ብዙዎች ዛሬም ንጹሕ ውሃ ፍለጋ ረጅም ርቀት ይጓዛሉ፡፡ በገጠራማው የአገሪቱ ክፍል ያሉ ጥቂት የማይባሉ እናቶች ውሃ ፍለጋ ማለደው በመውጣት ከአውሬ ጋር ተጋፍተው እንደሚቀዱም ይነገራል፡፡ በከተማም ቢሆን ውሃ ፍለጋ አሊያም ጥበቃ ብቻ ጊዜያቸውን የሚያባክኑ ነዋሪዎች ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡ በእርግጥ ይህ ችግር ለመፈጠሩ አገሪቱ አንገብጋቢ የሆነ የውሃ እጥረት ኖሮባት ሳይሆን፣ በዘርፉ ያሉ አካላት የቁርኝነት ጉዳይ ነው፡፡ ለሚያጋጥመው የውሃ ችግር እና ለቁርጠኝነቱ ማነስ መፍትሔው ምን ይሆን ስንል በውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ስር ከተቋቋመ አንድ ዓመት ከስድስት ወር የሆነው የውሃ ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ከሆኑት ዶክተር በሻህ ሞገሴ ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አሰናድተነዋል፡፡ መልካም ንባብ ይሁንልዎ፡፡
አዲስ ዘመን፡– የውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ካቋቋማቸው የተለያዩ ኮሚሽኖች መካከል የውሃ ልማት ኮሚሽን አንዱ ነው። በኮሚሽን ደረጃ መቋቋሙ ለምን አስፈለገ?
ዶክተር በሻህ፡– ኮሚሽኑ የተቋቋመው የመስኖ ልማት ኮሚሽንና ተፋሰስ ባለስልጣን በተቋቋሙበት ወቅት በ2011 ዓ.ም ነው። የተቋቋመበትም ዋና ዓላማ ሴክተሩ ብዙ ሥራዎች ያሉበት እንደመሆኑ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አገሪቷ ውስጥ ቅሬታ የሚበዛባቸው ተቋማት እንደ መብራት፣ ውሃ፣መስኖ ዓይነቶች አካቶ የያዘ በመሆኑ ያሉትን ሥራዎች ለመከፋፈል እንዲያመች ነው። ተከፋፍለው በሚገባ ካልተያዙ የህዝቡን ጥያቄ መመለስ በጣም አስቸጋሪ ይሆናል።
በተለይ ወደውሃ ኮሚሽን ስመጣ በመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ሥራዎች ላይ ነው ትኩረት አድርጎ የሚሠራው። ወደ ሳኒቴሽን ስንመጣ ከፍሳሽ ማስወገድ ጋር የተያያዙ ሥራዎች ናቸው ያሉትና ከዚህ አንጻር ያለው ሥራ በጣም ደካማ ምናልባትም በአገርም ደረጃ ብናየው በአዲስ አበባና በጣም ውስን በሆኑ ሁለተኛ ደረጃ ከተሞች ውስጥ ትናንሽ ሥራዎች የተሠሩበት ነው። ስለዚህም በሰፊው መሥራት እንዳለበት ይታመናልና እሱ ደግሞ ባለቤት እንዲኖረው ማድረግ ያስፈልገዋል።
ወደ መጠጥ ውሃ ስንመጣ በአገሪቷ ያለው የውሃ ችግርን ተከትሎ የሚነሳው ጥያቄና የመንግሥት የመመለስ አቅም አደረጃጀት በዚያ ልክ አይደለም፤ ስለሆነም ራሱን የቻለ፤ ለዚህ ብቻ ተጠሪ የሆነ ተቋም ስላስፈለገ ኮሚሽኑ እንዲቋቋም ተደርጓል። ቢያንስ 50 ሚሊዮን የሚሆነው ህዝብ በአግባቡ ውሃ ማግኘት በማይችልበት ደረጃ ላይ ነው ያለው። ይህን ጥያቄ ለመመለስ ያስችል ዘንድ ኮሚሽኑ መቋቋሙ ተገቢ ሆኗል።
አዲስ ዘመን፡– ኮሚሽኑ በቀጣይ በዋናነት አከናውናቸዋለሁ ያላቸው ተግባሮች ምንድን ናቸው? የሀገሪቱ የንጹሕ መጠጥ ውሃ ሽፋንስ ስንት ደርሷል? በቀጣይስ ስንት ለማድረስ ይሠራል?
ዶክተር በሻህ፡– ኮሚሽኑ ሥራው በሁለት የተከፈለ ነው፤ ማለትም የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ነው። ሁለቱ አንድ ላይ የተያያዙበትም የራሱ የሆነ ምክንያት ስላለው ነው። ይኸውም ከምናቀርበው ውሃ 80 በመቶ የሚሆነው ቆሻሻ ውሃ ሆኖ ተመልሶ ከቤት የሚወጣ በመሆኑ ነው። ስለዚህም ውሃን ብቻ አቅርበን ፍሳሽ ቆሻሻን ጥለን ብንሄድ ማህበረሰቡ አካባቢውን እንዲበክል ነው የምናደርገውና ያንን የማስወገድ ሥራም በተያያዥነት መሠራት ስላለበት ነው።
ከመጠጥ ውሃ ጋር በተያያዘ እንደአገራችን እስከአሁን ሪፖርት የምናደርገው የመጠጥ ውሃ ሽፋን 75 በመቶ ደርሷል ብለን ነው። ይህንን ሪፖርት ስናደርግ ግን ለምሳሌ በ2011 ዓ.ም 70 በመቶ ከነበረና በ2012 ዓ.ም ደግሞ 3 በመቶ ከሠራን ባለው ላይ እየደመርን የምንሄድ ነው የሚሆነው። ይህ ዓይነቱ የሪፖርት አቀራረባችን የምንሠራቸውን ተቋማት እንጂ ተበላሽተው ከአገልግሎት የሚወጡትን አይቆጥራቸውም። ተጠቃሚ የነበሩ ሰዎች ተጠቃሚ እንደሆኑ በማሰብ ነው የሚሠራው። ባለው ነባራዊ ሁኔታ ግን አንድ ተቋም ዕድሜ አለው፤ 15 ዓመትም ሆነ 20 ዓመት ካገለገለ በኋላ ወይ በሙሉ አቅሙ ማገልገል አይችልም አሊያም ደግሞ ይበላሽና አገልግሎት መስጠት ያቆማል። ስለዚህ አቆጣጠራችን አዲስ ተቋም እያመጣንና የሚበላሹትንም እየቀነስን ቢሆን የተቀመጠው አኀዝ ትክክል ይመጣ ነበር።
ሪፖርታችን ያንን ስለማያካትት በሚኒስቴራችን በ2011 ዓ.ም ቆጠራ እንዲደረግ ተብሎ ወደ 3 ሺህ 924 የሚሆኑ ታብሌቶች ተገዝተው ከዚሁ ቁጥር የማይተናነስ ቆጣሪዎች ተቀጥረው በሳይት እየሄዱ ምዝገባ አካሂደዋል። በዚያ ቆጠራም 155 ሺህ የሚሆኑ ተቋማት በኢትዮጵያ ውስጥ እንዳሉ መድረስ ተችሏል።
እነዚህም ያላቸውን አቅም ለማወቅ ጥረት ተደርጎ የብልሽትና መሰል ችግሮች ያሉባቸውን የመለየት ሥራ ተሠርቷል። ቀጥሎም ከክልሎች ጋር ግንኙነት መፍጠር ተጀምሮ ክልሎች ደግሞ የመጣውን ውጤት ዓይተው ከተቀበሉ በኋላ ነው ለህዝቡ ማቅረብ ያለብን ብለን እየሠራን ነው። ይህን ሂደት ካጠናቀቅን በኋላ ዎርክሾፕ ለማሰናዳት ስንዘጋጅ ከኮቪድ 19 ጋር በተያያዘ መገናኘት አልቻልንም። በመጨረሻ ያደረግነው ግን ከራሳቸው ከክልሎች ጋር ሆነን በየክልሉ ያለው ሽፋን በጥናቱ የተገኘው ምን እንደሚመስል ተናግረን ቅሬታ ካላቸው ደግሞ ቅሬታ የተፈጠረበትን ቦታ እንዲያስረዱን ተደርጓል።ስለዚህም ሽፋኑን በተመለከተ ከወረዳ እስከ ክልል ያለው ሁሉ በጥናት ነው የተሠራው፤ በየክልሉ ያለው ሽፋን ምን እንደሚመስል አሳይተን ችግር አለ የተባለበት ቦታ ላይ ደግሞ እንዲያመጡ ባልናቸው መሰረት አምጥተዋልና እያስረዳን መልሰናል። በ2011 ዓ.ም ቆጠራው በተካሄደበት ጊዜ ውጤቱም የሚያሳየው የገጠሩ 47 በመቶ ሲሆን፣ የከተማው ደግሞ ወደ 56 በመቶ አካባቢ ነው። ይህ መረጃ ሲጠናቀቅ የምንገልጸው ስለሆነ ቁጥሩ መነሻ መሆኑን ነው የማስቀምጠው።
የ2011 እና የ2012 ዓ.ም ደግሞ እዚሁ ላይ ተጨምሮበት አሁን በ2012 ዓ.ም መጨረሻ ላይ የት ነን የሚለውን በአጭር ጊዜ ውስጥ ከየክልሎቹ መልስ መጥቶ ካጠናቀርን በኋላ እናሳውቃለን። ምንም እንኳ መረጃው ተጠናቅቆ ባለመወጣቱ ይፋ ባናደርገውም ከ53 በመቶ በላይ የሆነ ሽፋን አለን ብለን አናምንም። ስናቅድም በእዚህ መሰረት ላይ ተቀምጠን ነው የምናቅደው ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡– በቀጣዮቹ አስር ዓመታትስ ሽፋኑን የት ለማድረስ ታስቧል?
ዶክተር በሻህ፡– እንደተቋም ዘርፉን ሙሉ ለማድረግ ነው የምናቅደው። የአስር ዓመት ስትራቴጂክ ፕላን አዘጋጅተን የፕላን ኮሚሽን ባዘጋጀው መድረክ ላይ መነሻ ረቂቁ ላይ ተወያይተናል። የዛሬ አስር ዓመት የመጠጥ ውሃ ሽፋንን መቶ በመቶ ለማድረስ ነው ያቀድነው።
መቶ በመቶ ማድረስ ይቻላል ወይ ቢባል? በእርግጥ አስቸጋሪ ነው። ውሃ በቀረበ ቁጥር የሰው ፍላጎት በዚያ ልክ ከፍ እያለ ይሄዳል። ይህ ኮሚሽን መቶ በመቶ አድርሻለሁና ግቤን አሳክቻለሁ ብሎ መቀመጥ አይችልም። ምክንያቱም ተጨማሪ የህዝብ ቁጥርና ፍላጎት ተያይዞ ይመጣል።
ለምሳሌ ከአስር ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ውሃ የምትቀዳ እናት ባለችበት ቤተሰብ ያለው የውሃ አጠቃቀምና ከቦኖ አሊያም በግቢ ውስጥ ወይም ደግሞ ቤት ውስጥ ተገጥሞ ያለ ውሃ አጠቃቀም በእጅጉ የተለያየ ነው። አገልግሎቱ እየቀረበ በሄደ ቁጥር ፍላጎቱም እየጨመረ ከመሄዱም ባሻገር የምናባክነውም ውሃ እየበዛ ይሄዳል። የውሃው ዘርፍ የቱንም ያህል ቢሠራ የሚመሰገን አይደለም። ምክንያቱም የሰው ፍላጎት ሁሌም ቢሆን በየጊዜው እየጨመረ ይሄዳል።
ለአብነት ያህል ያደጉ አገራትን እንደአሜሪካ ዓይነት የውሃ ፍጆታቸውን ብናይ በቀን በአንድ ሰው እስከ 400 ሊትር ውሃ ይጠቀማል። ውሃ በአግባቡ ነው የሚጠቀሙት የምንላቸው አውሮፓ አገሮች ደግሞ እስከ 170 ሊትር ውሃ በቀን ይጠቀማሉ። ወደእኛ አገር ደግሞ ስንመጣ ገጠርና ከተማ ብለን ስንመለከት በመጀመሪያ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ላይ ገጠር በቀን 15 ሊትር ሲሆን፣ ከተማ ደግሞ 40 ሊትር ነበር። ከተማ ሲባል አዲስ አበባም ሆነ ትንሽ ከተማም አብሮ የያዘ ነበር።
ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ላይ ተሻሽሎ ገጠር ወደ 25፣ ከተማ ደግሞ ከ40 እስከ 100 ሊትር ውሃ በቀን ተብሎ ተቀመጠ። ይህ ማለት ከደረጃ አንድ እስከ አምስት ማለት ነው። ስለዚህ ለአዲስ አበባ ደረጃ አንድ ሲሆን፣ 100 ሊትር፣ አነስተኛ ለሆነው ደረጃ አምስት ወደ 20 ሺህ ያህል ህዝብ ያላት ከተማ ደግሞ 40 ሊትር በሚል ተያዘ።
አዲስ ዘመን፡– ሀገራችን ለንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ትልቅ አቅም ናቸው ብላ የምትሰራባቸው አማራጮች ምንድን ናቸው?
ዶክተር በሻህ፡– ትልቅ አቅም ስንል አቅም የሚለካው በውሃም ሀብት አሊያም በገንዘብ አቅም ሊሆን ይችላል። በኢትዮጵያ በአብዛኛው ከአዲስአበባና ከተወሰኑ አካባቢዎች ውጪ የምንጠቀመው የከርሰምድር ውሃ ነው። አዲስ አበባ ያሉ እነ ለገዳዲ፣ ገፈርሳና በቅርቡም እየታሰበ ያለው ሲቢሉ የሚባል ግድብ አለ።እነዚህ በገጸምድር ያሉ ናቸው። ለመጠጥነት እንዲውል የሚያስወጡት ዋጋ ግን ከፍ ያለ ነው።
ከከርሰ ምድር ሲሆን፣ የኬሚካል ንኪኪ ሊኖረው ይችላል ተብሎ ይታሰባል። ወይም ደግሞ ፍሎራይድ አሊያም ብረት ሊኖረው ይችላል። ከዚያ ውጪ ገዳይ የሆኑ ጥቃቅን ህዋሳት የመገኘት ዕድሉ ጠባብ ስለሆነ ብዙ ድካም አይጠይቅም። ትንሽ ክሎሪን ይጨመርበትና በዚያ መልካም ይሆናል።
የከርሰ ምድር ውሃን በአማራጭ አገልግሎት ላይ እንዲውሉ የተደረገባቸው ቦታዎች ድሬዳዋ፣ ሐረር፣ ጎንደር፣ ሐዋሳ፣ መቀሌና አብዛኛው የኢትዮጵያ ትልልቅ ከተሞችም ሆነ መንደሮች ብንሄድ ከምንጭ ባለፈ ወደከርሰ ምድር ውሃ ነው የምንሄደው። ዋጋውም የዚያን ያህል ይቀንሳል።
አዲስ ዘመን፡– አዲስ አበባ ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች የንጹሕ መጠጥ ውሃ ችግር በከፍተኛ ደረጃ ይስተዋላል። ውሃ በፈረቃ ነው የሚዳረሰው፤ አንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ ለሳምንታት ውሃ አያገኙም።ይህ ችግር ከምን የመነጨ ነው ይላሉ፤ መቼስ ይፈታል ተብሎ ይታሰባል?
ዶክተር በሻህ፡– የውሃ መቆራረጥ ጉዳይ በተለይ ከተሞች ላይ ድብብቆሽ አስፈላጊ ባለመሆኑ እውነቱን ለመናገር በመጠጥ ውሃ ዙሪያ አንድ የምንከተለው ቅድም ተከተል አለ፤ እሱም የሕዝብ ብዛት ነው። ወደውሃ አቅርቦት ለመሄድ ስንነሳ የመጀመሪያው ጥያቄ የሚሆነው ስንት ሰው ይኖራል የሚለው ነው። ያንን የሰው ብዛት እንዴት ነው የምንገምተው የሚለው ዛሬ ላይ ትልቁ ፈተናችን ነው።
በአሁኑ ሰዓት የአዲስ አበባ ህዝብ ስንት ነው ወደሚለው ቢመጣ በትክክል የሚታወቀውና የሚሰጠን መረጃ በፍጹም የተለያየ ነው። ይህ ምናልባት የስታትስቲክ ኤጀንሲ የሚከተለው የራሱ አሠራር ሊኖረው ይችላል። ይህ ግን በውሃ ሲመጣ የሚሰጠው የህዝብ ቁጥር መሬት ካለው ጋር ስለማይመጣጠን አስር ሰው የሚኖርበት ቤተሰብ ውስጥ ያሉት አስር ሳይሆኑ ስድስት ናቸው የሚባል ከሆነ የማቀርበው ውሃ ለስድስት ሰው ብቻ የሚሆነውን ነው። በዚህ ዓይነት አራቱ ሰዎች ውሃ የላቸውም ማለት ነው። ያሉት ቤተሰቦች የመጣላቸውን ውሃ ሲሻሙ የውሃ እጥረቱ ይከሰታል።በየከተሞቹ ዲዛይን ሲሠራ ከፌዴራል በተመደበ በጀት ነው። ትክክለኛ መረጃችን ነው ብለን የምንወስደው ኤጀንሲውን ነው።
ኤጀንሲው ዘንድ ያለው መረጃ ደግሞ አስቀድሜ እንደጠቀስኩልሽ ነው። አብዛኛውን የአገራችንን ህዝብ ባህሪ ብናይ ትንሽ ከተማ በአካባቢው ካለ በዙሪያው ያሉ ቀበሌዎች ወደዛች ከተማ ይፈልሳሉ። ኤጀንሲው በአንድ ወቅት የዚያን ከተማ ህዝብ ብቻ ቆጥሮ ሊሆን ይችላል። ከተለያየ ቀበሌ በመምጣት የሚደመረው የሰው ብዛት ግን የከተማው አካል ተደርጎ ስለማይቆጠር አስቸጋሪ ነው የሚሆነው።
ሌላው ፈተና ነው ብዬ የምጠቅሰው የውሃ አጠቃቀማችንን ነው። አንድ በግሌም የሚያሳስበኝና ከቤተሰቤ ጋርም የምጣላበት ነገር የውሃ አጠቃቀማችን አግባብነት የሌለው መሆኑ ነው። ውሃ ሲፈስ ሳይ የማስበው ውሃው እንዴትና ምን ዓይነት ዋጋ ተከፍሎበት እንደመጣ ነው። ይህ የሚሆንበት ምክንያት ደግሞ በራችን ምናልባትም ቤታችን ድረስ ለሚመጣ ውሃ የምንከፍለው ገንዘብ የሚቆነጥጥ ባለመሆኑ ይመስለኛል። እኔ ቤት ያለአግባብ የሚፈሰው ውሃ ጎረቤቴ ውሃ እንዳያገኝ ማድረጉን ብዙዎቻችን ልብ አንለውም።
አንድ ውሃ ለገዳዲ ተመርቶ ቤታችን እስከሚመጣ ድረስ ስንት ብር እንደወጣበት ለማሰብ ብዙዎቻችን ፈቃደኞች አይደለንም። ብቻ ጠዋት ስንነሳ ቧንቧችንን ከፍተን ለምንፈልገው አገልግሎት ከማዋል ውጪ ማን እንዳመረተው፤ በስንት እንደተመረተና እንዴት ወዳለንበት እንደመጣ አስበን አናውቅም። ቧንቧችንን ስንከፍተው ውሃ ከሌለ ብቻ ነው ተቋሙ ትዝ የሚለንና የምንወቅሰው። መንግሥት ሁሌም ይለፋል፤ ነገር ግን ከትችትና ወቀሳ ተርፎ አያውቅም። ስለዚህ ተጠቃሚውም ኃላፊነት እንዳለበት ልብ ሊባል ይገባል ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡– መንግሥት አንዳንድ ተቋማት የራሳቸውን የውሃ አማራጭ እንዲከተሉ በማድረግ ጥልቅ ውሃ ጉደጓድ እያስቆፈሩ ፍላጎታቸውን እየሸፈኑ ይገኛሉ። ይህ ምን ያህል የመንግሥትን ጫና ይቀንሰዋል ተብሎ ይታመናል?
ዶክተር በሻህ፡– ሆቴሎች፣ ግለሰቦች የየራሳቸው የውሃ አቅርቦት እንዲኖራቸው ይፈለጋል፤ በእርግጥ ያላቸውም አሉ። ነገር ግን የፈቃድ አሰጣጡ ምን ይመስላል የሚለውን ለማወቅ ሙሉ መረጃው የለኝም።
ነገር ግን ገጠር አካባቢ ለራስ አቅርቦት (ሰልፍ ሰፕላይ) በሚል የየራሳቸው ውሃ እንዲኖራቸው ይበረታታሉ። ካልሆነ ግን ለሁሉም ማድረሱ አስቸጋሪ ነው። ይሁንና ቁፋሮው ሲካሄድ የውሃ ሀብት አስተዳደር የራሱ ሂደት ይኖሩታል። ማን መቆፈር እንደሚችልም ፈቃድ ማግኘት የግድ ነው።
ምክንያቱም ማንም ዝም ብሎ የሚቆፍር ከሆነ ከጉድጓድ ውሃ ጋር የተያያዘ ቁፋሮ ስናካሂድ ተጽዕኖ ሊፈጥሩ የሚችሉ አካባቢዎች አሉ። አንዱ ግቢ የሚቆፈረው ውሃ በሌላ ቦታ የተቆፈረውን ውሃ አሟጦ ሊወስድ ይችላል። ዝም ብሎ ለመቆፈር መነሳት ጎረቤት ካለው ጉድጓድ ጋር አንድ ሊሆን ይችላልና መሻማት ነው የሚሆነው። ከዚህም በተጨማሪ ሕንፃዎች ላይ የመሰንጠቅ ተጽዕኖ ሊፈጥር ይችላል። ስለዚህ ቁፋሮው በእውቀትና በፈቃድም ላይ የተመሰረተ መሆን ይጠበቅበታል። እንደዚያም ሆኖ ቢሠራ ግን የመንግሥትን ጫናን ያቀላል።
የውሃ አማራጮች ከሚባሉት ውስጥ አንዱ የዝናብ ውሃ ነው። ነገር ግን የዝናብ ውሃ አማራጭነቱ የት ላይ ነው የሚለው በራሱ ጥያቄ ነው። ለምሳሌ አዲስ አበቤን የዝናብ ውሃን ያዝና ጠጣ ቢባል እምብዛም አያስኬድም፤ነገር ግን ለእጥበትና መሰል ነገር በመጠቀም የመጠጥ ውሃ እጥረት እንዳያጋጥመው እንደአማራጭ ሊወሰድ የሚችል ነው። አንዳንድ ቦታ ደግሞ የዝናብ ውሃ ከጣሪያቸው ላይ ወደመሬት ጠብ እንዳትል የሚያዝበት ቦታ አለ። ስለዚህ እንደየሁኔታው ሊሠራበት ይችላል።
አዲስ ዘመን፡– በውሃ ነክ ሥራዎች በተቋራጭነት የሚሠሩት የኢትዮጵያ ኩባንያዎች መሆናቸው ይታወቃል። እነዚህ ኩባንያዎች ባለፉት ዓመታት ከውጭ ምንዛሬ አለመኖር ጋር በተያያዘ ክፉኛ መጎዳታቸውን ይገልጻሉ። ብድር ባለመግኘትም ሲቸገሩ መቆየታቸው ይነገራል። ከዘርፉ ለመውጣት የተገደዱም እንዳሉ ይገለጻል። ይህ ደግሞ የንጹሕ መጠጥ ውሃ አቅርቦታችሁ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳድራልና እንዴት ይመለከቱታል?
ዶክተር በሻህ፡– ከግል ዘርፉ ጋር የምናስበው አለ። የውሃ ልማት ኮሚሽን ከተቋቋመ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ለረጅም ጊዜ ከግሉ ዘርፍ ጋር በመግባባትና በመቀራረብ ሥራ ለመሥራት ብዙ ጥረቶች ይደረጋሉ። የግል ዘርፉ፣ አቅራቢዎቹም ሆነ አማካሪዎቹ መጥተው የማይረዱን ከሆነ ውጤታማ መሆን አያስችልም። በመንግሥት በኩል ግን በቅርቡ ራሱ ችግራችሁ ምንድን ነው በሚል ዎርክሾፖች ሊካሄዱ ነበር። በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ግን ያንን ማድረግ አልቻልንም።
የግሉ ዘርፍ አቅሙ ካልተገነባ በምንጠብቀው ልክ ጥራት ያለው ሥራ ሠርቶ ሊሰጠን አይችልም። ስለዚህ እኛ ያንን ገምግመን እጅና ጓንት ነው መሆን ያለብን። የተለያየ አካልም ብንሆን የምንሠራው ለአንድ አካል ነው። አንድ ኮንትራክተር ወይም አማካሪ በተለይ አገር በቀል የሆነ ተቋም እንደ አንድ የልማት አጋር ነው የምናየው። እነሱ ካልሠሩና ለህዝቡ ካልተቆረቆሩ ማህበረሰቡ ውሃ ማግኘት አይችልም።
አንድ አገር በቀል የሆነ በውሃው ዘርፍ የሚሠራ ተቋራጭና አማካሪ ተቋም ሁለት ዓላማ አለው ብዬ አስባለሁ። በዚህ ጉዳይም ከእነሱ ጋር ተነጋግረናል። አንደኛ አትራፊ ሲሆን፣ሁለተኛ ደግሞ በሠራው ሥራ የሚያገኘው እርካታ ነው።
እነርሱም እንደ ፈተና ያነሱት ነገር የውጭ ምንዛሬ ጉዳይ ነው፤ ቅድሚያ ይሰጠን ነው የሚሉን። ይህ ደግሞ እውነት ነው። ይህን ጉዳይ እኛ እንደ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ከግምት ውስጥ አስገብተናል። በውጭ ምንዛሬ በኩልም ክፍተት አለባቸው።
ለዘርፉ ጠቃሚ የሆኑ ማሽነሪዎችን ሲያስገቡ ከታክስ ነፃ የሚሆኑበት አሊያም ብድር እንዲያገኙ የሚባሉ ጉዳዮች አሉ፤ እንደተቋም ግን ይህንን ለማከናወን ከሌላ ሦስተኛ ወገን ጋር መነጋገርን ይጠይቃል። ለአብነት ያህል ከባንኮች ጋር መነጋገርን ይጠይቃልና ይህን እንደየቤት ሥራ የምንወስደው ጉዳይ ነው። በዚህ ጉዳይ ባለፈው ጥርና የካቲት ውስጥ ውይይት አድርገናል። እንዴት ልንረዳቸው እንደምንችልና እነርሱም ሊረዱን እንደሚችሉ ሰነድ ተዘጋጅቷል። ያንን ለማጽደቅ ሐሳቡ ቢኖርም በወረርሽኙ የተነሳ መሰብሰብ ስላልተቻለ ነው የዘገየው እንጂ በሰነዱ ውስጥ ከታክስ ነፃ መሆን የሚቻልበትና የምንዛሬ ጉዳይም የተካተተበት ነው። ይህን የተመለከተም ጥያቄ ያቀረብን ስለሆነ ምላሽ እየጠበቅን ነው። በጥቅሉ ከግሉ ዘርፍ ጋር ያለን አቋም ይህ ነው።
ከብድር ጋር ተያይዞ ከተነሳው ጥያቄ ጎን ለጎን የምንሠራቸው ቀጣይ ሥራዎች አሉ፤ እነርሱ እያገዙንና እኛም እያገዝናቸው በውሃ እጦት የተቸገረውን ህዝብ ውሃ ማጠጣት ነው ዓላማችን። ነገር ግን መንገድ ዘርፍ ላይ ያለው ዓይነት የብድር አገልግሎት ውሃው ዘርፍ ግን እምብዛም የሚታይ አለመሆኑ ግልጽ ነው፡
አዲስ ዘመን፡– ባለፉት ዓመታት በበርካታ ከተሞች የተጀመሩ የንጹሕ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ተጓተው እንደነበር ይገለጻል። እነዚህ ፕሮጀክቶች በአሁኑ ወቅት በምን ደረጃ ላይ ይገኛሉ?
ዶክተር በሻህ፡– የተጓተቱ ፕሮጀክቶች የተባለው ሲታይ ለመጓተታቸው አንዱ ምክንያት ከግሉ ዘርፍ ጋር ተያይዞ ነው፤ እንዲህ ስል መንግሥት ነፃ ነው ማለቴ አይደለም። መንግሥት፣ አማካሪና ኮንትራክተር የሆነው ገንቢው ሦስቱ ጋር የሚመላለሰው ጉዳይ ግንባታው እንዲጓተት ያደርጉታል።
ከ2010 ዓ.ም በኋላ ብዙ በመፍጠን የተሠሩ ሥራዎች አሉ። ለምሳሌ በዓለም ባንክ ሲሠራ የነበረ ፕሮጀክት ነው። ትልልቅ የሆኑትን ለመጥቀስ ያህል በአራት ዓመት ያህል ይጠነቃቃሉ ተብለው የታቀዱ ለመጓተታቸው ምክንያቱ ምንድን ነው ሲባል አንደኛ የምናቀርበው የጥናት ዶክመንቶች ጥራት ተጠቃሽ ነው፤ የቀረበው ጥናት ወደተግባር ሲገባ ነው ማነቆ የሚሆንብን። ያንን ለማስተካከል የሚደረገው ሂደት ጊዜ የሚያጠፋ ይሆናል። ሌላው ከካሳ ጋር የተያያዘ ችግርም ለመጓተቱ ተጠቃሽ ነው። ቧንቧ ወደቤቱ ይዘንልት ስንሄድ አጥሬ ተነክቷልና ካሳ ይከፈለኝ የሚል ማህበረሰብ ነው ያለው።
ይህን ችግር ለመፍታት ችግሮቹ ተለይተዋልና አማካሪዎችም ዘንድ ሆነ ህብረተሰቡ ዘንድ ግንዛቤ የማሳደግ ሥራ መሠራት ይኖርበታል። የአቅም ክፍተቱን ደግሞ በጀት በማስያዝ ከ2013 በጀት ዓመት ጀምሮ የአቅም ማጎልበት ሥራ እንሠራለን። በእርግጥ አሁንም ቢሆን የተጓተቱና ያልተጠናቀቁ አሉ።
ዋንዋሽ የሚባል ፕሮግራም አለን፤ አዲስ አበባን ጨምሮ ሁለተኛ ደረጃ የሚባሉ 23 ከተሞች ላይ የመጠጥ ውሃና የሳኒቴሽን ሥራ የሚባለው በዓለም ባንክ ብድር የሚሠራ ጠቅላላ ወደ 500 ሚሊዮን ዶላር ተመድቦ ካለፉት ሦስት ዓመታ ጀምሮ እየተሠራበት ያለ ፕሮጀክት ነው።
አዲስ አበባ ከተማ ግማሹን ይዞ 22ቱ ከተሞች ደግሞ እንደየአቅማቸው እየተሠራባቸው ነው። እነዚህ ከተሞች ላይም ለጥናት በሚል ረጅም ጊዜ ወስዶብናል። ከእነዚህ ውስጥ ግን ባህርዳር፣መቀሌ፣ድሬዳዋ፣ ሐዋሳና አዳማ ጥናታቸው በመጠናቀቁ ወደጨረታ ሂደት በመጓዝ ላይ ነን።
ሌላ ደግሞ ዋንዋሽ ናሽናል ፕሮግራም የሚባል ሥራ የጀመረው እ.ኤ.አ በ2013 ነው። የመጀመሪው ምዕራፍ የተጠናቀቀው ከዓመት በፊት ነው። ይሁንና ሳይሠሩ ብዙ የገጠር አካባቢዎች ቀርተዋል። የከተማ ውሃ የያዝናቸው 20 ነበሩ፤ ከ20 ውስጥ 11 ወደሥራ ገብተዋል። ከ11ዱ ሁለቱን ብቻ ነው ያስመረቅነው። የቀሩትን ዘጠኙን ለመጨረስ ብዙ ተለፍቷል፤ ነገር ግን በመሃል በተፈጠረው ወረርሽኝ ከውጭ የሚገቡ እቃዎችን ማስገባት አልተቻለም።
በመሆኑም የአንድ ዓመት ጊዜ ስለተጨመረልን አንደኛው በቤኒሻንጉል ክልል ያለ ከተማ በሦስት ሳምንት ውስጥ ይጠናቀቃል የሚል እምነት አለኝ። ኦሮሚያና ደቡብ ውስጥም በመኖራቸው የአብዛኞቹ እቃዎችም ስለገባላቸው በተለይ የቦዲቲ ከተማ እስከ መስከረም 30 ሌሎቹ ደግሞ ከሁለቱ በስተቀር እስከ መጪው ታኅሣሥ ይጠናቀቃሉ። ሁለቱ ባሌ ሮቤና አርባምንጭ ጬንቻ ግን በተባለው ጊዜ ስለማያልቁልን እስከ መጪው ሰኔ ድረስ ለመሄድ እንገደዳለን።
አዲስ ዘመን፡– በገጠርም በከተማም የሚካሄዱ አዳዲስ የንጹሕ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችስ አሉ ወይ፤ በተለይ ግዙፍ የሚባሉትን ቢጠቅሱልኝ ?
ዶክተር በሻህ፡– ለመሥራት የታሰቡት በገጠር ደረጃ 310 ወረዳ ላይ በከተማ ደግሞ በ60 ከተሞች ከእነዚህ ውስጥ 52ቱ ትንንሽ የሆኑ 8 መካከለኛ ከተሞች ላይ የውሃ አቅርቦት ይሠራል። ከዚያም ባሻገር ድርቅን መቋቋም የሚችሉ ተቋማት ወደ 41 የሚሆኑ አብዛኞቹ ክልሎች ውስጥ ይገነባሉ። በእነዚህ 41 ፕሮጀክት ውስጥ እስከ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ንጹሕ ውሃ እንዲጠጡ ነው። ይህ ፕሮግራም ይፋ የተደረገው እ.ኤ.አ በ2019 መጨረሻ ላይ ነው። በቀጣዮቹ አራት ዓመት ውስጥ ይጠነቀቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።
አዲስ ዘመን፡- የንጹሕ መጠጥ ውሃ ምንጮች ተብለው ከሚወሰዱት መካከል ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ አንዱ ነው። የሚቆፈሩት ጉድጓዶች አቅም ግን አጠያየቂ መሆኑ ይገለጻል። ሲመረቁ ጥሩ አቅም ያሳያሉ፤ ከጥቂት ወራት በኋላ በተለይ ከፍተኛ በጋ በሚኖርበት ወቅት ውሃ ለመስጠት ይቸገራሉ ይባላል። ይህ ከምን የመነጨ ነው? ችግሩ የሚመነጨው ከጥናት ጉድለት፣ ከተቋራጮች አቅም ውስንነት ወይስ የሌላ ነው?
ዶክተር በሻህ፡- ይህ ተፈጥሯዊ ነው። ጥልቅ ውሃ የሚታየው ምልክቱ ነው እንጂ ምን ያህል እንደሆነ ግልጽ አይደለም።
አዲስ ዘመን፡– በጥናት መለየት አይቻልም?
ዶክተር በሻህ፡– በጥናት መለየት ይቻላል። ጥናቱ መኖሩን ሊነግርሽ ይችላል። መጠኑን ግን አይነግርሽም። በአሁኑ ወቅት የጎንደር ችግር ይህ ነው። የጎንደር ጥልቅ ጉድጓድ ውሃ ተመርቆ በአራተኛው ወር አካባቢ የውሃ ማነስ ችግር ገጥሞታል። በድሬዳዋም ቢሆን ያስመረቅነው ከዓመት በፊት ነው። አሁን ግን ውሃው ወደታች ዝቅ እያለ በመምጣቱ የማነስ ምልክቶች እየታዩ ነው።
ይህ ከእኛ አቅም ማነስ ሳይሆን አካባቢውን ከመረዳት አንጻር፣ ያለው ቴክኖሎጂና የአየር ጸባይ ለውጡም ያመጣው ችግር ነው፤ በአየር ጸባይ ለውጡ መዛባት የተነሳ ወደመሬት የሚገባው ውሃ መግባት ሳይችል ቀርቶ ወደሌላ ቦታ ይፈሳል። ይህ ሲሆን ደግሞ የአካባቢውን የውሃ ሀብት ይጎዳዋል። የደኖች መጨፍጨፍ፣ አግባብ ያልሆነ የአስተራረስ ዘዴና መሰል ድርጊቶች የጣለው ዝናብ ወደ መሬት እንዳይሰርግና እየጋለበ እንዲሄድ ያደርገዋልና ነገሩ ውስብስብ ነው።
አዲስ ዘመን፡– ስለዚህ ችግሩን ለመፍታትስ ምን እየተሠራ ነው?
ዶክተር በሻህ፡– ምናልባት አሁን እየሄድን ባለንበት አካሄድ ችግኙን እየተከልን ከሄድን ያነሳሻቸው ነገሮች ሊቀየሩ ይችላሉ ብዬ አስባለሁ።
አዲስ ዘመን፡– የአየር ንብረት ለውጥ በሀገሮች የንጹሕ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ላይ ደንቃራ እየሆነ እንደሚገኝ ይገለጻል። ሀገራችን ይህን ችግር ታሳቢ ባደረገ መልኩ ምን እየሠራች ትገኛለች?
ዶክተር በሻህ፡– የአየር ንብረት ለውጥ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክትን የሚጎዳው በብዙ መንገድ ነው። በረሃማነት አሊያም ሙቀት እየተስፋፋ ሲሄድ የውሃ ፍላጎታችን እየጨመረ ይሄዳል። በአንጻሩ ደግሞ የውሃ መገኛዎቻችን እየተጎዱ ይሄዳሉ። ደኖችም እየተመናመኑ ስለሚሄዱ የሚጥለው ዝናብ ወደመሬት አይገባም። መሬት ያልገባ ውሃ ደግሞ ምንጭ አይሆንም። ከዚህም የተነሳ የከርሰ ምድር ውሃችን እየራቀ ይሄዳል።
ስለዚህ ችግሩን ለማቃለል ድርቅን መቋቋም የሚችል የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት በሚኒስትሩ ሐሳብ አመንጪነት ዶክመንት ተጠንቶ እንደ አንድ አማራጭ የውሃ አቅርቦት ትኩረት ተሰጥቶት በኮሚሽናችን እየተሠራ ነው። ይህ ማለት ድርቅም ጎርፍም ቢመጣ ባይመጣ የውሃ ተቋም ካለ ውሃ መስጠት አለበት የሚል መመሪያ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ጥናቶች እየተካሄዱ ናቸው። ወደሥራም እየገባን ነው። ችግር ያለባቸውም ቦታዎች ተለይተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተሠራ ነው።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ከእንግሊዝ መንግሥት የተገኘ ፈንድ 100 ሚሊዮን ዶላር የሚሆን ለዚህ ዓላማ ብቻ የሚውል በዋን ዋሽ ናሽናል ስር በሁለተኛው ምዕራፍ እየተጠቀምን ነው። የሁለተኛው ምዕራፍ ጠቅላላ ወደ 600 ሚሊዮን ዶላር የሚሆን በጀት ያለው የገጠር መጠጥ ውሃና ተጓተቱ ያልናቸው የከተሞችም አሉና በዚያ ረገድ እየተሠራ ነው።
አዲስ ዘመን፡– ለሰጡኝ ሰፊ ማብራሪያ አመሰግናለሁ።
ዶክተር በሻህ፡– እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 21/2012
አስቴር ኤልያስ