የትኛውም ማህበረሰብ በየትኛውም ዘመን እና የዓለም ክፍል ቢኖርም የኔ የራሴ ነው የሚለው ማንነት አለው። ይህ ማንነት ዝም ብሎ በዘፈቀደ የተገነባ ፤ ወቅታዊ ንፋስ በነፈሰ ቁጥር የሚፈርስ አይደለም። የዚያኔ ማህበረሰቡ ታሪካዊ እውነታ መሰረት አድርጎ በዘመናት መካከል በትውልዶች የሚገነባ፤ ለዚያ ማህበረሰብ ስጋና ደም ሆኖ የተንሰላሰለ የህያውነቱ መሰረት ነው። ከዚያም ባለፈ ቀጣይ ዕጣ ፋንታው የሚወሰነውም በዚሁ በእውነተኛ ማንነቱ መሰረት ላይ ነው።
በትውልዶች መካከል ለሚኖረው ሕያውነትም መሰረቱ ይኸው እውነተኛ ማንነቱን ፈልጎ የማግኘቱና በዚያ ማንነቱ የመገንባቱ ምስጢር ነው። ማንነቱን በታሪክ አጋጣሚ የተነጠቀ ማህበረሰብ እንደ ማህበረሰብ የመዝለቁ ጉዳይ በብዙ ለጥያቄ የሚቀርብ ነው። ከዚህ የተነሳም እያንዳንዱ ማህበረሰብ ትውልዶች በእውነተኛ ማንነታቸው ተቀርጸው እንዲያድጉ ብዙ ዋጋ ይከፍላል፡፡ በከፈለው ዋጋ መጠንም የተረጋጋ ማሕበረሰብ ሆኖ መቀጠል ይችላል። በዘመናት መካከልም ሀገርና ህዝብ ሆኖ መቀጠል ይችላል።
እኛ ኢትዮጵያው እንደሀገር እና እንደ አንድ ታላቅ ህዝብ የራሳችን የሆነ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍ ያሉ እውቅና እና ከበሬታ ያተረፉልን የብዙ ማንነቶች ባለቤት እንደሆንን ዛሬም ቢሆን ብዙ የታሪክ ጸሐፍት በብእሮቻቸው የሚመሰክሩት ነው።
በልዩነት ለሚፈጠር ማህበራዊ ውበት ተምሳሌት ሆነን ስንወደስባቸው የነበሩት ዘመናት ሰፊ ናቸው፤ በሞራል አሴቶቻችን ጥልቅነት በዓለም አቀፍ ደረጃ የነበረን ስምና ዝና ለጥያቄ የሚቀርብ አልነበረም። በከፉ የረሃብና የችግር ወቅቶች ከረሃብና ከችግር በላይ ሆነው ማንነታችንን በአደባባይ ያስመሰከሩ ነበሩ። ለሀገር ፍቅር የነበረን ቀናዊነት ከቋንቋ ባለፈ በአስቸጋሪና ፈታኝ ወቅቶች በእሳት ተፈትኖ እንደ ጠራ ወርቅ ነበር።
የብዙ ብሄር፣ ብህረሰቦችን እና ህዝቦች፤ ከዚያም በላይ ሃይማኖቶች ሀገር ከመሆናችን በላይ በብዙ ሰብዓዊ እስቶቻችን ከዘርና ከሃይመኖቶች በላይ ሆነን ተከባብረን፣ተዋደን እና ተቻችለን በመኖር የመቻቻል ተምሳልቶች ሆነን የተቀረጽንባቸው ዘመናት ብዙ ሩቅ አይደሉም።
ኢትዮጵያ አማራው ከኦሮሞው፤ ትግሬው ከጉራጌው፤ ሲዳማው ከከፋው፤ ሶማሌው ከአፋሩ፤ እስላሙ ከክርስቲያኑ፤ ዋቄፈታው ከክርስቲያን እስላሙ ከሁሉም በሚበልጠው ሰብዓዊ የፍቅር ጉልበት ተዋህዶ የሚኖርባት ሀገር እንደነበረች ዛሬ ላይ ሕያው የሆኑ
ምስክሮችን መቁጠር የሚከብድ አይደለም።
ኢትዮጵያውያን በዘመናት መካከል ባሳላፏቸው የፍቅርና የአብሮነት ህይወት ሕያው ምስክሮች ኢትዮጵያዊነት ያሳለፋቸው ዘመናትን መቁጠር ለብቻው ከምስክርነት በላይ እንደሆነ ለባለ አዕምሮ ፍጡር ግር የሚያሰኝ እውነታ ሊሆንም አይችልም። ለትናንትናው መሰረታችን ለሆነው ትውልድ ኢትዮጵያውያን የአብሮነት ግም ድ ደማቅ ውበት ነበር።
ዛሬ ግን አውቀነው ይሆን ሳናውቀው፤ አስበነው /የገበያ ሸቀጥ አድርገነው/ ይሁን ባለማወቅ ይህ የዘመናት አብሮነታቸውንና የውበታችን መሰረት የሆነው የማንነታችን አቁማዳ አርግበነዋል። በመርገቡም ልቅ ወጥተናል፤ ከእውነተኛ ማንነታችን ወርደን ማንነታችን ለሚያሰጋቸው ጠላቶቻችን እራሳችንን አሳልፈን ሰጥተናል።
በዘመናት መካከል በብዙ ትውልዶች የተገነባው ማንነታችንን በፖለቲካ ሊሂቃኖችንን የወንበር ጥማት በሴራ ተወስዶብናል። ከትልቁ ማንነታችን ከሱ ከመነጨው ከሰብዓዊ አስቶቻችን ወርደን እንፈስበት ዘንድ በተዘጋጀልን የዝቅጠት ቦይ እየፈሰስን እንገኝለን። እለት ተእለት እየወረድን ዓለምን ባስደነገጠ ሰብዓዊነት ባጣ ምግባር እየተገለጥን ነው።
እቤት ውስጥ ተወልዶ ያደገን የቤት እንስሳ አርዶ ለመብላት የሚጨንቃቸው አባቶች ልጆች ሆነን፤ ዛሬ የገዛ ወንድማችንን ፣አብሮ አደግ ወገናችንን ዘር እና ሃይማኖት ቆጥረን በጠራራ ፀሐይ ገድለን በበድኑ ላይ የምንፎከር ሆነናል። በችግር እየተፈተነ በሞትና በህይወት መካከል ሆኖ በቅርብ ያለን ምግብ ለመብላት ፈቃድ የሚጠብቅ ትውልድ ዘር ሆነን ዛሬ የወገናችንን ንብረት በጠራራ ፀሐይ ዘርፈን ለመሄድ፣ ለዝርፊያችን ምክንያት የምንፈልግ እስከ መሆን ምን አደነደነን?
ትናንት አባቶች እግር ስር ተቀምጠን ለመማር የነበረን ትልቅ ጥልቅ መሻት የት ጠፍቶ ነው፣ ዛሬ የአባቶችን ምክርና ተግሳጽ ላለመስማት የአመጻ ልጆች የሆነው። በህግ አምላክ ብለው ህግን ከቁሳዊው ዓለም ባለፈ ገዥ አድርገው የሚያስቡና በዚህም ዕለት ተዕለት ህይወታቸውን በታማኝነት የሚመሩ አባቶች ልጆች ሆነን ዛሬ ባልተገባ መፋነን ከህግ የበላይ የሆንን እስኪመስለን ድረስ የሳትነው እኝ ማን ነን?
እኛ የአባቶቻችን ልጆች ነን ! ከትልቁ ሰብዓዊ ማንነታችን ወርደን እና ዘቅጠን በዘር የድሪቶ ማንነት ገልምተን፤ ግራ ተጋብተን በራሳቸን እጅ ልንጠፋ አይገባም። መጪውን ትውልድ ግራ ተጋብተን ግራ ልናጋባ አይገባም። ከሰብዓዊነት በተጣላ ሃይማኖታዊ እሴቶች ስተን የነገውን ትውልድ መንፈሳና ቁሳዊ ህይወት ልናበላሽ አይገባም። ፖለቲከኞቻችን በሰጡን ትንሸ ማንነት ትልቁን ማንነታችንን አጥተን በፈጠሩልን ጭለማ ውስጥ ልንዳክርም አይገባም።
ኢትዮጵያዊነት ውበታችን ትልቁ ማንነታችን የአብሮነታችን አልፋና ኦሜጋችን ነው። ወደዚህ የአብሮነት ማንነታችን ልንመለስ ይገባል። የመንደር ማንነት እንደ ህዝብ ይህን ዘመን ሊያሸግረን ቀርቶ መንገድ ሊያስጀምረን አይችልም። በዘመነ ግሎባላይዜሽን ሰፊውን መንገድ ትተን ጠባቡን መንገድ መም ረጥ አንድም ማ ስተዋል ማጣት ነው። ከዚህ ካለፈ ደግሞ ለአዳኛችን የአደን ትሩፋት መሆ ን ነው።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 13/2012