“ስምህኮ ነው?”

“አይሽ አይሽና ሳቅ ይከጅለኛል፣

እኔ ያሳለፍኩት ባንቺ ይታየኛል።”

የሚለው የሙሉቀን መለሰን ዘፈን በምዘውረው ላንድ ሮቨር መኪና ሬዲዮ በስሱ ያንቆረቁራል። ስንኙን ተከትዬ የሃሳቤን ማግ ሳጠነጥን “ቅርብ ናቂ ሩቅ ናፋቂ ነው፤ አስተዳደጉ ግልብ አይደለም ወይ?” ከሚሉ ነገር ፈታዮች ጋር ተተበተበና ለኔ ዘመን ትውልድ በትረዘንግ ሆኜ የተቃጣበትን የስድብ ፍላጻ እከላከልለት ዘንድ ከኮሶ የሚመር፣ እንደርጥብ ቆዳ የሚከብድና እንደሳማ የሚለበልብ አመክኖ ከትዝታዬ ቋት ውስጥ መዠረጥኩ።

ከማን ምን አይተን ለማን ምን እናስተምር? የሚለው ጥያቄ በሕሊናዬ እየተንከላወሰ እረፍት ሲነሳኝ ጉንጭ የሚሞላ፣ አንጀት አርስና ሆድ የሚያጠግብ መልስ ፍለጋ ብኳትን የሀገሬን ባድማ የሰው ሀገር አረም ወርሶት ልብ አልኩ፤ እየተዟዟርኩ ስጎበኝ ጨንጨር ላይ የተዘራውን እህል ፍግ ላይ የበቀለው ቂሎ ሰልቅጦት ባየሁ ጊዜ አስተሳሰባቸውን የቀለም እንቦጭ የዋጠውና እድሚያቸውን የእንጨት ሽበት የወረረው ያንቱታ በሽታ ያለባቸው ሰዎች ታወሱኝ።

የዛሬ ተስፋቸው የነጠፈ፣ የነገ ሕልማቸው የቀነጨረ፣ ያልዘሩትን ለማጨድ የሚሹ ከንቱዎች የኔን ዘመን ትውልድ ለመንቀፍ ምን ሞራል አላቸው? በየሚዲያው ስክሪን እየተሰኩ፣ በየመድረኩ እየተደነቀሩ የሚነግሩን ቅድስናቸውን እንጂ ከስህተታቸው እንማር ዘንድ ልምዳቸውን በግልጽ አያወጉንም፤ ይባስ ብሎ ካገኙት በረከት እንድንካፈል ማቅረብ ሳይሆን መግፋት ነው የተጣባቸው። ለዚህም ይመስለኛል ድምጸመረዋው ሙሉቀን መለሰ

“ትናንትም አልበላሁ ዛሬም ጾሜን አደርኩ፣

ሰውም አልጠየቀኝ እኔም አልተናገርኩ።”

ያለው፤ ለነገሩ ከነዚህ ሰዎች ማጀት የሚያቅር ብስናታም ዝክር እንጂ ምን ጥሩ ነገር ሊገኝ? ይህን ሳስብ አንድ ጊዜ ባለቅኔው ሙሉጌታ ተስፋዬ አያ ሙሌ ያጫወተኝ ወግ ትዝ አለኝና ላካፍላችሁ ወደድኩ።

ከላይ ሙሉ ሱፍ ደርግሞ ከታች ባዶ እግሩን ሆኖ እየተጓዘ ነው፤ ያየው ሰው ሁሉ “አያ ሙሌ አንተስ አንዴ ለይቶልሃል፤ ባይሆን እንኳን ለልብሱ ክብር ብትጨነቅ ምን አለበት?” ይለዋል። እና ጎበዝ! ሳያውቅ ጠምጣሚ ሳይወድ ሳሚ እንጉላይ ሰዎች በበዙባት ሀገር የኔ ዘመን ወጣት ምን አይቶ ምን እንዲሆን ይከጀላል? በመልካም ሥነምግባር ትውልድ ቀርጾ በወዙ ሀገር አንጾ የላቡን አሻራ ከማስቀመጥ ይልቅ ጥፋቱን ብቻ እየነቀሰ የወጣቱን ሞራል ማድቀቅ ሥነልቦናውን ማሸማቀቅ ይቀናዋል፤ በዚህም ምክንያት ትውልድ የሚሰናሰልበት ድልድይ ተሰብሮ ክፍተቱን አስፍቶታል። ለዚህ ሳይሆን አይቀርም ባለቅኔው ገጣሚ አያ ሙሌ

“ለጥርሰፍንጭት ልጅ አውግቻት የሆዴን፣

ስትስቅ ብትበትነው ወፍ ለቀመው ጉዴን።”

ሲል የተቀኘው።

ትርምስ በማያጣው የአዲስ አበባ መንገድ ስሽሎከሎክ ቆይቼ አራት ኪሎ አምባሳደር አካባቢ ጋር ደረስኩና መኪናዬን ለማቆም ዩ ስትሪት ፓርኪንግ ስገባ ባለትህትና ወጣት በፈገግታ ተቀበለኝ። ትኬት ዘየረኝና መኪናዬን ሰልፍ ካሲያዝኩ በኋላ የሥራ ኃላፊዎችን አስፈቅጄ ድምጹንና ምስሉን ለማስቀረት መቅረጸ ድምጼንና ካሜራዬን ወድሬ ያሰናዳኋቸውን ጥያቄዎቼን በወግ እያዋዛሁ እሰልቅ ጀመር።

በወርሃ ሕዳር ሃያ አራት 1993 ዓመተ ምህረት ከአባቱ አቶ ገብረወልድ ሰቄና ከናቱ ከወይዘሮ መንበረ ናሁሰናይ የተወለደውና ለቤቱ የመጀመሪያ ልጅ የሆነው ናትናኤል “መጥላት ያለብን ዝቅ ብሎ መቅረትን እንጂ የመነሳት ዝቅታን አይደለም” ሲለኝ ማለፊያ ጨዋታው ቀልቤን ገዛውና እንደንብ ቀዋሁት። የጸደይ አበባ በመዓዛው ማረፊያ ፍለጋ የምትቃብዘውን ንብ ከሩቅ ይስባታል፤ ሸጋ ወግም ጋዜጠኛን እንዲሁ።

የቤት ቁመና ከመሰረቱ የልጅ አስተዳደግ ከሂደቱ እንደሆነ ይታወቃልና ለመሆኑ የመጣህበት ሁነት ምን ይመስላል? ስል የመኸር ጥያቄዬን አቀበልኩት። ሃሳቡን ለመቅለብ ጆሮዬን አቁሜ ልቦናዬን በማስላት ቆቅ እየሆንኩ። ጂባ፣ ቢታኒያ፣ ፕሪንስ፣ ብላቴናና ማይ ሊትል ኤንግል አካዳሚዎች፣ ስላሴ ካቴድራልና መነን ትምህርት ቤቶች እንዲሁም አድማስ ዩንቨርሲቲ ፊደል የቆጠረባቸው ቀለም የወጋባቸው የእውቀት ገበታዎቹ ሲሆኑ ለዛሬ እሱነቱ ደግሞ ይበልጡን ከልምድና ከንባብ የተገኘ የኑሮ ብልሃት ለሕይወቱ ማጣፈጫ ቅመምነት ጠቅሞታል።

“የከተማ ልጅ እጁ ለስላሳ ነው የሚለው ብሂል እኔን ይሻክረኛልና የሥራ ሞራሌን ለማጠንከር ገና በእድሜዬ ማለዳ ነው አሀዱ ያልኩት” በማለት የሕይወት ገጹን ያስነብበኝ ጀምሯል። “እንጨት ቤት ገብቼ ሥራ እንደጀመርኩ አካባቢ ወላጆቼ ካዩ ምን ይሉኛል? የሚል ፍርሃት ቢያድርብኝም ለተከታዮቼ እህትና ወንድሞቼ ምሳሌ ለመሆን፣ ጥሩ የሥራ ባሕል ለማዳበርና ራሴን ለመቻል የሸበበኝን ፍርሃት አሽቀንጥሬ በመጣል ብርቱ ሞራል መገንባት ችያለሁ” ሲለኝ የታይላንዳውያን በጎ እሳቢያዊ አስተምሮ በሕሊናዬ ሰሌዳ ተሰደረ።

በታይላንድ አውራ ጎዳናዎች ላይ የቡድሃ ሃይማኖት መወከያ ሃውልቶች ቆመዋል። ታዲያ በጊዜ ብዛት እርጅና የተጫናቸውን ሃውልቶች ለማደስና መንገዶችን ለማስፋት ሽተው ሥራ ሲጀምሩ ሃውልቶች ተሰባብረው እምነታቸውም ቅርሳቸውም እክል እንዳይገጥመው አብዝተው ፈሩ፤ ከስንት ጊዜ ማስታመም በኋላ ግንባታውን ሲጀምሩ ከፈራረሰው የሃውልቶች አካል ውስጥ የወርቅ ክምችት አገኙና ፍርሃታቸውን ረገሙት። አንዳንድ ሰው ከወርቅ የጠራ ሃሳብ ተሸክሞ ገና ለገና ወደፊት የሚገጥመውን ፈተና በማሰብ ከመቃብር በላይ የሚውለውን ሕልሙን ያጨነግፋል፤ እንዲህ አይነቱም በሀገርና በትውልድ ግንባታ ላይ የድርሻውን ከማዋጣት ይልቅ ጎታች እምነቶችን በመዝራት ከራሱ አልፎ ለሌላውም የሞራል ጋሬጣ፣ የሥነልቦና እንቅፋት፣ የሕሊና ጠንቅ ይሆናልና የታይላንዳውያን ሕያው ምስክርነት ይገስጻል።

እራት ከቀረበ በኋላ የሚደራው ጨዋታ በናትናኤል መጉደል ደብዝዟል፤ በዚህ ሁኔታው ግራ የተጋቡት አባቱ ማልዶ ከቤት ሲወጣ ተከታተሉትና ሲሚንቶ ሲሸከም አገኙት። የሚፈልገውና የጎደለበት ነገር ካለ በግልጽ እንዲጠይቃቸው አግባብተው ሥራውን ሊያስተውት ቢጥሩም እሱ ግን “ከናንተ የምሻው ጠንካራ የሥራ ባሕል እንጂ የምቀብጥበት ገንዘብ አይደለም” ሲል መለሰላቸውና ቁርጡን ሲያውቁ ጊዮን ሆቴል ባትክልተኛነት እንዲገባ አመቻቹለት።

“እድል ደፋሮችን ትመርጣለች” እንዲል የሮማው ንጉሰ ነገሥት ማርከስ ኦሪሊዬስ ወጣት ናትናኤልም ከሕይወት ጋር ግብግብ መግጠምና ማሸነፍ ሃሴት እንደሚፈጥርለት ይናገራል፤ ይህንንም አድማስ ዩንቨርሲቲ ገብቶ በኮንፒውተር ሳይንስ ሲመረቅ መውጫ ፈተና ውጤት በቀረበት ጊዜ አይቶታል። አሁናሁን የተንሰራፋው “የተማረ የት ደረሰ?” የሚል ፈር የለቀቀ ብሂል ወደኋላ ሳያስቀረው “የተማረ ወድቆ አይወድቅም” ብሎ ዳግመኛ በመፈተን አመርቂ ውጤት አምጥቶ አለፈ፤ ይሁን እንጂ በፈለገው ልክ ሥራ ማግኘት አልቻለም።

“ተመረቅ እንጂ ውለህ ሳታድር ሥራ እናስገባሃለን” ብለው የፎከሩት ወዳጆቹ ሁሉ ቃላቸውን ሊፈጽሙ ይቅርና የግዜር ሰላምታም ነፈጉት። በዚህ ሰዓት የቻይናዊውን የኮንፊሼስን የሕይወት አስተምሮ ከልቦናው በመከተብ ራሱን አበረታና ከነቀፌታ ከበሬታን ከዝቅታ ከፍታን ለመውለድ ጎንበስ አለ።

“በጋራ ተባብረን ያቆምነው ቤት ማእዘኑ ተዛንፎ ከወደቀ ተማሪውም ተማሪ እኔም መምህር አይደለንም” ይላል ኮንፊሼስ በንግግሩ። ናትናኤል ዩ ስትሪት ፓርኪንግ ሥራ ሲጀምር የምን ይሉኛል ፍርሃቱን የበታችነት መንፈሱን አሸንፎ ቢሆንም አንድ ቀን የትምህርት ቤት ጓደኞቹ ሲያዩት ሃፍረት ጠንካራ ሞራሉን ፈተነውና በራስ መተማመኑን ሸረሸረው። ምን ነበር ያጋጠመህ? አልኩት ተስገብግቤ። በዚህ ሁኔታዬ የታዘበኝ ወዳጄ ዮሃንስ “ላንተ እንጀራ ሲባል ሰፊው ሕዝብ ሚስጥር አይኑረው እንዴ?” ያለኝን ተረብ አስታውሼ ፈገግ አልኩ በናትናኤል ገጠመኝ አሳብቤ።

የግላቸውን ካንፓኒ የከፈቱና ኑሯቸውን አውሮፓ ያደረጉ ጓደኞቹ ለእረፍት በመጡበት አጋጣሚ ኤርፖርት ገብቻለሁ ያላቸው ናትናኤልን ፓርኪንግ ሲሠራ አገኙት፤ ድንጋጤው መሬት ተከፍታ ብትውጠው በወደደ ነበር። ሃፍረት አሸማቆት ላብ እያጠመቀው ለናቱ ሲያዋያቸው ሲሠራ እንጂ ሲሰርቅ እንዳልያዙት አስረድተው ከውጫዊ ማንነት ግፊቶች ይልቅ በሕያው ውስጣዊ ምንነቱ ጸንቶ ጠንካራ የሥራ ባሕል ይላበስ ዘንድ ገሰጹት። ከዚያ በኋላስ? አልኩት አሁናዊ ሞራሉን ለመመዘን እየጓጓሁ። “እሳት የጠበሰው ጀበና ፍልቅልቅ ቡና ይጋብዘን የለ፤ እኔም እንደዛው ነኝ” አለኝ ገጹን አፍክቶ። “አንድ ጊዜ ደግሞ ምን ሆነ መሰለህ?” ሲል ሌላኛውን ገጠመኙን ሊያወጋኝ ፈቀደና ቀልቤን ወሰደ። “ቴስላ መኪናውን እያንቸረቸረ መጥቶ ከርቀት አቆመና ክላክስ ሲያደርግ አልሰማሁትም፤ በንዴት ገንፍሎ ስጠራህ አትመጣም? አለኝ። እንዳልሰማሁ ባስረዳው ልንግባባ አልቻልንምና ቀድሜ በመሸነፍ ምን ልረዳው እንደምችል ጠየኩት፤ እሱ ግን የድሃ ድጋፍ አያሻኝም ብሎ ሞራሌን ለማጉደፍ ተጣደፈ። ይህም አልበቃው፤ ንቀቱን ቀጠለ። ክላክስ ሳደርግ ስምህን እየጠራሁ እንደሆነ እንዴት አጣሃው? አለ በምጸት እየሳቀ። የሥራዬ ክፍያ ትግስት በመሆኑ ሳልቆጣ በፍቅር ሳስተናግደው ልብ ገዝቶ ይቅርታ ጠየቀኝ” አለ ናትናኤል ብሩህ ተስፋ ፊቱን እያለበሰው።

ወጣቶችን ከነገ ሕልማቸው ወደኋላ የሚጎትታቸው ትልቁ ችግር ፍርሃት ነውና ምን ትመክራቸዋለህ? አልኩት እሱ ያመለጠበትን ብልሃት እንዲያካፍለኝ ሽቼ። ከሥራ ቦታው ሳይቀር ባገኘው ክፍተት ሁሉ እንደሚያነብ ገልጾ እሱነቱን ያነጹትን ገጾች ገለጠና ሃሳብ አዘገነኝ።

አንድ ገበሬ ነበር አሉ እጅጉን በስንፍናው የሚታወቅ። እግዜር ይመጣና “ስንዴ ዘርተሃል?” ሲል ይጠይቀዋል። ገበሬ ሆዬም “አይዘንብም ብዬ አልዘራሁም” ይላል። “በቆሎስ?” በማለት እግዜር ጥያቄውን አስከተለ። “ተባይ ይበላዋል ብዬ አልዘራሁም” አለ ያው ገበሬ። ሥራው ብቻ ሳይሆን ጸሎቱም የፈሪ እንደሆነ ነግሮ ምኑም ሳይባርክለት እግዜር ተለየው ይባላል። እንዲህና እንዲያ ቢሆንስ? ክፉ ነገር ቢያጋጥመኝስ? በሚል ተልካሻ ሰበብ ቀይደን ከፍርሃት ጀልባ የሰቀልነው ሃሳባችን እንዴት ልጓሙን ሊፈታ ይችላል? ሌላ ጊዜ እንደዚሁ አንድን ሰው እግዜሩ መታዘብ ቻለ።

ሰውዬው የፈረስ ጉግስ ውድድር ለማካሄድ ፈረስ ገዝቶ ቤቱ ሲገባ “ባለም ላይ ፈጣኑ ፈረስ” የሚል ጽሁፍ ከጀርባው ለጥፎ መንደሩን ጉድ አስባለ። መድረስ አይቀርምና ዳኞች ተሰይመው ውድድሩ ሲጀመር በወሬ ሀገሩን የናኘው ስሙ በተግባር ሲገለጥ የሰውዬው ፈረስ መጨረሸኛ ወጣ፤ ገና ሲገዛው ይሆናል አይሆንም የሚለውን መመዘን እንደነበረበት የሳተው የፈረሱ ጌታ ስህተቱን በፈረሱ አለመቻል አላከከና “ለፈረሱ ፈጣን የሆነችበት ዓለም” በሚል ጽሁፍ ተካው።

“ወደተፈጥሮ እንመለስ” በማለት አብዝተው የሚጽፉትና የሚናገሩት ሳድጉሩ ፍርሃት የውድቀት ምኩራብ፣ የመንፈስ ትብታብ፣ የሥነልቦና እዳ፣ የስንፍና ጓዳ እንደሆነ ይናገራሉ። ከዚህ እሳቤ የምንገነዘበው አያሌ ወጣቶችን በቀቢጸ ተስፋ ዳዴ ያስባላቸው በፍርሃት ካቴና የተቀየደ ሞራል የተከናነቡ ጊዜ ነውና ባፍላው ሃግ ያልተባለ የሃሳብ ድህነት እንደ ሕጻንነታችን ዘመን ያገጠጠው ችግር በጅቡ ይበላሃል ተረት ያስፈራራናል።

ናትናኤልን ከሄድኩበት ሰመመን ተመለስኩና ነገ ላይ የት ላግኝህ? ስል የማብቂያ ጥያቄ ሰነዘርኩለት። በልማድ እዚህ ያደረስነውን የፓርኪንግ ሥራ በቴክኖሎጂ ለመደገፍ እየሠራ መሆኑን ሲገልጽልኝ እጹብ ድንቅ በማለት ሃሳቡ ይሰምርለት ዘንድ በመመኘት ጽሁፌን ቋጨሁ።

ገፋ ገፋ አድርገህ ውጣው አቀበቱን፣

ልብ ያሰበው ነገር አይገኝ እለቱን።

አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 22 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You