በንዴት ላይ ጥናት እንዳደረገው የሥነልቦና ምሁር ቻርለስ ስፒል በርገር ንዴት ማለት ስሜታዊ ክስተት ሲሆን ከመጠነኛ እስከ ከፍተኛ ደረጃ የሚደርስ ነው። እንደ ሌሎቹ ስሜታዊ ክስተቶች ለምሳሌ ውጥረት፣ ደስታ፣ ሀዘን ….ወዘተ ንዴት በአካላዊ እና ስነልቦናዊ ለውጦች የታገዘ ነው፤ አንድ ሰው ንዴት ውስጥ የሚገባው ንዴት አምጪ ለሆነው ገፊ ነገር ምክንያት ሲሆን በዚህ ጊዜ ኤፒነፍሪን (Epinephrine) ወይም አድሪናሊን (Adrenaline) እና ኖርኤፒነፍሪን (Norepinephrine) ወይም ኖርአድሪናሊን (Noradrenaline) የተባሉ ኬሚካላዊ ንጥረ ነገሮች (ሆርሞን) መጠን ማሻቀብን ያስከትላል። ይህም ፈጣን የልብ ምት፣ የደም ዝውውር መጨመር፣ ፈጣን የአተነፋፈስ ሁኔታዎች፣ የሰውነት ሙቀት ይጨምራል።
ንዴት በውጫዊ እና ውስጣዊ ምክንያቶች ሊከሰት ይችላል። ለምሳሌ፡- ለተወሰነ ሰው (የስራ ባልደረባ፣ አሊያም የቅርብ አለቃ…ወዘተ)፣ ለተወሰነ ክስተት (የትራፊክ መጨናነቅ አሊያም የአውሮፕላን በረራ መሰረዝ…ወዘተ)፣ የሚረብሹን የኋላ ታሪክ ትውስታዎች ወይም አስፈሪ ክስተቶች፣ ወይም በግላዊ ችግር መረበሽ እና መጨነቅ የንዴትን ስሜት ሊቀሰቅሱ ይችላሉ።
ንዴትን መግለጽ
ሰዎች ንዴትን ለመግለጽ የተለያዩ መንገዶችን ይጠቀማሉ። ከነዚህም ውስጥ ሶስት ዋና ዋና ገጽታዎች ሲኖሩ እነሱም፡- ንዴትን መግለጽ፣ ንዴትን ማመቅ፣ ንዴትን ማረጋጋት ናቸው።
የንዴት አገላለጽ ግልፍተኝነት ያልታከለበትና ጤናማ የሆነ የንዴት አገላለጽ ሲሆን፤ ይህንን ለማድረግ አንድ ሰው ስኬትና ውድቀት፣ ፍቅርና ጥላቻ፣ እርጋታና ንዴት… ወዘተ በቀን ተቀን ህይወት ሊያጋጥመው እንደሚችል በግልጽ ማወቅ መቻል አለበት። ይህም የሚረዳን ነው።
ንዴት ሊታመቅ እና ራሱንም ሊለውጥ ይችላል። ይህ የሚከሰተው ግለሰቡ የንዴት ስሜትን ደብቆ ሲይዝ እና ስለ ንዴቱ ማሰብ አቁሞ አዎንታዊ ነገር ላይ ማተኮር በሚጀምር ወቅት ነው። ይህም ዓላማው ንዴትን አምቆ ወደ ሌላ የተረጋጋ እና አዎንታዊ ባህሪ ለመለወጥ ሲፈለግ ነው። የእንዲህ አይነቱ ምላሽ አደገኝነት ደግሞ ንዴቱ ወደ ውጪ እንዲወጣ (እንዲገለጽ) ካልተፈቀደለት ራስን ሊጎዳ ይችላል። በዚህም እንደ ደም ግፊት፣ ከፍተኛ የልብ ህመም እና ድብርት ሊፈጥር ይችላል።
ንዴትን ማረጋጋት ሌላው ንዴትን የመግለጫ መንገድ ነው። ንዴትን ውስጣችን በሚፈጠር አካላዊም ሆነ ስነልቦናዊ ምላሽ ልንቆጣጠረው እንችላለን ይህም የሚሆነው የልብ ምትን ደረጃ በደረጃ እንዲቀንስ በማድረግ ራስን አረጋግቶ ማየት እና ፍላጎትን በመግታት ነው።
ንዴትን መቆጣጠር
ንዴትን መቆጣጠር ዓላማው ስሜታዊ እና ስነአካላዊ ንዴት አምጪ ሁኔታዎችን መቀነስ ነው። አንዱና ዋናው የንዴት መገለጫ ግለሰቡን ከቁጥጥር ውጪ እና ግብታዊ ማድረግ ነው። ንዴት መቆጣጠር ማለት ንዴትን ማስወገድ ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ንዴትን ለእኛ በሚጠቅም መልኩ ማስተማሪያ ማድረግ ማለት ነው። በተጨማሪም ንዴትን መቆጣጠር ማለት ንዴትን እንዴት በአዎንታዊ መልኩ መግለጽ እንደምንችል፣ ንዴት ሊፈጥር የሚችለውን ችግርም ቀድመን መረዳት እና ንዴቱ ከተከሰተም የሚያጋጥመንን አካላዊና አእምሮአዊ ተጽእኖ ለመፍታት የሚያስችለንን ክህሎት የምናዳብርበት ዘዴ ነው። ንዴት ያስከተለብንን ሁኔታዎች ማራቅ አሊያም ማስወገድ ወይም መለወጥ አንችልም። ከዚህ ይልቅ ድርጊቶቻችን ንዴትን እንዳያስከትሉብን ልንማርባቸው ይገባል። ንዴት በህይወታችን ላይ ጉዳት እንዳያደርስብን የተለያዩ የንዴት መቆጣጠሪያ ዘዴዎች መጠቀም እንችላለን፤ ከዚህ በታች የተጠቀሱት መንገዶችም ይመከራሉ።
ጊዜ አለመስጠት
ይህ ዘዴ ንዴት ካመጣብን ሁኔታ ወይም ክስተት (ለምሳሌ ግለሰብ፣ ቁስ…ወዘተ) ለጥቂት ጊዜ ራስን ማራቅ ለምሳሌ ራቅ ብሎ ረጋ ያለ የእግር ጉዞ ማድረግ፣ ወደ ሌላ ክፍል መዛወር፣ በጥልቀት ወደ ውስጥ ዝም ብሎ መተንፈስ እና ለንዴቱ ምንጭ ምላሽ ከመስጠት ጥቂት መዘግየት ናቸው።
አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ
ይህ እንቅስቃሴ ውጤታማ የሚሆነው ያናደደንን ነገር እያሰብን የምንጀምር ከሆነ ነው። የአካል እንቅስቃሴ እንደ ውጥረት፣ ንዴት፣ ጭንቀት የመሳሰሉትን አሉታዊ ስሜቶች ለማስወገድ ትልቅ መፍትሄ ነው። ከንዴት መከላከያ የአካል እንቅስቃሴዎች መካከል ፈጠን ፈጠን ያለ እግር ጉዞ ማድረግ፣ ቴኒስ መጫወት፣ የውሃ ዋና፣ ሩጫ፣ ክብደት ማንሳት እና የቅርጫት ኳስ ጨዋታ ማዘውተር ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
ራስን ለማረጋጋት ጊዜ መውሰድ
የሰው ልጅ ተፈጥሮ እና ባህሪ እንደሚለያይ ሁሉ ሰዎች የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ንዴትን ይቆጣጠራሉ። ለምሳሌ ዘና ማለት፣ ያናደዳቸውን ነገር ከሃሳባቸው ለማውጣት አጫጭር ፅሁፎች፣ ግጥሞች ማንበብ፣ የሚወዱትን መዝሙር ወይም ሙዚቃ ማድመጥ፣ ፊልሞች፣ ቴአትሮች፣ ኮሜዲዎችን (አስቂኝ ቀልዶች)፣…ወዘተ መመልከት፣ የሚያዝናናቸውን ፕሮግራሞች መከታተል፣ መጽሀፍ ቅዱስ ማንበብ፣ ቅዱስ ቁርአን መቅራት፣ ልዩ ተሰጥኦ ካላቸውም እሱን መተግበር ወይም እንደ ዮጋ እና የተመስጦ ቴክኒኮችን በመጠቀም የንዴቱን ጊዜ ያሳልፉታል።
ለቀልዶችና ጭውውቶች ጊዜ መፍቀድ
ቀልድ ስኬታማ የንዴት ማቃለያ ወይም ማስወገጃ ዘዴ ነው። በቀላሉ የሚያዝናናን ቀልድ ማሰብ አሊያም ራስንና ሌላን ሰው በቀላሉ በሚያስቅ ሁኔታ ውስጥ አድርጎ በማለም ከገጠመን ወቅታዊ ንዴት ሃሳባችንን እንድናርቅ ያደርገናል።
ፈጣሪን ማሰብ
ይህ ዘዴ በፈጣሪ ህልውና በማያምኑ ሰዎች ላይ ሊሰራ ባይችልም፣ በፈጣሪ ላይ እምነት ላላቸው እና የአምላክ ፍጥረትን መውደድ በማስታወስ ብርታትን እንድንጨምርና ያጋጠመንን ጊዜያዊ ንዴት እንድንሻገር የሚያስችለን ነው። ይህም ተግቶ ወደ ፈጣሪ በመፀለይ እና በመጠጋት ነው ሊተገበር የሚችለው።
ውጤቱን ማሰብ
ይህን ዘዴ ንዴት በያዘን ሰዓት ለመተግበር በጣም ከባድ ነው ምክንያቱም በምንናደድበት ወቅት ንዴቱ ስለሚያመጣው አሉታዊ ውጤት እና ስለ ምንም ነገር ግድ ላይለን ይችላል። ነገር ግን ንዴት ስለሚያመጣው ውጤት ማሰብ ከባድ እና ከግምት ውስጥ ባናስገባውም በጣም ስለምንወደውና ስለምናፈቅረው ሰው ማሰብ ንዴቱ ስለሚያስከትለው የመጨረሻ ውጤት አሉታዊነትን አጉልቶልን ልንረጋጋ እንችላለን።
አንድ መቶ /100/ ያህል ቁጥር መቁጠር
ይህ ቀመር ብዙ ዘመናትን ያስቆጠረ እና ስኬታማ የንዴት መቆጣጠሪያ ዘዴ ነው። አካሄዱም በአካባቢያችን ያሉትን ማናቸውንም ነገሮች ከትኩረት ውጪ አድርጎ፤ ከአንድ ጀምሮ ቁጥር መጥራት፤ የቁጥሩም ማቆሚያ 100 ሲሆን እስኪደክመን ድረስ ልንቆጥርም እንችላለን። የአቆጣጠሩንም ሂደት ጣታችንን በመጠቀም ሊሆን ይችላል። ይህም ዘዴ ንዴትን በማርገብ በጣም ስኬታማ ነው።
ንዴትን እንደያዙ ማቆየት
ንዴት ወዲያውኑ ላለመግለፅ ጊዜ መስጠት እና ማሳለፍ በጣም ወሳኝ ክህሎት ነው። በተጨማሪም በድካምና ባለመረጋጋት ጊዜያት ንዴት ነክ ስለሆኑ ክስተቶች አለመወያየት ይመረጣል። ለንዴት ነክ ችግሮች መፍትሄ ለመሻት ጊዜን መምረጥ እና ምቾት ውስጥ መኖርን ማረጋገጥ እንዲሁም ምክንያታዊ የሆነ እሳቤን ማዳበር ስኬታማ ያደርጋል።
ለንዴት ምላሽ አለመስጠት
የንዴት አስተዳደር ዘዴ ዋናው ዓላማ ለንዴት ምላሽ የምንሰጥበትን የአስተሳሰብ መንገድ መለወጥ ነው። ለንዴት ምላሽ መስጠት በተፈጥሮ እና በአካባቢያዊ አስተምህሮት የሚመጣ ደመነፍሳዊ /Instinctive/ የሰው ልጅ ባህሪ ነው። በመጀመሪያ ያናደዱንን ነገሮችና እየተናደድን እንደሆነ መገንዘብ ወይም የንዴት ምልክቶችን ለይቶ ማወቅ ንዴትን በማዘግየት የተለያዩ መፍትሄዎች እንድናስብ እና አሉታዊ ስሜቱ እኛን በማይጎዳ መልኩ በእርጋታ በማስወገድ ጤናችንን እንዳንጎዳ እድል ይፈጥርልናል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 17/2012
ወርቅነህ ከበደ