እዚያ የዓባይ መድረሻ አገር ሌቱ የቀን ያህል ደምቆ ይታያል፤ በረሀው የክረምት ዝናብ በበቂ መጠን ያገኘ ያህል ለምልሞ ህይወት ለነዋሪው ምቹ ሆኗል:: መብራት እያንዳንዱ ቤት ተዳርሶ ውሃ በበቂ ሁኔታ ሁሉም ጋር ቀርቦ ያለ ስስት ይንቸረፈፋል፡፡ የዚህ ሁሉ ምንጭ ዓባይ ነው:: አዎ እዚያ ይህ ሁሉ የተፈጠረው የዓባይ ውሃ ትሩፋት በዓባይ ውሃ የተገኘ በረከት ነው፡፡ ሰፋፊ እርሻዎች ህዝብን የሚያጠግብ ምርት አቅርበው ገበያው ላይ ያለ ችግር ሸመታ ተጧጡፏል:: መድረሻው ከመነሻው በብዙ ተሽሎ ወደፊትም መቀበል እንጂ መስጠትም አልፈልግም የሚል እብሪት ተፀናውቶታል::
እዚህ ደግሞ ከአባይ መነሻ አገር እንኳን ሌቱ ቀኑም በጨለማ የሚያሳልፍ በርክቷል፡፡ ብዙ የመስራት ፍላጎት በኤሌክትሪክ ሀይል እጥረት ተገቷል:: 40 በመቶ ህዝብ መብራትን በናፍቆት ይጠባበቃል:: በምግብ እህል እራሱን ያልቻለና በድህነት የሚኖር አርሷደር፤ በግብርና ምርት እጥረት የሚቸገር ከተሜ ከመነሻው በርክቷል:: መነሻው ከመድረሻው በብዙ ርቆ መስጠትን እንጂ መጠቀም ሳይችል ዘመናትን ተሻግሯል፡፡
ይህ ልዩነት የሚታይ ለሁሉም ግልፅ የሆነ በዓባይ መነሻና በዓባይ መድረሻ አገራት ላይ የሚስተዋል እውነት ነው፡፡ ዛሬ ይህን እውነት ለመቀየር ለዘመናት ፍትህ የተቀሙት ነቅተው ለዘመናት ብቻዬን ያሉት ባይፈልጉም እኛም ልንጠቀም የሚገባንን ያህል የሰፋም ባይሆን ከሚገባን በጥቂቱ ብቻ መጠቀም እንጀምር ማለታቸው ለዚህም ወደ ተግባር ገብተው ወደ መሻታቸው እየገሰገሱ ይገኛሉ፡፡
እዚህ ከአባይ መነሻ አገር ባይፈልጉም የሚሰሙት እውነት ይታያል፡፡ በዚህ አገርን የተሻለች ለማድረግ ህዝብን የመለወጥ ያላሰለሰ ጥረት ውስጥ አገር ከማለት ይልቅ የግል ፍላጎት መሰረት አድርጎ ከተቃራኒ ወገን ጋር ሊቆሙ የሞከሩትን ማየት እጅጉን ያሳፍራል:: ፕሮጀክቱን እንዳይሳካ የሚሞክር ስለ አገር ግድ የማይሰጠው ስለ ወገኑ የማይጨንቀው በዚህች ሀገር ላይ መብቀሉ ሲታይ ምንኛ ይከፋል፡፡ አባቶች አገሬን ክብሬን ብለው የተዋደቁላት ምድር እንዴት ከባዕድ ጋር ቆሞ ለመናድ ይሞከራል፡፡
እዚያ ከአባይ መድረሻ አገር ካይሮ ደግሞ ይሄ ይታያል:: እርስ በርስ በተለያዩ ልዩነቶች ቢፋተጉም ስለአገራቸው ሲሉ አንድ ይሆናሉ፡፡ በአገር ውስጥ ጉዳያቸው ቢሻኮቱም በአገር ጥቅም ላይ ከማንም ጋር አያብሩም፡፡ የእነዚያ ፀብ በአገር ውስጥ ጉዳይ እንጂ በአገራዊ ብሄራዊ ጉዳይ ላይ ሲሆን ይረግባል፡፡
እዚያ የዓባይ መድረሻዋ አገር ላይ ስለ ዓባይ ሲነገር ሁሉም በአንድ ድምፅ የኛ ብቻ ማለትን ያዘወትራል:: ስለ ዓባይ ሲነገር ያለ ልዩነት የሀገር ጥቅም ለማስከበር ዓባይን ትክክል ባይሆንም የራስ ብቻ ለማድረግ በአንድነት ይዘመታል፡፡ ፍትሀዊ አለመሆኑን ሁሉም እያወቁት የሀገር ጉዳይ ብለው ዓባይማ ህይወታችን ነው እዚህ ላይ ልዩነት ብሎ ነገር አንቀበልም፡፡ ዓባይ ሊነካብን የሞከረ እረፍ ከማለት እንዲያርፍ እስከማድረግ በጋራ እንዘምታለን ማለትን ያዘወትራሉ::
እዚህ የዓባይ መነሻዋ አገር ላይ ስለ ዓባይ የማይገደው ስለ ግድቡ የማይጨንቀው አፉን ሞልቶ ሲናገር ይሰማል፡፡ አንድ መሆን ቆርቶ መቀራረብን እንኳን አርቆ እቅዱ እንዳይሳካ ከእነዚያ ጋር አብሮ የሚሰራ ከአገሩ የራቀ አገሬ ማግኘት ከባድ አይደለም:: ሁሉም አንድ ሆኖ ቆሞ ስለ ዓባይ ጉዳይ ስለ ግድቡ መስመር ስለ አገሩ ለውጥና እድገት ሲናገር መስማት ይናፍቃል፡፡ ዓባይ የመድረሻው ያህል መፈጠሪያው ላይ ህብረትና አንድነት ይጎለዋል፡፡ አንዳንድ ለሀገር ሁሉ ነገራቸውን ሰጥተው ከራስ ጥቅም ይልቅ እሷን ብለው የሚተጉ ልጆች በዓባይ መነሻ ላይ አልነጠፉምና የሌሎኞቹ ከንቱ ጥረት እንዳይሰምር ሆኗል፡፡
ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ጉዳይ አይደራደሩም እየተባለ ለዘመናት ሲነገር በእውነትም ሲታይ የቆየው ልማድ ዛሬ ላይ በአንዳንድ እራስ ወዳዶችና ጥቅም አሳዳጆች ጥያቄ ውስጥ የወደቀ ይመስላል፡፡ ደግነቱ ጥቂት ናቸውና ከበዙት አገር ወዳዶች እጅግ ያነሱ ናቸውና የእነርሱም የላኳቸውም ህልም መክኖ አገሬን የሚሉት ወገኔን ብለው ለፀኑት የተሻለ መሆኑን ቀጥሏል፡፡
እንዴት አገር ላይ ይህን ያደርጋሉ የሚባሉት የሚበልጡ አገሬን ክብሬ የሚሉ እርግጥም በዝተው አሉ:: በዓባይ መነሻ ላይ ለአገር የሚሞቱ ለእናት ምድራቸው እራሳቸውን የሚሰጡ እልፎች፡፡ አዎ ! ኢትዮጵያውያን ለዘመናት የናፈቀቻቸውን ብርሀን እንደሌሎቹ ሁሉ እነሱም ማየትን ተመኝተው ከራሳቸው ግዛት የሚመነጨውንው ሀብታቸውን አልምተው ለመጠቀም ቆርጠዋል፡፡ ግብፆች የኢትዮጵያን ለውጥ ባይወዱም ኢትዮጵያውያን ግን መለወጥን ከዚያ በላይ ፈልገውት ነበርና በዓባይ ግድብ ህዳሴያቸውን አልመው ጅማሮውን በተሳካ መልኩ በመከወን ላይ ይገኛሉ፡፡
እነዚያ የአባይ መዳረሻ አገራት ሀሰት የያዙት ጩኸታቸው በርትቶ ዓለም ላይ ቢናኝም እዚህ የአባይ መነሻዋ ምድር ያለው እውነት ነውና አድሮ መጉላቱ አይቀርም፡፡አዎ! ኢትዮጵያ እውነት አላት፡፡ ለእውነት መቆም ነፃነት ያጎናፅፋል፡፡ ሀገሬን ማለት ክብርን ያላብሳል:: እነዚያ ሀሰት ላቆመው የጮሁትን ያህል እኛ እውነት ላይ ሆነን የሚገባን የራሳችን ሆኖ ሳለ ድምፃችን መለዘቡ ለዚህ ትልቅ ማሳያ ነው፡፡
ወዳጄ ህዝብህ ደስታህ ከእጅህ እንዳይወጣ ከራስህ አስቀድመህ ወገኔን በል፡፡ ባንተ አገርህ እንዲደሰት ትፈልጋለህን? ስለ አገርህ እራስህን ስጥ፤ አገርና ወገንህን ካስቀደምክ ባትለብስ የሰው ፍቅር ትሞቃለህ፤ በአገርህ ለውጥና ክብር ምቾት ይሰማሀል:: ወገን ስለ አገር ብለህ ከእነዚያ መሻልን እንጂ መባሰን አትተግብር፡፡እነዚያ ስለ አገራቸው ጥቅም ብለው ብዙ ሲሉ እኛ ስለ አገራችን ጥቅም ስለ ህዝባችን ለውጥ ዝም ካልን እነዚያ ከኛ ተሻሉ ማለት አይደል፡፡
ይህች ታላቅ አገር ታላቅ ሀሳብ ይዘን ይበልጥ ማተለቅ ሲገባን ለማሳነስ መሞከራችን ያስተዛዝባል:: ፍቅር አተን እንጂ ምን ይጎለን ነበር፡፡ በተጓዝንበት በደረሰበት ሁሉ ስለ አገራችን የሚሰብከው መልካም ነገር ስንቶቻችን ይሆን ጆሮ ሰጥነት የምንሰማው፤ ምን ያህሎቻችንስ ነን ከልብ የምናዳምጠው፡፡ ከምንም ነገር አስበልጠን አገር ማለትንስ ምን ያህል ተገበርን፡፡
እኛና እነሱ በዚህ ያለን እነሱ ስለአገራቸው ጥቅም አንድ ሆነው ሲቆም እኛ የአገር ጥቅም ከማስቀደም ይልቅ የግል ጉዳያችን ከፊት አድርገን የአገር ጉዳይ ላይ ለዝበን እንታያለን:: አባይ እዚያ ቱርፋቱን በብዙ ሲጠቀሙበት አባይ እዚህ ትርፉ ርቆን ዘመናት አልፎናል፡፡ አባይ እዚያ ህይወት ሲሉት አባይ እዚህ በዘፈን እና በዜማ እየተሸኘ ዘመናት አልፏል፡፡ዛሬ ያ ቀን ተለውጦ ዓባይ እዚያ የነበረውን ለውጥ እዚህም ለመጀመር እዚያ በዓባይ መድረሻ ላይ እየሄደ ይፈነጥቀው የነበረው ብርሀን እዚህ በመነሻውም አጥለቅልቆ እንዲያልፍ ተገዷል፡፡አዲስ ዘመን ሐምሌ 12, 2012
ተገኝ ብሩ