
ፕሬዚዳንት ትራምፕ ወደ ዋይት ሐውስ ከተመለሱ በኋላ ለሦስተኛ ጊዜ ይሸጥ አሊያም ይታገድ የሚለውን ውሳኔ ለማራዘም መዘጋጀታቸውን ተከትሎ ቲክ ቶክ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ቢያንስ ለተጨማሪ ሦስት ወራት ሕልውናውን ጠብቆ ይኖራል። የዋይት ሐውስ የፕሬስ ሴክሬታሪ ካሮሊን ሌቪት ማክሰኞ እንደተናገሩት “ፕሬዚዳንት ትራምፕ ቲክ ቶክ እንዲቀጥል በዚህ ሳምንት ተጨማሪ የሥራ አስፈፃሚ ትዕዛዝ ይፈርማሉ” ብለዋል።
የቲክ ቶክ ባለቤት የሆነው የቻይናው ባይትዳንስ መተግበሪያውን እስካለፈው ጥር ድረስ በተቀመጠለት ቀነገደብ ለአሜሪካዊ ድርጅት ባለመሸጡ ተንቀሳቃሽ ምስሎች የሚጋሩበት መተግበሪያ በአሜሪካ መታገድ ነበረበት። ሌቪት ተጨማሪዎቹ 90 ቀናት “ነገሩ መቋጫ እንዲያገኝ እና አሜሪካውያን መረጃቸው አስተማማኝ እና ደኅንነቱ የተጠበቀ መሆኑን አውቀው ቲክ ቶክ መጠቀማቸውን እንዲቀጥሉ ያረጋግጣል” ብለዋል
ሌቪት ይህን ውሳኔ ከማስተዋወቃቸው በፊት ትራምፕ ቲክ ቶክን “ምናልባት” ሊያራዝሙት እንደሚችሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል። ትራምፕ “ምናልባት የቻይናን ይሁንታ ማግኘት ሊኖርብን ይችላል”፤ “እሱን የምናገኝ ይመስለኛል፤ ፕሬዚዳንት ዢ በመጨረሻ ያፀድቁታል ብዬ አስባለሁ” ብለዋል። ቀነ ገደቡን ለማራዘም የሚፈቅድላቸው የሕግ መሠረት ስለመኖሩ ለቀረበላቸው ጥያቄ “አለን” ሲሉ መልሰዋል።
የትራምፕ ቀነ ገደቡን የማራዘም ዕቅድ ባለፈው ዓመት በኮንግረስ ቲክ ቶክ እንዲሸጥ ወይም እንዲታገድ ከተወሰነው ውሳኔ ጋር ይቃረናል። ከትራምፕ በፊት ሥልጣን ላይ የነበሩት ጆ ባይደን ረቂቁን ሕግ አድርገው የፈረሙት ወዲያው ነበር። ሕጉ 170 ሚሊዮን አሜሪካውያን ተጠቃሚዎች ያሉት ቲክ ቶክ፣ ቻይና ለስለላ እና የፖለቲካ መጠቀሚያ መሣሪያ በማድረግ ልትጠቀምበት የምትችልበትን ስጋት ለመፍታት ያለመ ነው።
ትራምፕ ዋይት ሐውስን ከመርገጣቸው ጥቂት ቀደም ብሎ የሀገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የስር ፍርድ ቤት ጋር ተስማምቶ ሕጉን አጽንቶት ነበር። ከትራምፕ በዓለ ሲመት በፊት በሳምንቱ መጨረሻ መተግበሪያው ለሰዓታት ከአገልግሎት ውጭ ሆኖ ነበር። ቲክ ቶክ ዳግም ወደ አገልግሎት ከተመለሰ በኋላ ትራምፕ መተግበሪያውን በመታደጋቸው አሞግሷቸዋል።
ትራምፕ በመጀመሪያ የሥልጣን ዘመናቸው እኤአ በ2020 ቲክቶክን ለአንድ አሜሪካዊ ገዥ እንዲሸጥ ለማስገደድ ሞክረዋል። ነገር ግን ባለፈው ዓመት ትራምፕ እአአ በ2024 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንዲያሸንፉ እንደረዳቸው በማመን መድረኩን እንደወደዱት ተናግረዋል። ምንም እንኳን አብዛኛዎቹ ወጣት መራጮች የዴሞክራቲክ እጩ ካማላ ሃሪስን ቢደግፉም ትራምፕ በታኅሣሥ ወር ላይ “ለቲክቶክ በልቤ ውስጥ ሞቅ ያለ ቦታ አለኝ፣ ምክንያቱም የወጣቶችን ቀልብ በ34 በመቶ ገዝቻለሁ” ብለዋል።
የትራምፕ የአንድ ወገን የጊዜ ገደብ መራዘም አንዳንድ ተንታኞች በሥልጣን ዘመናቸው እገዳ ሊደረግ ይችላል የሚለውን ሀሳብ ውድቅ እንዲያደርጉ አስገድዷቸዋል። የፎርስተር ዋና ተንታኝ ኬልሲ ቺከርንግ “የምን እገዳ ነው? ስለ ቲክ ቶክ እገዳ ምንም ‘የሚመጣ’ ነገር የለም” ብሏል። ትራምፕ ቲክ ቶክ ክላውድ ኮምፕዩቲንግ ላይ ለሚሠራው እና ለረዥም ጊዜ ወዳጃቸው ላሪ ኤሊሰን ለተመሠረተው ግዙፉ ኦራክል ሲሸጥ ለማየት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ቢሊየነሩ ፍራንክ ማኮርት፣ ካናዳዊ ነጋዴ ኬቨን ኦሊሪ እና የሬዲት መሥራች አሌክሲስ ኦሃኒያን ቲክ ቶክን ለመግዛት ፍላጎት ካሳዩት መካከል ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በዓለም ላይ ትልቁ ዩቱዩበር ጂሚ ዶናልድሰን ወይም ‘ሚስተር ቢስት’ ቲክ ቶክን ለመግዛት ፍላጎት እንዳለው ተናግሯል ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው።
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 12 ቀን 2017 ዓ.ም