ጥቁሯ ድቡልቡል የወንዝ ጠጠር ዛሬም እንደወትሮዋ በሐዘን ጭብጥ ኩርምት ብላለች። ምክንያቷ ትላልቆቹ ጥቁር ድንጋዮች ስላበሳጯት ነው። የሚያበሳጯት ዋነኛ ምክንያት ደግሞ ትንሽ በመሆኗ ነው። ኃጢያቷ ሕፃንነቷ ነው። በደሏ እንደነሱ ግዙፍ ድንጋይ አለመሆኗ ነው። እንደነሱ በሰዎች ዘንድ ተፈላጊ አለመሆኗ። ሰዎች ብዙ ጊዜ ትላልቆቹን ነው የሚፈልጓቸው፤ በተለይም ቤት ሊሠሩ ሲፈልጉ፣ መንገድ ሊገነቡ ሲፈልጉ፣ እነሱን ነው የሚፈልጉት። እንጂማ እሷም የድንጋይ ዘር ጠጠር ናት። ለእዚያውም ጥቁር ድቡልቡል። ግን ሁልጊዜ ስለታናሽቷ ስታስብ ደርሶ ክፍት ይላታል። እኔስ መቼ ነው ትልቅ ሆኜ በወገኖቼ ሳልናቅ ተከብሬ የምኖረው ትላለች። መቼ ነው በሰዎች ህልውና ውስጥ የማይሽር አሻራ የማሳርፈው ትላለች። ስለዚህም ሁልጊዜ ለፈጣሪዋ ጸሎቷ እባክህ አምላኬ ጠጠርነቴ ያብቃና ትልቅ ድናጋይ አርገኝ ነው። በህያዋን ፍጥረታት ከሚያስቀናት ነገር መካከል ከተወለዱበት ጊዜ ጀምሮ ማደግ መቻላቸው ነው። እነሱኮ እንደተፈጠሩ ባሉበት እንደድንጋይ እየረገጡ አይቀሩም እያለች ብዙ ጊዜ የአርባ ቀን ዕድሏን ታማርራለች።
አንድ ቀን አንድ የበግ እረኛ መጣና እንደወትሮው በሰዎች የሚፈለጉትን ትላልቅ ጥቋቁር ድንጋዮች ትቶ ከበርካታ ጥቋቁር ጠጠሮች መሀል እሷንና ሌሎች እንደሷ ሚጢጢ የነበሩ አራት ባልንጀሮቿን በመውሰድ ኮረጆው ውስጥ ከቷቸው በመጣበት ፍጥነት ተመልሶ ሄደ።
ትላልቆቹ ጥቋቁር ድጋዮች ይሄን ሲመለከቱ ተንጫጩ። “እኛ ትላልቆቹ እያለን ትናንሾቹ መመረጣቸው የምን አትርሱኝ ነው?” አሉ። በጣም ተበሳጩ። ተቆጡ። “ለካንስ ትናንሽ ጥቁር ድቡልቡል ጠጠሮችም ይፈለጋሉ” ሲሉ አሰቡ።
ሌሎቹ ትናንሽ ጥቁር ድቡልቡል ጠጠሮች ደግሞ አቻዎቻቸው በመመረጣቸው ሐሴት አደረጉ። ጊዜ መጣልን የመፈለጊያችን አሉ።
የተመረጡት አምስት ጥቋቁር ድቡልቡል ጠጠሮች በትንሹ እረኛ ኮረጆ ውስጥ ሆነው ይንሾካሾካሉ።
“ኧረ ጉድ ነው እኛም ለእዚህ ወግ በቃን ማለት ነው?”
“ኧረ በጣም ነው የሚገርመው ለመሆኑ ለምን ይሆን ይሄ እረኛ ግዙፎቹ እያሉ እኛን ደቂቆቹን መምረጡ?”
“እንጃ ምናልባት ቤቱ ወስዶን ከጌጣጌጦቹ እንደ አንዶቹ ሊያረገን ይሆን?”
“አይመስለኝም፤ እኔ እንደሚመስለኝ ይሄ እረኛ ለታላቅ አላማ የመረጠን ይመስለኛል”
“ኡኡቴ ለታላቅ ዓላማ ብሎ ነገር፣ እኛ የምንሠራው ታላቅ ዓላማ ደግሞ ምን የሚሉት ይሆን?”
“ለምን እንደዚያ ልትይ ቻልሽ?”
“ትናንሾች ስለሆንን በምድር ላይ በሰውና እንስሶች እግር ከመረገጥ ውጪ ለምንም ጥቅም የማንሰጥ ከንቱ ፍጡር ነን ብዬ ነው የማስበው” ይሄን ያለችው ሁሌ ስለትንሽነቷ ስታስብ የምትብሰከሰከው ሚጢጢዋ ጥቁር ጠጠር ነበረች።
በእዚህ መሀል የእረኛው እጅ ኮረጆ ውስጥ ገባና ከአምስቱ ድንጋዮች መርጦ ያቺ ሁሌ በትንሽነቷ ሀፍረት የሚሰማትን ድቡልቡል ጠጠር መርጦ ወሰዳት።
አራቱ ጓደኞቿ ኮረጆ ውስጥ ሆነው፣
“የሚገርም ነው ከኛ ተመርጣ ተወሰደች ዝም ብላ ዕድሏን ስትረግም እንዳልነበረ ሁሉ”
“ለምን ይሆን ከኛ ተለይታ መመረጧ ግን?”
“ምናልባት የድንጋዮች አምላክ ትንሽነቷ ታላቅነቷ እንደሆነ ሊያስተምራት ይሆን?”
እረኛው ትንሿን ጥቁር ድቡልቡል ጠጠር በጣቶቹ ውስጥ ካመቻቸ በኋላ ወንጪፉ ውስጥ ከተታትና፣ ወንጩፉን ሶስት ጊዜ በጭንቅላቱ ላይ አሽከርክሮ ሲወነጭፈው ትንሿ ጥቁር ድቡልቡል የወንዝ ጠጠር አየሩን እየቀዘፈች ትበር ጀመር።
እንዲህ አይነት በረራ ስታደርግ ለመጀመሪያ ጊዜዋ ነበር። በሕይወቷ አልማም ሆነ አስባ የማታውቀው በረራ ነው። ለካንስ ትንሽ ድንጋይም በአየር ላይ መብረር ይችላል ስትል ላፍታ አሰበች። ከፊት ለፊቷ ከላይ እስከታች ብረት የለበሰ፣ ብረት ያነገተ ግዙፍ ጦረኛ ሰውዬ ጦሩን እየሰበቀ በሷ አቅጣጫ ይሮጣል። ከትንሹ እረኛ ሊፋለም እንደሆነ ደመ-ጠጠር ነፍሷ ነገራት።
ያምሆኖ ትንሹ እረኛ ባልንጀሮቿ እንደገመቱት ለትልቅ ዓላማ መርጧት እንደነበረ ዘግይቶም ቢሆን የገባት አሁን ነው። በእሷ አማካይነት የጃዊሳውን ጎልያድ ነፍስያ መንጠቅ። ትልቁ ዓላማ ይሄ ነበር። ባለ በሌለ ኃይሉ እየገሠገሠ የነበረው ግዙፉ ሰው እሷ ደርሳ ግንባሩ ውስጥ ስትቀረቀር ፈጣኑ ሩጫው ተገታ። ያን የሚያህል የሰማይ ስባሪ፣ የገደል ቅራፊ የሚያህል ጦረኛ ጀግናን ትንሿ ጥቁር ድቡልቡል ጠጠር ከአፈር አደባየችው።
ከተቀረቀረችበት ግንባርም ውስጥ ሆና አሁን ለምን እንደተፈጠረች ገባት። አሁን ከእዚህ በኋላ ማንም ትልቅ ጥቁር ድንጋይ ከመሬት ተነስቶ እንደማይነቃት ገባት። ዋናው ቁምነገር በአካል መግዘፍና ማነስ ሳይሆን ምስጢሩ ሙያ መሆኑ ገባት። በመጨረሻም በትንሽ እሷነቷ ግዙፍ ነገር ያደረገውን አምላኳን አመሰገነች ከጎልያድ ግንባር ውስጥ እንዳለች። ከእዚያም በኋላ ነው እንግዲህ የጸሎት ርእሷን በመቀየር፣ “እባክህ አምላኬ ትልቅ ድንጋይ አርገኝ ሳይሆን በእኔ በትንሿ ትልቅ ሥራ ሥራብኝ” ማለት እንደሆነ የተገነዘበችው።
(ዳዊት ወርቁ ግንቦት 16፣2006 አዲስ አበባ)
አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 22 ቀን 2017 ዓ.ም