ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለሥላሴ የተወለዱት ከ128 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሐምሌ 16 ቀን 1884 ዓ.ም ነበር።
ተፈሪ መኮንን ከአባታቸው ከልዑል ራስ መኮንን እና ከእናታቸው ከወይዘሮ የሺ እመቤት ሐረርጌ ውስጥ ኤጀርሳ ጎሮ በምትባል መንደር ተወለዱ። ተፈሪ እናታቸውን በህጻንነታቸው፣ አባታቸውን ራስ መኮንንን ደግሞ በአሥራ ሦስት ዓመት ዕድሜያቸው አጥተዋል። በወቅቱ የሐረርጌ ገዢ የነበሩት አባታቸው ራስ መኮንን ወልደ ሚካኤል ከሸዋው ንጉሥ ሣህለ ሥላሴ ከሚወለዱት እናታቸው ልዕልት ተናኘ ወርቅ ሣህለ ሥላሴና ከአባታቸው ከአቶ ወልደ ሚካኤል ጉዲሳ ተወላጅ ናቸው። ራስ መኮንን ከንጉሥ ኃይለ መለኮት ሣህለ ሥላሴ ለሚወለዱት ለዳግማዊ አፄ ምኒሊክ የአክስት ልጅ ናቸው።
ተፈሪ ለኃላፊነትና ለአስተዳደር ስራ የታጩት አባታቸውን በሞት ካጡ በኋላ ገና በለጋነት ዕድሜያቸው በ13 ዓመታቸው ነበር። በዚህ ዕድሜያቸው የሰላሌ አስተዳዳሪነት ሹመት ከደጃዝማችነት ማዕረግ ጋር ተሰጣቸው። እርሳቸው ግን ከማስተዳደር ይልቅ ትምህርት መቅሰም እንደሚሻል ተረድተው ዳግማዊ ምኒልክን ከእነ አቤቶ ኢያሱ ጋር በመሆን ትምህርታቸውን ለመከታተል ጠይቀው ተፈቀደላቸው።
በ1897 ዓ.ም የሐረርጌ ግዛት ለወንድማቸው ለደጃዝማች ይልማ መኮንን ተላልፎ እሳቸው ከሐረርጌ ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ ተደረገ። ለአምስት ዓመታት ያህል አዲስ አበባ በዳግማዊ አፄ ምኒሊክ ቤተ መንግሥት ውስጥ የቤተ መንግሥት ሥርዓት በቅርብ እየተከታተሉ አድገዋል። ታላቅ ወንድማቸው ደጃዝማች ይልማ መኮንን ከሦስት ዓመታት በኋላ ሲያርፉ ሐረርጌ ከሲዳሞ ጋር እንዲቀላቀል ተደርጎ በወቅቱ የሲዳሞ ገዥ ለነበሩት ለደጃዝማች ባልቻ ሳፎ ተላልፎ በተደራቢነት ሲተዳደር ቆየ። ከሁለት ዓመታት በኋላ በ1902 ዓ.ም በእቴጌ ጣይቱ አሳሳቢነት ሐረርጌ ለደጃዝማች ተፈሪ እንዲተላለፍ በመወሰኑ፣ በ18 ዓመት ዕድሜያቸው ወደ ሐረር በመዛወር እስከ 1909 ዓ.ም የልጅ ኢያሱ መንግሥት መውደቅ ድረስ ግዛቱን ሲያስተዳድሩ ቆዩ።
በ1909 ዓ.ም የልጅ ኢያሱ መንግሥት በመኳንንቱ ሴራ ተወግዶ ዘውዲቱ ምንሊክ በንግሥተ ነገሥታትነት ሲሾሙ፣ ቀደም ሲል ባልነበረ ሥርዓት ተፈሪ መኮንን በ25 ዓመት ዕድሜያቸው የንግሥቲቱ አልጋ ወራሽ ሆነው ተሾሙ። ከዚያ በፊት በነበረው ልማድ ንጉስ አልያም ንግስት ዘውድ ሲጭኑ አልጋወራሽ ይሰየም የነበረው ዕድሜያቸው ለጋ ሲሆን ነው። በዘውዲቱና በተፈሪ መካከል የሆነው ግን የተገላቢጦሽ ነበር። ለተፈሪ እናት ሊሆኑ የሚችሉት ዘውዲቱ ለስሙ ንግስተ ነገስት ተብለው ልጃቸው ሊሆኑ የሚችሉት ተፈሪ በአልጋ ወራሽነት ሙሉ ስልጣኑን ጠቀለሉ። ቀስ በቀስም ተፈሪ አልጋወራሽ ብቻ መሆናቸው ቀርቶ እንደ ሙሉ ባለስልጣን መታየት ጀመሩ።
በዚህ የአልጋ ወራሽነት ሥልጣን ላይ 13 ዓመታት ከመንፈቅ ቆየተዋል። በቆይታቸውም ኢትዮጵያን ከዘመናዊ አስተዳደር ጋር ለማስተዋወቅ ታትረዋል። ለመጀመሪያ ጊዜ በከፍተኛ ባለሥልጣን ደረጃ በአውሮፓ ጉብኝት ያደረጉ መሪ መሆን ችለዋል። ፊትአውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ ይህ ጉብኝታቸው ስለፈጠረባቸው መነሳሳት ሲገልጹ፣ “ራስ ተፈሪ፣ የፈረንጆቹን አገር አይቶ ከመጣ በኋላ፣ አገሬ ለሥልጣኔ መፍጠን አለባት ብሎ እንቅልፍ አጥቷል” ማለታቸውን የአምባሳደር ዘውዴ ረታ “ተፈሪ መኮንን ረዥሙ የሥልጣን ጉዞ” መጽሐፍ ላይ ተጠቅሷል።
በአገር ውስጥ ከነበሩ ኤምባሲዎች ጋርም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን በማጠናከር የተሳካላቸው ነበሩ። ከሁሉ የሚልቀው ስኬታቸው ግን ኢትዮጵያን በዓለም አቀፉ የመንግሥታቱ ማኅበር ቀደምት አፍሪካዊት አገር በማድረግ በአባልነት ማስመዝገባቸው ነው።
ቆይቶም በብልሃት የንግሥት ዘውዲቱን አስተዳደር እጅ በመጠምዘዝ ቆይቶም በንግስት ዘውዲቱ ዘውድ ተጭኖላቸው ንጉስ ለመባል በቁ። በ1921 ዓ.ም ንጉሥ ለመባል በቁ። የነበሩበት የአልጋ ወራሽነት ማዕረግ ያስገኘላቸው ዲፕሎማሲያዊ ስኬት፤ የሰገሌንና የአንቺም ጦርነቶችን በማሸነፍ የልጅ ኢያሱንና የንግሥት ዘውዲቱን ደጋፊዎች ማንበርከካቸው፤ ከዚህም በላይ የውስጥ ተቃዋሚዎቻቸውን አንድ በአንድ ከጨዋታ ውጪ እያደረጉ በመምጣታቸው እና በጥርጣሬ አይን ይመለከቷቸው የነበሩት ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስና አቡነ ማቴዎስ በተከታታይ ማረፋቸው በ39 ዓመታቸው ንጉሠ ነገሥት ተሰኝተው የስልጣን ጫፍ ላይ እንዲገኙ አስችሏቸዋል።
ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የዘውዱ አልጋ ወራሽና የመንግስቱ አስተዳዳሪ በኋላም ንጉሥ፣ በማሳረጊያውም ንጉሠ ነገሥት በተባሉበት ከጣሊያን ወረራ በፊት በነበረው ዘመን በርካታ ታሪካዊ ተግባራትን አከናውነዋል። መሠረተ ልማቶችንና ትምህርትን አስፋፍተዋል ፤ የሆለታ ገነት የጦር ትምህርት ቤትን አቋቁመዋል፤ ኢትዮጵያን ከሕገ መንግስት ጋር አስተዋውቀዋል፤ የኢትዮጵያን ወደብ ባለቤትነት በማስመልከት ባደረጓቸው ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ዘመቻዎች በ1924 ዓ.ም የአሰብ ወደብን ኢትዮጵያዊነት የሚያረጋግጥ ስምምነት ከጣሊያን ጋር ተፈራርመዋል። ንጉሡ በጣሊያን ወረራ ወቅት በማይጨው ጦርነት ላይ በጀግንነት ከተዋጉ በኋላ በጄኔቫ የመንግስታቱ ማህበር ስብሰባ ላይ ተገኝተው ስለኢትዮጵያ ህዝብ በደል አስረድተዋል።
ከጣሊያን ወረራ በኋላም ዘመናዊ ትምህርትን በከፍተኛ ደረጃ አስፋፍተዋል፤ ገነተ ሉዑል በመባል የሚታወቀውን ቤተ መንግስታቸውን የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንዲመሰረትበት አበርክተዋል። ኢትዮጵያ በሁሉም መስክ ሁሉን አቀፍ የስልጣኔ ጮራ እንዲበራላት በየመስኩ ዕውቅ ምሁራንና ልዩ ልዩ ባለሙያዎች በማፍራት የዘመነች አገር ለመገንባት ተንቀሳቅሰው በርካታ ታሪካዊ ተግባራትን አከናውነዋል።
የወሎው ንጉሥ ሚካኤል የልጅ ልጅ የእቴጌ መነን አስፋው ሦስተኛ ባል የሆነት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሃያ የሚበልጡ የክብር ዶክትሬት ዲግሪዎችን ከተለያዩ አገራት መሪዎችና ዩኒቨርሲቲዎች ተቀብለዋል። በፍቅር ላይኩን የተባሉ የታሪክ ባለሙያ ንጉሡ አገራቸውን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማስተዋወቅ ረገድ የተጫወቱትን ሚና ሲገልጹ “ምናልባትም አገራችን ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከምትታወቀበት ድርቅ፣ ርሀብና የእርስ በርስ ጦርነት ባሻገር በአንጻራዊ መልኩም ቢሆን በአዎንታዊነት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የአገራችንን ስም በመልካም እንዲነሣ ምክንያት ከሆኑ የኢትዮጵያ መሪዎች መካከል አፄ ኃ/ሥላሴ ብቸኛውና ዋንኛው ናቸው ብል ብዙም ያጋነንኩ አይመስለኝም።” ብለዋል።
ቀዳማዊ ኃይለሥላሴን የሚወቅሷቸው ወገኖች በዘመናቸው የተከሰተውንና ብዙዎች እንደ ቅጠል የረገፉበትን አስከፊ ርሃብ በመደበቃቸውን፣ ደጃዝማች በላይ ዘለቀን ከእነ ወንድማቸው በአደባባይ ለመስቀል ከባንዶች ጀርባ መሰለፋቸውን ፣ በእነ ቢትወደድ ነጋሽ በዛብህ መዝገብ የቀረቡት እነ አለቃ ፈጠነ ከ1943 እስከ 1966 ዓ.ም ድረስ ለ23 ዓመታት በብረት ሰንሰለት እንዲታሰሩ ማድረጋቸውን፣ እንዲሁም በጄኔራል መንግሥቱ ንዋይ መዝገብ ተከሰው ፍርድ ቤት እስር የፈረደባቸውን ሻምበል ክፍሌ ወልደ ማርያምንና የመቶ አለቃ ድጋፍ ተድላን በሞት መቅጣታቸውን በዋነኝነት ያነሱባቸዋል።
እስካሁን ሁነኛ ማስረጃ ባልተገኘላቸው የንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ፣ የሌተና ጄኔራል መርዕድ መንገሻ፣ የሠዓሊ አገኘሁ እንግዳ፣ የተማሪ ጥላሁን ግዛውና የጋዜጠኛ አሳምነው ገብረ ወልድ ድንገተኛ ሕልፈቶች፣ መሰል ምስጢራዊ ግድያዎችና አፈናዎች የእሳቸው ዕውቀት እንዳለበት ይጠረጠራል።
የንጉሡ አስተዳደር ወደ ውድቀት እያዘመመ መምጣቱን በማሳየት ለለውጥ እንዲዘጋጁ የሚጠቁሙዋቸው ወገኖች ነበሩ። ጸሐፌ ትእዛዝ ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ በ1948 ዓ.ም ያቀረቡት የዘመናዊ አደረጃጀት ምክረ ሐሳብ ፣ በ1953 ዓ.ም የተሞከረው የጄኔራል መንግሥቱ ንዋይ መፈንቅለ መንግሥት አንግቦ የተነሳው ሕገ መንግሥታዊ የፓርላማ ሥርዓት ሀሳብ እና አምባሳደር ብርሃኑ ድንቄ በ1958 ዓ.ም ያቀረቡት የምክር ደብዳቤ በዋናነት ይጠቀሳሉ። ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ግን መንግሥታቸውን ዘመናዊ በሆነ መንገድ እንዲያሸጋግሩና የመሬት ሥሪትን እንዲያሻሽሉ ከቅርብ ሰዎቻቸው ጭምር የተሰጣቸውን ማሳሰቢያ አልቀበልም አሉ፤ መጨረሻቸውም ሳያምር ቀረ።
አንጋፋው ጋዜጠኛ ንጉሴ አክሊሉ ከስልጣን እንዴት እንደተነሱና የአገዳደላቸውን ሁኔታ አስመልክተው በአንድ ወቅት ለጀርመን ድምጽ እንደገለጹት፤ መስከረም ሁለት ቀን 1967 ዓ.ም የዛሬ 40 ዓመት ነው ከስልጣን የወረዱት። መጀመሪያ ወደ አራተኛ ክፍለ ጦር ነው የተወሰዱት። የሚገርመው ለእርሶ ደህንነት ሲባል ነው ተብለው በቮልክስዋገን መኪና ነበር የወሰዱዋቸው። ጀነራል ሉሉ በሚባሉ በሹፌራቸው ቮልክስዋገን ነበር የተወሰዱት። ታድያ ለምንድነው በቮልክስዋገን የምትወስዱኝ? ብለው አልጠየቁም። ግቡ አልዋቸው ገቡ፤ ሲወስዱዋቸው ህዝቡ ሌባ ሌባ እያለ ይጮኽ ነበር። እና አብረዋቸው የነበሩትን መኮንኖች ህዝቡ ምን እያለ ነው? ሲሉ ጃንሆይ ጠየቁ። ከዚያም መኮንኖቹ ሌባ ሌባ ነው የሚለው ብለው መልስ ይሰጡዋቸዋል። ጃንሆይም መለስ አድርገው፤ ታድያ ምን ያድርጉ በጠረራ ፀሐይ ንጉሳቸውን ሰርቃችሁ ስትሄዱ ምን ያድርጉ አሉ ይባላል።
ጃንሆይን ወስደው አራተኛ ክፍለ ጦር አስቀመጡዋቸው። እንደገናም ወደ ታላቁ ቤተ- መንግስት አመጡዋቸው። ታላቁ ቤተ- መንግስት ስዕል ቤት ኪዳነ ምህረት እየፀለዩ ለብቻ እየኖሩ ነበር። ድንገት ነሐሴ 21 ቀን አረፉ ተብሎ ተነገረ። ነገር ግን ከጠዋት ጀምሮ ቤተ ክርስቲያኑ አካባቢ ጉድጓድ ይቆፈር እንደነበር ታውቋል። እዚያ የነበሩ መነኮሳት ለምን ይህ ጉድጓድ ይቆፈር እንደነበር እንደማያውቁ ተናግረዋል። በኋላ ኢህአዴግ ስልጣን እንደያዘ አንድ የቅርብ ሰው የነበረ የመቃብር ቦታቸውን ጠቁም ተብሎ ከአንድም ሁለት ቦታ አሳይቶ ነበር፤ ግን በትክክል ሊያሳይ አልቻለም። በኋላ ከኮሎኔል መንግስቱ ቢሮ ስር አፅማቸው እንደተገኘና እንደወጣ ነው የሚታወቀው። ከዚያም አፅማቸው አፄ ምንሊክ ባረፉበት ቦታ አረፈ። ከተወሰነ ዓመት በኋላ አፅማቸው ብሔራዊ ክብርም ሳይሰጠው አፍሪቃ ሕብረትን የመሰረቱ ጀግና የአፍሪቃ መሪዎች ሳይሸኟዋቸው፤ ሳይቀብሩዋቸው የቀብሩ ሥነ- ስርዓት ተቻኩሎ በአሰሩት ቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያን ተፈፅሟል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 15/2012
የትናየት ፈሩ