ግንቦት 19 ቀን 1967 ዓ.ም የታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ” ምላስ ሲተርፍ ” በሚል ርዕስ ከዚህ ቀደም ስልጣን ላይ የነበሩ ኃይሎች ለውጡን ለማደናቀፍ እየጣሩ ስለሆነ ሕዝቡ ለእነዚህ አካላት ጆሮውን መስጠት የለበትም ሲሉ አንድ ተሳታፊ የላኩትን ተከታዩን ጽሑፍ አስነብቦ ነበር።
ምላስ ሲተርፍ
በሰፈራችን ከተነገሩ ታሪኮች ሁሉ ምንጊዜም የማይረሳኝ የቅጅነሽ ታሪክ ነው። ወይዘሮ ቅጅነሽ ባለቤቷ በሌብነት ታስሮባት ከጎረቤቶቿ ጋር ሆና ልትጠይቀው ሄደች። ፖሊስ ጣቢያው እንደደረሰች ያልጠየቋትን ሁሉ ቀባዠረች ፤ እሷም እንደ ባለቤቷ እዚያው ቀረች። አብረዋት ያልሄዱት ጎረቤቶቿ አጅበዋት የሄዱትን ጎረቤቶቿን ሁኔታውን ቢጠይቁ ቅጅነሽም እንደ ባሏ እስር ቤት መቅረቷን አበሰሩ። ከዚያ ቀን አንስቶ የመንደሩ ሰው አንድ ሰው የማይረባ ወሬ ሲያወራ “ቅጅነሽ በምን ታሰረች?” በማለት ሰውዬውን ከንግግሩ ያቋርጡታል። የቅጅነሽን ታሪክ የሚያውቅ ሰው ባቅራቢያው ካለ መልሱን በቶሎ ይሰጣል። ያልጠየቋትን ስትለፈልፍ !
ታዲያ አሁንም በአገራችን አልፎ አልፎ የሚታየው ይህን የመሰለ ታሪክ ነው። አንዳንድ አድሃሪያን ሳይጠየቁ የባጥ የቋጡን ያወራሉ። መቼም አፋቸው ብቻ ስለቀራቸው ለጥቂት ጊዜ ቱልቱላቸውን መንፋታቸው ይቀጥላል። ቀን ሲያጋልጣቸውም መድረሻቸውን ያጣሉ።
ከውስጥም ሆነ ከውጭ የአዲሲቱን የኢትዮጵያ ቀጥተኛ እርምጃ ለማደናቀፍና ለማወናበድ የሚሞክሩ ሁሉ የፍየል ወጠጤ ናቸው። ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ነጻ ወጥቷል። ነጻነት ምን አይነት እንደሆነ ቀምሷል። ከእንግዲህ ወዲያ እንደገና ባሪያችን ሁንና ተገዛልን በማለት የሚደረገው ሙከራ ሁሉ ከንቱ ነው።
በእፍኝ የማይሞሉ አንዳንድ ጥቅማቸው የተነካ የውስጥ ጠላቶች በየጊዜው አንዳንድ የፈጠራ ወሬ እያዘጋጁ ለጡት ልጆቻቸው ይረጫሉ። ጥቂት ደጋፊዎቻቸውና በፍርፋሪያቸው ያደጉት ልጆቻቸው በተራቸው ከጌቶቻቸው የተሰጣቸውን ፍሬ ከርስኪ ወሬዎች በመያዝ በየመሸታ ቤቱ፣ በትምህርት ቤቶች፣ በየመስሪያ ቤቱ ወዘተ …ይበትናሉ። ሰውንም ግራ ለማጋባት ይሞክራሉ። ሆኖም ማን ይሰማኝ ብለው? ሰፊውን ህዝብ ደጋግሞ ማታለል የማይቻል ነው።
እንዲሁም አንዳንድ የውጭ አገር ዜጎች ካገራችን ከወጡ በኋላ በያገራቸው ሬዲዮ በመጠቀም ስለኢትዮጵያ ሁኔታ ብዙ ልቦለድ ታሪኮች በየጊዜው ያሰራጫሉ። ሆኖም ለብዙ ጊዜ ሲበደል የቆየው እውነተኛው የኢትዮጵያ ህዝብ በእጁ ያገባውን የለውጥ እርምጃ ለማደናቀፍ የሚሞክሩትን ጠላቶቹን ያውቃቸዋል።
ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ለብዙ አመታት እንደ አህያ ተገዝቶ ነበር። ባደረገው ንቅናቄ እውነተኛ ክብሩን አስመልሷል። ለአያሌ ዘመናት የኢትዮጵያን ህዝብ በልዩ ልዩ ዘዴ አደንዝዘውት ነበር። ዛሬ ከዚያ ድንዘዛ በጣጥሶ ወጥቷል። ይሁን እንጂ እርዝራዦቻቸው የጥንቱን የድንዛዜ ከቀድሞ በበለጠ ብልሃት እንደገና ለመርጨት ከመፍጨርጨር ስለማይቆጠቡ እያንዳንዱ ተራማጅ ኢትዮጵያዊ እውነቱን ላልገባው ማስተማር የዘወትር ተግባሩ መሆን አለበት። ጠላቶቻችን አተኩረው ያዩናል። ቀዳዳም ዘወትር እየፈለጉ ነው። ነቅቶ መጠበቅ የእያንዳንዱ እውነተኛ ኢትዮጵያዊ ግዴታ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ማወቅ የሚገባው ከእንግዲህ ወዲያ ጠላቶቻችን የቀራቸው ነገር ቢኖር ምላሳቸው ብቻ መሆኑን ተገንዝቦ በየጊዜው የሚበትኑትን ዝባዝንኪ ወሬዎች ከማስተጋባት መቆጠብ አለበት። ለወሬ ጊዜ የለንም ወደፊት !
ጌታቸው ገብረ ወልድ (ከብሔራዊ ባንክ)
አዲስ ዘመን ሐምሌ 15/2012
የትናየት ፈሩ