በዛሬው ምልከታችን ከውልደት ጀምሮ እስካሁን ድረስ በኮሮና ዙሪያ በስፋት የተሰራጩ የሴራ ትንተናዎችን በማሳየት በሽታው ለሴራ ተጋላጭ ሆኖ ወደ ምድራችን መምጣቱንና አሁንም የሴረኞች ግብዓት ሆኖ መቀጠሉን ተጨባጭ ማሳያዎችን እያነሳን ለማየት እንሞክራለን። ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ እስካሁን ድረስ በዓለም ላይ በስፋት እየተሰራጩ የሚገኙ የሴራ ትወራዎችን በሁለት ዋና ዋና ምድቦች ከፍሎ ማየት ይቻላል።
የመጀመሪያው የሴራ ትወራ “ቫይረሱ ሆን ተብሎ የተፈጠረ ነው፤ በሽታው እንደሚመጣም ይታወቅ ነበር” በሚል መሰረታዊ መነሻ ሃሳብ ላይ የተመሰረተ ሲሆን፤ ከዚህ ጋር ተያይዞ በገሃዱ ዓለም ውስጥ የሚገኙ ትንቢት መሰል መረጃዎችን እያቀረበ የሚሞግት ነው። ለዚህም የኮንታጅን ፊልምን፣ የቢል ጌትስና የባራክ ኦባማ “የአየር ወለድ በሽታ ወረርሽኞች” ቅድመ ትንበያን እና ሌሎች በጉዳዩ ላይ የተጻፉ መረጃዎችን በማሳያነት ያቀርባል።
በሁለተኛው ምድብ ውስጥ የሚገኙት የሴራ ትወራዎች ደግሞ በድህረ ኮሮና ክስተቶች ላይ የሚያተኩሩ ሲሆኑ፤ ከወረርሽኙ በኋላ የተከሰቱና እየተከሰቱ የሚገኙ ሁነቶች ላይ ተመርኩዘው “ኮሮና ሆን ተብሎ የተፈጠረ ነው” የሚለውን የመጀመሪያውን ትወራ መነሻ ሃሳብ “ጀስቲፋይ” የሚያደርጉ ናቸው። በመሆኑም ወረርሽኙ ከተከሰተ በኋላ ከቫይረሱ መከላከያ መንገዶችና ቁጥጥር፣ በሽታው ካስከተላቸው ዘርፈ ብዙ ተፅዕኖዎችና ችግሮች፣ እንዲሁም ከክትባትና ከመድኃኒት ፍለጋ ጋር ተያይዞ ለወረርሽኙ በጊዜያዊነትና በቋሚነት መፍትሔ ለማግኘት ከሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ጋር ተያይዞ ባለው ሂደት ላይ “ለሴራ ተጋላጭ የሆኑ” ጉዳዮችን በመጠቀም ግምቱ ትክክለኛ መሆኑን በውጤቱ ለማረጋገጥ ይሞክራል።
በምድብ አንድ ውስጥ የሚገኙ የሴራ ትንተናዎች
ሀ፡- የኮንታጅን ፊልማዊ ትንቢት
ልብ ወለድ “የፈጠራ ድርሰት” ነው ሲባል በእውነታ ላይ ተመስርቶ የሚጻፍ የገሃዱ ዓለም ነጸብራቅ እንጂ የሌለውን የሚያወራ በሬ ወለደ ዓይነት ውሸት አይደለም። ሳይንሳዊ ልብ ወለድም እንዲሁ በሌሎች የልብ ወለድ ዓይነቶች የማይቻለውን ያለና የነበረውን ብቻ ሳይሆን የሌለውንም ግን ወደፊት ሊኖር የሚችለውን የወደፊቱንም ጊዜ “የመፍጠር” እና ሊከሰቱ የሚችሉ ነገሮችንም አስቀድሞ የማለም(Imagination) ነጻነት የተሰጠው ቢሆንም ጭብጥን “ካለው ነገር ላይ ከአሁኑ ጊዜ ተነስቶ” ወደፊት ሊሆን የሚችለውን መገመት እንጂ መተንበይ የማይችል በመሆኑ ነው። መተንበይ ወይንም ትንቢት መናገር መገመት ሳይሆን የወደፊቱን ጊዜ ቀድሞ ማወቅን ይጠይቃልና! ሆኖም ኮንታጅን ወደፊት የሚሆነውን መገመት ብቻ ሳይሆን በትክክል “መተንበይ” ችሏል። ይሄ ደግሞ ሰዎች “ፊልሙን ያዘጋጁት አካላት ወደፊት ስለሚሆነው ክስተት የሚያውቁት ነገር ነበር ማለት ነው” ወደሚል ምክንያታዊ ጥርጣሬ እንዲገቡ አስገድዷል።
የኮንታጅንን ፊልም አሰራር አስመልክቶ ዊኪፒዲያ ላይ በግልጽ የተቀመጠው ይፋዊ መረጃ (Officiall evidence)ደግሞ ጥርጣሬውን ይበልጥ ያጎላዋል።መረጃው እንደወረደ እንዲህ ይላል፡-“ዳይሬክተሩ ሶደርበርግና ስክሪፕት ጸሃፊው ስኮት በርንስ የ2002-2004ቱን ሳርስ ወረርሽኝና የ2009ኙን የኢንፍልዌንዛ ወረርሽኝ ከተመለከቱ በኋላ ይህንኑ መነሻ በማድረግ በፍጥነት የሚዛመት ቫይረስን የሚያሳይ ፊልም ለመስራት ተወያዩ”። ይሄ ብቻ አይደለም።ፊልም ሰሪዎቹ ብቻቸውን ሆነው አይደለም አምሳለ ኮሮና የሆነውን የኮንታጅን ቫይረስ በፊልም ለመስራት የተወያዩት፤ በዘርፉ አንቱ የተባሉ ባለሙያዎችን፣ ያውም ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተውን የታላቁ የዓለም የጤና ድርጅት ተወካዮችንና እንደ ደብልዩ. ኢያን ሊፕኪን እና ላውረንስ(ላሪ ብሪሊያንት) የመሳሰሉ ዕውቅ የህክምና ጠበብቶችንም አማክረዋል። የኮሮናን መንትያ የሳርስ ቫይረስ ወረርሽኝን መሰረት አድርጎ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተውን አካል እና የህክምና ተመራማሪዎችን አማክሮ የተሰራው ፊልም በገሃዱ ዓለም ከተከሰተው ኮሮና ቫይረስ ሙሉ በሙሉ አንድ ዓይነት መሆኑ ደግሞ ተራውን ዜጋም ይበልጥ እንዲጠራጠር አደረገው። ይህም “ታዲያ ይሄ እንዴት ልብ ወለድ ፊልም ብቻ ሊሆን ይችላል?” የሚል ተገቢ ጥያቄን በማስነሳቱ “ኮሮና ቫይረስ ሆን ተብሎ የተፈጠረ ነው” ለሚለው የሴራ ንድፈ ሃሳብ (ቲዎሪ) ተንታኞቹ እጅጉን ተስማሚ የሆነ ምቹ ሁኔታ ፈጠረላቸው።
ለ፡- በነቢይነት ከማይታወቁ ሰዎች የተነገሩ “ትንቢቶች”
ቢል ጌትስ የሚባል ስምን ለማስተዋወቅ መሞከር ለአዝማሪ ልጅ እስክስታን እንደማስተማር ይቆጠራል።ወይንም ፈረንጆቹ “Selling an ice to the Greenland” እንደሚሉት ስለዚህ የስም ምንነት ለማብራራት መሞከር ትርፉ ድካም በመሆኑ የታወቀ መስተጻምርን በመጠቀም በቀጥታ ማንሳት ወደምፈልገው ጉዳይ አልፋለሁ። ከሜክሲኳዊው ቱጃር የአማዞኑ ጀፍ ቤዞ ጋር ተራ በተራ እየተፈራረቀ የዓለማችንን የሃብት የደረጃ ሰንጠረዥ በበላይነት የሚመራው የማይክሮሶፍት ኩባንያ መስራችና ባለቤት የቴክኖሎጂ ሊቁና ባለሃብቱ ቢል ጌትስ በዓለም ዙሪያ የሚታወቅበትና ታዋቂ የሆነበት የራሱ ቅጽል መለያ ማንነት አለው።“የቴክኖለጂ ሊቁና ባለሃብቱ” ከስሙ ቀጥሎ በዚህ ቅጽል የሚታወቅ ሰው ነው በቃ።ከዚህ ውጪ ቢል ጌትስ በነቢይነት አይታወቅም፤ ነቢይ አይደለምና፣ ነቢይ ሆኖም አያውቅምና ዓለምም ይህን ስም በነቢይነት አያውቀውም፡፡
ይሁን እንጂ አወዛጋቢው ቫይረስ ኮሮና በወረርሽኝነት መልክ ተከስቶ ዓለምን ማስጨነቅ ከጀመረ በኋላ በየአይነት የሚታወቁ ምግብ ቤቶች ደንበኛ ሲቀንስባቸው ያንኑ በየአይነታቸውን ሳይቀይሩ “በአዲስ መልክ ሥራ ጀምረናል” እንደሚሉት የሃገራችን ነጋዴዎች ቢል ጌትስም ከዚህ ቀደም በማይታወቅበት ማንነት እንደ አዲስ መታወቅ ጀመረ።ከኮሮና በኋላ ማንም ባልጠበቀው መንገድ ቱጃሩ ቴክኖሎጂስት “ነቢይ” ሆኖ ብቅ አለ። ለምን ቢሉ ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት ቢል ጌትስ ኮሮና እንደሚከሰት ትንቢት ተናግሮ፤ ከመናገርም በላይ እርግጠኛ ሆኖ ወረርሽኙን ለመከላከል ዓለም በተጠንቀቅ እንዲቆም መንግስታትን አስጠንቅቆ ነበርና።በአሁኑ ሰዓት በ104 ነጥብ አንድ ቢሊዮን ዶላር የዓለማችን ሁለተኛው ሃብታም ሰው የሆኑት የ64 ዓመት አዛውንቱ አሜሪካዊ ቱጃር አነጋጋሪውን ትንቢታቸውን የተናገሩት ከአምስት ዓመት በፊት በዓለም ላይ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑ ሰዎች በሰዓት የተገደበ ንግግር በሚያደርጉበት “ቴድ ቶክ” በተባለ ዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ነበር፡፡
በአውሮፓውያኑ መጋቢት 2015 በካናዳ ቫንኮቨር ቴድ ቶክ ላይ ንግግር እንዲያደርጉ በተጋበዙበት ወቅት ቢልጌትስ ከሌሎች ተናጋሪዎች ለየት ባለ መንገድ በርሜል እያንከባለሉ ነበር መድረክ ላይ የወጡት። ከዚያም በእጃቸው በርሜሉን እያመላከቱ፤ “ልጅ እያለሁ ዋነኛው የዓለማችን ስጋት የኒክሊየር ጦርነት ነበር። እናም ውሃና ምግብ ማጠራቀሚያ እንዲሆነን በቤታችን ጓሮ ምድር ቤት ውስጥ ይህን በርሜል እናስቀምጥ ነበር” በማለት ንግግራቸውን ጀመሩ።“…በቀጣይ ዓመታት ግን የዓለም ስጋት የሚሆነው ኒውክሊየር ሳይሆን ቫይረስ ነው፤ በመጪዎቹ አስር ዓመታት ውስጥ ምናልባትም ከአስር ሚሊዮን በላይ ሰዎችን የሚገድል መቅሰፍት የሚከሰት ከሆነ እርሱ ጦርነት አይደለም፤ ይህ ከሆነ ሊሆን የሚችለው በጦርነት ሳይሆን በቫይረስ አማካኝነት ሊከሰት በሚችል በከፍተኛ ደረጃ ተላላፊ የሆነ ወረርሽኝ ነው” የሚል ትንቢታዊ ንግግራቸው ነበር ቢል ጌትስን ነቢይ ያስባላቸው፡፡
ቢል ጌትስ ይህን ተናግረው ብቻ አላበቁም፤ “…እናም ለዚህ አይቀሬ የቫይረስ ወረርሽኝ ከአሁኑ ካልተዘጋጀን በኋላ ጉድ ነው የሚፈላው” በማለት ትንቢት መናገር ብቻ ሳይሆን ወረርሽኙ እንደሚከሰትና ትንቢታቸውም እንደሚፈጸም እርግጠኛ ሆነው በማስጠንቀቅም ነበረ ንግግራቸውን የቋጩት። ያሉት ደግሞ ሆነ፤ በቀጣይ አስር ዓመታት ውስጥ ባሉት መሰረት እነሆ ትንቢቱ ከተነገረ ከአምስት ዓመታት በኋላ “በቫይረስ ምክንያት የመጣ”፣ “በከፍተኛ ደረጃ የሚዛመት” “አደገኛ ተላላፊ ወረርሽኝ” ይህ ጽሁፍ ለህትመት እስከተዘጋጀበት ሰዓት ድረስ ከ14 ሚሊዮን 860 ሺ 510 በላይ ሰዎችን በማጥቃትና ከ613 ሺ 387 በላይ የሚሆኑትን በመግደል መላ ዓለምን እያስጨነቀ ይገኛል።
በዚህ ደረጃ የተነበዩት መድረሱና ከመናገርም ባለፈ ትንቢት እንደሚፈጸምም እርግጠኛ ሆነው ማስጠንቀቂያ ሰጥተው የነበሩ መሆናቸው ነው እንዲህ ቢልጌትስን በሴራ ቲዎሪ አራማጆች ብቻ ሳይሆን በብዙሃኑ የዓለም ሕዝብ ዘንድም በጥርጣሬ ዓይን እንዲታዩ ያደረጋቸው። ምክንያቱም ከኮሮና ጋር ተያይዞ አሁን በዓለም ላይ የተፈጠረውን ሁኔታ የተመለከተ ሁሉ ወደ ኋላ መለስ ብሎ የ2015ቱን የቢል ጌትስን ንግግር በሚያስታውስበት ወቅት “ይሄማ ቀድመው የሚያውቁት ሴራ ቢኖር እንጂ በዚህ ደረጃ የተናገሩት ሁሉ የሚፈጸምላቸው ቢል ጌትስ ባለ ሃብት እንጂ ነቢይ አይደሉ” የሚል አመክንዮን በመፍጠሩ ነው። በመሆኑም ወትሮም ቢሆን ምክንያት የሚፈልጉት የሴራ ቲዎሪ አራማጅ አካላት ይህንን መነሻ በማድረግ “ኮሮና በተፈጥሮ የመጣ ሳይሆን ሆን ተብሎ በላቦራቶሪ የተፈበረከ ቫይረስ ነው፣ ይህ የተደረገው ደግሞ በቢል ጌትስ የገንዘብ ድጋፍ ነው፤ ቢል ጌትስ ኮሮናን የሚመስል የቫይረስ ወረርሽኝ እንደሚመጣ አስቀድሞ የተናገረበት ምክንያትም ጉዳዩን አስቀድሞ ያውቀው ስለነበረ ነው” በማለት የሴራ ትንተናቸውን በስፋት በዓለም ላይ ማሰራጨታቸውን ተያይዘውታል።ለምን? ተብለው ሲጠየቁም “የዓለምን ሕዝብ ቁጥር በተለይም የብዙሃኑን የድሃ ሕዝብ ቁጥር ለመቀነስና ዓለም ለእንደነ ቢል ጌትስ ዓይነት ሃብታሞች ብቻ ምቹ እንድትሆን ለማድረግ ነው” የሚል ምላሽ ይሰጣሉ።
የቢል ጌትስን የክትባት አምራች ኩባንያዎችን የመደገፍ የኋላ ታሪክ በማስረጃነት በማጣቀስም “ ቢል ጌትስ ከዚህ ቀደምም በክትባት ሽፋን የዓለምን ሕዝብ ቁጥር ለመቀነስ የሚያደርገው ሴጣናዊ እንቅስቃሴ አካል ነው” በማለት የሴራ ትንተናቸውን ያጠናክራሉ። እናም በቫይረስ የሚመጣ አደገኛ ተላላፊ ወረርሽኝ እንደሚከሰት “ትንቢት” መናገር ብቻ ሳይሆን “ትንቢታቸውም” እንደሚፈጸም ትንቢት በመናገራቸው ከኮሮና ወረርሽኝ መከሰት በኋላ በአዲስ መልክ መታወቅ የጀመሩት ሚስተር ጌትስም ቫይረሱ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ ከቫይረሱ እኩል የሴራ ቲዎሪ ተጋላጭ ሆነው ቀጥለዋል።
ከቢል ጌትስ በተጨማሪ አርባ አራተኛው የመጀመሪያው ጥቁር አሜሪካዊ የአሜሪካ ፕሪዚዳንት ባራክ ሁሴን ኦባማም ከስድስት ዓመታት በፊት በተመሳሳይ በአየር ወይም በትንፋሽ አማካኝነት ሊተላለፍ የሚችል ተላላፊ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ሊከሰት እና በርካቶችን ህይወት ሊቀጥፍ እንደሚችል ትንቢት የሚመስል ነገር ተናግረው እንደነበርም ታውቋል። እናም የቢል ጌትስን ያህል ባሆንም ይህን ንግግር በማስረጃነት በማቅረብ “እርሳቸውም ኮሮና እንደሚከሰት ያውቁ ነበር፣ የምስጥራዊ ማህበር አባልና ህዝብን የመቀነሱ የዓለም አቀፍ ሴራም አካል ናቸው” በሚል ከኮሮና ጋር ተያይዞ ለሴራ ቲዎሪ ትንተና ሰለባ ከሆኑ ሰዎች መካከል ኦባማም ተካትተዋል።ታዋቂው ጣሊያናዊ አሜሪካዊ ዶክተር አንቶኒዮ ፋችም ከዚህ ምድብ ውስጥ የሚካተቱ ናቸው። የኮሮና ቫይረስ ሆን ተብሎ የተፈጠረ ነው የሚለውን ሃሳባቸውን ተቀባይነት ለማስፋት የሴራ ተንታኞች በቃል የተቀረጹ እንደነ ቢል ጌትስ ዓይነት ትንቢት መሰል ንግግሮችን ብቻ ሳይሆን በሩቅና በቅርብ ጊዜያት ከተጻፉ መዛግብት ጭምር ተመሳሳይ ማስረጃዎችን እስከ መጥቀስ ርቀው ሲሄዱ ተስተውለዋል። በዚህ ረገድ ከተገኙ የጽሁፍ ማስረጃዎች መካከል በአስራ ስድስተኛ ክፍለ ዘመን ይኖር የነበረውን የታዋቂው ፈረንሳዊ ትንቢት ተናጋሪ የኖስትራዳመስ አንድ ግጥም እና ከአርባ አንድ ዓመታት በፊት በእውቁ አሜሪካዊ ደራሲ ዲያን ኮንቴዝ የተጻፈው “The Eyese of Darkness” በዋናነት ይጠቀሳሉ። ከዚያም የጽሁፎችን ቤቶች ከሴጣናዊ የምስጢራዊ ማህበራት ጋር በማገናኘት “የዓለምን ሕዝብ ቁጥር ለመቀነስና መላውን የዓለም ሕዝብ በአንድ ዓለም የሴጣናዊ ሥርዓት በቁጥጥር ስር አውሎ ለመግዛት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሆን ተብሎ ሊፈጠር እንደሚችል ከጥንት ጊዜ ጀምሮ ታውቆ የኖረ ነው” የሚለውን ድምዳሜያቸውን ለማስረዳት ይሞክራሉ፡፡
በምድብ ሁለት ውስጥ የሚገኙ የሴራ ቲዎሪዎች
2ሀ፡- “ቶሎ እንዳይጠፋ ይፈለጋል”
በምድብ ሁለት የሴራ ቲዎሪዎች ስር የሚጠቃለሉ ትንተናዎች መነሻቸው ሴራ ቲዎሪ አንድ ነው። እነዚህኞቹ የሴራ ትንተና ዓይነቶች ከመጀመሪያዎቹ የሚለዩት በዋነኛነት የሚያተኩሩት ወረርሽኙ እንዴት ተፈጠረ በሚለው ላይ ሳይሆን ከተፈጠረ በኋላ ባሉት ሁኔታዎች ላይ መሆኑ ነው። ከበሽታው ስርጭት፣ ቁጥጥርና መከላከያ መንገዶች እንዲሁም ከሚደረጉ የመፍትሔ እንቅስቃሴዎች ጋር ተያይዞ በተጨባጭ የሚስተዋሉ እንከኖችን መነሻ በማድረግ “ሆን ተብሎ የተፈጠረ ነው የሚለውን” የመጀመሪያውን ሴራዊ ሃሳብ በማጠናከርና ትክክለኛነቱን በማስረጃ የተደገፈ ለማድረግ ይሞክራሉ።
ለወረርሽኙ ክትባትና መድሃኒት ለማግኘት የሚደረጉ ምርምሮች ሆን ተብሎ እንዲዘገዩና በተለያየ መንገድ ጫና እንደሚደረግባቸው፤ ጫናውን ተቋቁመው ውጤት ላይ የሚደርሱ ተስፋ ሰጪ ክትባቶችና መድሃኒቶችም ጥቅም ላይ እንዳይውሉ እየተደረጉ መሆናቸውን ተጨባጭ መረጃዎችን በማሳያነት በማቅረብ ይሟገታሉ።“ይህን ማድረጉ ለምንና ለማን ይጠቅማል?” ተብለው ሲጠየቁም “ምክንያቱም የታቀደው የሕዝብን ቁጥር የመቀነስ ዓላማ እስኪሳካ፤ ወረርሽኙም መግደል የሚገባውን ያህል እስኪገድል ድረስ እንዲቆይ ይፈለጋል” በማለት ከመጀመሪያው የሴራ ትነተናቸው ዓላማ መሳካት ጋር የተገናኘ ምላሽ ይሰጣሉ።
በሌላ በኩል የወረርሽኙን በፍጥነት ተዛማችነትና በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊያስከትለው ከሚችለው ውድመት አኳያ አጠቃላይ የበሽታውን አስከፊነት ግምት ውስጥ በማስገባት ስርጭቱን ለማስቆምና በሽታውን ለማከም እየተደረጉ የሚገኙ የምርምር ውጤቶች ከተለመደው አካሄድ በተለየ በፍጥነት ሥራ ላይ የሚውሉበትን ለመፍጠር ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል። በዚህ ረገድ እየተደረጉ ከሚገኙ በርካታ የምርምር ሥራዎች መካከል አንዳንዶቹ ተጠናቀው ለትግበራ ዝግጁ መሆናቸው ከዛሬ አራትና አምስት ወራት በፊት ጀምሮ ቢገለጽም አሁንም ድረስ አንዳቸውም ጥቅም ላይ ውለው አለመታየታቸው በዚህኛው ምድብ ውስጥ ለተፈጠሩ የሴራ ቲዎሪዎች አመች ሁኔታን ሳይፈጥር አልቀረም።
ባህላዊና ዘመናዊ የህክምና ዘዴዎችን በማጣመር በእኛ ሃገር የተገኘውን ጨምሮ ተፈጥሯዊ የሰውነት ሴሎችን በመጠቀም የኮቪድ-19 በሽታን ውጤታማ በሆነ መንገድ ማከምና ማዳን እንደሚቻል የገለጹት የእስራኤል ሳይንቲስቶች የምርምር ውጤት ለዚህ ጥሩ ማሳያዎች ናቸው። በቫይረሱ ተይዘው ካገገሙ ሰዎች ደም ተወስዶ የተዘጋጀውና አስደናቂ ውጤትን አሳየ የተባለው የብሪታንያ የኮሮና ክትባት ግኝት፣ የቻይና፣ የጀርመን፣ የአሜሪካ፣ የሩስያና የሌሎችም አገራት ተስፋ ሰጭ የተባሉ የምርምር ውጤቶች ከወራት በፊት ጥቅም ላይ ለመዋል ደርሰዋል ከተባሉ በኋላ የውሃ ሽታ ሆነው መቅረታቸው “ወረርሽኙ ቶሎ እንዲጠፋ አይፈለግም” ለሚለው ሴራ የእሳት ላይ ቤንዚን ሆነው አገልግለዋል። ይህም የሴራ ተንታኞቹ ሃሳብ ተጨማሪ ኃይል አገኝቶ ይበልጥ እንዲቀጣጠልና ከእነርሱም አልፎ ህብረተሰቡ ውስጥም እንዲስፈፋፋ አስቻይ ሁኔታ ፈጥሯል። ከሦስት ወራት በፊት አሜሪካ ውስጥ ….የዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ የሆኑት ታላቁ ቻይናዊ ዶክተር ለቫይረሱ መፍትሔ ለማግኘት ጫፍ ላይ መድረሳቸውን ባሳወቁ ማግስት ባልታወቁ ሰዎች በጥይት ተገድለው መገኘታቸው ደግሞ ከላይ ከቀረቡት ተጨባጭ ምክንያቶች ጋር ተደማምሮ የሴራ ተንታኞችን ሃሳብ እውነት አስመስሎታል።
እንደ መውጫ
እናም ኮሮና ከገዳይነቱና ከጥፋቱ እኩል በታሪክ ከተከሰቱት ወረርሽኞች ሁሉ በአወዛጋቢነቱና ለሴራ ቲዎሪዎች አመችነቱ ወደር ያልተገኘለት እጅግ ሴረኛ ቫይረስ በመሆኑ ሰዎችን በማዘናጋት ለከፋ ተጋላጭነት እየዳረገ መሆኑን መታዘብ ይቻላል። በዚህ ሁሉ የሴራ ቲዎሪ ባህር ውስጥ ሆኖም “ሴረኛው ቫይረስ” በየጊዜው በሚፈጥረው የሴራ ትንተና የዓለምን ህዝብ አስተሳሰብ እያወናበደ አሁንም በገዳይነቱ ቀጥሏል።ይህን የተገነዘቡት የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርም “በወረርሽኙ አሳሳች ባህሪ ሕዝቡ ሳይዘናጋ ራሱን እንዲከላከል ተገቢውን ጥረት አላደረጉም” በሚል የሃገራት መንግስታትን ወቅሰዋል። እርሳቸው እንዳሉትም በማዘናጋት ውስጥ ሆኖ ወረርሽኙ ከምንጊዜውም በላይ ስርጭቱን በመጨመር ላይ ይገኛል። እያደረሰ ካለው መጠነ ሰፊ ሞትና የህይወት ጥፋት በተጨማሪም በዓለማችን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴዎች ላይ የሚያደርሰውን አውዳሚ ጥፋት አጠናክሮ ቀጥሏል። እኛም በሴራም ይሁን በተፈጥሮ ሥራ ወረርሽኙ ለመኖሩ ጥፋቱ ማሳያ ነውና ደግሞም አንዳንዶቹ የሴራ ትንተናዎች እውነትነት ያላቸው ቢመስሉ እንኳን ሃሳቦቹ የተፈጠሩት በሴራ ተንታኞቹ ክፋት ብቻ ሳይሆን በራሱ በኮሮና አሳሳች ባህሪ መሆኑን ተገንዝበን በሴራ ቲዎሪዎቹ ሃሳብ ሳንዘናጋ “ሴረኛውን ቫይረስ” እንከላከል በማለት የዛሬውን መልእክታችንን እናጠናቅቃለን። የክፉ ሰዎችም የኮሮናም ሴራ እንዲያበቃ እግዚአብሔር ይርዳን!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 15/2012
ይበል ካሳ