት ደረጃ ማልማት ይችላሉ። ከአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጪ ጆይንት ቬንቸር ፈጥሮ በተለይ የውጭ አገር ኩባንያ ከአገር ውስጥ ኩባንያ ጋር በጋራ መስራት ይችላሉ፡፡
‹‹በሌላ በኩል ደግሞ ከመንግስት ጋር በመንግስትና የግል አጋርነት /ፒፒፒ/ በምናወጣው የግዥ ሂደት የግሉ ዘርፍ ከመንግስት ጋር መስራት ይችላል።ስለዚህ ጥናቶች የሚያሳዩት ለአብነት መጥቀስ ካስፈለገ የውጭ አገር ኩባንያ የሚሳተፈው ምን ቢያደርግ ነው የሚለውን በቅድመ እይታ በአዋጭነት ጥናት (ፊዚቢሊቲ ስተዲ) የተከናወኑ ነገሮች አሉ። በዚህም እያንዳንዱ ኩባንያ የሚመረጥበት መስፈርት አለው። መስፈርቱ ወደፊት በዝርዝር ይወጣል፡፡
በጥቅሉ ግን የተፈለገው ነገር እዚህ አገር ላይ በሁለት ዓላማ ነው።አንደኛ የግንባታ ቴክኖሎጂ የሚባለው ነው። የኢትዮጵያ የግንባታ ቴክኖሎጂና በውጭ በተግባር የሚታየው የግንባታ ቴክኖሎጂ ይለያያሉ። በመሆኑም የግሉ ዘርፍ ይህን ቴክኖሎጂ ይዞ ይመጣል የሚል ነው አንዱ ተስፋ ተደርጎ እየተሰራበት ያለው።ሁለተኛው የቤት ግንባታ ፋይናንስ ይዘው ይመጣሉ የሚለው ነው። በጥቅሉ ሲታይ የግንባታ ቴክኖሎጂና ፋይናንስ እንዲሁም እውቀት ይዘው ይመጣሉ ነው።
መንግስት ደግሞ በአገሩ ውስጥ በእጁ የያዘው ነገር ቢኖር አንዱ ፕሮጀክት ነው።ራሱ ፕሮጀክቱ መኖሩ እንደ አንድ ትልቅ መሳቢያ ነው።ሌላው በመንግስት እጅ ትልቁ ያለው ነገር ደግሞ መሬት ነው።ስለዚህ መንግስት ይህንን ይዞ ከቀረበ ግለሰቦች ደግሞ የተጠቀሱትን ነገሮች ይዘው ከቀረቡ ሁለቱን የሚያስማማቸው የውል ኮንትራት ይኖራል።በዛ የውል ኮንትራት መሰረት ቤቶቹ ይገነባሉ ማለት ነው።
ዋናው ነገር በህጋዊ መንገድ አብሮ መስራት የሚያስችለውን መንገድ መክፈት ነው።ከተከፈተ በኋላ ጥናቶች ይደረጋሉ።እያንዳንዱ ፕሮጀክት ላይ የአዋጭነት ጥናት ተካሂዶ ነው የሚገባበት።እኛ ስለፈልግን አሊያም የውጭ አገር ኩባንያ ስለወደደው ብቻ አይደለም የሚሰራው። የትኛው ነው ለኢትዮጵያ ዜጎች የሚያዋጣው? በምን ያህል ቤቶች ተገንብቶ ለዜጋው ሊተላለፍ ይችላል? ተብሎ ተሰርቶ ነው እንጂ ለዜጋው ካልጠቀመ ቢቀር ነው የሚመረጠው።ለዜጋው የሚተላለፈው በስንት ሂሳብ ነው? የሚለውም ታይቶ ነው።ስለዚህ በዋናነት አዋጭነቱ ተጠንቶ ነው ወደተግባር የሚገባው ማለት ነው እንጂ እንደሚባለው ፒፒፒ ዝም ብሎ የሚገባበት አይደለም።ጉዳዩ በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ አዲስ ነው።በተለይ ደግሞ በቤቶች ደረጃ ውስብስብና አዲስ የሆነ ነው።
የአገር ውስጥ ኩባንያ በዚህ ደረጃ ራሱን አብቅቶ ቢቀርብ ተመራጩ እንደ አገር እሱ ነው የሚሉት ኃላፊው፣ ወደውጭ እንድናማትር የሚያደርገንና የሚያሰገድደን ጉዳይ ግን እየተስተዋለ ነው ሲሉ ይናገራሉ።ቤት ግንባታ ከተጀመረ በ15 ዓመታት ውስጥ በአዲስ አበባ ከ300 ሺህ ቤት በላይ አለመገንባቱንም ያስታውሳሉ።ይህ እንግዲህ በአገር ውስጥ ባለሀብት የተሰራ ነው።ሌሎች አገሮች ግን የሚገነቡት በሚሊዮን የሚቆጠር ቤት ነው።ለአብነት ያህል በብራዚል በሁለት ዓመት ውስጥ ከሁለት ሚሊዮን ቤቶች በላይ ተገንብተዋል።ኮሪያውያን ደግሞ በአስር ዓመት ውስጥ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ቤት ነው የሚገነቡት፡፡
በአፍሪካ ደረጃ ግን እምብዛም ሲሆን፣ እንዲያውም አንዳንዶቹ ተሞክሮ እያሉ መጥተው ልምድ የሚወስዱት ከኢትዮጵያ ነው። ለምሳሌ እነሩዋንዳ፣ ኬንያ ተሞክሮ የወሰዱት ከኢትዮጵያ ነው። ግን በአፍሪካ ደረጃ በቤት ልማት መርሃግብር የዚያን ያህል ርቀው ሄደዋል ተብው የሚጠቀሱ አገሮች የሉም ማለት ያስደፍራል።
ስለዚህ የእኛ አገር ኮንትራክተሮች ወይም ቤት መገንባት በደንብ መጠናከር አለባቸው። ለ4 ነጥብ 4 ሚሊዮኑ ቤት ግንባታ ተሳትፏቸው ከፍተኛ ስለሆነ ራሳቸውን ከወዲሁ ዝግጁ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አስታውቀዋል። በአምስት ዓመት ውስጥ እንኳ ለመገንባት የታሰበው ቤት 2 ነጥብ 17 ሚሊዮን ቤት እንደሆነም ነው የገለጹት፡፡
አዲስ ዘመን ሐምሌ 21/2012
አስቴር ኤልያስ