የትውልድ ቦታቸው ወሎ ገፍረ በሚባል አካባቢ ነው። እስከ ሰባት ዓመታቸው በከብት ጠባቂነት አሳልፈዋል። ቤተሰቦቻቸውን በሞት ሲነጠቁ ሳዑዲ ዓረቢያ በሚኖሩ ታላቅ ወንድማቸው አማካኝነት ወደሳዑዲ ለመሻገር ቻሉ። እስከ 12ኛ ክፍል የተማሩት በመካ መዲና ነው። ከንጉሥ አብዱል አዚዝ ዩኒቨርሲቲ በፐብሊክ አድምኒስትሬሽንና ኢኮኖሚክስ የመጀመሪያ ዲግሪ ይዘዋል። በኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፍ ቢሰማሩም፤ በደርግ ዘመን የግል አስጎብኚ ተቋማት እንዲወረሱ በተላለፈው ትእዛዝ መሠረት ሥራቸውን ለማቆም ተገድደዋል።
ኢህአዴግ አገሪቱን እንደተቆጣጠረም በተፈጠረው የመናገርና የመጻፍ ነፃነት የመጀመሪያውን ‹‹የአፍሪካ ቀንድ›› መጽሄት መሠረቱ። ኢትዮጵያ በውጭ አገራት የምትታወቅበትን የረሃብና የድርቅ ስያሜ ለመቀየርም ጥረት አድርገዋል። ግን ከሥርዓቱ ጋር ባለመስማማታቸው ከርቸሌ ከመወርወር አላመለጡም።
ከሦስት ዓመታት እሥር በኋላ ተፈትተው ወደውጭ አገር ተጓዙ። አጋጣሚው ሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪያቸውን እንዲማሩ አስቻላቸው። እርሳቸው በዲፕሎማሲ፣ በኢኮኖሚ፣ በቱሪዝም እና በመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ የዳበረ ተሞክሮ አካብተዋል።
16 የሚደርሱ መጽሐፎችንም ለንባብ አብቅተዋል። ከሠሯቸው 33 ጥናቶች መካከል ሰባቱ ለህትመት በቅተውላቸዋል። በአፍሪካ ቀንድ ዙሪያ የታሪክ ተመራማሪ እና ፀሐፊው፣ ባለትዳርና የአምስት ልጆች አባት ከሆኑት ከፕሮፌሰር አደም ካሚል ጋር በዓባይና በግብጽ ዙሪያ የተነጋገርነውን እንደሚከተለው አቅርበናል።
አዲስ ዘመን፡– ስለ ኢትዮጵያ ሲነሳ የሚቆጭዎት ነገር ምንድን ነው ?
ፕሮፌሰር አደም፡– ኢትዮጵያ ከመካከለኛው ምሥራቅ ጋር የሚያገናኛት የተለያዩ ጉዳዮች አሏት። በኢንቨስትመንት፣ በቱሪዝም፣ በንግድ አልተጠቀምንበትም። ይህንን ሁኔታ ባቅሜ ለማሳየት ትግል ላይ ነኝ። ሐበሻ የሚለው ስያሜ ከዓረብ አገር ከደቡብ ዓረቢያ የፈለሰ ነው፣ ሥልጣኔያችን እስከ አስዋን ግብጽ ይደርሳል። ሱዳንማ የእኛ ክልል ነበር። የመንን ከ72 ዓመታት በላይ ገዝተናል። ታሪካችንና ቅርሳችንን በሙሉ እዛ ታገኘዋለህ።
የውሃ ጉዳይ ከሰሜኑ (ከመካከለኛው ምሥራቅ) ጋር ያስተሳስረናል። የዓባይ ውሃ ባይኖር ግብጽ፣ ሱዳንም ባልነበሩ ነበር። እኛ የሰጠናቸው ውሃ እኮ ነው ለእነርሱም ሥልጣኔ ያመጣው፣ የቋንቋ ግንኙነት አለን። ግዕዝ ከጅዛን ከሳዑዲ ነው የመጣው። ዓረብኛና ትግርኛ ቅልቅል ነው። የእምነት ግንኙነትም ያስተሳስረናል።
የእስላማዊ ስደት ወደ ሐበሻ ዕቅድ፣ ዓላማውና ውጤቱ ከእዛው ጋር የሚያስተሳስረን ነው። አይሁድ ከ580 ከልደት በፊት፤ ክርስትና በ350 በኢዛና ዘመን ከእዛው ነው የመጣው። እስልምናም በ615 ከእዛ የመጣ ነው። ክርስቲያኖች ወደ ኢየሩሳሌም፣ ሙስሊሞች ወደ መካ መዲና ይሄዳሉ። ይሄ ሁሉ ታሪክ ነው፤ ግንኙነት ነው። ይሄ የኢትዮጵያ ትልቁ አሻራዋ ነው። በክርስትናም በእስልምናም ትልቅ ታሪክ አላት።
የንግድ ግንኙነትም ነበረ። በፊት ኢትዮጵያ የምታመርተውን በሙሉ የመካከለኛው ምሥራቅን በብቸኝነት ትመግብ ነበር። ከአክሱም ወደ አዱሊስ ቀጥሎም ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ይጓዝ ነበር። ምክንያቱም መሬታቸው የግመል ወተትና ቴምር ብቻ ነበር የሚያመርተው። የዓረባዊ ግንኙነት ወደ ኢትዮጵያ ቀጥሏል። እኛ ከሌሎች በተለየ እንግዶች እናከብራለን በመሆኑም ተከብረውና ተንከባክበው ወደ ሚይዟቸው ይሰደዱ ነበር። ተጋብተው ነግደው አገራቸው በኢኮኖሚ ሲሻሻል የአገራቸውን ባህልና የዘር ሐረጋቸውን ይዘው ተመልሰዋል። የሚያስተሳሰር የዘር ሐረግም አለን። ይሄንን ሁሉ ወደ ኢንቨስትመንትና ቱሪዝም መቀየር ነበረብን።
ግን በአገሪቱ ትልቁ ስህተት የነበረው በአፄዎቹ ዘመን የውጭ ግንኙነቱ ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት ብለው ከአሜሪካና ከምዕራባውያን ጋር አድርገው የቀደመውን ተውት። በፖለቲካ መቀራረብ የነበረው ሲሰረዝ ንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ ቱሪዝም ላይ ተጽዕኖ አስከተለ።
በደርግ ዘመን ደግሞ ግንኙነታችን ከሶሻሊስት አገሮች ኪዩባ፣ ራሺያ ጋር ተደረገ ። በኢህአዴግ ዘመንም አንድ የተሠራ ትልቅ ስህተት ነበር። ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ለዲፕሎማሲ የሚመደብ ዓረብኛ ቋንቋ የሚያውቅ መሆን አለበት። ለምን ቢባል ዲፕሎማሲ ማለት ሰርተፊኬት ያለው ሰላይ በመሆኑ። ማንበብ፣ መጻፍ ካልቻለ እንዴት ሪፖርት ማዘጋጀት ይችላል፣ ባስተርጓሚኮ ሚስጥራዊ ነገር አይሠራም። ጥያቄ አቅርቤም ‹‹መለኪያችን ለድርጅት ተአማኝነቱ ነው እንጂ ዓረብኛ ቻለ አልቻለ…›› የሚል መልስ አግኝቻለሁ። የእዛ ሁሉ ውጤት ኢትዮጵያ እንድትረሳ፣ ተፈጥሮዋ እንዳይታወቅ ለኢኮኖሚ፣ ለኢንቨስትመንት፣ ለቱሪዝም ያላትን ጥቅም እንድታጣ አድርጓል።
በቱሪዝም ዘርፍ ለገልፍ ነዋሪዎች የአገራቸው ሙቀት ሲጨምር ብንቀበላቸው የኢትዮጵያን አየር በቀን አንድ ሚሊዮን ብር ልንሸጥ እንችል ነበር። ሁሉም ተመሳሳይ የአየር ችግር ስላለባቸው ይፈልሳሉ። ስድስቱ የገልፍ አገራት ቀዝቃዛ አየር ለማግኘት በመጓጓዝ በዓመት 32 ቢሊዮን ዶላር ያወጣሉ። ባለመሥራታችን ያጣነው ነው። በፊት ወደ ሲሪያ ይሄዱ ነበር አሁን ፈርሳለች አታስተናግድም፣ በሊባኖስና በግብጽም አስተማማኝ ሁኔታ የለም። ትንሽ ሞሮኮ ትሻላለች። ባለፈው ዓመት 10 ሚሊዮን ቱሪስቶችን አስተናግዳለች።
ቱርክ በ2014 እ.ኤ.አ 34 ሚሊዮን የገልፍ ቱሪስቶችን አስተናግዳ 35 ቢሊዮን ዶላር አተረፈች። የነፍስ ወከፍ ገቢዋንም ከሁለት ሺህ ወደ አስር ሺህ ዶላር አደረሰች። ከውጭ ዕዳዋም ነፃ ሆነች። ኢትዮጵያ እንዳቀፈችው አይነት ደጋ፣ ወይና ደጋ ቆላማ አየር የትም መሬት አይገኝም። አሁን ህጋዊም ሆነ ሕገ ወጥ ስደት አይኖርም አገራት አዋጅ እያወጡ ናቸው። በመሆኑም አገር ውስጥ መሠራት አለበት። ሥራ አጥነት ካደገ፣ የኑሮ ውድነት ከጨመረና የውጭ ምንዛሬ ከጠፋ እልቂት ይሆናል። ባለፉት 27 ዓመታት ኢትዮጵያዊነት ተሰርዟል። ይሄ ትውልድ እንደገና መታደስ አለበት። አሁን ወጣቱን ወደ ልማት ማስገባት ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡– ስለ ዓባይ የሚነግሩኝ ነገር ምንድን ነው?
ፕሮፌሰር አደም፡– ትውልዱ ስለዓባይ ወይም ናይል ሙሉ መረጃ የለውም። ናይል ማለት በዓለም ትልቅ ርዝመት ያለው ወንዝ ነው። 6 ሺ 825 ኪሎ ሜትር ይረዝማል። 10 የአፍሪካ አገራትን ያካትታል። በእኛ ውሃ 25 ሚሊዮን ሱዳናዊ፣ 100 ሚሊዮን ግብጻውያን ይጠቀሙበታል። እርሱ እስትንፋሳቸው፣ ኑሯቸው፣ ህይወታቸውና ማገዷቸው ነው። ናይል ባይኖር ግብጽና ሱዳን ባልነበሩ። ወይም ስልጣኔያቸው ባልነበረ። 86 በመቶ ውሃ የሚሄደው ከኢትዮጵያ ነው። ናይል በእስልምና እምነት ውስጥ ትልቅ ክብር አለው። ናይል ለሰው ጥቅም እንዲሰጥ ተብሎ ከገነት የመጣ ነው።
ነብዩ አንድ ጊዜ ተጠየቁ፤ የሆነ ሰው አታክልቱን ለማጠጣት በመስኖ ይጠቀም ነበር። ከታች ያሉት ተነስተው ውሃ ገደበብን በማለት ለነብዩ ክስ መሰረቱ። ነብዩ እርሱ ከጨረሰ በኋላ ላንተ ደግሞ ይለቅልሃል አሉት። አንተ ከተጠቀምክ በኋላ በቃኝ ስትል ልቀቅለት ነበር ያሉት። ስለዚህም በነብዩ አባባልና አካሄድ መብታችሁ ስለሆነ በመጀመሪያ እናንተ ከተጠቀማችሁ በኋላ ወደሌላው እንድትለቁ ነው። በአንደኛነት ናይልን ኢትዮጵያ እንድትጠቀም የሚልም ነብያዊ ቃል አለ። ግብጾች ግን ይሄንን ክደውታል። ነብዩ መሀመድ ሐበሾች እስካልነኳችሁ ድረስ እንዳትነኳቸው ያሉትንም አንቀጽ ዘልለውታል። የሦስት ሺ ዓመት ስልጣኔ አለ ሲባል፤ ግዛታችን እስከ አስዋን ይደርስ ነበር። ስለናይልና ታሪካችንን የሚዘግብ በዓረብኛ ቋንቋ የተጻፉ 120 መረጃዎችን እናገኛለን። ናይል የኢትዮጵያ መሆኑን ያረጋግጣል።
ከውሃ በተጨማሪ በየዓመቱ 110 ሚሊዮን ቶን አፈር ጠርጎ ይወስዳል። ግን ሱዳኖችና ግብጾች የሚመጣው ደለል ግድባችንን እየሞላብን እየተቸገርን ነው። ለማውጣት ብዙ እናወጣለን ሲሉ ይደመጣል። ሆኖም አፈሩን ያነሱና ማዳበሪያ ጨምረው ለእርሻ ይጠቀሙበታል። ግብጾችም ሆኑ ሱዳኖች በመስኖ ልማት ተጠቃሚ ናቸው። የህዝባቸውን የአትክልት፣ የፍራፍሬና የምግብ ፍላጎት በሙሉ የሚያሟሉት የእኛን ውሃ ተጠቅመው ነው።
ከፍተኛ ኢንቨስትመንትም ይሰሩበታል። ሱዳን ውስጥ ስድስቱ የገልፍ አገራት የምግብ ዋስትና ችግር አለባቸው። የሳዑዲ ኢንቨስተሮች ትራክተራቸውን ይዘው ሱዳን ውስጥ ያመርታሉ። በተመሳሳይ ኢምሬቶች ከግብጽ መለዮ ለባሽ ጋር ተባብረው ግብጽ ውስጥ ያመርታሉ። የአሁን የግብጽ ጩኸት ግድቡ ኢትዮጵያ ውስጥ ቢገደብ ኢንቨስተሮች በሙሉ ወደ ኢትዮጵያ ይሄዳሉ ከሚል ስጋትም ነው። እስካሁን ይሄን የተገነዘበ ማንም የለም። ባለፉት 40 ዓመታት ታሪክ የናይልን ጉዳይ በሚመለከት በዓረቡ ዓለም 560 ጥናቶች ተካሂደዋል። የናይል አደጋ በምግብ ዋስትና፣ በመስኖ ልማት፣ በምግብ ስለሚያጋጥም ሁኔታና የመሳሰሉት ጥናቶች በዓረብኛ ቋንቋ ተካሂዷል። ኢትዮጵያ ግን አንድም ቀን አልተሳተፈችበትም።
በናይል ላይ ግድብ ቢሰራ ስለሚያስከትለው ችግርና የመሳሰሉት ቀደም ብሎ የተሰሩ ናቸው። እኛ በየዋህነት፣ ዓረብኛን ችላ በማለት ዋጋ ከፍለናል። እነ አሜሪካ፣ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝ፣ ራሺያ 24 ሰዓት በዓረብኛ ቋንቋ የሚሰራ ፕሮግራም አላቸው። የውሃ ምንጭ፣ የፖለቲካ ቀውስ፣ የመሣሪያ ሽያጭ የሚካሄድበት አገር ነው። ዓረብ ሆነው አይደለም ግን ጥቅም ፍለጋ ነው። እኛ ግን ካለን ግንኙነት፣ ከሚሰራብንም ደባ አውቀን ለመረዳትና ለመገንዘብ ዓረብኛ ቋንቋን አገለልን፤ ዓረብኛ ቋንቋ ማምጣት ማለት እስልምናን እንደማስገባት ተቆጠረ።
እንግሊዝና ግብጾች በዓባይ ወንዝ ጉዳይ አራት ስምምነቶች ተፈራርመዋል። 1906 እ.ኤ.አ ግን ኢትዮጵያ የለችበትም፣ 1929 እንግሊዝና ግብጾች የተፈራረሙበት ኢትዮጵያ አልተሳተፈችም። 1902 ግብጽና እንግሊዞች የተስማሙበት እንዲያውም ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ማንኛውንም ግድብ መሥራት የለባትም የሚል አንቀጽ ተካትቶበታል። ከዛም 1959 እ.ኤ.አ ግብጽና ሱዳን ኮታውን እራሳቸው የተከፋፈሉበት ነበር። ግብጾች 55 ነጥብ 5 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ እንዲያገኙ ተደረገ፤ በእዛውም ዕቅድ አወጡ 730 ሺ ሄክታር ለማልማት። ሱዳኖች በተፈቀደላቸው 17 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ አራት ሚሊዮን ሄክታር እንዲያለሙ ታቀደ። ይህ ስምምነት ሲካሄድ ኢትዮጵያ ለመሳተፍ አልተፈቀደላትም። ይሄ የተሰራብን ሌላው ደባ ነው።
አሁንም የውሃችን ጉዳይ በንቃት እንዳንከታተል በተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ የነበረውን የግብጽ ተወላጅ ቡትሮስ ቡትሮስ ጋሊን በመጠቀም ኤርትራን የማስገንጠል አጀንዳ ተጠነሰሰ። በቀይ ባህር ሱዳን፣ ጂቡቲ፣ ሶማሌ የዓረብ ሊግ አባል ናቸው። ስለዚህ ኤርትራ የምትባል ዓረባዊ ይዞታ የሚኖራት አገር መፍጠር አለብን ብሎ ነው የተሟሟተው። ይህንንም ተግባራዊ አደረገ። ኤርትራን በማስገንጠል ትልቅ ሚና የተጫወተው ቡትሮስ ቡትሮስ ጋሊ ነበር።
ቀይ ባህር በሙሉ ዓረባዊ ይዞታ እንዲኖረውና ኢትዮጵያን የማግለል ሁኔታ ነበር። ኢትዮጵያን ማግለል ማለት የናይል ጥያቄን አብሮ ማግለል ነበር። ኤርትራን በማስገንጠላቸው ትልቅ ችግር እንደቀለለላቸው ነበር የወሰዱት። ግን ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ መጀመሪያ ሥልጣኑን ሲረከቡ ወደ ጅዳ ሳይሆን ወደ እሥራኤል ነበር የሄዱት። ድካማቸው በሙሉ ዋጋ አጣ። እነዚህ ሁሉ ደባዎች ያኔ ሰርተውላቸዋል። አሁን በ21ኛው ክፍለ ዘመን ግን ኢትዮጵያ ነቅታ ግድቡን እየገነባች ትገኛለች።
አዲስ ዘመን፡– ግብጾችና ሱዳኖች ጋ ያለው አቋም እና ታሪካዊ እንቅስቃሴን እንዴት ይገልፁታል?
ፕሮፌሰር አደም፡– ሰላም ሂንዳዊ የምትባል የአልጀዚራ ጋዜጠኛ ኢትዮጵያ መጥታ ባህር ዳር ተጉዛ ስለዓባይ የሠራችው ዘገባ ነበር። እሷ የሠራችውን ያህል ለዓለም ግንዛቤ የሰጠ መረጃ ማንም አልሠራም። የባህር ዳር ነዋሪዎች በማገዶ ሲያበስሉ አየች፤ የዓባይ ልጆች ብላ ዘገበች። ወደ ሱዳን ተጉዛ በኤሌክትሪክ ሲጠቀሙ በኢትዮጵያ በዓባይ ውሃ ብላ ዘገበች፣ ወደ ግብጽ ሄደች ነውራቸው እንዳይታወቅ ቃለ ምልልሱን ከለከሏት ተመልሳ የያዘችውን አሰራጨች። ኢትዮጵያውያን ያለን ጥያቄ እነርሱ በኤሌክትሪክ እየተጠቀሙ ለእኛ ለምን ወንጀል ይሆናል? የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጨት፣ የህዝብን ኑሮ ማሻሻል ቀዳሚ ጥያቄ ነው።
ግድቡ ከሱዳን ጠረፍ በ40 ኪሎ ሜት ርቀት ነው ያለው። በአፍሪካ አንደኛ በዓለም 10 ኛ ሆኖ ተመድቧል። ከ1956 እስከ 1964 እ.ኤ.አ አሜሪካኖች ጥናት አድርገው በኢትዮጵያ ውስጥ ረሃብን ለመቅረፍ ግድብ ያስፈልጋል በሚል ተጠንቶ ቦታ ተመደበ። ከ2009 እስከ 2010 እ.ኤ.አ የኢትዮጵያ መንግሥት ጥናት፣ የቦታ ጠረጋ ዝግጅት አድርጎ በ2011 ለጣሊያናዊው ሳሊኒ ኩባንያ ተሰጠ። በእዛው ዓመትም በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ አማካኝነት የመሰረት ድንጋይ ተጥሏል። ኢትዮጵያ ከግብጽ ጋር መተባበር እችላለሁ ብላ መግለጫ ሰጠች፤ በቀጣዩ ዓመት የሚመነጨው የኤሌክትሪክ ሃይል መጠንን ይፋ አደረገች።
ግብጾችና ሱዳኖች ጋ ያለው አቋም ምን ይሆናል? የሚለውን ስናይ፤ ሱዳኖች ሶርሳ የሚባል ግድብ ሠርተዋል። ከእኛ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል። ሲናር እና መረዌ የሚባሉ ግድብም አላቸው። ግብጾች ሰዴ ለአሌ የሚባል ናስር ያቋቋመው ግድብ አላቸው። ሁለቱም የገደቡት የእኛን ውሃ በመተማመን ነው። በግድቡ ለእርሻም ይጠቀሙበታል። የግብጽ ደባና ሴራን ወደኋላ ተመልሰን እንይ። በመሃመድ አሊባሻ ጊዜ በምጽዋና በሐረር ገብተውብን ነበር። የኢትዮጵያን አንድነት የማፈራረስ ሁኔታ ነበር። በኸዲው እስማኤል ገዢያቸው ዘመን 1875 እ.ኤ.አ. የመጀመሪያውን የሠራዊት ዘመቻ አካሄዱብን። ተሸንፈው ወጡ። 1876 ሁለተኛውን ዘመቻ አካሄደ በኸዲው እስማኤል 20 ሺ ሠራዊት ነበር ይዞ የመጣው ተሸንፎ ወጣ። ዛሬ አይደለም ጥንትም ጀምሮ የግብጾች ተንኮል ነበር። ዛሬ በትንሹ ክብሪት እየጫረ ዕሳት የሚያቀጣጥለው ትውልድ ከውጭ የታቀደለትን ቢገነዘብ አንድም ነገር ባላደረገ ነበር።
የገማል አብድልናስር የሥልጣን ዘመን ሲመጣ አንድ ትልቅ የሠራው ነገር ቢኖር የአስዋንን ግድብ መገንባቱ ነው። ከእኛ ኢትዮጵያውያን ጋር በሚሰሩትም በሚያቅዱትም ጦርነት ከምንገባ ግድብ ከሰራን በኋላ ውሃውን ማጠራቀም እንችላለን የሚል ዕቅድ ነበረው። ኢትዮጵያ የሙስሊሙም የክርስቲያኑም አገር ስለሆነች በኢትዮጵያ ላይ መዝመት አንፈልግም ነበር ገማል አብድልናስር ያለው። በእርሱ ዘመን ያንን ግድብ ሠርቶ አለፈ። የአንዋር ሳዳት ዘመን ይዞ የመጣው ኢትዮጵያውያኖች አንድ ግድብ እንሰራለን ቢሉ ሠራዊቴን ይዤ እዘምትባቸዋለሁ የሚል ማስፈራሪያ ነበር። ግን አልዘመተም፣ አላደረገውም። መጨረሻ እርሱም ተገደለ።
የሁስኒ ሙባረክ ዘመን የጀኔራሎች አማካሪ ነበሩት፤ የፀጥታ አማካሪው፣ ጀነራል ዑመር ሱሌማን የጦር አዛዡና የመከላከያ ሚኒስቴሩ በመሆን በ2012 እ.ኤ.አ. ወደ ሱዳን ተጓዙ። ከአልበሽር ጋር ተነጋገሩ በኢትዮጵያና በሱዳን ድንበር የጦር ካምፕ ለማቋቋም ጠየቁ። ኢትዮጵያኖች ግድብ ለመሥራት ካቀዱ ከእዚህ ተነስተን እንመታለን የሚል ምክንያትም አቀረቡ። አልበሽር ፍቃደኛ አልሆነም። ቀጥሎ የሙርሲ ዘመን መጣ። ትልቅ ደባ የተፈፀመው አሁን ነው። በእዚህ ጊዜ ግድባችንን መሰረት ጥለናል። ግንቦት 26 ቀን 2005 ዓ.ም ኢትዮጵያኖች በታሪክ ሊከቱት ይገባል። ሙርሲ አስቸኳይ ስብሰባ ጠራ። የሃይማኖት መሪዎች፣ የጦር አዛዦች፣ ተፎካካሪ ፖለቲከኞች በተሳተፉበት፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ አደጋ እንደተጀመረና ምን መደረግ እንዳለበት ጥያቄ አቀረበ።
አምስት ዕቅዶች ቀረቡ። ያኔ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል እርቅ አልነበረም። ኤርትራ በኢትዮጵያ ላይ ያላትን ጥላቻ መነሻ በማድረግ አስፈላጊ ትጥቆችን በማሟላት በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት እንዲከፈት ማድረግ። ጂቡቲ በዓረብ ሊግ አባልነቷ በመጠቀም የምትሰጠውን የወደብ አገልግሎት እንድታቋርጥ። ሼክ ሙሀመድ አሊ አላሙዲ መሰረታቸው በኢትዮጵያ ቢሆንም ዜግነታቸው ሳዑዲ ስለሆነ ከሳዑዲዎች ጋር በመነጋገር በአገሪቱ ኢንቨስትመንታቸውን እንዲያቆሙና ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ማድረግ በዕቅድ ተቀመጠ። የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን በሥርዓቱ ላይ ማነሳሳት እንዲተገበር ከታለመው ይመደባል። የኦጋዴን ነፃ አውጭዎችን ቢሮ ሰጥቶ ማስታጠቅ። ከጀርባቸው ሶማሌ ስላለ ሱማሌን ይዘው እንዲዘምቱ ማድረግ የሃሳቡ አካለ ሆነ። ይህ በቀጥታ ሥርጭት የተላለፈ ነበር። ሙርሲ የምታወጣው ዕቅድ የነብዩን ቃላት፣ አደራ፣ ኑዛዜ መተላለፍ አይሆንም? ሐበሾች እስካልነኳችሁ እንዳትንኳቸው አላሉም ወይ በደንብ አስብበት በማለት ያሳሰቡም ነበሩ። ሙርሲም ከዚህ በኋላ ሁለት ወራት አልቆየም። ወደ እስር ቤት ተወረወረ።
አዲስ ዘመን፡– አሁነኛ ጩኸት በግብጽ በኩል መበርታቱ ምን ምክንያት አለው ይላሉ?
ፕሮፌሰር አደም፡– የአልሲሲ ዘመን ከመጣ በኋላ በ2015 እ.ኤ.አ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ፣ የሱዳን የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽር ባሉበት ስምምነት ተደርጓል። በውሉ እስከግድቡ ሙሌት ድረስ ተጠቅሷል። ያኔ አልሲሲ ተስማምቷል። አሁን ግብጾች ያንን ካዱት። ምክንያቱም ያኔ አልሲሲ ለሥልጣኑ አዲስ ስለነበር፣ የፖለቲካ ችሎታው በሳል ስላልነበረ፣ በቂ ግንዛቤ ስላልነበረው፣ አገር ውስጥ ከሙርሲ ደጋፊዎች ጋር ውዝግብ ውስጥ ስለነበር በቅን ልቦና ፈርሟል የሚል ነገር አለ። ግን በፖለቲካ ቅን ልቦና የሚባል ነገር የለም።
ያኔ የመነሻ ስምምነት ቢኖርም በእነርሱ የነበረው ግንዛቤ ኢትዮጵያኖች ሊሠሩ አይችሉምና ማንኛውንም ፈንድ ከውጭ እንዳያገኙ ገደብ እናድርግ የሚል እሳቤ ነበራቸው። ግብጾች በውጭ አገራት 80 ሺ የሚሆኑ ምሁራን አሏቸው። በተባበሩት መንግሥታት፣ በዓለም ባንክ፣ በዓረብ ሊግ፣ በጂሲሲና በመሳሰሉት ተቋማት አሉዋቸው። የጀርባ አጥንት የሆኗቸው የተማሩ ዜጎቻቸውን በተለያዩ ቦታዎች በትነዋቸዋል። ስለዚህ ኢትዮጵያ ከውጭ ዕርዳታ እንዳታገኝ ማዕቀብ መጣልን በዋናነት አስቀመጡ። ግን ባልጠበቁት ሁኔታ ግድቡ 40 በመቶ ደረሰ የሚል ዜና ተሰማ። አሁን መንቃት ጀመሩ። የአደጋ መብራት ቦግ ማለት ጀመረ። ያለረዳት በሁሉም ርብርብ መሠራት ሲጀመር ሊተገብሩ ነው በሚል ጩኸቱ በረታ። ለዚህ ብለውም ሦስት የተለያዩ ዘርፎች በአሁኑ ሰዓት አዋቀሩ።
ፖለቲካዊና ወታደራዊ ይዞታ ያለውና በአልሲሲ የሚመራ ሙሉ ሥልጣን ፓርላማው አፀደቀለት። አስፈላጊ ከሆነ ሚሊተሪውን፤ ቢያስፈልግ ደግሞ ፖለቲካውን በመጠቀም የሚያስፈልገውን እርምጃ መውሰድ እንዲችል ሥልጣን ሰጡት። ለእዚሁ ብሎ መዋቅሩን ዘረጋ። የወታደራዊ ክንፉን በሙሉ ያዘ።
የውጭ ቅስቀሳን በሚመለከት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለሳሚ ሽኩሪ ሃላፊነት ተሰጠ። ዲፕሎማሲያዊ ጫና እንዲያደርግ ነው። በመጀመሪያ በዓረብ ሊግ የግድቡን ግንባታ እና የዓባይን ውሃ ሙሌት የማስተጓጎል ሥራ ተጀመረ። ‹‹በእኛ ላይ ደባ አለ፣ አደጋ እየመጣ ነው፣ እኛንና ሱዳንን ሊያጠፉ ነው›› በሚል ጫና ለማድረግ ነበር። የዓረብ ሊግ ማዕከሉ ግብጽ ላይ ነው። በዓረብ ሊግ መሪነት በራሱ ዜጎች አማካኝነት መወንጀል ተጀመረ። ሳዑዲ፣ ግብጽ ባህሬን በየመን ጦርነት ህብረት ስላላቸው እነርሱንም ማቀፍ ጀመረ። ሌሎች ዓረብ አገራትንም ጎበኘ። አደጋው ለእኛም ለእናንተም ነው የሚል ቅስቀሳ በዓረቦች ተደረገ።
ወደ ተባበሩት መንግሥታት ቀጠለ። በመጀመሪያ ወደ አሜሪካ ተጓዘ። የውጭ ጉዳይን ሳይሆን የገንዘብ ሚኒስቴርንና የዓለም ባንክን አነጋገረ። በኢትዮጵያ ላይ በፈንድ ደረጃ ተጽዕኖ እንዲደረግ ወይም ማዕቀብ እንዲጣል ነበር። ቀጥሎም ወደ ፀጥታው ምክር ቤት ሄደ። በቅርቡ ዓረብ ሊግ ላይ ግብጽ ባደረገችው ሙከራ ከማዕቀብና ከእርምጃ በአቋም ደረጃ የረዱን ሱማሌ፣ ጂቡቲና ኳታር ናቸው። ትልቅ መስዋዕትነት ከፍለውልናል። የማይረሳ ውለታ ነው። አቋማቸው የመጣው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶክተር) ከሚሰጣቸው ግምት እና አክብሮት ነው። ስለሚያከብራቸው አከበሩት።
በተባበሩት መንግሥታት ሲቀርብ የመጀመሪያውን ትግል ያደረገችልን ደቡብ አፍሪካ ናት። ያም ከሸፈባቸው። ሁለተኛ ዙርም አስገብተው ነበር። የሰላምና የፀጥታ ጉዳይ በሚል አጀንዳውን አቀረቡ። ግን ውጤት አልባ ሆኑ። ወደአሜሪካ ቀረበ የአሜሪካም ተወካይ ‹‹ይሄ አፍሪካዊ ጉዳይ በመሆኑ በአፍሪካ ሕብረት ይፈታ›› ተብሎ ተመልሷል። ይህ ሁሉ ሲሆን ግብጾች አፍሪካዊነታቸውን ክደዋል። አፍሪካውያን ኢትዮጵያን ያከብራሉ። አሁን የዓባይ ጉዳይ ፍጥጫው እዚሁ ነው።
የግድቡን ቦታ አስመልክተው የመሬት ይዞታ ጥናት አድርገናል በሚል ስያሜ የመሬት መንቀጥቀጥ ባህሪ እያመጣ ነው፤ በቀን ሁለት ጊዜ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከስቷል። በእዚሀ የተነሳ በሳዑዱ ዓረቢያ ሁለት ክፍለ አገሮችን ነክቷል የሚል ቅሬታ አቅርበዋል። ግድቡ ደግሞ ውሃ ሙሌት ጨርሶ 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ውሃ በሚይዝበት ጊዜ ቢያንስ በአምስት ቀናት 17 ጊዜ የመሬት መንቀጥቀጥ ያመጣል። በእዚህ የተነሳ ቀይ ባህርን ይነካል፤ በዙሪያ ያሉትን አገራት በሙሉ ድምጥማጣቸውን ያጠፋል የሚል ጥናት ይዘዋል። ይህንንም ተቀማጭነቱን ግብጽ ላደረግው የሳዑዲ ኤምባሲ፣ ለገልፍ አገሮች ከእኛ ጋር አቋማችሁን አንፀባርቁ የሚል ጥያቄ አቀረቡ። ይሄ ሌላው በቴክኒክ ክፍሉ የተቀነባበረ ደባ ነው።
የፕሬሱን እንቅስቃሴ ለብቻው በባለቤትነት ይዞ የሚመራ አለ። ግብጾች አራት ሺ የሚሆን የዜና አውታሮች አሏቸው። ሁሉም በአንድ ጊዜ ይጮሃሉ። 99 በመቶ አጀንዳ የያዙት የናይልን ግድብ ጉዳይ ነው። የመሬት መንቀጥቀጥ ሊከሰት ነው፣ ኢትዮጵያ በህልውናችን መጣች፣ እኛ ልንጠፋ ነው፣ ግድቡ ቢሠራ እንኳን አገራቸው ውስጥ የተረጋጋ ሰላም ባለመኖሩ (ሰሞኑን የተፈጠረውን እንደማስረጃ ይዘው) የመጠበቅ አቅሟ ደካማ ነው፣ በተለማማጅ መሃንዲሶች የተሠራ ነው ወዘተ… የሚል ደባ አለ።
አዲስ ዘመን፡– የግብጽ የጦርነት ዘቻ ተግባራዊ የሚሆን ይመስልዎታል ? የግብጽ ጩኸት የአልሲሲን የሥልጣን ዘመን ለማራዘም የታቀደ ነው የሚሉም አሉና ምን ይላሉ ?
ፕሮፌሰር አደም፡– የሐሰት ፕሮፖጋንዳ መንዛት እንጂ ወደ ጦርነት አይገቡም። ኢትዮጵያን በቀጥታ ከመጋፈጥና ከመምታት ይልቅ እውስጧ የእርስ በእርስ ጦርነትና ግጭት መፍጠር ወደሚል ድምዳሜ ደርሰዋል። እነርሱ በቀጥታ ሠራዊት ማዘመት አይሆንላቸውም። ይልቅ ኢትዮጵያን እርስ በእርስ አበጣብጦ ክፍተት ሲገኝ ሃሳባቸውን መተግበር ነው። ይሄ ነው ጥንቃቄ የሚያሻውም። አልሲሲ ሥልጣን ሲረከብ የግብጽ የውጭ ዕዳ 6 ቢሊዮን ነበር። አሁን 122 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል። 36 በመቶ ሥራ አጥነት ተከስቷል። 60 ሺ የሚሆን የፖለቲካ እስረኛ አለ። በዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብት ኮሚቴ እየተወገዘች ትገኛለች። አልሲሲ ከቱርክ ጋር በሊቢያ የተነሳ ፍጥጫ ላይ ነው። በመሆኑም ሆን ተብሎ የአልሲሲን ሥልጣን ለማራዘም የሚሠራ የቤት ሥራም ነው።
ዋናው የቤት ሥራችን ሊሆን የሚገባው የኢትዮጵያውያንን አንድነት ማጠናከር ነው። ህዝቡ አንድነቱን ከጠበቀ ማንም የሚደፍረን የለም። ደግሞ ግድቡ የተገነባው እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ከኪሱ አውጥቶ ነው። ይሄንን ለመመከት ተዘጋጅቶ መጠበቅ ይገባል።
ግብጾች እስከ መጨረሻው አይተኙም። ሱዳኖችን ለማቀፍ የሚያደርጉት ጥረት አለ። ሱዳኖች ግን በሁለት እግር ነው የቆሙት። አንዱ ለኢትዮጵያ ድጋፍ የሚሰጥ ነው። ምክንያቱ ለሱዳን ሰላም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጥረት ባያደርጉ ዛሬ እንደ የመን፣ ሶሪያና ሊባኖስ ተወዛግበን ነበር በሚል ውለታ ይዘዋል። ከሱዳኖች ጋር በባህል፣ በድንበር በወግና በመሳሰሉት የተሳሰርን ነን። ዋናው የውስጥ አንድነታችንን ማጠናከር ነው፤ እንጂ የውጭው ሊያሰጋን አይችልም። ግድቡ ኤሌክትሪክ ያመነጫል፣ የውጭ ምንዛሬ ያስገኛል፣ ስደትን ይቀንሳል፣ መስኖ ማልማት ያስችላል፤ ይህ ደግሞ የምግብ ዋስትናን ያረጋግጣል፣ ሥራ አጥነትን ይቀርፋል። ግን ትልቅ የቤት ሥራ ይጠይቃል። ህብረት፣ አንድነት፣ ሰላምና መረጋጋት ይጠይቃል። ይህ ካለ ቱሪስቱም ይመጣል። እንዳጋጣሚ ቱሪስት፣ ንግድ፣ ኢንቨስትመንት እንደአፋር ግመል የተሳሰሩ ናቸው። አንዱ ሌላውን ይስባል።
አዲስ ዘመን፡– ኢትዮጵያ አሁን በያዘችው የውሃ ሙሌት ግብጽ እውነት እንደምትለው ትጎዳለች?
ፕሮፌሰር አደም፡– በትክክለኛ ሁኔታ ግብጾች አማራጭ አላቸው። ለአንድ ሺ ዓመት የውሃ እጥረት አያጋጥማቸውም። አንድም ሰድአሌ የሚባለው ትልቁ ግድባቸው ይመግባቸዋል። ሁለተኛ የከርሰ ምድር ውሃ ተጠቃሚ ይሆናሉ፤ አላቸው። ሦስተኛ የዝናብ ውሃ ማቆርም ሊከሰት ይችላል። ከቀይ ባህርና ከነጭ ባህር መጠቀም ይችላሉ። አጠቃቀም ላይ ልቅ ናቸው። 60 በመቶ የግብጽ ህዝብ ዓባይ ከኢትዮጵያ እንደሚሄድ አያውቁም እኮ። ኢትዮጵያውያኖች ዓባይን እንደማያውቁት፤ በአንፃሩ ግብጾች የራሳቸው አድርገው ነው የሚቆጥሩት። ስለዚህ ግብጾች አማራጭ አላቸው። የግብጽ ህዝብ ምንም ሳይከፍል የአባይን ውሃ ያገኛል።
መስኖ ያለማሉ፣ በመርከቦች ለቱሪስት ኪራይ ገቢ ያገኛሉ። አሁን ይህንን ትተው ውሃ ቆፍረው ለማግኘት መድከም አይፈልጉም። ውሃው ህይወታችን ብለው የሰየሙት ጉዳይም አለ። ይህ የአመለካከታቸው ችግር ነው። አሁን እጅ አንሰጥም። ውሃ ካልሞላን ትልቅ ሞት ነው፤ ገንዘብ አፍስሰንበታል። ከችግራችንም መውጣት አለብን። በእኛ ውሃ የሚኖር ግብጻዊና ሱዳናዊ እኮ ተጠንቀቁ እንደ ኢትዮጵያ እንዳትራቡ በሚል የ1977 ዓ.ም ረሃብን እያስታወሱ ይሳለቁብናል። ምሳሌ አድርገውናል። ያለፈው ታሪካችን ይበቃናል።
አዲስ ዘመን፡– ከድርድሩ በፊት የውሃ ሙሌቱ ቢከናወን ምን ይፈጠር ነበር? የግድቡን ሥራ ለማስተጓጎል በርካታ ነገር ሞክረዋል በቀጣይስ ምን ሊሞክሩ ይችላሉ ?
ፕሮፌሰር አደም፡– እውነቱን ልንገርህ ምንም የሚመጣ ነገር የለም! ሁልጊዜ ፕሮፖጋንዳቸው ከፍተኛ ነው። ጩኸቱ ሊያስደነግጠን አይገባም። ከግብጽ ጦር ሠራዊት ይልቅ የሚያሰጋኝ አገር ውስጥ ያለው አደጋ ነው። የመበታተን፣ እርስ በእርስ መጋጨት፣ ሃላፊነትን ያለመረዳት አገር ውስጥ ለማስፈን የሚደረገው ጥረት ትልቅ አደጋ ነው። ግብጾች የግድቡን ሥራ ለማስተጓጎል ከዚህ በኋላ ሊጠቀሙ የሚችሉት ብዙ ነገር አለ። ያልቆፈሩት መሬት፣ ያላንኳኩት በር የለም። ግን ሁሉም እየከሸፈ ነው የመጣው። አገር ውስጥ ግን ባልተሰራው ሥራ ለእነርሱ ድልን እያመቻቸን ነው ያለነው።
የግድቡን ጉዳይ ሲፈልጉ እስላማዊ ገጽታ ያስይዙታል። ለእስልምና ከእነርሱ በፊት የከፈልነውና ባለቤት መሆናችንን ለሙስሊሙ ዓለም ማሳሰብና ማስረዳት አለብን። የተጠናከረ የመጅሊስ ጉባኤ ቢኖር ኮንፍረንስ በማዘጋጀት፣ ጉዞ በማድረግ የነጃሺ ቢላል አገር መሆናችንን ማሳየት ያስፈልገናል። እስላማዊ ገጽታ የሚያንፀባርቁትን በዚህ ማምከን ይቻላል። እነዚህ ካሉ ግብጾችን ማሸነፍ ይቻላል። የግብጽ ተመራማሪ ምሁር ዛሬ ግብጻውያን እንደመረጃ የሚጠቀሙበትና የሚኮሩበት አብደልረሃማን ኢልጀበርቲ መሠረቱ ኢትዮጵያዊ ነው። ቱርክ፣ ኢንዶኔዢያ አሻራችን ይገኛል፣ ሳዑዲ የኡለማዎች፣ ሊቃውንቶች ይገኛል። ይህንን ታሪክ ማውጣት ያስፈልጋል። የዓረብኛ ቋንቋን በማስፋት የሚሰነዘርብንን ፕሮፓጋንዳ ለማፍረስ እና ትክክለኛ ገጽታ ለማንፀባረቅ መሠራት አለበት።
በሊቢያና በሶሪያ የደረሰው አይነት እንዳይረስ መጠንቀቅ ያስፈልጋል። የብዙሃን መገናኛ ሥራ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት መተግበር አለበት። የልማትና የሰላም ጉዳይ ከፍተኛ ቦታ ተሰጥቶት መሠራት አለበት። ሰላም ከሌለ ኢንቨስትመንት አይኖርም፣ ቱሪዝምና ንግድም አይኖርም። የኢትዮጵያን ትክክለኛ ገጽታ መገንባት በመካከለኛው ምሥራቅ ባሉ አምባሳደሮች አማካኝነት መሠራት አለበት። የግብጾችን ሴራ ለማፍረስ ጠንካራ ዲፕሎማሲ መሠራት አለበት። በሰሞኑ ግርግርም በዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብት ኮሚቴ ሰዎች ይታሰራሉ የሚል አጀንዳም ሊያመጡብን ይችላሉ ለእዚህም መጠንቀቅ ያስፈልጋል። በዚህ ወቅት ዋናው ኢትዮጵያዊነት ወሳኝ ነው። አፍሪካውያን በሙሉ ኢትዮጵያን ያመልካሉ ለእዚህም ነው ግብጽ ዘግይታ የመጣችው። እናም ብዙ ሥራ ይጠብቀናል።
አዲስ ዘመን፡– ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ!
ፕሮፌሰር አደም፡– እኔም ለተሰጠኝ ዕድል አመሰግናለሁ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 15/2012
ዘላለም ግዛው