የታላቁ የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያውን የውሃ ሙሌት 4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ሜትር ኩብ በመያዝ ተጠናቋል፡፡ እንደ አድዋ፣ ካራ ማራ፣ የታላቁ የህዳሴ ግድብ መሰረተ ድንጋይ እንደተጣለበት፣ የለውጥ ኃይሉ ወደ ስልጣን እንደመጣበት፣ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር በሰላም የኖቤል አሸናፊና ተሸላሚ እንደሆኑበት ዕለት ሀምሌ 15 ቀን 2012 ዓ.ም በኢትዮጵያ ታሪክ ልዩ ቀን ሆና በትውልድ ቅብብሎሽ ስትዘከርና ስትከበር ትኖራለች፡፡ የትውልዱም ገድል አብሮ ሲወሳ ይኖራል፡፡
በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመራር ግድቡ ገጥመውት የነበሩ ስር የሰደዱ ብልሹ አሰራሮች፣ ሙስናና ደካማ የኮንትራት አስተዳደር ተለይተው የእርምት እርምጃ መወሰዱ ታላቁን የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ከክሽፈትና ከለየለት ውድቀት ከመታደግ አልፎ ኢትዮጵያውያንን ለዚች ታሪካዊ ቀን አብቅቷል፡፡ በሴራ ፖለቲካ፣ በተላላኪውና በባንዳው በጣት በሚቆጠር የትህነግ ገዢ ቡድንና ተባባሪዎች ደባ በየዕለቱ ቅርጹንና ይዘቱ እየቀያየረ በሚቀፈቀፍ ቀውስ ውስጥ ኢትዮጵያውያን ተስፋ የሚያሰንቅ መልካም ዜና በናፈቃቸው በዚህ ቀውጢ ወቅት የመጀመሪያ ዙር ግድቡን ውሃ የማስያዝ ጥረት በስኬት የመጠናቀቁን ብስራት መስማት አሁን ከሚገኙበት ጥልቅ ድባቴና ቁዘማ አውጥቶ ለተሻለ ገድል የማነሳሳት ጉልበት አለው፡፡
ለለውጥ አመራሩም ትልቁን የኢትዮጵያንና የኢት ዮጵያውያን ስዕል እየተመለከተ ብልፅግናዋን እውን ለማድረግ አቅም ይሆነዋል፡፡ ቅኝ ካለመገዛት ጋር ብቻ ተያይዞ የነበረውን ነጻነትና ሉዓላዊነት በኢኮኖሚያዊ ብልፅግና ለመድገምም መስፈንጠሪያ ሰሌዳ ( ስፕሪንግቦርድ) በመሆን በድህነትና በተመፅዋችነት አንገታቸውን ደፍተው የነበሩ ዜጎች አንገታቸውን ቀና አድርገው በኩራት እንዲራመዱ የሚያደርግ ብሔራዊ ( ፍላግሺፕ )ፕሮጀክት ነው። ነጋድራስ ገብረህይወት ባይከዳኝ እንዳሉት በድህነትና በኋላ ቀርነት የሚማቅቅ ሕዝብ የተሟላ ሉዓላዊት ሊኖረው አይችልምና፡፡ ስንዴ እየለመኑ፣ እየተመጸወቱ ሉዓላዊነቷን ያላስደፈረች፤ በነጻነት ታፍራና ተከብራ የኖረች አገር ብሎ መመጻደቅን ምሉዕ አያደርገውም፡፡
የትህነግ እፉኝት ቡድን ለፖለቲካዊ ጥቅምና ስልጣን ሲል ወላጅ እናቱንም ሆነ ሀገሩን እንደ አስቆርቱ ይሁዳ ከመሸጥ አይመለስም፡፡ ለትህነግ ፖለቲካ ማለት ብሔራዊ ጥቅምን አስይዞ መገበያየት፣ የንግድ ውል መፈጣጠም (Transactional) ነው፡፡ በዚህ የልቦና ውቅር ( ማይንድሴት) ነው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ተሽጧል የሚለው፡፡
የአሜሪካውን ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በ”አሜሪካ ትቅደም! “መሰረት ላይ በመቀረጹ እና ትራምፕ ከዓለም አቀፍ የጸረ ሽብር ዘመቻ ግብዛዊ ማፈግፈግ በማድረጉ የተነሳ እንዲሁም ፊቱን ወደ አሜሪካ የውስጥ ጉዳይ በማዘሩ የኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታም ሆነ ጂኦፖለቲካዊ ስፍራ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ መፍጠሩ አልቀረም፡፡ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመራው የለውጥ ኃይል ወደ ኃላፊነት መጥቶ ፖለቲካዊ ምህዳሩን ከፊት ከፊት በማድረጉ ከኤርትራ ጋር የሰላም ስምምነት በመፈራረሙና ከ19 አመታት በኋላ እርቅን በማውረዱ፣ በአረንጓዴ አሻራ ከአራት ቢሊዮን በላይ ችግኞች እንዲተከሉ በሰጠው አመራር ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩም በሰላም የኖቤል ተሸላሚ በመሆናቸው በዓለምአቀፉ መድረክ እንደገና እንድታንሰራራ አስችሏታል፡፡
የአረቡ አለም የነዳጅ ባለቤት መሆኑ ከተረጋገጠ እኤአ በ1948 ዓ.ም እስራኤል የአይሁዶች መንግስት ሆና ከቆመች፣ ከ1993 ዓ.ም የመስከረም 1ቀን የሽብር ጥቃት በኋላ የአሜሪካ የምዕራባውያንና የዓለምአቀፍ ተቋማት የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ማጠንጠኛ ነዳጅ፣ የእስራኤል ደህንነት እና የጸረ ሽብር ዘመቻ ሆነ፡፡ ለእነዚህ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዎች እና ስትራቴጂዎች ተግብራዊነት ዳግም ከአረቡ አለም ግብፅ ቀዳሚዋ ስትራቴጂካዊ አጋር ሆና ተመርጣለች፡፡ ግብፅን ተመራጭ ያደረጋት ለምዕራባውያን የጡት ልጅ እስራኤል ጎረቤት መሆኗ ፤ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጧ በተለይ የስዊዝ ቦይ ባለቤት መሆኗ ፤ የእስላማዊ ትምህርት ማዕከል እና የአረብ ብሔርተኝነት አቀንቃኝ መሆኗ፤ ዜጎቿ ከሌላው የአረብ ዓለም ጋር ሲነጻጸር በዓለማዊም ሆነ በእስላማዊ ትምህርት የገፉ በመሆናቸው በምዕራባውያንም ሆነ በእስላማዊው ዓለም ዘንድ ሞገስ አግኝታለች፡፡ ይህን ሞገሷን የአረቡን አለም ጨምሮ የአረብ ሊግን እንዳሻት ለማሽከርከር ትጠቀምበታለች፡፡
በልዩነትና በክፍፍል የሚንጠራወዘው የአረቡ ዓለም ግብፅ ከፍ ብላ እንድትታይ ረድቷታል፡፡ ይህን መከፋፈል እስራኤልን ጨምሮ አሜሪካውያን ሆኑ ምዕራባውያን ይፋ ባያወጡትም የሚደግፉት ስለሆነ ግብፅ ሽብልቅ ሆና እንድታገለግል አሞሌ እያላሱ (ብድርና እርዳታ እየሰጡ) በአናቱ የጦር መሳሪያ እያስታጠቁና ወታደራዊ ስልጠና እየሰጡ ይንከባከቧታል፡፡ አሜሪካ ብቻ በየአመቱ በቢሊዮኖች የሚገመት የጦር መሳሪያ እርዳ ወታደራዊ እርዳታና የልማት ድጋፍ ታደርግላታለች፡፡
ግብፅ በአጸፋው ይህን ውለታ ከግምት ያስገባ እና እኤአ በ1979 በአንዋር ሳዳትና በእስራኤል መካከል የተፈረመውን የሰላም ስምምነት መሰረት ያደረገ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ቀርጻለች፡፡ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ፣ ደህንነትና ፖለቲካ በመዳፉ የጠቀለለው የግብፅ ጦርና ደህንነት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲን ተግባራዊነት ያረጋግጣል በዓይነ ቁራኛም ይከታተላል፡፡ ከአረቡ አብዮት በኋላ በምርጫ የፈርኦኖችን በትረ ስልጣን ጨብጠው የነበሩ የመጀመሪያው የእስላም ወድማማቾቹ አባል ፕሬዚዳንት ሞሐመድ ሙርሲ እንኳ የድርጅታቸውንም ሆነ አክራሪ እስላሞች ግፊት ተቋቁመው የግብፅና እስራኤልን የሰላም ስምምነት ማክበር ችለዋል። መጀመሪያ በመፈንቅለ መንግስት በኋላ በምርጫ ወደ መንበሩ የመጡት ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲም ከሳዳት፣ ከሙባረክና ከሙርሲ በላይ የሰላም ስምምነቱን እያስፈጸሙ ነው፡፡ የእስራኤል ጉዳይ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸው ቀኖና ነው ማለት ይቻላል፡፡ ከእስራኤል ጀርባ ደግሞ አሜሪካ አለች፡፡ ግብፅ ናይል የህልውናዬ ጉዳይ ነው ብላ በሕገ መንግስቷ ብታካትተውም በውስጠ ታዋቂ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ የማዕዘን ራስ ቢሆንም በግላጭ ትኩረቱ እስራኤል፣ ፍልስጤምና አሜሪካ ላይ ነው፡፡
ግብፅ አባይን ከምንጩ ለመቆጣጠር ፣ ሀገራችንን ቅኝ ለመግዛት እና ጠንካራ ሉዓላዊ ሀገር ሆና እንዳትወጣና ይህ ቀን (አባይ የተገደበበት ቀን ) እውን እንዳይሆን ከ11 ጊዜ በላይ ወራናለች ፡፡ በስውር ደግሞ ምን አልባት ለሺህ ወይም ለሚሊዮን አመታት አሲራለች፡፡ በተለይ ከ20ኛው ክ/ዘ ወዲህ ደግሞ በእነ ሶማሊያ ፣ ሱዳን ፣ ጀብሀ ፣ ሻዕቢያ ፣ ትህነግ ፣ ኦነግና የኦጋዴን ነጻ አውጭ በመጠቀም የውክልና ( proxy ) ጦርነት በማካሄድ ሀገራችንን ስታዳክም ኖራለች። ይህ እኩይ አላማዋ ከሞላ ጎደል በመሳካቱ የቤት ስራዋን በማጠናቀቋ ዝቅ አድርጋ ስታየን ኖራለች፡፡ ከታሪካዊዋ ሀምሌ 15 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ግን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሁኔታዎች ተቀይረዋል፡፡ በሴራና በደባ በቀጣናውም ሆነ በዓለምአቀፍ መድረክ ያሳጣችን ጂኦ ፖለቲካዊ እና ስትራቴጂካዊ ስፍራ ከ29 ዓመታት በኋላ መልሰን ተረክበናል፡፡ ምርኳችንም ተመልሷል፡፡
የቀጣናው ጂኦ ፖለቲካዊ አሰላለፍ በታላቁ የህዳሴ ግድብ እንደ አዲስ ተበይኗል የምለው ለዚህ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ የሀገራችን ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታና ጂኦ ፖለቲካዊ ስፍራ ከ1983 ዓ.ም በፊት ወደነበረው ከመመለሱ ባሻገር ከግብፅ የሚተናነስ አይደለም፡፡ታዋቂው የግሪክ የታሪክ ሰው ሔሮዶተስ እንዳለው ግብፅ የአባይ / የኢትዮጵያ / ስጦታ ሆነች፡፡ በተላላኪዋና በአስካሪሷ ትህነግ የተነጠቅነውን አንድነት ደግሞ በአጭር ጊዜ አስመልሰን ወደ ቀደመው ገናና ከፍታችን በኩራት እንመለሳለን፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ፈጣሪ አብዝቶ ይባርክ ! አሜን !
አዲስ ዘመን ሐምሌ 21/2012
በቁምላቸው አበበ ይማም ( ሞሼ ዳያን )