ከሞቱ ነገሮች

ውድቅት ለሊት ላይ በግራ እጄ ጎኔን በቀኝ እጄ ደግሞ የብዕር ወገብ አንቄ ወዲያ ወዲህ እየተንቆራጠጥኩ ሃሳብ ሳምጥ የቤት አከራዬ እማማ ሽጉልቴ “አንተ አይናማው” ሲሉ ተጣሩና ሽፍንፍን አግቧቸውን ከበሬ ስር ተለጥፈው “አታየው አያይህ፤ እና ታዲያ መብራቱን ብታጠፋው ምን ይመስልሃል?” አሉ ሰላላ ድምጻቸውን እያቅጨለጨሉ። ለዚህ ነበርኮ አምፖል ስለማልጠቀም የኪራይ ዋጋ ይቀንሱልኝ ማለቴ ስል መለስኩላቸው።

ደግሞም ዋናው ማመን ነው፤ ነጭ ወረቀቱ ጋር የመብራቱ ብርሃን ሲፋጭ የምናቤ ወጋገኑ ይደምቅና የጋዜጣዬን ጽሁፍ አግተለትላለሁ አልኳቸው በማስከተል። ጨዋታ ሲፈልጉ አውቅባቸዋለሁና በሩን ከፍቼ ጆሮዬን ስሰጣቸው “ላንባው በኮረንቲ ተቀይሮ፣ እህሉ በባቡር ሆኖ፣ ውሃው በቧንቧ ተስቦ በደረስንበት ዘመን ባል ይጥፋ?” አሉና እየሳቁ ከሩቅ ለመጣ እንግዳ ቡና አፍልተው ኖሮ እጠጣ ዘንድ አስከትለውኝ ቀደሙና ከቤታቸው እንደዘለቅን ከጥቁሩ የግዜር እንግዳ ጋር እጅ ተነሳሳንና እመይቴዋ ከዘረጉልኝ ሲኒ ጋር ያቀበሉኝን ወግ እንደአቦሉ ላፍኩት።

አልመረቁምኮ አልኳቸው ያስለመዱኝ ምርቃት ቀርቶብኝ ቅር ሲለኝ ተሰማኝና። “ሞት ይርሳኝ” አሉና ሆድ የሚያጠግብ ምርቃታቸውን አዥጎደጎዱት። “ከነቶሎ ቶሎ አንባቢ ወቀሳ፣ ከይርዳው ጤናው ጠቀሳ ይጠብቅህ፤ በተበዳሪ ሰፈር ከሚንጎራደድ ገንዘብ፣ ፈቅዶ ጋብዞ ከሚታዘብ ይጠብቅህ፤ ከሰፊው ሕዝብ ምላስ፣ ከኮንዶሚኒዬም ጠባብ ክላስ ይሰውርህ፤ ሚስኮል አድርጎ ከሚጀነጅን፣ ሳያዳምጥ ከሚበይን ይጠብቅህ፤ በባዶ ሆድ አንቦሃ ጠጥቶ ሃሳብ ከመበተን ይጠብቅህ፤ ፍቅረኛህ ስትቀር አልጋ እየደበደቡ ከማደር፣ ከመንግሥት ብድር ይሰውርህ፤ ምቀኛህን የናትህ አድባር አዋምሳግና የአያ ሙሌ አሲያሞ እንደዕግር ኳስ ብሔራዊ ቡድናችን ታልፈስፍሰው፤ እንደኦሎንፒክ ኮሚቲያችን ከእልህና ፉክክር ይጠብቅህ፤ ከቴሌ የጽሁፍ መልዕክት ጋጋታ፣ ከፖለቲከኛ አሉባልታ ይጠብቅህ፤ ከቂም ይዞ ጸሎት፣ ከስጋ አምሮት ይጠብቅህ” በማለት ሲመርቁኝ ቆይተው እንትፍ እንትፍ ካሉልኝ በኋላ መልሰው ከገንዳው በመሰየም የጀበናውን ጆሮ ሳሙና ረጃውን አሲያዙኝ። “የስጋ አምሮት” ያሉት ነገር ሰኔ ዘቅዘቅ ማለቱን አስታወሰኝና በምናቤ የተሰነቀረችውን ስንኝ ለቀም አደረኳት።

እንደምን ነህ ጎመን የድሆች ቅቅል፣

ሃብታሙን ጣለልህ የሚያቀማጥል።

እማማ ግን አያይም ብለው ነው አይን የሌለው እንጀራ የሰጡኝ? አልኳቸው ድቁስ ቀብተው የዘየሩኝን የቡና ቁርስ እየጎመድኩ። “አይናማውዬ ብላኝ እንጂ ምራኝ ብሎሃል?” አሉና በሳቅ ወደቁ። ቀጠሉና “እኔ የምልህ፤ በጊዜ እንደዶሮ መስፈር ጀምረሃል፤ ፖለቲከኛ ሆንክ እንዴ?” አሉ ለሶስተኛው ቡና ጀበናውን እየጣዱ።

አለማየሁ ገላጋይ “ደራሲ ምን ይመስላል?” ሲል ያስነበበው መጣጥፍ ትዝ ስላለኝ ፖለቲከኛስ ምን ይመስል ይሆን? የሚል ጥያቄ ጫረብኝና የሳቸውን መረዳት ይነግሩኝ ዘንድ ሃሳቡን ሰነዘርኩላቸው። “እነሱማ ጨካኝና አስመሳይ፣ አረመኔና ወላዋይ፣ ፈሪና ተጠራጣሪ እንዲሁም ወስላታ ናቸው” አሉ የምጸት ፈገግታ እያሳዩኝ። ጥቁሩ የግዜር እንግዳም ቀበል አድርጎ “ሃይማኖት አልባ እንዲሁም ስለሌላው ግድ የማይሰጣቸው ድሆችም ናቸው” አለ።

የሁለቱን ሰዎች እሳቢያዊ ትርጉም ይዤ ዓለም አንቱታን የቸረቻቸው ስመ ጥር የቀለም ቀንዲሎቻችንን ማለትም ፕሉቶን ከዲዮጋን፣ ጀረሚ ቤንታምን ከጆን ስቷርት ሚልና ጆንጃክ ሩሶ ጋር ጎራ ያስለየ በተቃራኒው ደግሞ ቶማስ ሆፕስን ከማካቬሊና ሂትለር ጋር ያቆራኛቸውን ድርሰታዊ፣ ፖለቲካዊና ፍልስፍናዊ የስነጽሁፍ ሃረጋቸውን ሃሳብንና ስብዕናን ሳልዘንቅ ለማሰስ ብዳክርም ያልቀመሱትን ነገር ጣእሙን ሊገልጹት አይቻልምና ማንነታቸውንና ምንነታቸውን የብዕራቸው ዳና ጠቁሞኛልና ትዝብቴን አጋራችሁ ዘንድ እነሆ ጳውሎስ ኞኟዊ የስነጽሁፍ መነጽሬን ወለወልኩ።

“ሪፐብሊካን” የተሰኘ መጽሃፍ ጽፎ ያስነበበን ፕሉቶ ሽቅርቅር ሲሆን ዲዮጋን ባንጻሩ “ጥበብ አትሸፋፈንም፤ ተፈጥሮም አትከለልም” ሲል እራፊ ጨርቅ እንኳን ገላው ላይ ሳይጥል ነው እድሜውን የፈጀው። ፍልስፍና የፖለቲካል ሳይንስ አባቱም አይደል? አንድ ገበሬ በእጁ እየቀዳ ሲጠጣ የተመለከተው ዲዮጋን “ለካስ ተሳስቻለሁ?” ብሎ ብቸኛ ሃብቱን ቅሉንም ሰበረው፤ እንዲህ ያለው ጠባዩም “የሰው ልጅ ለራሱ ሲል ነው ውዴታም፣ ሃዘኔታም፣ ምጽወታም የሚከጅለው” ከሚል እምነት አድርሶታል። ይህን መሳይ ሃሳብም “ዘ ፕሪንስ” በተሰኘ መጽሃፉ እውቁ “የሪያሊዝም ቲዎሪን” አቀንቃኙ ማካቪሌ አንጸባርቆታል።

“ዘ ኢንድ ጀስቲፋይ ዘ ሚንስ፤ [የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው] ውጤቱ ካማረ ምክንያቱን ይገልጸዋል” የሚል ጭብጥ ያለው ይህ መጽሃፍ “ጊዜ የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል” እንዲሉ በጣሊያን ጥንታዊት ከተማ ለፍሎረንሱ መስፍን በፐብሊክ አድቫይዘርነት ይሠራ የነበረው ማካቬሌ እንደሆኑት አልሆን ስላለ ጊዜ፣ ቦታና ሁኔታ የፈጠረላቸውን አጋጣሚ ተጠቅመው ከሥራ ሲያባርሩት “ለነሱ ስኬት ሲባል የኔ ሕይወት መጎሳቆል የግድ ነበረበትና እኔም በተራዬ ለመኖር ስል ያልመሰለኝን እገላለሁ” በሚል ጭካኔ የተሞላ እሳቤ መላበሱን ያስነብባል።

የሀገራችንን ስነጽሁፍ ውበት የኳለው በዓሉ ግርማም “ኦሮማይ” በተሰኘው መጽሐፉ ተከስተ በሚል ስም የሳለው ገጸባህሪ “ሰባት አመት የዕስር ዘመኑን ጠጥቶ ከማረሚያ ቤት ሲወጣ ለመኖር ሲል ይገድል ዘንድ ሻቢያ ያቀረበለትን ምርጫ አልባ ሕይወት ሳያቅማማ ተቀበለ” ይለናል። ጀርመናዊው ፈላስፋ ኒቼም “ዘ ጆይ ኦፍ ዊዝደም” በተሰኘው መጽሐፉ “ሃይማኖትና ዲሞክራሲ የደካሞችና የድሆች ስብስብ በመሆኑ መብታችን ይከበር፤ ሁሉም ለበጎ ነው፤ የሚሉ ድምጾች ተሰሚነት የላቸውም” ሲል የጭካኔ ገመዱን ያጠብቀዋል፤ ካርል ማርክስም ይህን ሃሳብ ሲጋራው ይስተዋላል።

“አይ ዎዝ ቦርን ዊዝ ማይ ፊር፤ [እኔ የተወለድኩት ከፍርሃቴ ጋር ነው]” በሚለው አነጋገሩ የምናውቀው እንግሊዛዊው ቶማስ ሆፕስም የሰውን ልጅ “ጨካኝ፣ አረመኔ፣ ገብጋባ፣ ባለጌ” ሲል ይገልጸዋል፤ እንዲህ ለማለት ያበቃው ሰበብም “ሊቢያታን” በተሰኘው መጽሐፉ ቁልጭ ተደርጎ ተሰንዷል።እኤአ 1518 አካባቢ ስፔንና እንግሊዝ የፈጠሩት ጦርነት ቶማስ ሆፕስ በሰባት ወሩ እንዲወለድ ምክንያት ሆኗል። እናቱ ከባህር ዳርቻ በመዝናናት ላይ እንዳለች ሲመጣ የተመለከተችው ወራሪው የስፔን ሰራዊት አስፈርቷት የፈጠረባት ድንጋጤ ሰቆቃዋን አብዝትቶት ያለቀኗ ለመውለድ ተገደደች፤ ታዲያ ይህን እየሰማ ያደገው ቶማስ ሆፕስም በግዕዝ ቋንቋ “ሊዋታ ወይም ቤሂሞት” የምንለውን በመጽሐፍ ቅዱስም የተገለጸውን አስፈሪውንና ግዙፉን የባህር ውስጥ አውሬውን ከስፔን ሰራዊት ጋር በማስተሳሰር በብዕሩ ልሳን “ሊቢያታን” ሲል ገለጠው ፤የራሱን ታሪክ እንደዕርሾ በመጠቀም።

“ያቺን ቀን እስከምናገኛት ድረስ ደግ እንመስላለን እንጂ ሁላችንም በውስጣችን ክፉዎች ነን” እንዲሉ መጋቢ ሃዲስ እሸቱ አለማየሁ የናዚው ዘዋሪ ጀርመናዊው መሪ ሂትለርም በአራጣ አበዳሪዎች የወላጆቹ ኃብት ተመጥምጦ በማለቁና ርሃብ እየጠበሰው ከማደጉ የተነሳ እልህና ቁጭት አድሮበት “የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳምና” ጊዜ፣ ቦታና ሁኔታ ፈቅዶ መንበረ ስልጣኑን ሲጨብጥ ቂሙንና የጥላቻ መርዙን በአይሁዶች ላይ እንደተፋው ግለታሪኩን በሚያትተው “ማይ ከምፐፍ” በተሰኘው መጽሐፉ ውስጥ በግልጽ ሰፍሯል። ለዚህ ሳይሆን አይቀርም ሩሲያዊው ደራሲ ዶስቶቭስኪ ኢቫን በተባለው ገጸባህሪው በኩል “የሰውን ልጅ አውሬ ብሎ መሳደብ የእንስሳትን ክብር ማጉደፍ ነው” ማለቱ።

እርግጥ ነው ፖለቲካ “ማን ያገኛል?፣ የት ይገኛል?፣ እንዴት ይገኛል?” ለሚሉ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥ ኃይል ሲሆን ደራሲውም፣ ፖለቲከኛውም፣ ፈላስፋውም የጥበብ ብልጭታን የተገነዘበና ከማህበረሰቡ ልማዳዊ አተያይ የቀደመ ብሎም “በዲቫይን ማድነስና ፊዚካል ማድነስ [በመለኮታዊና አካላዊ እብደት]” የተቃኘ “ድቪያንት [አፈንግጤ]” ነው።

ዲቫይን ማድነስ [መለኮታዊ እብደት] ጠባይ ይታይባቸዋል ተብለው ከሚነሱት መሃል የሚገኘው ጆንጃክ ሩሶ አምስት ጊዜ አግብቶ አምስት ጊዜ የፈታ ሲሆን በአንደኛው የሰርግ አጋጣሚ ላይ እንዲህ ሆነላችሁ። የሴት ወገን ሙሽራው ይመጣል ብሎ ደጅ ደጁን ቢያይ ቢያንቃቃ የሩሶ ሰርገኛ ግን የውሃ ሽታ ሆነባቸው፤ በነገሩ እርር ድብን ያለችው ሙሽሪትም ምንተፍረቷን ጥላ እየበረረች ከቤቱ ስትሄድ አንገቱን አቀርቅሮ ሲሞነጫጭር አገኘችውና በድርጊቱ እጅጉን በግና ጉንጩን በጥፊ ብታቀላው ጊዜ ከማር በሚጣፍጥ ትህትና “የኔ ውድ የኔና ያንቺ ደስታ ይደርሳል፤ አሁን ግን እንደምታዪኝ አለምን ለመለወጥ እየጻፍኩ ነው” አላትና ብዕሩን ወደማቅለም ተመለሰ።

ማግባትንና መፍታትን አስመልክቶ “እንደልቡ” የሚባለው ጀረሚ ቤንታም ባስነበበው “ኢንትሮዳክሽን ቱ ሌጅስሌሽን” መጽሐፉ ውስጥ ባሰፈረውና በሚያቀነቅነው ሄዶኒዝም ፍልስፍና “ዘ ግሬተስት ፕሌዠር ፎር ዘ ግሬተስት ነምበር፤ [ታላቁን ደስታ ለታላቁ ቁጥር መስጠት]” ይላል። ሃሳቡን በውል ስንበረብረው “ሕዝቡን ደስ የሚያሰኘው ነገር ካለ በባህልና በሃይማኖት ሳንተበተብ መብት የወለደውን ሃሴት ልናቀዳጀው ይገባል” ማለቱ ነው። ጆን ስቷርት ሚል በበኩሉ “ደስታ ተቆጥሮ ባግባቡ ካልተያዘ መረን የለቀቀ ትውልድ ይፈራል” ሲል ስጋቱን ይገልጻል፤ አያይዞም ለሃሳቡ አጽንኦት ሲሰጥ “ሶቅራጠስ ሳድነስ ግሬተር ዛን ፒግሚ ሃፒነስ፤ [የሶቅራጠስ መከፋት ከአሳማ ደስታ ይበልጣል]” ይላል።

በዚህ እሳቤ መሰረት የሀገራችንን ጥቂት የማይባሉ የኪነ ጥበብ ሥራዎችን በጀረሚ ጫማ ውስጥ ተደንቅረው እንታዘባለን። ከጃኖ ባንድ ሙዚቃዎች ውስጥ ዘላቂነትን ሳይሆን ወረትን የሚሰብከው

“መገኔ ጎጃም መገኔ ጎንደር፣

ባንዘልቅ እንኳን አብረን እንደር።”

የሚለው ስንኝ የሚገኝበት ሲሆን ይህም የቤንታምን “ሄዶኒዝም” ፍልስፍናን ያስተጋባል። “የዛሬን ተደሰቺ” አብነት አጎናፍር፣ “ነይ ማታ ማታ” አቤል ሙሉጌታ፣ “ላግኝሽ ማታ ማታ” ጃኪ ጎሲና ያልጠቀስናቸው በርከት ያሉ የሙዚቃ ሥራዎችም “የሄዶኒዝም” ጥላ ያረፈባቸው ናቸው።

እማማ ሽጉልቴ “ላግኝሽ ማታ ማታ” የሚለውን የጃኪ ጎሲን ዘፈን የሰሙ ወቅት “ጅብ ላህያ የጋበዘው መሆን አለበት?” ብለው እንደነበር አስታውሳለሁ።

ይህን በተመለከተ የሀገራችን የስነጽሁፍ መሰረቶች ማለትም ጋሼ ስብሃትን የመሰሉቱ “ጥበብ ለጥበባዊነት” ዳኛቸው ወርቁን የመሰሉቱ ደግሞ “ጥበብ ለተግባራዊነት” በሚል ጎራ ለይተው በሂስ አለብላቢት ሲጠዛጠዙ ኖረዋል። “ጥበብ ለጥበባዊነት” የሚሉቱ እንደጀረሚ ቤንታም ሁሉ “ተፈጥሮ ሳትሽሞነሞን እንደወረደ እርቃኗን መቅረብ አለባት” ይላሉ።

“ጥበብ ለተግባራዊነት” የሚሉቱ ደግሞ “ማህበራዊ ፋይዳ ተሸክሞ ማስተማር ካልቻለ መቅረብ የለበትም” ሲሉ የጆን ስቷርት ሚልን ሃሣብ ያራምዳሉ።

እንደጥጥ ፈታይ እንዝርት በሃሳብ ስሾር ቡናው ማክተሙን ብቻ ሳይሆን ጣእሙንም ሳላውቀው ገንዳው ተነሳና ከሄድኩበት ሰመመን የመለሰኝን የጥቁሩን የግዜር እንግዳ ጥያቄ አመነዥግ ገባሁ። “ይህን መለኛ የሚያናግረው ጠፍቶ ነው አቧራ የወረሰው?” አለ ግርግዳው ላይ የተሰቀለውን መሰንቆ እያስተዋለ። “በላይ ዘለቀን ጃንሆይ የሰቀሉት ለምንድነው?” አሉ በፈንታቸው። ስለማይችሉት ብዬ መልስ የመሰለኝን ሃሳብ ባቀብላቸው “እኔና ይህ መሰንቆም እንደዚያው ነን” አሉ እማማ ሽጉልቴ መኝታ እያሰናዱ።

አይገርማችሁም ጎበዝ! የሞተ የፈረስ ጭራ መሰንቆ ሆኖ በትዝታ ቅኝት ያረሰርሰናል፤ የሞተ ሸንበቆ ዋሽንት ሆኖ የሙዚቃ ጥማችንን ያረካናል፤ በሞተ በሬ ቆዳ ከበሮ ሠርተን ዳንኪራውን እናቀልጣለን፤ በሞቱ ጀግኖቻችንም አጥንትና ደም ነጻ ሀገር ወረስን፤ እና ጎበዝዬ! ከሞቱ ነገሮች እልፍ ቁምነገር አልገበየንም ትላላችሁ?

ሃብታሙ ባንታየሁ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 12 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You