አራት ኪሎ የሠልስቱ ፓርላማዎች ወንበር
ከታሪክ ምሁራንና ተመራማሪዎች በተሻለ ቅርበት አራት ኪሎን የሚናፍቋት፣ የሚመኟትና በህልምም ሆነ በቅዠት የሚንገበገቡላት ከታሪክ ምሁራን ይልቅ ሥልጣን ናፋቂዎቹ ፖለቲከኞች መሆናቸው በሚገባ ይታወቃል። “ለታሪክ ባለሙያዎች ይብላኝላቸው እንጂ” አራት ኪሎ፤ በተለይም ፓርላማው የቆመበት ማዕከላዊው ስትራቴጂክ ቦታ፤ በአግባቡ ቢመረመር ብዙ ጉዳዮችን ማጤን ይቻላል።
አራት ኪሎ የሀገሪቱ የሥልጣን ሽክርክሪት ማዕከል ከመሆኑ የተነሳ በርካታ ታሪኮቻችን የሰመሩበት፣ የጨነገፉበት፣ ያለቀስንባቸውና የፈነደቅንባቸው በርካታ ትርዒቶች የተከወኑበትና እየተከወኑ ያሉበት መድረክ ስለመሆኑ የበረታ ብዕረኛ ዕድሉን ባገኘበት ጊዜ ዝርዝሩን ያስነብበን ይሆናል።
በግሌ አራት ኪሎን የማውቀው የመኖሪያ ቤቴን ያህል በቅርበት ነው። የሠልስቱ ፓርላማዎቻችን ወንበረተኞች ሲወጡና ሲገቡ መመልከት የጀመርኩት ገና ከጨቅላ ዕድሜዬ ጀምሮ ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ ከምድረ ኮልፌ ተስፈንጥሬ ራሴን አራት ኪሎ ያገኘሁት “ማሙሽ” እየተባልኩ በምጠራበት የዕድሜ ዘመኔ ሲሆን ሰበቡ ደግሞ የትምህርት ጥማቴ ነበር።
ፓርላማውን በቅርብ ርቀት ተጎራብቶ የሚገኘው የጥንቱ የአራት ኪሎ ወጣቶች ወንዶች ክርስቲያናዊ ማኅበር-ወወክማ (የዛሬው ሕጻናትና ወጣቶች ቴያትር ቤት) የቋንቋ፣ የብሔር፣ የሃይማኖት ልዩነት ሳያደርግ በልዩ የሙከራ ፕሮጀክት በውድድር ፈትኖ ለአንደኛ ደረጃ ትምህርት ከመረጣቸው ጥቂት “የትውልድ ተስፋ” ተማሪዎች መካከል አንዱ ስለነበርኩ ከአራት ኪሎ ጋር የተዋወቅሁት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነው። የመለስተኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ለሦስት ዓመታት ያህል እዚያው አራት ኪሎ ዳግማዊ ምኒልክ ት/ቤት፣ የሦስተኛ ደረጃ ትምህርቴን ስድስት ኪሎ ዩኒቨርስቲ፣ የመጀመሪያ የሥራ ቦታዬ መሃል አራት ኪሎ በሚገኘው አንጋፋው ማተሚያ ቤት፣ ዛሬም ቢሮዬ የሚገኘው ከፓርላማው አጥር ትይዩ ስለሆነ የዕድሜዬ አብዛኛው ጉዞ የተከወነው እዚሁ ታሪካዊ አካባቢ በመሽከርከር ነው ብዬ በድፍረት የምናገረው ስለዚሁ ነው።
በጥቂቱም ቢሆን ያስተዋልኳቸው የዓለማችን አንዳንድ ታላላቅ ከተሞች የፓርላማችን መቀመጫ የሆነውን የአራት ኪሎን ያህል ታሪክ ይኑራቸው አይኑራቸው እርግጠኛ አይደለሁም። የፖለቲካ ታሪኮቻችን እምብርት ስለሆነው ስለ ፓርላማው ውሎ አምሽቶ መለስተኛ ቅኝት ከማድረጋችን አስቀድሞ ሕንጻው የቆመበትን ጂኦግራፊያዊ ዙሪያ ገብ በጥቂቱም ቢሆን መቃኙቱ አግባብ ይሆናል። በሰሜን አቅጣጫ ቤተ ክህነቱና የሀገሪቱ ቀደምት ዩኒቨርስቲ ይጎራበቱታል። በስተምዕራብ አንጋፋው ማተሚያ ቤትና የፕሬስ ድርጅት ለቡና በሚጠራሩበት ርቀት ተጠግተውታል። በስተደቡብ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት፣ ታላቁ የምኒልክ ቤተ መንግሥትና የታችኛው የኢዮቤልዩ ቤተ መንግሥት ሽቅብ ደግፈውታል።
በደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ ብሔራዊ ቴያትር፣ ብሔራዊ ባንክና የብሔራዊ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ሕንጻ ተንጠራርተው ይመለከቱታል። በስተምስራቅ የአፍሪካ ኩራት የሆነው አየር መንገድ በቅርብ ርቀት ይቃኘዋል። የሚኒስቴር መ/ቤቶች ከፓርላማው ጋር ያላቸውን ድንበረተኝነትና ርቀት ስንመለከትም ግጥምጥሞሹ ለግርምት የሚዳርግ ይሆናል። የትምህርት፣ የገንዘብ፣ የውጭ ጉዳይ፣ የመከላከያ፣ የትራንስፖርት፣
የባህልና ቱሪዝም፣ የሠራተኛና ማሕበራዊ ጉዳይ ወዘተ. ሚኒስቴር መ/ቤቶች የሚገኙበትን አድራሻ እንኳን ብናጤን የፓርላማ ሕንጻውንና ተጎራባች ተቋማቱን በስትራቴጂክ ጥናት የገነቡትን አስተዋይ መሪዎቻችንን ማመስገን ብቻ ሳይሆን በርካታ ትርጓሜ እንድንሰጥም እንገደዳለን። ስለዚህ ስለ ምሥጢረኛው ፓርላማ ዙሪያ ጋብ የማደርገውን መለስተኛ ቅኝት ለጊዜው እዚህ ላይ ገታ በማድረግ የተነሳሁበትን የሠልስቱን ፓርላማዎቻችንን የዘመን ቀለማት ወግ በጥቂቱም ቢሆን እያዋዛሁ ልጠቃቅስ።
ቀዳሚው የባለ ካባዎች ፓርላማ፤
የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ጸድቆ ሥራ ላይ የዋለው ሐምሌ 9 ቀን 1923 ዓ.ም ሲሆን፤ የሕገ መንግሥቱን መጽደቅ ተከትሎ የላይኛው ምክር ቤት (በጊዜው አጠራር ሴናው) እና የታችኛው ምክር ቤት (ፓርላማው) ለመጀመሪያ ጊዜ ሥራቸውን የጀመሩት ጥቅምት 23 ቀን 1924 ዓ.ም ነበር። ከሃያ አምስት ዓመታት በኋላ በ1948 ዓ.ም የተሻሻለው ሕገ መንግሥትም ቢሆን በአቀራረብ ይለይ ካልሆነ በስተቀር በመሠረታዊ ይዘት ሲመረመር እጅግም ልዩነት ነበረው ማለት የሚቻል አይመስለኝም። በተቋቋሙት ምክር ቤቶች የሚወከሉትን የሕዝብ ተወካዮች በተመለከተ ንጉሠ ነገሥቱ የመጀመሪያውን ምክር ቤቶች የመጀመሪያ ስብሰባ በንግግር ሲከፍቱ የተናገሩትን ብንመረምር ለወንበሮቹ ይታጩ የነበሩት ካባ ለባሾቹ የምክር ቤት አባላት እነማን እንደነበሩ በቀላሉ መገመት ይቻላል። “መሣፍንትና መኳንንት፣ ባላባቶችም እናንተ ለዚህ ጉባኤ ተጠርታችሁ የተሰበሰባችሁት የመንግሥታችንን የሥራ ሃሳብ ትካፈላላችሁ ብለን አደራ ስለጣልንባችሁ ነው።” (ቀ.ኃ.ሥ. ሐምሌ 14 ቀን 1924 ዓ.ም)።
በዓይነ ግቡ ካባዎችና በተንቆጠቆጡ የደረት ኒሻኖችና ሜዳሊያዎች ተውበው የገዘፉት እነዚያ የቀደምት ፓርላማው አባላት በአብዛኛው አመራረጣቸው በመወለድ፣ በደም ትሥሥር፣ ወይንም በሀብትና በአካባቢ ተጽእኖ ፈጣሪነታቸው እየተመረጡ እንጂ ሕዝቡ በአንድ ድምፅ ይወክሉኛል፣ ለልማቴም ሆነ ለጥቃቴ ቀድመው ይቆሙልኛል በሚል ሕዝባዊ ወገንተኝነት እንጂ “ዲሞክራሲው ደግፏቸው” አይመስለኝም። እንደዚያም ቢሆን ግን ለሀገራቸውና ለሕዝባቸው ጥቅም የሠሩ፣ ለተመረጡበት አካባቢ ቁም ነገር በማበርከት የተመሰገኑና የሕዝብ አክብሮት የተጎናጸፉ የሕዝብ ተወካዮች አልነበሩም ማለት አይደለም።
ይህ ጸሐፊ በጨቅላነት እድሜው የፓርላማ ሕንጻውን እየታከከ ወደ ወወክማ ት/ቤቱ ዘወትር ሲመላለስ እነዚያን ጎምቱና የገዘፉ የፓርላማ አባላት ወደ ስብሰባቸው እስኪገቡ ድረስ በሕንጻው ፊት ለፊት በጥቂት ቡድኖች ተሰባስበው በጉባዔያቸው ላይ ስለሚያራምዱት አቋምና ስለሚደረስባቸው ውሳኔዎችና ጉዳዮች ሲከራከሩና ሲመካከሩ ደጋግሜ አስተውያለሁ። ምናልባትም የልጅነት ዕድሜዬ ምክንያት ሆኖም ሊሆን ይችላል እነዚያን “ለምድር ለሰማይ የከበዱ” አዛውንት የፓርላማ አባላትን አንድ ሁለቴ ተጠግቼ በምን ርዕሰ ጉዳይ ላይ እንደሚነጋገሩ ለመስማት “ወግድ ሳይሉኝ” የልጅነቴን ቅን ጆሮዎች ጣል አድርጌ ጭውውታቸውን ማድመጤን አስታውሳለሁ።
በዚያው ደጉ የልጅነት ዘመን በየአካባቢው የፓርላማ አባላቱ “ምርጫ” ሲከናወን እጩዎቹ ያድርጓቸው የነበሩት ቅስቀሳዎችና በየቦታው የሚለጠፉት ፖስተሮችና የምርጫ ምልክቶች ዛሬም ድረስ ከትዝታዬ አልጠፉም። ካልተሳሳትኩ የምንኖርበትን አካባቢ ወክለው የተወዳደሩት የተከበሩ አቶ ዘውዴ ቢራቱንና አቶ በሪሁን የሚባሉ ግለሰቦች የህልም ያህል ውል ይሉብኛል። የተመራጭ ወገኖችና ደጋፊዎች ቤት ለቤት እየዞሩ “እከሌን ምረጡ!” በማለትም ይቀሰቅሱ እንደነበር በሚገባ አስታውሳለሁ። አንዳንድ የወቅቱ ተመራጮች በነፍስ ወከፍ ሁለት ብርና አንዳንዴም ከዚያ በላይ እየሰጡ ለመመረጥ ቀብድ ያሲዙ እንደነበር በስፋት ሲወራ አድምጫለሁ።
በጅባትና ሜጫ አውራጃ የግንደበረት ወረዳን ወክለው “በእጅ ጭራ ምልክት” በመወዳደር አንድ የምርጫ ዙር ያሸነፉትና ለቤተሰቤ ቅርብ የነበሩት ባላምባራስ ምናሴ ነገዎ ያሳተሙትን ፖስተር ለእናቴ ልከው ለረጂም ጊዜያት ያህል በቤታችን ግድግዳ ላይ ተለጥፎ በክብር እንደኖረ አስታውሳለሁ። እኒሁ ሰው በሁለተኛው ምርጫ ልዩ ምልክታቸው የነበረውን ጭራ ለለውጥ ያህል ከቀኝ ወደ ግራ አድርገው ቢወዳደሩም በሌላ ሰው ስለተሸነፉ ውጤት አልባነታቸውን “እንደ መጥፎ ምልኪ” በመቁጠር “የግራ ነገር ግራ ነው” በማለት መጸጸታቸው በስፋት ተወርቷል።
የቀድሞ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት የነበሩትና በወዳጅነታቸውና በአባትነታቸው ሁሌም ሳከብራቸው የምኖረው ነፍሰ ሄር ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ያጫወቱኝ እውነተኛ ወግ ዛሬም ድረስ ፈገግ ያስደርገኛል። ክቡርነታቸው በአዲስ አበባ ከተማ የተወዳደሩት መኖሪያቸው ጄኔራል ዊንጌት ት/ቤት አካባቢ ከነበረው ከካህኑ ከመምሬ ዘውዴ ጋር ነበር። እኒህ ካህን የጓደኞቼ ወላጅ አባት ስለሆኑ በቅርብ አውቃቸዋለሁ። ውድድራቸው እየተፋፋመ በሄደበት አንድ ዕለት ትንታጎቹ የጄኔራል ዊንጌት “ጂኒዬስ” ተማሪዎች ሁለቱ እጩዎች ስለ ሀገራቸው ያላቸውን ራእይ ፊት ለፊት ቀርበው እንዲያስረዱና እንዲከራከሩ ይጋብዟቸዋል። በመጀመሪያ የክርክሩ እድል የተሰጠው ለግርማ ወ/ጊዮርጊስ ነበር። ክቡርነታቸው ጊዜ ሳያባክኑ ለእነዚያ ባለ ምጡቅ አእምሮ ተማሪዎች አንድ ጥያቄ ብቻ ሰንዝረው ንግግራቸውን አቆሙ። እንዲህ ነበር ያሏቸው፤ “የመንግሥተ ሰማያትን ጽድቅ የምትናፍቁ ከሆነ መምሬ ዘውዴን ምረጧቸው፤ የለም ኢትዮጵያ ወደፊት እንድትራመድ እንፈልጋለን የምትሉ ከሆነ ደግሞ እኔን ምረጡ።” ክርክሩ ከዚያ በኋላ አልቀጠለም። መምሬ ዘውዴ በሀዘን፣ ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ደግሞ የአሸናፊነት ድል ቀንቷቸው ክርክሩ በአጭሩ ተጠናቀቀ። ይህ ቀዳማይ የፓርላማ ዘመን ብዙ ኅብረ ቀለማት ያለው ስለሆነ ለማሳያነት የጠቃቀስኳቸው ወጎች ይበቁ ይመስለኛል።
የዝሆኖቹ ስብስብ የዘመነ ደርግ ሸንጎ፤
ዘመነ ደርግን የተሻገርነው ወጣትነታችን አሳቆን፣ በሞት ጥላ መካከል እያለፍንና የጓደኞቻችን በድን በየጎዳናው ተሰጥቶ ስናይ ከደም ጋር የተቀላቀለ እንባ እያነባን ጭምር ነበር። ከበርካታ የእልቂትና የጦርነት ዘመቻዎች ለወሬ ነጋሪ ተርፈን የዛሬን ጀንበር ለማየት የታደልነው እኔና ዘመነ አቻዎቼ ፈጣሪን ደጋግመን ብናመሰግን ቢያንስበት እንጂ አይበዛትም። እ.ኤ.አ ከ1977ቱ የሶቪዬት ሕብረት ሕገ መንግሥት የተቀዳው የወታደራዊው ደርግ ሕገ መንግሥት ጥር 24 ቀን 1979 ዓ.ም ጸድቆ ሥራ ላይ የዋለው መስከረም 1 ቀን 1980 ዓ.ም ነበር። በሕገ መንግሥቱ መሠረት በተደረገው የይስሙላና የማጭበርበሪያ የብሔራዊ ሸንጎ (ፓርላማ) ምርጫ 835 መቀመጫዎቹ በሙሉ የተያዙት የዝሆን ምልክት በነበራቸው የኢሠፓ አባላት ነበር። ለነገሩ ለአጃቢነት በተለያዩ ምልክቶች የተወዳደሩት ሌሎች እጬዎችም ሙሉ ለሙሉ የዚያው ፓርቲ ውላጆች ነበሩ።
በእለቱ የተደረገው “ብሔራዊ ምርጫ” ሳይጠናቀቅ ውጤቱ ቀደም ብሎ ተዘጋጅቶ ለህትመት መላኩ በማስረጃ ሊረጋገጥ የሚችል ታሪክ ነው። ከሰሜን ኮርያ በተቀዳ ደማቅ ሰማያዊ ካኪ ዩኒፎርም የደመቁት አዲሶቹ የሸንጎው አባላትና ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች የመጀመሪያ ጉባኤያቸውን ባደረጉ እለት በአራት ኪሎና በአካባቢው የነበረውን መሬት አንቀጥቅጥ ትርዒት ያዩ የዓይን ምስክሮች ትዝታው ከአእምሯቸው ይጠፋል የሚል ግምት የለኝም።
ሸንጎው በስራ ላይ በነበረባቸው ጥቂት ዓመታት በአብዛኛው ሲመክርባቸውና ሲያዳምጣቸው ከከረ መባቸው ዋነኛ አጀንዳዎች መካከል ከወቅቱ አማፅያን ጋር በሀገራችን ሰሜናዊ ክፍል ሲደረጉ የነበሩ የወንድማማቾች የእርስ በእርስ ጦርነቶች እንደነበር አይዘነጋም። ይህ የደርግ ሸንጎ በዋነኛነት ትቶልን ያለፈው የጋራ ትዝታ
የወያኔ/ኢህአዴግ በረኸኞች አራት ኪሎ አፍንጫ ሥር ተቃርበው በነበረበት የመጨረሻ ሰዓት በተጠራው ጉባኤ ላይ የማከብራቸው መምህሬ ዶ/ር ኃይሉ አርአያ “መንግሥትና ሕዝብ ሆድና ጀርባ ሆነዋል” በማለት የተናገሩትና አንድ ካህን ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለ ማርያምን ከፍና ዝቅ አድርገው “እዚሁ ወንበርዎት ላይ ቋንጣ ሆነው ደርቀው ይቀራሉ እንጂ የሚከዱን አይመስለኝም” የሚለው ትንቢታቸው ባይሰራም ድፍረታቸው ግን በታሪክ ተደጋግሞ ሲጠቀስ የሚኖር ይመስለኛል። የዚህ የዳግማዊ ሸንጎ የዘመን ቀለማት ወግ የተቀመመው በአብዛኛው በሕዝብ እንባና ደም፣ መግለጽ በሚያዳግት የዜጎች እልቂትና በጦርነት የፍልሚያ ታሪኮች ስለነበር ሁሉን ዘርዝሮ ለመዝለቅ ያዳግታል።
ሣልሳዊው የዘመነ ኢህአዴግ ፓርላማ፤
ኅዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም ጸድቆ ከነሐሴ 15 ቀን 1987 ዓ.ም ጀምሮ በሥራ ላይ በዋለው ሕገ መንግሥት መሠረት እስከ ዛሬ አምስት “የሕዝብ ተወካዮች” ምርጫዎች ተደርገዋል። የፌዴራል ሥርዓትንና የመገንጠልን ሃሳብ አቀንቃኙና “ኮሮጆ ገልባጭ” እየተባለ የሚወቀሰው የኢህአዴግ መንግሥት “ሳይቸግር ጤፍ ብድር” እንዲሉ ለዘር፣ ለቋንቋና ለብሔር እንጂ ለትልቋ ሉዓላዊት ኢትዮጵያ ደንታ ስላልነበረው የደረሰውንና እየደረሰ ያለውን አደጋ በየእለቱ እየተጋፈጥን ስለሆነ ብዙ ማለቱ ተገቢ አይመስለኝም።
ከሰኔ 30 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ የአምስት ዓመታት ሥራውን አጠናቆ በኮቪድ 19 ምክንያት ጥቂት ወራቶች የተመረቁለት ባለ 547 መቀመጫ ባለቤቱ ፓርላማ (ያለፉትን ሁለት የሪፎርም ዓመታትን ሳይጨምር) “ተወካዮቹ” እንደምንና በእነማን ትእዛዝና ሥልጣን ሲመሩ እንደነበር መዘርዘሩ ቀባሪን የማርዳት ያህል የቀለለ ስለሚሆንብኝ ብዙ ትንታኔ ለመስጠት አልደፍርም። “አንድ ወንበር” እንኳ አሳልፎ ለሌሎች ለመስጠት ንፍገት የተጠናወተውና መቶ በመቶ የገዢው ፓርቲ አባላት የተከማቹበት ይህ ፓርላማ የድፍርስ ታሪኩ ድብልቅልቅ ቀለማት ወደፊት በታሪክ መዝጋቢዎች በዝርዝር እስኪገላለጥ ድረስ መጠበቁ ግድ ነው። ከሪፎርሙ ወዲህ ባሉት ሁለት ዓመታት ውስጥ “የወተት ጥርስ” ማብቀል የጀመረው ፓርላማ “በሕገ መንግሥት ትርጉም መልካም ፈቃድ” በተመረቁለት የተወሰኑ ወራት የተሻለ ነፍስ ዘርቶ እንደምናየው ተስፋ አደርጋለሁ።
እስከዚያው ግን ምንም እንኳ በተወካዮቹ መካከል የትምህርት፣ የብቃትና የአቅም ልዩነት መኖሩን ሳንዘነጋ ጠቅላይ ሚኒስትሩንና ፈጻሚ ተቋማትን ጠርተው ሥራቸውን ሲገመግሙ ቢቻል የሚጠይቋቸውን ጥያቄዎች በጥናትና በምርምር አበልጽገው በቃል እያብራሩ ይሞግቷቸው። ይህም የማይሆን ከሆነ ተጽፎ የሚሰጣቸውን በአግባቡ የሚያነቡ ተወካዮች ይመረጡ። በሀገር እና በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ወይንም በሀገር ውስጥ ሚዲያዎች ላይ የሚቀርቡ “ተወካዮች” ብቃትና አቅምም በአግባቡ ይፈተሽ። በተረፈ የፓርላማ አባላቱ ቢያንስ “የሕዝብ ተወካዮች” የሚል ማዕረግ ስለተሸከሙ በማሕበረሰቡ መካከል ሲመላለሱ ጥበብና ትህትና ተላብሰው ቢሆን ተከብረው ይከበራሉ።
አንድ ምሳሌ ላስታውስ፤ በአንድ ወቅት በዚሁ ጋዜጣ ላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ሀገራዊ የሽልማት ፕሮግራም በሚካሄድበት አንድ ስብሰባ ላይ ከፓርላማችን ወንበረተኞች መካከል አንዱ ከተቀመጥኩበት ቦታ ድረስ መጥተው “ይህ የፊት ለፊት ወንበር ሁሌም የተመደበው ለፓርላማ አባላት ነው ተነሳልኝ!” በማለት የዜግነት መብቴን የተጋፉትን “የተከበሩ የሕዝብ ተወካይ” ድርጊት እስከ እለተ ሞቴ ድረስ የምረሳው አይደለም። የሚገርመው ነገር እኒያ “የተከበሩት” ግለሰብ አላወቁትም እንጂ ተሸላሚዎቹን ከመረጡት አምስት ዳኞች መካከል አንዱ ስለነበርኩ የፕሮግራሙ አዘጋጆች እዚያ ቦታ ያስቀመጡኝ ተገቢ ቦታህ ነው ብለው ቀድመው በመወሰን ነበር። ይህንን ለአብነት አነሳሁ እንጂ ብዙዎቹ “የተከበሩ” የሚለውን ማእረጋቸውን በምሳሌነት ቢያሳዩ ይበልጥ እንደሚከበሩ ይጠፋቸዋል ብዬ አልዳፈርም። በተረፈ ይህ በታሪካችን ሦስተኛ ረድፍ ላይ የተቀመጠውን የፓርላማ ክራሞት ወግ እንደ ጀማሪ ሠዓሊ የቀለም ብሩሾች አልከስክሼው ከሆነ ወደፊት ደግሜ ስለምመለስበት ያን ጊዜ እክሳለሁ። ሰላም ይሁን!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 15/2012
በጌታቸው በለጠ/ዳግላስ ጴጥሮስ