የእግር ኳሱ ባለውለታዎች የሚታሰቡበት ውድድር

የኢትዮጵያ እግር ኳስ የሚገኝበት ደረጃ ብዙዎችን የሚያበሳጭና የሚያስቆጣ ነው። ያም ሆኖ ኢትዮጵያ በአፍሪካ እግር ኳስ ትልቅ ዐሻራ ያኖረች ሀገር መሆኗን ስፖርቱ አሁን የሚገኝበት ዝቅተኛ ደረጃ ሊሽረው አይችልም። ለዚህም ኢትዮጵያ ብቸኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ስታነሳ ጀምሮ በየጊዜው ከሀገር አልፈው በአሕጉር አቀፍ ደረጃ ምስጉን ስም ያላቸው የእግር ኳስ ባለውለታዎችን ያፈራች ሀገር ነች። በተለያዩ ዘመናት በተጫዋችነት እንዲሁም በአሠልጣኝነት ትልቅ ታሪክ የሠሩ ኢትዮጵያውያን በርካታ ናቸው።

ጥቂት የማይባሉ ታሪካዊ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች ኑሯቸውን ባሕር ማዶ አድርገዋል። በርካቶች ደግሞ ከነመፈጠራቸው ተዘንግተው ችግር ውስጥ ሲገቡ እንዲሁም ሕይወታቸው የማለፉን ዜና ድንገት መስማት የተለመደ ነው። እነዚህ ታሪካዊ ከዋክብቶች በእግር ኳስ ዘመናቸው የሠሩት ጀብድ፣ የዋሉት ውለታ እንኳን ሊዘከርና ለአዲሱ ትውልድ እንዲተዋወቅ ማድረግ በቅጡ የተሰነደ ታሪካቸውን ማግኘት አዳጋች ነው። ሐውልት ሊቆምላቸውና አዲሱ ትውልድ የእነሱን ታሪክ አውቆ ተነሳሽነት እንዲፈጠርበት ለማድረግ የተሠራ ነገር ባለመኖሩ ብዙዎች ይቆጫሉ።

ሰሞኑን ግን ይህን ታሪክ ለመቀየር መነሻ የሚሆን አንድ ጉዳይ ተሰምቷል። ይህም ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ትልቅ አስተዋፅዖ አበርክተው ያለፉ የስፖርቱ ሰዎችን ለማስታወስ እና ለማመስገን ያለመ የመታሰቢያ ውድድር መዘጋጀቱን ሰሞኑን በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ ተደርጓል።

የጤና ቡድኖች ኅብረት የመታሰቢያ ውድድሩ አዘጋጅ ነው። ስለዚህ ታሪካዊ የእግር ኳስ ሰዎች የሚታሰቡበት ውድድር ዓላማ እንዲሁም ስለ ውድድሩ ቀጣይነት አዘጋጁ ባስረዳበት መግለጫ ውድድሩን በወጥነት በየዓመቱ ለማድረግ ስለመታሰቡ ተጠቁሟል።

በዘንድሮ ውድድር በርካታ ታሪካዊ የእግር ኳስ ሰዎች የሚታሰቡበት ነው። ከነዚህም መካከል ኢንስትራክተር መንግሥቱ ወርቁ፣ አሠልጣኝ አሥራት ኃይሌ፣ ሥዩም አባተ፣ ሐጎስ ደስታ፣ አስናቀ ደምሴ፣ አዳነ ገብረእየሱስ፣ ወንድምአገኝ ከበደ እና ጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ (ሊብሮ) ሲታሰቡ በቀጣይ የሌሎቹም እንደሚካተቱ ተገልጿል።

የኅብረቱ አባላት የአዲስ አበባ ስፖርት ቢሮ ትብብር እንዳደረገላቸው ገልፀው፣ የኢትዮ አፍሪካንስ ቡድን ተወካይ ሚካኤል ታደለ የጤና እንቅስቃሴ እየተደረገ የቀድሞ እግር ኳስ ባለውለታዎችን ማመስገን እና ማሰብ እንዲሁም አንዳንድ ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ ስለመታቀዱም ተናግሯል።

ሌላኛው የውድድሩ አስተባባሪ ፈቀደ ቲጋ በበኩሉ፣ ውድድሩ ከተሳታፊ ቡድኖች የመመዝገቢያ ገንዘብ በስተቀር ምንም አይነት ገቢ እንደሌለው ጠቁሞ፤ ውድድሩ ዓላማውን በሳተ መልኩ እንዳይሆን ገንዘብ ከማሰባሰብ እንቅስቃሴ መቆጠባቸውን አስረድቷል። ሆኖም ከተሳታፊ ቡድኖች በሚገኘው ገቢ ከወጪ ቀሪ ተሰልቶ ለቀድሞ ተጫዋች ፍቃዱ ተካ (ዶቃ) ፕሮጀክት የገንዘብ እና ኳስ ድጋፍ እንደሚውል ተናግሯል።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አምበል ንጉሤ ገብሬ በበኩሉ፣ ታላላቆችን ማክበር እና ማስታወስ ላይ በደንብ ሊሠራበት እንደሚገባ አስታውሷል። የቀድሞ ተጫዋች እንዲሁም አሁን የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የውድድር ቴክኒክ ኮሚቴ አባል በሀብቱ ገብረማርያም የውድድሩን ቀጣይነት ለመጠበቅ እንደሚሠሩ ተናግረው የሚመለከታቸው ሁሉ ለዓላማው ድጋፋቸውን እንዲያሳዩ ጥሪ አቅርበዋል።

ዘጠኝ የጤና ቡድኖች በሁለት ምድብ ተከፍለው እንደሚወዳደሩ የተገለፀ ሲሆን በምድብ “ሀ” ሻላ፣ ዓድዋ፣ ኢትዮ አፍሪካንስ፣ ፊኔክስ እና ኢትዮጵያ ቡና ሲሆኑ፤ በምድብ “ለ” አበበ ቢቂላ፣ ኢትዮ አዲስ፣ ኳስ ሜዳ እና መርካቶ ጤና ቡድን ተደልድለዋል። ውድድሩም ትናንት ስምንት ሰዓት ላይ በአበበ ቢቂላ ስቴዲየም ሻላ ከኢትዮ አፍሪካን ጤና ቡድን ባደ ረጉት ጨዋታ በይፋ ተጀም ሯል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 12 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You