በተለያዩ አገራት የሚገኙ ታዋቂ ህንፃዎችን ስንመለከት በተገነቡበት ወቅት የነበሩ ታሪኮችና ባህሎችን እንድናስታውስ ያደርገናል፡፡ዛሬም ዘመናቸውን የሚገልጹ ዲዛይኖች የታከሉባቸው ግንባታዎች በስፋት ይስተዋላሉ።የአንድ ማህበረሰብ የእድገት ደረጃ ፣አለባበስ ፣የሚጠቀምባቸው ቁሳቁስ በአጠቃላይ አኗኗር በሚገነባቸው ዋሻዎች፣ ቤቶች፣ህንፃዎች ዲዛይን ውስጥ ሲንጸባረቁ ቆይተዋል፡፡እነዚህ ዲዛይኖች እንደተመልካቹ ልዩነት ቢኖርም ቀልብን በመሳብ ይታወሳሉ።በዛሬው እትማችን በአለም ላይ የሰዎችን ቀልብ የሚስቡ የህንፃ ዲዛይኖችን ከተላበሱ ግንባታዎች የተወሰኑትን እንመልከት።
ሳጋርዳ ፋሚላ ባርሴሎና
አንቶኒ ጉአዲስ ሳጋርዳ ፋሚላ በመባል የሚታወቀው ህንፃ ግንባታ የተጀመረው እኤአ 1882 ሲሆን፣ ግንባታው ተጠናቋል ተብሎ ከ130 ዓመት በኋላ ይፋ ቢደረግም አሁንም ድረስ የግንባታው 70 በመቶ ብቻ ነው የተጠናቀቀው።በቅርቡም ህንፃውን ለማጠናቀቅ ፈቃድ ለማግኘት እንቅስቃሴ የተጀመረ ሲሆን፣ እኤአ 2026 ላይ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።በስፔይን ወይም ካታላን አርክቴክት አንቶኒ ጋውዲ ዲዛይን የተሰራለት የዚህ ህንጻ የዲዛይን ስራዎች በዪኔስኮ ጭምር ተመዝግበዋል፡፡
ዲዛይኑ የጎቲክ እና የህንጻው ግንባታ የተጀመረው እኤአ 1882 መጋቢት ወር በአርክቴክት ፍራንሲስኮ ዴ ፓውላ ዴል ቪላር ሲሆን፣ የኩርቪሊኒያር አርት ኖቪው ጥበቦች የተንጻባረቁበት መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡የህንጻው ዲዛይን ቀደምት አርክቴክት ጋውዲ ህይወቱን ሙሉ ለህንጻው ፕሮጀክት የሰጠ መሆኑን ታሳቢ በማድረግም እኤአ በ1926 ከዚህ አለም በሞት ሲለይ በህንጻው ምድር ቤት አስከሬኑ እንዲያርፍም ተደርጓል፡፡
ህንጻው በ1936 አብዮተኞች በቀሰቀሱት ነውጥ ሳቢያ ለቃጠሎ የተዳረገ ከመሆኑም በተጨማሪ የአርክቴክቱን ውብ አሻራዎች እስከ መውደም ደርሰውም ነበር፤የአርክቴክቱን የስእል ፣የፕላስተር እና የመሳሰሉትን ጥበቦች መልሶ ቦታው ላይ ለማኖርም አስራ ስድስት አመታትን ወስዷል፡፡
ሀይደር አሊይቭ ሴንተር ባኩ
የሀይደር አሊይቭ ሴንተር ባኩ ህንጻ የሚገኘው በአዛርባጃን ባኩ ከተማ ነው።የሕንጻው ንድፍ የተሰራው በኢራቅ እንግሊዛዊ አርክቴክት ዛሃ ሀዲዲ ነው።የንድፍ ስራው አዲስ መንገድን የተከተለ ሲሆን፣ ግንባታውም እአአ 2012 ነው የተጠናቀቀው።የንድፍ ስራው የህንፃው አወራረድና የተጠቀማቸው ስእል መሰል መስታወቶች ይበልጥ ውበት ሰጥተውታል።ዛሃ ሀዲድ እኤአ 2007 በተካሄደው የንድፍ ስራ ውድድር በዚህ ህንጻ ንድፍ ስራው ተሸላሚ መሆን ችሏል።ከሽልማቱ በኋላ ሀዲድ ፤ የህንጻውን ንድፍ የሰራው በአለም ልዩና ሊረሳ የማይችል የህንጻ ዲዛይን እንዲኖር አስቦ መሆኑን ገልጧል፡፡
የባርሲላ ካቴድራል
በብራዚል የሚገኘው የብራሲላ ካቴድራል ግማሽ ቅርፅ ያለው ሲሆን ውስጡና ውጪው በመስታወት የተዋበ ነው።እኤአ ከ1958 እስከ 1970 ንድፉ በኦስካር ኒሚየርና ሉኮ ኮስታ የተሰራ ነበር።አርክቴክቶቹ ለካቴድራሉ ቀደም ብለው ሌላ ንድፍ ያስገቡ ቢሆንም ውድቅ ስለተደረገባቸው አሁን በህንጻው ላይ የሚታየውን ንድፍ ለመስራት ችለዋል፡፡
ሀይፓ ኮንክሪት ሄል ሪያክጃቪካ
ሀይፓ ኮንክሪት ሄል በሪያክጃቪካ የሚገኝ ሲሆን የንድፍ ስራው የተከናወነው በኦላፍር ኢላሶን እንዲሁም ሀኒንግ ደላርሰን ነው።ህንጻው ውጫዊ ክፍሉ በመብራት የተጌጠ ሲሆን ፣መብራቱ ሰዎች ወደ ህንጻው ሲገቡ ልዩ ስሜት እንዲላበሱ ያደርጋል።በህንፃው ውስጥ የተለያዩ ቅርፃቅርፆችና ሀውልቶች የሚገኙ ሲሆን፣ እያንዳንዱ ክፍልም በስዕል ያሸበረቀ ነው፡፡
ሚላዋኪ አርት ሙዚየም
የማላዋኪ አርት ሙዚየም ሶስት ህንፃዎችን የያዘና የንድፍ ስራ ውሃ ልክ ተደርጎ ይወሰዳል።እኤአ 1957 የጦርነት ቦታ የነበረው ህንፃ ንድፉ የተሰራው በኢሮ ሳራኒ ቢሂንም የካህለር ህንፃ እኤአ 1975 በዴቪድ ካህለርና ኳድራሲ ፓቪዎን እንዲሁም እኤአ 2001 በሳንቲያጎ ካላትራቫ ለውጥ ተደርጎለታል።ሚሺጋን ሐይቅን በመመልከት፣ በቀጥታ ከዊስኮንሲን ጎዳና በኬብል መንገድ ተገናኝቷል።እግረኞች የሊንከንን የመታሰቢያ ስፍራ በድልድዩ ላይ ማቋረጥ ወደ ስፍራው መጓዝ ይችላሉ፡፡መኪናዎች በሙዚየሙ በተዘጋጀ መኪና ማቆሚያ ሲገቡ የ ቪ ቅርፅ ይዘው እንዲቆሙ የሚያደርግ አሰራር አለው፡፡
ፎርቢድን ሲቲ ቤጂንግ
እኤአ 1406 እስከ 1420 እንደተገነባ የሚነገርለት የፎርቢድን ሲቲ በቤጂንግ ከተማ ከሚገኙ ታዋቂ ግንባታዎች አንዱ ነው።ፎርቢድን ሲቲ ከሚንግ ስርወ መንግስት እስከ ኪዊንግ ስርወ መንግስት ድረስ ለነገስታት መኖሪያነት ያገለገለ ነው።ቦታው ለግማሽ ሚኒሊየም የቻይና ፖለቲካ ማዕከል በመሆን አገልግሏል።
የቀድሞ የነገስታት መኖሪያ የነበረው ስፍራ አሁን ሙዚየም ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።ቦታው እኤአ 1987 ላይ አለም አቀፍ የቱሪስት መዳረሻና ቅርስ እንዲሆን ተመዝግቧል። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፥ የሳይንስ እና የባሕል ተቋም(ዩኔስኮ) ፎርቢድን ሲቲን በእንጨት የተገነባ ትልቅ ቤተመንግስት በሚል እውቅና የሰጠው ሲሆን እኤአ ከ2016 ጀምሮ ቦታን በዓመት 16 ሚሊዮን ሰዎች የሚጎበኙት ሲሆን በቀን 40 ሺህ ሰዎች ቦታውን ያያሉ፡፡
ደናሹ ቤት ፕራጉ
ደናሹ ቤት በሚል ቅፅል ስም የሚታወቀው በፕራጉ የሚገኘው ብሄራዊ ኔዳርላንድ ህንፃ ንድፍ የተሰራው በቫልዶ ሚሉኒክ እና በፍራንክ ግሬህ ነው።ህንጻው ከንድፍ ጀምሮ ሲሰራ የሚደንስ አይነት ቅርፅ እንዲይዝ ተደርጎ ነው።በውስጡ 99 ቋሚ ኮንክሪቶች ያሉት ሲሆን እያንዳንዱ የተለያየ ቅርፅና አቋቋም አላቸው።ህንጻውን ለመጎብኘት ሁለት ሺህ የቼክ ኮሩና ኮይን ያስከፍላል፡፡
የዲጅኒ ታላቁ መስኪድ ዲጅኒ
በማሊ የሚገኘው መስኪድ ከአፍሪካ በዲዛይኑ በግንባር ቀደምትነቱ ይጠቀሳል።መስኪዱ ከክርስቶስ ልደት በኋላ 1200 ጀምሮ መገንባቱ ይነገራል።አሁን ያለውን ዲዛይን ይዞ ድጋሚ እንዲሰራ የተደረገው እአአ 1907 ላይ ነው።አሁን ያለው ንድፍ እንዲመረጥ ያደረገችው ፈረንሳይ ብትሆንም በወቅቱ ማሊ ከፈረንሳይ ቅኝ ግዥ ውጭ ነበረች።የመስኪዱ ግንባታ ከጭቃ ጡብ የተገነባ ሲሆን በፀሀይ ሙቀት እንዲደርቅ ተደርጓል።በተጨማሪም ከአሸዋ በተሰራ ጭቃም እንዲለሰን ተደርጓል።በዓመት አንዱ የዲጂኒ ነዋሪዎች ክብረ በዓል በማዘጋጀት መስኪዱ የሚያስፈልገውን ጥገና ያደርጉለታል።መስኪዱ ለማሊ ለቱሪስት መስህብነት ከፍተኛ ገቢ እያስገኘላት ነው፡፡
ሎቱ ቴምፕል ኒውደልሂ
የሎቱስ ቴምፕል በኒውደልሂ የሚገኝ ሲሆን ቦታው ከአምልኮነት እያገለገለ የሚገኝ ነው።ቴምፕሉ 40 ሜትር ከፍታ ያለው ሲሆን 27 ቋሚዎች አሉት። ዘጠኝ ጎኖች፣ ዘጠኝ በሮችና ሁለት ሺህ 500 ሰዎች የመያዝ አቅም አለው።የቴምፕ ወለል በነጭ እምነበረድ ያጌጠና እምነ በረዱ ከግሪክ የመጣ ነው፡፡እኤአ 1986 በተደረገ ውድድር ቴምፕሉ በጎብኚዎች ቁጥር የመጀመሪያ ደረጃን ይዞም ነበር።በወቅቱ መቶ ሚሊዮን ሰዎች ቦታውን እንደጎበኙት ይነገራል፡፡
አዲስ ዘመን ሐምሌ 14/2012
መርድ ክፍሉ