መንግሥት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቷል፤ እያደረገም ይገኛል:: ለአብነት በመዲናዋ የተከናወነው በኢትዮጵያ ኢንቨስት ያድርጉ ፎረምን መጥቀስ ይቻላል:: ፎረሙ ኢንቨስትመንትን ለማነቃቃትና ለማሳደግ እየተከናወኑ ካሉ ተግባሮች መካከል ይጠቀሳል:: ዋና ዓላማው ሀገሪቱ በተለያዩ ዘርፎች ያሏትን ጸጋዎች በማስተዋወቅ የውጭ ባለሀብቶችን ወደ ኢትዮጵያ በመሳብ ፤ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰትን ማሳደግና ከዘርፉ ተጠቃሚ መሆን ነው::
እንደሚታወቀው፤ ኢትዮጵያ ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ያላትን ምቹ ሁኔታ ለማስተዋወቅ ጥረት ተደርጓል:: በዚህም ለካፒታል ፍሰት፣ ለቴክኖሎጂና እውቀት ሽግግር ወዘተ.ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ፣ በውጭ ምንዛሬ ግኝት በኩልም የራሳቸውን ዐሻራ ያኖሩ የውጭ ኢንቨስትመንቶችን ወደ ኢትዮጵያ መሳብ ተችሏል:: ባለሀብቶቹም በተለያዩ ዘርፎች ተሠማርተው ይገኛሉ::
ኢትዮጵያ አሁንም አዳዲስ የውጭ ባለሀብቶችን መሳብ የሚያስችሉ በርካታ ዕድሎች እንዳሏት መረጃዎች ያመለከታሉ:: እነዚህን ጸጋዎች በማስተዋወቅ ወደ ኢትዮጵያ የሚሳበውን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ቁጥር ለማሳደግ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ይመክራሉ::
የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ይበልጥ ለመሳብና ከዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማረጋገጥ ምን መደረግ አለበት? በሚል ያነጋገርናቸው የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች፤ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን መሳብ የሚያስችሉ በርካታ ጸጋዎች ያሏት ኢትዮጵያ እነዚህን በረከቶቿን አሟጣ ለመጠቀም አሁንም ብዙ መሥራት አንዳለባት አመላክተዋል::
በኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ማህበር ተመራማሪ ዘነበች አድማሱ (ዶ/ር)፤ በአንድ ሀገር ላይ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማምጣት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ወሳኝ እንደሆነ ጠቅሰው፣ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ የፋይናንስ እጥረት ለሚገጥማቸው ሀገሮች የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ትልቅ አበርክቶ እንዳለው ተናግረዋል::
እሳቸው እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ለመጀመር የተሻለ ዕድል ያለው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ነው:: የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ይዞት የሚመጣው ካፒታል እንዳለ ሆኖ ከሥራ ዕድል ፈጠራና ከቴክኖሎጂ ጋር የሚመጣው በረከት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገትና መነቃቃት ትልቅ ድርሻ አለው::
ኢትዮጵያ ውስጥ ላለው ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰው ኃይል የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የሚፈጥረው የተሻለ የሥራ ዕድል ሌላው የኢንቨስትመንቱ ፋይዳ ነው:: በተለይም ርካሽ የሰው ኃይል ባለበት የሥራ ዘርፍ ማለትም በኢንዱስትሪ ፓርኮች የተሰማሩ የውጭ ባለሀብቶች ጥሩ የሥራ ዕድል የመፍጠር፣ ክህሎትን የማጎልበትና ቴክኖሎጂን የማስተላለፍ ዕድል አላቸው::
በተመሳሳይ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች የገበያ ትስስር የመፍጠር ሰፊ ዕድል ያላቸው በመሆኑ፤ የሀገር ውስጥ ምርቶችን በዓለም አቀፍ ገበያ ተደራሽ በማድረግ ወጪ ንግድ እንዲጨምር ያደርጋሉ:: ይህም የሀገሪቷን የውጭ ምንዛሪ ግኝት ከፍ በማድረግ የላቀ ድርሻ አለው::
ከዚህ በተጨማሪ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በሀገር ውስጥ ያለውን ባለሀብት በማነቃቃት የተወዳዳሪነት ስሜት መፍጠር እንደሚያስችልም ዘነበች (ዶ/ር) ጠቁመዋል:: በተለይ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ከውጭ ባለሀብቶች ጋር ተቀራርበው ቢሠሩና ቢመጋገቡ የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ አቅማቸውን ለማገዝና ለመደገፍ ያስችላቸዋል ብለዋል:: ይህም ተወዳዳሪነታቸውን ከፍ በማድረግ ጠንክረው እንዲሠሩ እንደሚያበረታታቸው ተናግረዋል::
ይህን ሃሳብ የሚጋሩት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ቆስጠንጢንዮስ በርኸተስፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ለሀገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ምቹ እንደሆነች አስታውቀዋል:: ለዚህም ከ70 በመቶ በላይ ወጣት የሚሠራ ኃይል፣ የውሃ ሀብት፣ እምቅ የማዕድን ሀብቶችና ሌሎችም ባለሀብቱ የሚፈልጋቸው መሠረታዊ ጸጋዎች ሀገሪቱ እንዳሏት ያስረዳሉ::
ባለሀብቱ በዋናነት የሚፈልጋቸው መሠረታዊ ጉዳዮች ቢኖሩም ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ያለመኖሩ፤ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሙስናና ብልሹ አሠራር መዘፈቅና የኮንትሮባንድ ንግድ ኢንቨስትመንቱ በሚፈለገው ልክ እንዳይስፋፋ አንቀው የያዙት ግዙፍ ችግሮች ናቸው ሲሉም አመልክተዋል::
እሳቸው እንዳሉት፤ እነዚህን ችግሮች መቅረፍ ከተቻለ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በቀላሉ ማግኘት ይቻላል:: የሀገር ውስጥ ባለሀብቱንም እንዲሁ በእነዚህ ሥራዎች ላይ በማሳተፍ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ችግር አይሆንም:: ምክንያቱም ኢትዮጵያ ትልቁን የሰው ኃይል ጨምሮ በርካታ ለኢንቨስትመንት ምቹ የሆኑ ዕድሎች ያላት በመሆኑ ችግሮቹን በመፍታት ላይ በመሥራት ውጤት ማምጣት ይቻላል::
ከዚህ ቀደም ችግሮች ነበሩ፤ በርካታ የተሻሻሉ ጉዳዮች አሉ ሲሉ የጠቀሱት ቆስጠንጢንዮስ(ዶ/ር) ፤ ለአብነት የፋይናንስ ሥርዓቱን አንስተዋል:: የፋይናንስ ሥርዓቱ ግልጽነት የጎደለውና አመቺ እንዳልነበረ አስታውሰው፤ በቅርቡ የውጭ ባንኮች ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ መፈቀዱ ለዘርፉ ትልቅ አበርክቶ እንዳለው አስረድተዋል:: የትኛውም ኢንቨስተር የሚሠራው ከባንክ ተበድሮ ነው፤ በመሆኑም ሊያበድረው የሚችል ባንክ መኖር አለመኖሩን አረጋግጦ ይመጣል እንጂ የሚሠራበትን ዶላር በሙሉ ይዞ አይመጣም ሲሉም አስገንዝበዋል::
ሌላው የካፒታል ገበያ ሥርዓት አለመኖርም በዘርፉ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሲያሳድር ቆይቷል ሲሉም አስታውሰው፤ ይህ ችግር አሁን መፈታቱ ጥሩ ዕድል ይዞ እንደሚመጣ ተናግረዋል::
እንደእሳቸው ገለጻ፤ ካፒታል ገበያ መኖሩ የውጭም ሆነ የሀገር ውስጥ ባለሀብቱ ከባንክ ብቻ ይበደር የነበረበትን ዕድል ያሰፋዋል:: በመሆኑም ትላልቅ ሥራ መሥራት ሲፈልጉ ለካፒታል ገበያው ሃሳባቸውን በማቅረብ አክሲዮን እየሸጡ ካፒታል ሊያመነጩ የሚችሉበት ዕድል ይፈጠራል:: እነዚህንና መሰል ሥራዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል የውጭና የሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንትን ማስፋት ይቻላል::
ዘነበችም (ዶ/ር) እንዲሁ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ማስፋት የሚያስችሉ አሠራሮች መሻሻላቸውን ጠቅሰው፤ የሚታዩት ሥራዎች አበረታች እንደሆኑ ገልጸዋል::
እሳቸው እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት አመቺ መሆኗን ከማስተዋወቅ ባለፈ ለአሠራር አመቺ የሆኑ ፖሊሲዎችን ከማውጣት ጀምሮ መመሪያዎችን ማሻሻልና ምቹ ሁኔታን በመፍጠር የውጭ ካፒታል የበለጠ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣበትን ሁኔታ ማመቻቸት ያስፈልጋል::
ለአብነት በቅርቡ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፖሊሲ ላይ የተደረገው ማሻሻያ አንድ ማሳያ ነው:: ይህም የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚው ላይ ጉልህ ሚና መጫወት እንዲችል ያግዘዋል:: ሌላው የተለያዩ ማበረታቻዎች መኖራቸውም ኢንቨስትመንቱን ለመሳብ ያግዛሉ:: ለውጭ ባለሀብቶች ክልክል የነበሩ ዘርፎችም እንዲሁ በተሻሻለው አዋጅ ክልከላው መነሳቱ በርካታ ዕድሎችን መፍጠር ያስችላሉ::
ለኢንቨስትመንት ምቹ የሆኑ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሞችም ውጤታማ እንደሆኑ ያነሱት ዘነበች(ዶ/ር)፤ ይህም የዘርፉን ማነቆዎች በመፍታት ትልቅ ድርሻ እንዳለው ይገልጻሉ:: በዋናነት በባለሀብቱ ዘንድ መተማመን መፍጠር እንደሚገባም ተናግረዋል:: ይህ ሲሆን ባለሀብቱ በሀገሪቷ ኢንቨስት ባደርግ ያዋጣኛል ብሎ እንደሚመጣ ገልጸው፣ ይህን መተማመን በመገንባት ምርትና ምርታማትን ማሳደግና ዕድገት ማምጣት ያስፈልጋል:: የተለያዩ ኢኮኖሚክ ሪፎርሞች መደረጋቸውም በዚሁ ምክንያት ነው ብለዋል::
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የሚፈልጋቸውን መሠረተ ልማቶች ማሟላት ሌላው ኢንቨስትመንቱን መሳብ የሚቻልበት መንገድ ነው:: ለዚህም ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችን (የኢንዱስትሪያል ፓርኮችን) ጨምሮ የኢትዮጵያ አየር መንገድን መጥቀስ ይቻላል:: የኢንዱስትሪ ፓርኮችም እንዲሁ መንገድ፣ የኤሌክትሪክ ኃይልና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን ያሟሉ በመሆናቸው የተቀላጠፈ አገልግሎት በመስጠት ኢንቨስትመንቱን መሳብ ይቻላል::
የተለያዩ ፍላጎቶችን ይዘው ለሚመጡ የውጭ ባለሀብቶች ዝግጁ ሆኖ መጠበቅ አንዱ አማራጭ ነው ያሉት ዘነበች(ዶ/ር)፤ በርካታ የሰው ኃይል ያላት ኢትዮጵያ ተመራጭ ናት ብለዋል:: የተፈጥሮ ሀብትና ጥሬ ዕቃ ፈልገው ለሚመጡ የውጭ ባለሀብቶችም ኢትዮጵያ ተመራጭ በመሆኗ ዕድሉን መጠቀም ይገባል::
ቴክኖሎጂ አላምደው ለመሸጥ አልያም መግዛትን አልመው የሚመጡ የውጭ ባለሀብቶችም አሉ ያሉት ዘነበች (ዶ/ር)፤ ስትራቴጂካሊ ወደፊት ሊያዋጣን የሚችል ሀገር የቱ ነው? በማለት ፖለቲካዊ ሁኔታው የተረጋጋና ቀጣይነት ያለው ኢንቨስትመንትን ሊፈቅዱ የሚችሉ ሁኔታዎችን ከግምት አስገብተው የሚመጡ እንዳሉም አስረድተዋል::
ኢትዮጵያ በእነዚህ መመዘኛዎች ጥሩ ሆና ስትገኝ፤ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በሚፈለገው ልክ መሳብና ከዘርፉ የሚፈለገውን ካፒታል ማግኘት ይቻላል ሲሉ አስታውቀዋል::
እንደ እሳቸው ማብራሪያ፤ ኢትዮጵያ አብዛኞቹን መመዘኛዎች ማሟላት የምትችል ናት:: ለአብነት በጨርቃጨርቅ ምርት ላይ መሰማራት የፈለገ የውጭ ባለሀብት ጥሬ ዕቃውን ኢትዮጵያ ውስጥ ማግኘት በመቻሉ ወደ ኢትዮጵያ ይሳባል:: ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶችን መጠቀም የሚያስችሉ ኢንቨስትመንቶችም እንዲሁ ባለሀብቱን ይስባሉ::
ሀገሪቷ ካላት የተፈጥሮ ሀብትና ሌሎች ምቹ ሁኔታዎች በተጨማሪ ኢትዮጵያ ለአውሮፓና ለኤዥያ ያላት ቅርበትም ወሳኝ ነው ሲሉም ጠቁመዋል:: ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ያለውን ምቹ ሁኔታ ከመፍጠር ባለፈ ማስተዋወቅ ወሳኝ ነው ያሉት ዘነበች (ዶ/ር)፤ ‹‹ኢንቨስት ኢን ኢትዮጵያ›› የተሰኘው ፎረም ለዚህ ጥሩ ማሳያ እንደሆነ ጠቅሰዋል::
ተመሳሳይ መድረኮችን በስፋት በማዘጋጀት ማስተዋወቅ እንደሚገባ አስገንዝበዋል:: የማስተዋወቅ ሥራው በሀገር ውስጥ ብቻ የተገደበ መሆን እንደሌለበት አስገንዝበው፤ ባለሀብቱ ባለበት ቦታ ጭምር በመሄድ መሥራት አለበት ብለዋል:: ይህንንም በተለያዩ ሀገራት በሚገኙ ቆንጽላዎች አማካኝነት ማድረግ እንደሚቻል አመላክተዋል::
አንድ ሀገር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ስለፈለገ ብቻ አያገኝም ያሉት ዘነበች (ዶ/ር)፤ አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር የግድ ነው ብለዋል:: እሳቸው እንዳሉት፤ አዳዲስ ባለሀብቶችን ለማምጣትም ሆነ የገቡትን ለማቆየት ለባለሀብቱ አመቺ ስትራቴጂዎችን መቅረጽ እደሚገባ ጠቁመዋል::
ባለሀብቱ በተለያየ መንገድ መተማመኑ ከፍ እንዲል መሥራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል:: ለዚህም ሀገሪቷ ውስጥ ያለው ሰላም ወሳኝ እንደሆነ ጠቅሰዋል:: ‹‹ኢንቨስትመንት በዋናነት ሰላም የሚፈልግ በመሆኑ የባለሀብቱን መተማመን መገንባት ያስፈልጋል:: ይህም አዳዲስ ባለሀብቶችን ከመሳብ ባለፈ ያሉትን ለማቆየት ይረዳል›› ያሉት ዘነበች (ዶ/ር)፤ በሀገሪቷ ሰላም ላይ መሥራትና የባለሀብቱን መተማመን በመገንባት ዘላቂ የሆነ ኢንቨስትመንት መሳብ አስፈላጊ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል::
ኢንቨስትመንትን ለማሳለጥ ሰላም መሠረታዊ ጉዳይ እንደሆነ ቆስጠንጢንዮስም (ዶ/ር) አመላክተዋል:: ከሰላምና ጸጥታ ባለፈ ሙስናን ጨምሮ ሌሎች የተጠቀሱ ችግሮችንም መቅረፍ ተገቢ እንደሆነ አስረድተዋል:: ይህን ተግባራዊ ማድረግና ኢትዮጵያ ያሏትን ጸጋዎችና በረከቶች በመጠቀም ኢንቨስትመንትን ማሳደግ ይቻላል ብለዋል:: ምክንያቱም ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገሮች አንጻር የተሻለ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን የመሳብ ዕድል አላት ይላሉ::
እሳቸው እንዳሉት፤ ከጎረቤት ሀገራት መካከል ኤርትራ ለኢንቨስትመንት ዝግ ስትሆን፤ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳንና ሶማሊያ ጦርነት ላይ ናቸው:: ስለዚህ ከጎረቤት ሀገሮች አንጻር ኬንያ ብቻ ኢትዮጵያን የምትገዳደር ሲሆን፤ ያም ሆኖ ኢትዮጵያ የተሻለ የኢንቨስትመንት ዕድል ያላት ሀገር ናት::
ኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ያሏትን ዘርፈ ብዙ ዕድሎች አሟጣ ለመጠቀም መንግሥት እያከናወናቸው የሚገኙ ሥራዎችን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስታውቀዋል:: በተለይም በከፍተኛ ሁኔታ የተንሰራፋውን ሙስና መታገል የግድ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተው አስገንዝበዋል::
ለዚህም ሚዲያ ትልቅ መሣሪያ ነው ያሉት ቆስጠንጢንዮስ (ዶ/ር)፤ ሚዲያው የሙስና ምንጮች እነማናቸው? በሚል በምርመራ ዘገባ መርምሮ ይፋ ማውጣት ይጠበቅበታል ብለዋል:: በዚህ በኩል ሚዲያ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ጠቁመው፣ በተለይም ፖሊስ የማጣራት ሥራን በማከናወን የሙስና ምንጮችን ማድረቅ ይጠበቅበታል ብለዋል::
ሀገር ውስጥ ያለው ሚዲያ ሌሎች ያወጡትን መረጃ ከማስተጋባት ባለፈ በራሱ የምርምራ ሥራ ሰርቶ ሙስናን ሲያጋልጥ አይታይም ሲሉ ጠቁመዋል:: ‹‹ሙሰኞች ህብረተሰቡ ውስጥ ያሉ በመሆናቸው የተለያዩ እንቅፋቶች ሊገጥሙ ይችላሉ:: ለዚህም መንግሥት አስፈላጊውን የሕግ ከለላ በመስጠት ሚዲያው ሙስናና ብልሹ አሠራሮችን በሙያው መታገል እንዲችል ሁኔታዎችን ማመቻት ይጠበቅበታል›› ብለዋል::
በተያዘው በጀት ዓመት አስር ወራት የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ በተደረገው ጥረት ፍሰቱን ሁለት ነጥብ ስምንት አራት ቢሊዮን ዶላር ማድረስ ተችሏል:: አዳዲስ የውጭ ቀጥተኛ የኢንቨስትመንት ፈቃድ የወሰዱ የውጭ ባለሀብቶች ቁጥርም እየጨመረ መጥቶ ከ363 በላይ ደርሷል::
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቦርድ ከዚህ ቀደም ዝግ የነበሩ ዘርፎችን ክፍት አድርጓል:: ከእነዚህም መካከል ለውጭ ባለሀብቶች ዝግ የነበረው የንግዱ ዘርፍ አንዱ ነው፤ በዚህም አጠቃላይ የገቢ፣ የወጪ፣ የጅምላና የችርቻሮ ንግድን ለውጭ ባለሀብቱ ክፍት በማድረግ ፈቃድ እየተሰጠ ይገኛል:: የንግድ ዘርፉ ክፍት በመደረጉ ምክንያትም ትላልቅ የውጭ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት ያሳዩ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅትም 260 ኩባንያዎች ፍላጎት እንዳላቸው መረጃዎች ያሳያሉ::
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 12 ቀን 2017 ዓ.ም