ላለፉት በርካታ ዘመናት አባይ በተረት፣ በስነቃል፣ በግጥምና በዜማ ሲወደስ ታላቅነቱ ሲነገር ቆይቷል። ይሁን እንጂ ይህን በጥበብ አቆላምጦ ታላቅነቱን የመግለፅ ያህል ደፈር ብሎ ቁልቁል ያለከልካይ እየተንጎማለለ የሚሄደውን ውሃ በመከተርና ለልማት የማዋሉ ሙከራ ለሺህ ዓመታት አልተሳካም ነበር። ድህነት ደግሞ ይህንኑ እድል ተጠቅሞ የኢትዮጵያውያንን ጎን ሲያደቅ፣ ለልመና እጅ ሲያዘረጋና በአሸናፊነት መንፈስ ኩሩው ኢትዮጵያዊ ላይ ሲፈነጭ ከራርሟል።
የህሊና ቁስል ትቶ የሚያልፍ ትዝታ በዚህ ትውልድ ላይ ሊያበቃ ዳር ዳር ማለቱ ደግሞ የዘመኑ እውነታ ነው። ሃይ ባይ አጥቶ የነበረው ታላቁ የአፍሪካ በረከት አባይ፤ ጉዞው ለልማት ከተገታ ዓመታት ተቆጠሩ። ዘንድሮ ደግሞ የድል ብስራት መጀመሪያ የሆነው የመጀመሪያው ዙር ሙሌት ያለፉከራና ቀረርቶ እጅግ አስደናቂ በሆነ መንገድ ተሞልቶ ተጠናቀቀ። ከባዶ ተስፋ ወደሚጨበጥ እውነታ አንድ እርምጃ ወደፊት ተሸጋገረ። ታሪክም የድል ጅማሮውን በምእራፍ አንድ ላይ መዘገበ።
አባይን ያጀገነው የኪነጥበብ ፋይዳ ቀደም ባሉት ዘመናት የኪነ ጥበብ ፋይዳ ብዙ መሆኑ ባይካድም የጠቢባኑ ኑሮ ግን ያን ያህል የሚያኮራና የሚወደድ አልነበረም። ምክንያቱ ደግሞ ጠቢባኑ መስጠትን እንጅ መቀበልን ከቁብ ሳይጥፉ ወደውና ፈቅደው ለመረጧት ጥበብ እጃቸውን በመስጠታቸው ከመቀበል ይልቅ መስጠትን ይመርጡ ነበርና ነው። በጥበብ ለመስጠት በጥበብ መሰጠትን የሚጠይቅ ሙያ በመሆኑ ሙያተኞቹም ከምንም ነገር በላይ ለሙያው ፍቅርን ነበር የሚያስቀድሙት። ለዚያም ነው ሙያተኞቹ በሰዎች አድናቆት ብቃታቸውን እየመዘኑ ከራሳቸው ኑሮ ይልቅ ለሌሎች ኖረው የሚያልፉት።
አሁን አሁን የጥበብ ባለሙያዎች በተለያዩ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ውስጥ በአምባሳደርነት በመሳተፍ የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርጉ ይስተዋላሉ።የበጎ አድራጎትና የልማት ድርጅት ሥራ ከሚመሩት ባለፈ ዋናዎቹ አምባሳደሮች በስራቸው የምናውቃቸውና የምናደንቃቸው የጥበብ ሰዎች ናቸው። ሁሌም በየማእከላቱ የሚረዱትን አረጋውያን፣ ወላጅ የሌላቸው ሕፃናትና ሴቶችን በሙያቸውና በገንዘባቸው ይደግፋሉ። በገቢ ማሰባሰቢያዎች ላይም ከማንም በፊት ቀድመው ከተፍ ይላሉ።
ድርጊቱ በቀላሉ የሚያመለክተን በሁሉም ዘርፍ ላይ የሚገኙ የጥበብ ባለሙያዎች ያላቸውን ተቀባይነት እና ተፅዕኖ ፈጣሪነት በትክክለኛው መንገድ እየተጠቀሙበት መሆኑን ነው። ዛሬ ለምናነሳው ቁልፍ ጉዳይ እንዲረዳን ብሎም ሃሳቡን በተጨባጭ ለመገንዘብ ከዚህ ቀደም ባጋጠሙ ችግሮች ላይ የጥበብ ቤተሰቡ ስኬታማ ተግባራት ምን ምን ነበሩ የሚለውን በጥቂቱ ለማንሳት እንሞክር።
ለትውስታ
ዛሬ ለሚደረገው ጥረት የትናንቱ ስኬት የሞራል ስንቅ ይሆናል። የጥበብ ባለሙያዎች እራሳቸውን ከመርዳት አልፈው ለህዝባቸው መኖር ከጀመሩ ሰነባብተዋል። የተለያዩ አሳሳቢ ጉዳዮች በገጠሙ ቁጥር ከፊት በመሰለፍ አጋርነታቸውን እያሳዩ ይገኛሉ። እየተደረገ ያለው ነገር ሙሉ ማለት ሳይሆን ጅምሩ እጅግ አመርቂ መሆኑን ለማሳየት ጭምር ነው።
ወደኋላ መለስ ብለን የጥበብ ቤተሰቡን ተሳትፎ ስናነሳ ቅድሚያ በህሊናችን ውስጥ የሚመጣው በህዳሴው ግድብ ላይ የተደረገው ተሳትፎ ነው። በርካቶች ዜጎች ከድህነት ይወጣ ዘንድ መተባበርና ግድቡን ከዳር ማድረስ አለበት ሲሉ አለኝታነታቸውን አሳይተዋል። ቀስቃሽ ኪነ ጥበባዊ፣ ስነጥበባዊና አስተማሪ መልዕክቶችን በጥበብ ስራዎቻቸው በማንሳት በጎ ምግባር ላይ ተሳትፈዋል።
ጥቂት ቢሆንም ጥበባዊ ስራዎቻቸውም ይህን መሰል ጉዳዮችን እንዲዳስስ በማድረግ ግንዛቤን ሲፈጥሩም አስተውለናል። የተለያዩ ማህበራዊ ቀውሶች ሲመጡ የጥበብ ቤተሰቡ አስመስጋኝ ስራዎችን ሰርቶ ከዜጎች ጎን እንደሚቆም አሳይቷል። ይህ የሚያመለክተው ማህበራዊ ግዴታን መወጣትና የሙያውን የመጨረሻ ግብ መረዳት ነው።
አዲስ ቃል ኪዳን
ባሳለፍነው ሳምንት ታላላቅ የጥበብ ሰዎች፣ ሙዚቀኞች፣ ሰዓሊያን፣ ፀሃፍት እንዲሁም በርከት ያሉ የጥበብ ባለሙያዎች በአንጋፋው የአገር ፍቅር ትያትር ቤት ተሰብስበው ነበር። በአንድ ስፍራ ያገናኛቸውም ጉዳይ ደግሞ ከሰሞኑ የኢትዮጵያውያንንም ሆነ ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ትኩረት ይዞ የሰነበተው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ወደ አዲስ ምዕራፍ መሸጋገር ነበር።
በዚህ የውይይት መድረክ ታዋቂው የአባይ ተፋሰስ ተደራዳሪ የሆኑት ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ በመገኘት ግድቡ የደረሰበትን ምዕራፍና በቀጣይ ሊሰሩ የታሰቡ የፕሮጀክቱ ክፍሎችን ለኪነጥበብ፣ ስነጥበብና ስነፅሁፍ ባለሙያዎቹ ገለፃ አድርገዋል። በተለይም ግድቡ ሲጠናቀቅ ለኢትዮጵያውያን ብልፅግና ያለው ፋይዳ ምን እንደሚመስል በሚገባ አብራርተዋል። ከዚህ ባሻገር የጥበብ ባለሙያዎች ድርሻ ምን መምሰል ይኖርበታል የሚለውን ጉዳይ በአስተያየት መልክ አስቀምጠዋል።
ዶክተር ያዕቆብ ባለፉት ጊዜያት ከታችኛው ተፋሰስ አገራት ጋር ሲደረግ የነበረውን የድርድር ሂደትና የተደረሰበትን ደረጃ ማብራራት ችለዋል። ግድቡ ለኢትዮጵያውያን እድገት የማይተካ ሚና ስላለው መንግስት ጠንካራ አቋም ይዞ የአገሪቷን መብት ለማስጠበቅ እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል። በተለይ በዚህ ዓመት የውሃ ሙሌት በስኬት መጀመሩን ከማብሰራቸው ባሻገር የህዳሴው ግድብ ተጠናቆ በሙሉ ኃይሉ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጨት ሲችል በዜጎች እድገትና ለኢትዮጵያ በቀጠናው የሚኖራትን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ የጎላ እንደሚያደርገው በስፋት አብራርተዋል። ይህን ሂደትም የጥበብ ባለሙያዎች ባላቸው ተሰጥዖና ህዝብን የማንቃት ኃላፊነት ተጠቅመው በርካታ ስራዎች መስራት እንደሚገባቸው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የጥበብ ባለሙያዎች በተገኙበት ሂደቱን ያብራሩት እውቁ የናይል ተፋሰስ ተደራዳሪው ዶክተር ያዕቆብ ‹‹የመጀመሪያው ዙር ውሃ ሙሌት 4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ነው›› በሚል ግድቡ የደረሰበትን ደረጃ ከማብራራታቸውም በላይ ለሱዳንና ግብፅ የሚኖረውን ፋይዳ አስረድተዋል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ የደረሰበትን ደረጃ በስፍራው ለተሰበሰቡ እውቅ የጥበብ ባለሙያዎች ዶክተር ያዕቆብ ገለፃ ካደረጉ በኋላ በሁሉም ሰው ላይ የድል አድራጊነትና የአሸናፊነት ስሜት ይነበብ ነበር። ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያውያን በሚያጋጥማቸው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ከፊት በመሰለፍ የተለያዩ ንቅናቄዎችን በመፍጠር የሚታወቁት እነዚህ ባለሙያዎችም በቀጣይ በግድቡ ዙሪያ ሊሰሩት ላሰቡት የተለያየ ስራም ከፍተኛ መነቃቃት እንደፈጠረላቸው በመድረኩ ላይ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። በተለይ ከዚህ ቀደም ከተሰሩ የጥበብ ስራዎች ላቅ ያለ በአይነቱ ልዩ ተግባርን ለማከናወን ቃል የገቡበት መድረክ ነበር።
የጥበብ ባለሙያዎች ቃል
በስፍራው ተገኝተው የህዳሴው ግድብ ወሳኝ ምእራፍ ላይ በመድረሱ ታላቅ የደስታ ስሜት እንደፈጠረባቸው ከገለፁት የጥበብ ቤተሰቦች መካከል ረዳት ፕሮፌሰር ሙሉጌታ ጀዋሬ ይገኝበታል። እንደ እርሱ ገለፃ፤ ግድቡ እውን እንዲሆን ሌት ተቀን የሚሰሩ ሰራተኞች፣ ተደራዳሪዎችና ሌሎች ቀጥተኛ ተሳታፊዎች ታላቅ ምስጋናና ድጋፍ ሊቸራቸው ይገባል። አሁን የደረሰበት ደረጃ መድረሱን በመስማቱ የላቀ የደስታ ስሜት ፈጥሮበታል።
እንደ ሙሉጌታ ሃሳብ ግድቡን እውን ለማድረግ ሁሉም ዜጋ ሃላፊነት አለበት። በተለየ መልኩ ደግሞ የጥበብ ቤተሰቡ ማህበረሰቡ የተፈጥሮ ሃብቱን በአግባቡ እንዲጠብቅና እንዲጠቀም፣ ባህሉንና ወጉን እንዲጠብቅ፣ ያለፉት አባቶች ያቆዩትን ጥበብ ጠብቆ በብልሃት እንዲገለገልበት የማስተባበር የማንቃት ሃላፊነት አለበት። ይህን ማድረግ ከተቻለ መጪው ትውልድ ኃላፊነት በመውሰድና ኢትዮጵያዊ ዘርፈ ብዙ ሃብቶችን በመጠበቅ ከዘመን ዘመን እንዲሸጋገር እንደሚሰራ ተናግሯል።
‹‹ይህ እውነት መሬት ላይ ወርዶ እንዲታይ ከኛ በላይ ኃላፊነት ያለበት የለም›› የሚለው ረዳት ፕሮፌሰሩ፤ ወጣቱ ትውልድ የህዳሴው ግድብ ከዳር እንዲደርስም ሆነ ኢትዮጵያዊ ማንነቱን የሚጠብቅ ታጋይ እንዲሆን አርቲስቱ የማስተማር ኃላፊነት እንዳለበት ተናግሯል።
በውይይቱ ላይ ተሳታፊ የነበረው አንጋፋውና እውቁ ሙዚቀኛ አረጋኸኝ ወራሽም የታላቁ ህዳሴ ግድብ የደረሰበት ወሳኝ ምዕራፍ በእጅጉ የደስታ ስሜት እንደፈጠረበት ተናግሯል። በተለይ የመጀመሪያው የውሃ ሙሌት እውን መሆኑን ሲሰማ ደስታው እጥፍ ድርብ እንደሆነ ከመግለፅ አልተቆጠበም። ተወዳጁ ሙዚቀኛ ጊዜው ከምንም በላይ መተባበርና አንድነት የሚያስፈልግበት በመሆኑ ሁሉም ዜጋ ይህን እውን ለማድረግ እንዲነሳ ጥሪውን አቅርቧል።
‹‹በዚህ ጊዜ አንድነት ከእኛ እርቋል። ህብረት ይጎለናል። የጋራ ማንነታችንንና ጥቅሞቻችንን እንዳናረጋግጥም እንቅፋት እየሆነብን ነው›› የሚል ጠንካራ መልዕክቱን ለሁሉም ኢትዮጵያውያን አስተላልፏል። ታዋቂው የፊልም ተዋናይ ይገረም ደጀኔ በበኩሉ ‹‹አሁን ሁሉም ኃላፊነቱን የመወጣት፤ ግዴታ ውስጥ የሚገባበት ግዜ ላይ ተደርሷል›› በማለት በተለይ የጥበብ ባለሙያው ከእስካሁኑ በተለየ መልኩ የፊት መስመሩ ላይ በመሰለፍ ማህበራዊ መነቃቃትና ግንዛቤ ማስጨበጥ እንደሚገባው አሳስቧል።
ይገረም ከላይ ካነሳነው ጠንካራ ሃሳብ ውጪ ግብፃውያን የአባይን ውሃ በመጠቀም ምን ያህል እንደበለፀጉ ስፍራው ድረስ ሄዶ መታዘቡን በውይይቱ ላይ ለተሳተፉ የጥበብ ባለሙያዎች አብራርቷል። ኢትዮጵያውያን ግን ለዘመናት የግብፅን ደጃፍ ሲያበለፅጉ መቆየታቸው አሁን ይሄ መብቃት እንዳለበትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት መረጋገጥ እንደሚገባም በቁጭት አንስቷል።
አንጋፋውና ተወዳጁ አያልነህ ሙላቱ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የደረሰበትን ምእራፍ በማስመልከት ስሜታቸውን ከገለፁት መካከል ነበሩ። በተለይ ከሁለት ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበርን በመወከል በግብፅ አገር የነበራቸውን ቆይታ አስታውሰው ሃሳባቸውን ይጀምራሉ።
‹‹በጊዜው ከግብፅ ደራሲያን ማህበር ጋር ተገናኝቼ በተወሰኑ ነጥቦች ላይ ውይይት አድርገን ነበር›› የሚሉት ፀሃፊ ተውኔት አያልነህ ፤ በተለይ በቆይታቸው የግብፅ ቤተ መጽሐፍትን የመጎብኘት እድል ባጋጠማቸው ሰዓት የቤተመጽሐፍቱ አስጎብኚ‹‹መጥፎ አጋጣሚ ሆኖ የግብፅ የመጀመሪያዎቹ ቅኝ ገዥዎች ኢትዮጵያውያን ነበሩ›› በሚል የተናገረችው ንግግር መቼም እንደማይረሱትና እንደሚያስገርማቸው ይናገራሉ። ግብፃውያን በተንኮል ድርጊት የተካኑ መሆናቸውን ለመገንዘብም በአገራቸው የአስዋንን ግድብ የገነቡት በቀድሞው የሜሮይ ስልጣኔ በነበረበት ስፍራ መሆኑን በማንሳትም በጊዜው የኢትዮጵያውያን ስልጣኔ ማሳያ የነበረውን ይህን ስፍራ በማጥፋት ውሃ እንደሞሉበት ያነሳሉ። አሁንም ድረስ በውሃው ውስጥ ትልቅ ኢትዮጵያዊ ቅርፅ መኖሩን ከተለያየ የታሪክ ድርሳናት መረዳታቸውንም ይናገራሉ። የፈርኦን መልክም የኢትዮጵያውያን እንጂ ከሌላ ስፍራ ፈልሰው የመጡ የአረቦች አለመሆኑን ታሪክ መዝግቦታል፡፡ የአባይ ወንዝ ግብፅም የኢትዮጵያውያን የስልጣኔ ማሳያ ስፍራ መሆኗን በቁጭት ተናግረዋል።
በሁለተኛ ደረጃ በቁጭት የሚያነሱት የሁለት መቶ ዓመታት ታሪክ የተሰራበት ሚሊኒየም ክብረ በዓልን አንድም የረባ የኪነ ጥበብ ስራ ሳይሰራ ማለፉ፤ ንጉሰ ነገስቱ ትልቅ አሻራ ያሳረፉበት የአፍሪካ ህብረት 50ኛ ዓመት ክብረ በዓልም የኢትዮጵያውያን የኪነ ጥበብ አሻራ ሳይነካው ማለፉን በቁጭት አንስተው የሚከተለውን ምክረ ሃሳብ ለአዲሱ ትውልድ አቀብለዋል።
ግብፆች የአስዋን ግድብን ሲገነቡ ‹‹አይዳ›› የሚል ኦፔራ መስራታቸውን በመግለፅ፤ ይህ የጥበብ ስራ ዓለምን ያንቀጠቀጠና እስካሁንም ድረስ በቢሊዮን የሚቆጠር ገቢ የሚገኝበት ስራ መሆኑን ፀሃፊ ተውኔት አያልነህ ይናገራሉ። ይህች የኢትዮጵያውያን ንግስት እንደግብፃዊ ተቆጥራ ግድባቸውን ሲገነቡ የጥበብ ማነቃቂያ አድርገው ኦፔራ ከሰሩ እኛ ኢትዮጵያውያን ምን ይጠበቅብናል? በማለት ጥያቄ የሚያጭር ሃሳብ ይሰነዝራሉ። እርሳቸውና የኢትዮጵያ የረቂቅ ሙዚቃ አባት ሙላቱ አስታጥቄ ይህን መሰል ስራ ለመስራት ከአራት አመት በፊት ለመንግስት ጥያቄ ቢያቀርቡም እስካሁን መልስ አለማግኘታቸውን አንስተው በኪነጥበብ መስክ እስካሁን በዚህ የግዝፈት መጠን ምንም አለመሰራቱ እንደሚያሳስባቸው ተናግረዋል።
‹‹በቀጣይ ሁሉም የጥበብ ባለሙያ በየዘርፉ ነቅቶ ታላቅ ስራ ማበርከት አለበት›› በማለት በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ከዚህ ቀደም ባልተሞከረ መልኩ ኪነጥበቡን ሊወክል የሚችል ግዙፍ ስራ መስራት እንደሚገባ በመናገር ሃሳባቸውን ቋጭተዋል።
በመጨረሻም
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ወሳኝ ምእራፍ ላይ መድረስ ተከትሎ ‹‹የጥበብ ባለሙያው ድርሻ ምን መሆን ይኖርበታል?›› በሚል የተሰናዳው ውይይትም ተወዳጅና አንጋፋ ባለሙያዎች የሰነዘሩትን ሃሳብ እንደ መሰረት መውሰድ ችሏል። ግድቡ ተሰርቶ እስኪጠናቀቅ ድረስ ተከታታይ፣ ማህበረሰቡን የሚያነቁ፣ ትውልዱን የሚያስተምሩ፤ በአንድነት መቆም፣ መበልፀግና ከምንም ነገር በላይ ለዘመናት ኢትዮጵያን ጨምድዶ ከያዛት ድህነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መላቀቅ የሚዳስሱ ስራዎች ለመስራት መግባባት ተችሏል። ታላላቅ የየኪነ ጥበብ፣ ስነፅሁፍ፣ ስነ ጥበብ እንዲሁም መሰል አንቂ ስራዎችን በአንድነት ለመስራት ቃልኪዳን በመግባትም መቋጫውን አግኝቷል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 19 ቀን 2012 ዓ.ም
በዳግም ከበደ