
ሊቃውንት ቀለም በጥብጠው ብራና ፍቀው ጽሕፈትን በሚያሳልጡበት በዚያ ዘመን ዓይነ ስውሩ መምህር ኤስድሮስ በድም ጫማ እያነበቡ “የላይ ቤትና የታች ቤትን“ መፍጠሪያ ጽንሰ ሃሳብ ያፈለቁ የትርጓሜ ሊቅ ሲሆኑ፤ ንባብን በተመለከተ “እኛ እውሮች ካላነበብን ከዓይናችን እክል ላይ የልብ መታወርም ይገጥመንና ኑሯችንን ያከፋዋል” ሲሉ ማንበብ ምን ያህል ለልብ ብርሃንነት አበርክቶ እንዳለው ይገልጻሉ::
አለቃ አያሌውም “እማምላክ ኢትዮጵያ” በተሰኘው መጽሐፋቸው ውስጥ በጉልህ ያሰፈሩት ሃሳብ አላቸው:: ዓይነ-ስውር የተዘጋውን ቤት ውስጡን መፈተሽ የሚችለው በንባብ ነው:: ለዚህም ነው እሳቸው አብዝተው “እኔ ከምድር እስከጸራሪያም ድረስ ያየሁት በንባብ ነው” ማለታቸው።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ዮሐንስ ታከለ (ዶ/ር) ዓይነ-ስውርነትንና ንባብን አቆራኝተው በመድረኮችም በጽሑፍ ሥራዎቻቸውም የሚያነሱት፤ ንባብ ለዕለት ተዕለት ኑሯችን ቅንጦት ሳይሆን በመርሕ የዳበረ፣ በባህል የጎለበተ ብሎም የሕይወት መሠረትነቱ የማያሻማ የሕሊናችን ማገር፣ የሥነልቦናችን አጥር፣ የሞራላችን ምሰሶ መሆኑን ነው። “መጽሐፍት የሚጻፉት እንድናነባቸው ቢሆንም ቅሉ መቅድም ዓላማቸው ግን እኛ ራሳችን መጽሐፍ እንድንሆን ነው” ይላሉ ምሑሩ ሃሳባቸውን ሲቀጥሉም።
“ከቀደምት አበው አስተምሮት እንደተገነዘብነውና በኑረታችን እንዳረጋገጥነው የንባብና የእውቀት መንገድ ውጥኑ ከልብ የሚጀምር ሲሆን፤ በበርካታ ሳንካዎች ሰበብ ልባችንን ማንበብ ያቃተን እንደሆነ ተፈጥሮን ወደ ማንበብ እንሻገራለን፤ ተፈጥሮንም ማንበብ ቢሳነን መገለጥን ልብ እንበል፤ መገለጡም ባይገለጥልንና እሳቤያችን ቀንጭሮ እይታችን ተሸርሽሮ የቸገረን እንደሆነ የመጨረሻው ብልሃታችን መጽሐፍትን ማንበብ ነው:: ምክንያቱ ደግሞ ልብንም ተፈጥሮንም አዋሕዶ የያዘው መጽሐፍ ነው። ከዚህም የተነሳ ዓይነስውራን ረቂቁ እንዲጎላልን የራቀው እንዲቀርብልን ከንባብ የተፋታ የሕይወት ዘይቤ እንዳይኖረን የአደራ መልዕክቴ ነው” ይላሉ ከሕይወት ልምዳቸው ያለስስት እያካፈሉን።
እኔም ይህን አደራቸውን ይዤ በከተማችን ያሉት የሕዝብ ቤተ-መጽሐፍትን በቁጥራቸው ቀላል ለማይባሉና በማኅበረሰቡ ክፍል ውስጥ አንድ ክንፍ ለሆኑት ለዓይነስውራን ምቹ የማንበቢያ ከባቢ በመፍጠር ረገድ የሠሩትን ሥራ እፈትሽ ዘንድ በመሻት ከኢትዮጵያ ዓይነስውራን ብሔራዊ ማኅበር አጠገብ ከሚገኘውና በአዲስ አበባ ባህል ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ከሚተዳደረው የአዲስ አበባ ቤተ-መጽሐፍት ዘንድ ጎራ አልኩ። ገና ከቅጥር ግቢው ስደርስ ተርብ የሆኑት ጥበቃዎች ዓይነ-ስውራንን በፍቅር ተቀብለው ወደ ማንበቢያ ክፍላቸው ሲያደርሷቸው ስመለከት መልካም እንክብካቤ መኖሩን ከዓይነ-ስውራን ገጽ መረዳት ችያለሁና ከልቤ አክብሮት ቸርኳቸው።
የፀጥታው ድባብ ከነፋሻማው አየር ጋር ተዳምሮ ነፍስን ሐሴት አላብሶ “አንብብ አንብብ” ያሰኛል። በሰጠኋቸው ቀጠሮ መሠረት ወደውስጥ ስዘልቅ የቤተ-መጽሐፍቱ የመረጃ ሃብቶች አገልግሎት ቡድን መሪ አቶ አየናቸው ዘነበን አገኘኋቸው:: በትሕትና ተቀብለውኝም ወደ ጠባቧ ክፍል ገባን:: ጠባቧ ክፍል በመማሪያ የብሬል መጽሐፍት ተጠቅጥቃለች። የዓይነ-ስውራን ማንበቢያ ክፍል ማቋቋም ያስፈለገው ቤተ-መጽሐፍቱ ከማኅበራቸው ጎን ከመገኘቱ ጋር ተያይዞ እንደሆነና የብሬል መጽሐፍቱን ድጋፍ ያደረገላቸው ማኅበሩ እንደሆነም አያይዘው አነሱልኝ::
የመጽሐፍቱን የኅትመት እድሜ ከጀርባቸው ሳነብ ጊዜያቸው ራቅ ያለ በመሆኑ ሥርዓተ-ትምህርቱ ሲቀየር የተዘጋጁት አዳዲስ መጽሐፍት አልቀረቡላችሁም እንዴ? ስል ጥያቄ ሰነዘርኩላቸው። “ምንም እንኳን አጋዥነታቸው ቢታወቅም ለተጠቃሚዎች ወቅቱን ያማከለ መጽሐፍት ማቅረብ እንዳለብን ይሰማናል፤ ይሁን እንጂ የዓይነ-ስውራን መገልገያ ቁሳቁሶች በሽያጭ ደረጃ ውድ መሆናቸው ለሥራችን ትልቁ እንቅፋት ሆኖብናል:: ነገር ግን በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ የሚሠሩ ግብረ-ሠናይ ድርጅቶችን ከመንግሥት አቅም ጋር በማቀናጀት የተሻለ የማንበቢያ ክፍል ለማድረግ እየጣርን እንገኛለን” በማለት ገለጹልኝ።
በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዓመት የሕግ ተማሪ የሆነው ዳንኤል በላይነው ሲጠቀም አግኝቼው ስለቤተ-መጽሐፍቱ አገልግሎት አሰጣጥ ሃሳብ እንዲሰጠኝ የጠየኩት:: ቤተመጽሐፍቱን በተመለከተ ብዙ ሃሳቦችን አንስቶልኝ ነበርና ክፍሉን እያስጎበኙኝ ሳለ ጥያቄዎቹን ወደ ኃላፊው ዳግመኛ ሰነዘርኩ:: ይህም የኮምፒውተር ጉዳይ ነበር:: እርሳቸውም “ከብሬል መጽሐፍት አገልግሎት በተጨማሪ ባሉን ኮምፒውተሮች ላይ ጃውስ በመጫን የኢንተርኔት አገልግሎት ለመስጠት በዝግጅት ላይ እንገኛለን” ሲሉ አስረዱኝ። በድምፅ ለማንበብ የሚፈልግ ካለ የተሰናዳለት ክፍል ይኖራቸው ወይ ላልኳቸው ጥያቄ ይህን መልስ ሰጡኝ ‹‹እንደዚህ ዓይነት ፍላጎት ያላቸው ዓይነ-ስውራን ለጊዜው የሕጻናት ክፍሉ ባዶ ሲሆን ይጠቀማሉ:: ከዚያ ውጪ አገልግሎት የሚሰጥበት መንገድ የለም:: ለወደፊት ግን ታሳቢ ተደርጎ እየተሠራበት ይገኛል::››
ከሠራተኞች መሐል ሃሳቧን የተቀበልኳት አልማዝ ባየም ለዓይነ-ስውራን ምቹ የማንበቢያ ስፍራ ለማመቻቸት ከአቀባበል አንስቶ መልካም የሥራ መንፈስ አለ:: ይህንንም ተዟዙረን ስንመለከተው ያረጋገጥነው ነው:: ነገር ግን እኛም ሆንን ተጠቃሚዎቹ እንዲሁም አቶ አየናቸው ቤተመጽሐፍቱ ሙሉ እንዲሆንና ዓይነ-ስውራኑ የንባብ ባህላቸውን እንዲያጎለብቱ ድጋፎች ሊደረጉላቸው ግድ ይላልና በዚሁ አጋጣሚ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
ሃብታሙ ባንታየሁ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 12 ቀን 2017 ዓ.ም