መንገድ የየእለት ኑሮን፣ልማት እና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎችን ከሚያቀላጥፉ መሰረተ ልማቶች አንዱ ነው።ወደ ስራ ለመሄድ፣ ምርትን፣ የምርት ግብአትን፣ የኢንዱስትሪ ውጤቶችን፣ ወዘተ ለማጓጓዝ ጥራት ያለው መንገድ አስፈላጊነት ችላ ሊባል አይገባም።የመንገድ መሰረተ ልማት ለሀገር ኢኮኖሚ ፣ማህበራዊና ፓለቲካዊ እንቅስቃሴ ወሳኝ ሚና ይጫወታል፡፡
የመንገድ መሰረተ ልማት የሚፈለግበትን እንዲወጣ ለማድረግ የዘርፉ በተለይም የመንገድ ግንባታ ፈጠራ ስራዎች ያስፈልጋሉ፡፡እስከ አሁን በዘርፉ የተካሄዱ ፈጠራዎች መንገድ በዚህ ዘመን የደረሰበት ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ አድርገዋል፡፡በአሁኑ ወቅትም የፈጠራ ስራዎች ይታያሉ፡፡ ፈጠራዎቹ ደህንነትና ዘላቂነት ላይ ያተኮሩ ናቸው። በየዓመቱ የመንገድ ግንባታ ቴክኖሎጂዎች እየተፈጠሩ ይገኛሉ።የመኪና አምራች ድርጅቶች መኪኖቻቸው ደህንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን እንደሚተጉ ሁሉ የመንገድ ግንባታ ድርጅቶች መንገዶች ምቾት፣ የተረጋጋና ያልተጨናነቀ መንገድ መገንባት ላይ ያተኩራሉ።መንገድ አጭር እንዲሆን ያላሰለሰ ጥረት ያደርጋሉ፡፡ለዛሬ በመንገድ ቴክኖሎጂ የቅርብ ጊዜያት ፈጠራዎችን እንመልከት፡፡
ዲላይሲንግ የመንገድ ንጣፎች
የሹፌሮች ትልቁ ፈተና በክረምት ወቅት መንገድ በበረዶ ሲሸፈን ነው።በየዓመቱ አምስት ሺ ሰዎች በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በሚፈጠር የመሬት መንሸራተትና መፍረስ የተነሳ በሚደረመሱ መንገዶች ሳቢያ ይሞታሉ።ለዚህ ደግሞ የአየር ንብረትን ሊቋቋሙ የሚችሉ የመንገድ ግንባታ ቴክኖሎጂ ለመፍጠር ሳይንቲስቶች እየጣሩ ይገኛሉ፡፡
ጨዋማ ውሃ የሚለቅ መንገድ
በቱርክ የሚገኘው የኮ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪዎች ለመንገድ ግንባታ የሚውል ጥሬ እቃ በቅርቡ አስተዋውቀዋል።ጥሬ እቃው በረዶን ከመንገድ ላይ በፍጥነት አሟሙቶ የሚያጠፋ ነው።ጥሬ እቃው ከፖታሽየምና ስቲሪነ-ቢንያዲን-ስትራኒሪየም ፖሊመር የተሰራ ሲሆን፣በአስፋልት መንገድ ላይ የተጋገረን በረዶ ማቅለጥ ያስችላል፤የቀለጠው በረዶም ከጎዳናው ፈሶ ይወገዳል ።ቴክኖሎጂው በቤተ ሙከራ ውስጥ ለመንገዶች ምቹ እንዲሆን ለሁለት ወራት ያህል ቆይቷል።ቴክኖሎጂው በአንድ ርጭት ብቻ ዓመት ሊገለግል ይችላል።ቴክኖሎጂው በተደረገበት
መንገድ የሚጓዙ መኪናዎች ጎማቸው ላይ ጨው ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል ሳይንቲስቶቹ አስገንዝበዋል፡፡
የሀይድሮሊክ ማሞቂያ
ሌላኛው በረዶን ከመንገድ ላይ የማቅለጫ ቴክኖሎጂ ደግሞ የሀይድሮሊክ ማሞቂያ ነው።ቴክኖሎጂው እንዲሰራ የሚደረገው በመንገዱ ላይ ቱቦ በመዘርጋት ነው፡፡ በቱቦው ውስጥ ፈሳሽ በመልቀቅ በበረዶ የተሞላው አስፓልት ሙቀት እንዲያገኝ ይደረጋል።በበጋ ወቅት ቱቦው ሙቀት የሚሰበስብ ሲሆን፣ የተሰበሰበው ሙቀት በክረምት ወቅት አገልግሎት ይሰጣል።ከቀዳሚው ዘዴ በተቃራኒ ሀይድሮሊክ ማሞቂያ መንገድ ተሽከርካሪዎችን ሊጎዳ የሚችል ጨው አይጠቀምም፤ ለብዙ ዓመታትም ሊቆይ ይችላል ፡፡
ለአየር ንብረት ለውጥ ምቹ የሆኑ መንገዶች
የአስፓልትም ሆነ የኮንክሪት መንገድ ለአየር ንብረት ምቹ አይደሉም፤ ለምሳሌ የአስፓልት መንገድ የነዳጅ ተረፈ ምርት በሆነው ሬንጅ የሚሰራ ነው።የኮንክሪት መንገድ ደግሞ ሲገነባ ከፍተኛ የሆነ ኃይል እንዲያወጣ ተደርጎ በመሆኑ የተፈጥሮ ሀብቶች ይባክናሉ።ኢንዱስትሪዎች በአሁኑ ወቅት የተፈጥሮ ሀብቶችን በአግባቡ ለመጠቀም ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
እንደ ኤ.ቢ.ሲ የመንገድ ግንባታ ድርጅት አብዛኛው የመንገድ ተቋራጭ ድርጅት የአስፓልት መንገድና ኮንክሪት መንገዶችን በመደባለቅ አዲስ የግንባታ ዘዴ ፈጥረዋል።ይህ ደግሞ ሀብቶች በአግባቡ ስራ ላይ እንዲውሉ ያደርጋል።ለአየር ንብረት
ምቹ የሆነ መንገድ ሁለተኛ የመንገድ ግንባታ አማራጭ እየሆነ ይገኛል።የኮርጋኒክ ሬሲን የመንገድ ግንባታ ዘዴ የአስፓልትና የኮንክሪት መንገድ ግንባታዎችን በቅርቡ እንደሚተካ ይጠበቃል፡፡
ተለዋዋጭ ቀለም
አሽከርካሪዎች እየተጓዙበት ያለውን መንገድ ከሳቱ ጉዳት ያጋጥማቸዋል።በተለይ መንገድ በአግባቡ እየታየ ካልተነዳ ሊደርስ የሚችለው አደጋ የከፋ ይሆናል።በተለይ ምንም እንኳ ተሽከርካሪዎች መብራት ቢኖራቸውም በጨለማ ወቅት መንገዱንና በመንገዱ ላይ የሚደረግ እንቅስቃሴ በሚገባ ለመለየት ያስቸግራል።ይህን አይነቱን ችግር ለመፍታት ሲባል ተለዋዋጭ ቀለም እንዲፈጠር ተደርጓል፡፡
የፎቶ ሉሚንሰንት ዱቄት ለመንገድ ምልክት ማድረጊያነት ይውላል።ዱቄቱ ቀን ቀን ከፀሀይ ኃይል የሚሰበስብ ሲሆን ማታ ላይ ደግሞ ብርሃን ይሰጣል። በተጨማሪም መንገዱ ላይ የተቀባው ምልክት የአየር ሁኔታን በመመርኮዝ ለአሽከርካሪው ልዩ ምልክት መስጠት ይችላል።ይህ የመንገድ ላይ ቀለም በአሁኑ ወቅት በኔዘርላንድ ስራ ላይ ውሏል። ቴክኖሎጂው በበቂ ሁኔታ ቻርጅ ከተደረገ በደመና ወቅት ለአስር ሰዓት ለምሽት ማገልገል ይችላል፡፡
በንፋስ የሚሰራ መብራት
ለአየር ንብረት ለውጥ ምቹ የሆነ መንገድ ግንባታ ለማከናወን ብዛት ያለው ኃይል ያስፈልጋል፡፡ኃይልን ለመቆጠብ በንፋስ የሚሰራ የመንገድ መብራትን መጠቀም የግድ ይላል።ለመንገድ ላይ መብራቱ የሚያስፈልገው ንፋስ መኪና በፍጥነት በሚያልፍበት ወቅት የሚፈጥረውን ሽውታ ነው።ይህ ከንፋስ የተገኘው ኃይል ለመንገድ ላይ መብራት ኃይል አቅራቢነት ያገለግላል፡፡ቴክኖሎጂው በንፋስ እጥረት ለሚሰቃዩ አካባቢዎችም የጎላ ፋይዳ አለው።አብዛኛዎቹ በፍጥነት መንገድ አካባቢ የሚገኙ መብራቶች የሚሰሩት በጸሀይ ወይም በንፋስ ነው።
ሌላው ፈጠራ ደግሞ የተለየ የንፋስ መንገድ ተከትሎ የሚሰራ ሲሆን፣ መኪና በአጠገቡ ሲያልፍ የሚበራና የሚጠፋ ነው።ይህ ደግሞ መንገዱ በመኪና በማይጨናነቅበት ወቅት ሀይል መቆጠብ ያስችላል፡፡
የኤሌክሪትክ መኪና ቻርጅ አድራጊ መንገድ
የኤሌክትሪክ መኪና በአሁኑ ወቅት በመላው አለም እየተስፋፋ ይገኛል።መኪናዎቹን ቻርጅ ማድረግ ግን በጣም አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል።መኪናዎቹን ቻርጅ ለማድረግ ረጅም ሰዓት ከመፍጀቱም በላይ ቻርጅ ማድረጊያ ቦታም እንደልብ አይገኝም፡፡
ለእዚህም እኤአ 2018 በስቶኮልም የመጀመሪያው ኤሌክትሪክ የሚያመነጭ መንገድ ተገንብቷል፡፡ይህም በኤሌክትክ የሚሰራ መኪናን ቻርጅ ማድረግ ያስችላል።እንደዚህ አይነት መንገዶች በሌሎች ከተሞች ላይ መገንባት ቢችሉ የኤሌክትሪክ መኪና ባትሪ ዋጋ መቀነስ ይችል ነበር፡፡በተጨማሪም የኤሌክትሪክ መኪናዎችን በብዛት ማዳረስም ይቻል ነበር፡፡
ከመንገዱ ወደ መኪናው የኤሌክትሪክ ኃይል በተንቀሳቃሽ መስመር የሚገባ ሲሆን፣ መስመሩ ከሌላ መኪና ጋር የተያያዘ ነው።ዲዛይኑም የኤሌክትሪክ ተቀጣጣይ መኪናዎችን ያስታውሳል። ነገር ግን መኪናዎቹ ከኤሌክትሪክ መንገዱ ሲወጡ ገመዱ ቻርጅ ማድረግ ያቆማል፡፡
ተንቀሳቃሽ አስፓልት
የአስፓልት መንገድ ሲገነባ ለየትኛው መኪና ተስማሚ ይሁን አይሁን የሚታወቅ ነገር የለውም።በዚህም መኪናዎቹ አስፓልትን ሲጎዱ ይታያል።የአስፓልት መንገዶች በመጎዳታቸው የትራፊክ መጨናነቆች እንዲፈጠሩ ምክንያት ይሆናሉ።በአሁኑ ወቅት ግን መንገዶች በተንቀሳቃሽ አስፓልቶች እየተገነቡ ይገኛሉ።ተንቀሳቃሽ አስፓልቶቹ በተለያዩ መንገዶች ላይ ተግባር ላይ ውለዋል።በዚህም ከባድ መኪናዎች በመንገድ ላይ የሚያደርሱትን ጉዳት መቀነስ ተችሏል።የአየር ንብረትን መቆጣጠር አስችሏል።በሌላም በኩል ጥሬ እቃዎችን ለማጓጓዝ የሚወጣንም ወጪ እንዲቀንስ አድርጓል፡፡
አዲስ ዘመን ሐምሌ 14/2012
መርድ ክፍሉ