ኢትዮጵያውያን የዛፍ ችግኝ ተከላን የሕይወታቸው አንድ አካል አድርገውታል፡፡ በየአቅራቢያቸው በደጃቸው የሚተክሉት እንዳለ ሆኖ በየዓመቱ ችግኞችን ሆ ብለው ራቅ ብለው ሄደው ይተክላሉ፡፡ ይህ ተግባራቸው ሰኔ ግም ሲል አንስቶ ባሉት የክረምት ወራት አይስተጓጎልም፡፡ ይህን ተከትሎም እየተመናመነ ሄዶ 4 በመቶ ብቻ ቀርቶ የነበረው የሀገሪቱ የደን ሽፋን ወደ 15 በመቶ ከፍ ማለት ችሏል፡፡
ኢትዮጵያውያን የችግኝ ተከላን ባህል አድርገውታል፡፡ ሰኔ ግም ሲል በየደጃቸው፣ በየክፍት ቦታቸው እንደ ዛፉ ዓይነት በየጓሮአቸውም ይተክላሉ፤ አጥበቀውም ይንከባከባሉ፡፡ ለኢትዮጵያውያን ደን ማለት ብዙ ነገር ነው፤ ቤት መሥሪያው አጥር ማጠሪያው፣ ማገዶው፣ ተሰባስቦ መምከሪያው፣ ማሩ፣ ወዘተ ነው፡፡ የአፈር መሸርሸርን መከላከያው፣ የእንጨት ኢንዱስትሪው ግብዓት ነው፤ ከፀሐይ ሃሩር መሸሺያው፣ ቀዝቃዛ ንፋስ ለጋሹ ደን ነው፡፡ በሐዘን በደስታውም አረንጓዴ ነገር እና የእንጨት ውጤት በእጅጉ ይፈለጋል፡፡ ዛሬ ብዙ ነገሮች የእንጨትን ቦታ ብረት፣ ኮንክሪትና የመሳሰሉት እየተኩት ቢመጡም እንጨት ውበት ሆኖ ለተለያዩ ነገሮች እየዋለ ነው፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ መከላከያው አንዱ መሣሪያም ደን ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያም ከአየር ንብረት ጋር የሚስማማ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመግንባት ስትወስን የደን ልማትን ዋና ሥራዋ ለማድረግ አስባ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ደግሞ የደን ልማት ማለት ታላቁ ህዳሴ ግድብን ወደፊት ሊከሰት ከሚችል መታደግ ማለት ነው፡፡ በመሆኑም የደን ልማት ለኢትዮጵያ እጅግ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያም በየዓመቱ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን መትከል ውስጥ የገባቸው ለእዚህ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥታት ይህን የደን ልማት በማስተባበር በኩል ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን እየመራ ያለው የለውጥ መንግሥትም ይህንኑ የቅብብሎሽ ሥራ አጠናክሮ ቀጥሏል፡ ፡ ባለፈው ዓመት አራት ቢሊዮን ችግኞችን መትከል ተችሏል፡፡ በዚህ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በአንድ ጀምበር 200 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ ከዕቅዱ በላይ ችግኞችን መትከል ተችሏል፡፡ ይህም በዓለም በአንድ ጀምበር የተካሄደ ከፍተኛው የችግኝ መጠን በሚልም ተመዝግቧል፡፡
በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብርም አምስት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ ተከላው እየተካሄደ ይገኛል፡፡ ለእዚህም 5 ነጥብ 9 ቢሊዮን ችግኞች ተዘጋጅተዋል፡፡ እስከ አለፈው ሳምንት መጨረሻ ድረስም ሁለት ቢሊዮን ችግኞችን መትከል ተችሏል፡፡ በእዚህ በሐምሌ አጋማሽ ላይ ይህን ያህል አፈፃፀም ላይ መድረስ አበረታች ሊባል የሚችል ቢሆንም ተከላውን ከወዲሁ አጠናክሮ መቀጠል በችግኞች የጽድቀት ዕድል ላይ ፋይዳው ከፍተኛ እንደመሆኑ ሊተኮርበት ይገባል፡፡
የዘንድሮው የችግኝ ተከላ ሀገሪቱ በኮቪድ 19 ሳቢያ ችግር ውስጥ ባለችበት፣ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ መገኘት ያላስደሰታቸው ግብጽን ጨምሮ የተለያዩ ኃይሎች ግንባታውን ለማደናቀፍ ሰፊ ርብርብ እያደረጉ ባለበት ወቅት መሆኑ በሚፈለገው ፍጥነት እንዳይካሄድ ሊያደርገው ይችል ይሆናል፡፡ እርግጥ ነው ዘንድሮ በኮቪድ የተነሳ እንዳለፈው ዓመት እንደ ሀገር ሁሉም ሰው ወጥቶ ችግኝ ሊተክል የሚችልበት ሁኔታ ላይኖር ይችላል፡፡
መንግሥትም እንደ ሀገር የሚካሄደውን ተከላ ሰርዞ በክልል እና በተቋማት ደረጃ በሚካሄደው ላይ አተኮሮ እየሠራ ነው፡፡ ኮሮናን እየተከላከሉ ችግኝ ተከላውን ማካሄድ እንደሚቻል ታምኖበት እየተሠራ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት በአማራ ክልል በአንድ ጀምበር 200 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ ከ190 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለመተከል ተችሏል፡፡ በኦሮሚያ ክልልም እንዲሁ በሚቀጥለው ሳምንት እንደ ክልል የችግኝ ተከላ ይካሄዳል፡፡ በዚህም በአንድ ቀን 304 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዷል፡፡ ሌሎች ክልሎችም የራሳቸውን መርሃ ግብር አውጥተው ተከላውን እያካሄዱ ናቸው፡፡ እንደ ትምሀርት ሚኒስቴር ያሉ ተቋማትም በራሳቸው መርሃ ግብር ቀርፀው እየተንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ በዚህ በአስቸጋሪ ወቅት ችግኝ ለመትከል እየተደረገ ያለው ይህ ርብርብ ሊበረታታ ይገባዋል፡፡
ባለፈው ዓመት በአንድ ጀምበር ለመትከል ከተያዘው 200 ሚሊዮን በላይ ችግኞች በአንድ ጀምበር መተከሉ ሲታወስ አሁን በክልሎች አቅም በቀን እየተተከለ ያለው የችግኝ ብዛት የተቀመጠውን ዕቅድ ማሳካት እንደሚቻል ያመለክታል፡፡ የችግኝ ተከላው ዜጎች አረንጓዴ አሻራቸውን የሚያሳርፉበት እንደመሆኑ ይህን ለማሳካት የኮሮና ቫይረስ መስፋፋትን በማያስከትል መልኩ የቀደሙት ዓመታት የችግኝ ተከላ ልምዶቻችንን በመቀመር በችግኝ ተከላው የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት ከሁላችንም ብዙ ይጠበቃል፡፡
አዲስ ዘመን ሀምሌ 14፣ 2012