
እኛም አለን ጨዋታ
ስልቱ ትጥቅ የሚያስፈታ።
እኛም አለን ሙዚቃ
ወይሳ ከቅዱ ለጥበብ ጣቃ።
ዓይነት ግሩም ጥበብ ይወዳሉ፤ ወይሳን የፈጠሩ አሪዎቹ። ከሰማዩ እንብርት ውስጥ አንገቷን ያሰገገችን ፀሐይ በጥበባቸው ማሞቅን ያውቁበታል። ወደ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያዊቷ አሪ ጎራ ላለ የጥበብ ፈገግታው ከፀሐይም የላቀ ነው። ይህችኑ ፀሐይ እየሞቁ፣ በባሕላቸው ውስጥ ተወልደው ያደጉ ጥበባት እልፍ ናቸው። አድገው ወግ ማዕረግን ያዩ ግን ከተወለዱት አንጻር ጥቂቶች ናቸው። ጥቂቶቹም ዛሬ ላይ ይኖራሉ ብለን ከምንገምታቸው በላይ ናቸው። ከእነዚህ መካከልም ሙዚቃዊ የባሕል ጨዋታዎቻቸው አንደኛዎቹ የማንነት ዘውጎቻቸው ናቸው። ቤሪ፣ አሽካ፣ አላ እና ወይሳ ከፊት ተጠቃሽ ናቸው። ለዛሬው ግን፤ በዚህች ጽሁፋ ጫፏን ካልሆነ በስተቀር ዳሰን የማንደርስባትን ወይሳን ከሰባቱ የዜማ ላምባዎቿ ጋር ልንከተላት እንሞክራለን።
‹ወይሳ› በአሪ ማሕበረሰብ ዘንድ እራት፣ ቁርስ፣ ምሳ የምትቀርብ ባሕላዊ የትንፋሽ ሙዚቃ መሣሪያ ናት። ይህቺኑ የትንፋሽ ሙዚቃ መሣሪያ ለመተዋወቅና ተዋውቆ ከወጉ ለመቋጠር፣ የአሪ ዞን ዋና ከተማ በሆነችው ጂንካ ላይ ከሚገኘው የባሕል ኪነት ቡድን ዘንድ መድረስ አስፈላጊ ነበር። እናም ወይሳን በመጫወት ብቻ ሳይሆን፣ ዙሪያ ገባዋን አበጥሮ በማወቅ ምስጉን ነው የተባለውን አንድ ወጣት አገኘሁት። በኪነት ቡድን ውስጥ ፊታውራሪና የትንፋሽ ሙዚቃ ተጫዋች የሆነው ስዩም ሹዑና ስለ ወይሳ ካወጋኝ ብዙ መካከል ጥቂቱን ልከትበው ተነሳሁ።
አሪዎች ባሕላቸውን ከጥበብ አዛምደውና አጋምደው “ወይሳ” ያሉትን የትንፋሽ ሙዚቃ መሣሪያን ለማበጀት ሲያስቡ የግኝት ዓይኖቻቸውን ያሳረፉት ቀርክሃ ላይ ነበር። በአካባቢያቸው የሚገኙ የቀርክሃ ዝርያዎች 10 ቢሆኑም፤ ሙዚቃዊ ቀመራቸውን ያሰሉት ግን “ማሃ” እና “ሃላ” በተሰኙት ሁለቱ ላይ ብቻ ነው። ታዲያ “ወይሳ” ብለው የሚጠሩት ጥበባዊ ግኝታቸው በጥቅል ስሙ እንጂ ከስሙ ስምን፣ ከጥበቡ ጥበብን ነስተው የቆሙ መልኮቹ ሰባት ናቸው።
ክራር፣ መሰንቆ፣ በገና፣ ዋሽንትና ሌላውም በተናጠል ቢጫወቷቸው ሙዚቃዊ ናርዶስ አላቸው። በጊታር የሚያዜመውን ድምጽ መስማት ደስ የሚያሰኝ ነው። የፒያኖ ኮርዶችን ተጭነው ለስለስ ያለ ረቂቅ ሙዚቃ ቢጫወቱ ጆሮና ልብ ይፈስሃሉ። የኪቦርድ ሪይትሞችና የድራም ምቶች ኳ! ከሽ! ባሉ ቁጥር ሁሉ አንድ ድንቅ ሙዚቃ ልንሰማ እንችላለን። ድንቅ የሙዚቃ ጥበብም ልንመለከት እንችላለን። ከምንም በላይ የሆነውን የሙዚቃ ጥበብ ግን፤ እነዚህን ልዩ ልዩ የሙዚቃ መሣሪያዎች አንድ ላይ አሰልፎ በማጣጣሙ ውስጥ ነው። ወይሳዎች ሁሉም በተናጠል የሚሾሩት ሙዚቃዊ ጨዋታ ሲኖራቸው፣ ፍጹም በተለየ መልኩ አስገራሚ የሙዚቃ ዓለም የሚፈጥሩበት ሌላ ዓይነት ውበት ደግሞ አላቸው። ትንንሽ ውበቶች ተዋህደው፣ አንድ የትልቅ ውበት ግንባር ይፈጥራሉ። ሰባቱንም ወይሳዎችን አንድ በአንድ በመጫወትና ሰባቱንም እንደ አንድ አድርጎ በመጫወት መካከል ትልቅ ልዩነት፣ ፍጹም የተለየ ሙዚቃዊ ስልትና ጨዋታ አላቸው። “አንድ ላይ ሲጋጩ ጥሩ መልዕክት ያለውን ዜማ ይፈጥራሉ” አለ ስዩም። ልክ የተለያዩ ቃላት የየራሳቸውን ልዩነት ይዘው አንድ ወጥ ትርጉም ያለውን ቆንጆ ዐረፍተ ነገር እንደሚሠሩት ዓይነት ነው።
ባለ ወይሳው ስዩም ሹዑና፤ ከሰባቱ መሃከል ትንሽየዋን ዋሽንት የመሰለችዋን መዞ ከአፉ ሊነደግናት ሲል “ማን ትባላለች?” አልኩት። “ቲቲ” አለኝ በትንፋሹ እያሽኮረመማት። የትንሽዋ ቲቲ ድምጽ ልክ እንደ ወፍራም ዋሽንት ነበር። እንዳላት ቅጥነት ድምጽዋም በቀጭኑ የሚቅጨለጨል ይሆናል ብዬ ብጠብቅም፤ ድምጽዋ ከራሷ የሚገዝፍ ነው። ስዩም ሁለተኛውን ወይሳ ጨብጦ “ይቺ ደግሞ ‹ኤላ› ወይንም ‹ጸተ› ነው የምትባለው” ካለኝ በኋላ ልክ እንደመጀመሪያው ሁሉ በትንፋሹ አናዘዛት። ድምጽዋ ከቲቲ ጋር የሚመሳሰል ቢመስልም፤ ግን ኤላ ረዘም ባለ ትንፋሽ የተለየ የምታዜም ናት። ቀጥሎ “ዶካ” የምትባለዋን ዝግዛግ እያባባለ ከተጫወታት በኋላ፤ በሌላ ስሟ “ውሪ” ተብላ እንደምትጠራ ነገረኝ። ዶካ ዜማ ብቻ ሳይሆን ምትም እንዳላት ስገነዘብ፣ ስዩም መጀመሪያ ላይ “ሰባቱም ድምጾች አንድ ላይ ሲሆኑ ሙሉ ናቸው” ያላት ነገር ትዝ አለችኝ። እስካሁን ሲጫወታቸው የነበሩትን የሦስቱንም ድምጾች ለማስታወስ ስሞክር፣ የስዩም አባባል ግልጽ ሆነለኝ።
አሪዎች በወይሳ ውስጥ የደረሱበት፣ ግን በአንደበታቸው ያልገለጡት አንድ የሙዚቃ ቀመር ጥንቱን የገባቸው ነገር ነበር፤ በዘመናዊው ሙዚቃ ውስጥ ሪትም፣ ምት፣ ስልት…ስለምንላቸውና ስለሌላውም። ሰባቱን የወይሳ ጥንቅሾች አፋቸው ላይ ደግነው ሙዚቃን መጫወት የጀመሩት ዛሬ ሳይሆን፣ ገና ያኔ የዘመናዊ ሙዚቃ ሳይጸነስና ስለ ምትና ስልት ሳይታወቅ በፊት ነበር። ስለ እነዚህ ሁለት ነገሮች ሳይንሱን ባይገልጡትም፤ ድምጾችን አሰባጥሮ ስልትና ምት የመፍጠርን ጥበባዊ ቀመር ግን አግኝተውት ነበር። ኋላ ሰባቱም ወይሳዎች መድረክ ላይ ቆመው አንድ ዓይነት ስልትና ምት ያለውን ወጥ መሳይ ሙዚቃ ሲያሰሙ፣ ሁሉም እርግጥ ሆነ። የወይሳ ተጫዋቹ ስዩም ግን ቀጣዩን ድምጽ የመሸጋገሪያ ነው ሲል ጨዋታውን ቀጠለ።
አራተኛው የጨዋታ ስልት ቀያሪ ማኢ (በሽም) ነው። ማኢ ሁል ጊዜም በሰባቱ መካከል ሆኖ ከአንድ የጨዋታ ዓይነት ወደሌላኛው መሸጋገሪያነት የሚያገለግል ዘዋሪ ነው። በዘመናዊው ሙዚቃ ውስጥ ‹ብሪጅ› ከምንለው ጋር በተወሰነ መልኩ ተመሳሳይነት አላቸው። በአንድ ሕብረ ዝማሬ ውስጥ ሁሉም ድምጾች የሙዚቃውን ፍሰት ጠብቀው በእኩል እንዲሄዱ ከፊት እንደሚዘውራቸው የኳየሩ መሪ ነው። በአምስተኛነት ተሰልፎ የሚከተለው ወይሳ ዱኢ ነው። የሚሰጠው ድምጽ ከዘመናዊው ‹ፍሉት› ጋር መንታ ያስመስለዋል። ሲጫወቱት ለስለስ ብሎ ይንቆረቆራል። ከማናቸውም በላይ የትንፋሽ እርጋታ የሚያስፈልገውና የሚያወጣውም ድምጽ ሰክኖ ቀዝቀዝ የሚያደርግ ነው። ምናልባት ምቱን በባር ልኬት ብናስቀምጠው ወደ ‹ዋልትዝ› የሚወስድ ነው። ሞቅ ካለው የጭፈራ ስልት ይልቅ፤ እንደ ትዝታ ባሉ ሙዚቃዎች ውስጥ ይበልጥ ጎልቶ መውጣት የሚችል ነው።
ኩልዲ (ባቤ) የተሰኘው ስድስተኛው የወይሳ ዓይነት ‹ትራምፔት› መሳይ ነው። ድምጹ ወፍራምና ጉልበት ያለው ነው። ባቤን ለመጫወት ግን ኃይለኛ ግፊት ካለው የትንፋሽ አወጣጥ ይልቅ፤ በቀላሉ በብልሃት የሚለኮስ ስልት ነው። ስልት ብቻ ሳይሆን ምትም የሚሰጥ ነው። ከላይ ያነሳነው የዘመናዊው ሙዚቃ ‹ሪትም› ከእዚህ ጋር እንድናመሳስላቸው ያስገድደናል። በአንድ ባንድ ውስጥ ሪይትሙን የሚመራው ፊታውራሪ ኪቦርዲስቱ ነው። የጨዋታውን ዓይነትና ምት ተከትለው ሌሎቹ ይከተሉታል። አራተኛውን መሃከለኛው ማኢ ምልክት በሰጠበት ቅጽበት ኩልዲ የምት ምጣኔውን ሰፍሮ ስልቱን እየሰጠ የሪትምን ዓይነት ሚና ይጫወታል። የኩልዲ ‹ቴምፖ› ፍጥነቱ እየጨመረ በሄደ ቁጥር ጨዋታው እየደራ ይሄዳል። ለምሳሌ ኪቦርዲስቱ የሚጫወተው ‹ዋልትዝ› ከሆነ በአብዛኛው ቴምፖው ከ90-120 ነው። በዚህም የምት ፍጥነት የወሎን ሊጫወት አይችልም። ስለዚህ የሪትሙን ቴምፖ ወደ 180 ገደማ ከፍ ማድረግ ይኖርበታል። ኩልዲን ተጫዋችም እኚህን መሰል የልምድ ቀመሮችን እያሳለጠ ሙዚቃውን ከጭፈራው ጋር አዋዶ ጨዋታውን ይመጥነዋል። ሰባተኛውን የመጨረሻው ወይሳ “ዳኢ” ይሉታል። ዳኢ ጨዋታው መሃል ከፍ ዝቅ እያለ ምቱን ጠብቆ ዝግዛግ እየመታ ሄዶ ‹ባር› ላይ ያርፋል። ከባር ተነስቶ አግድም፣ እንደገና ሰያፍ፣ ሲያስፈልገው ሽቅብ እየወጣ ተመልሶ ‹ባር› ላይ ያርፋል። በሌሎቹ ድምጾች ላይ እየተደረበ ደስ የሚል የሙዚቃ ጣዕም እንዲፈጠር ያደርጋል። የድምጻዊውን ዜማ፣ የመሣሪያ ተጫዋቾቹን የአጨዋወት ስልት፣ ምቱንና ባሩን እየጠበቀ፤ አገባቡ በትክክኛው ቦታና መስመር ላይ ካልሆነ አፈንግጦ የሚረብሽ ስሜት ሊፈጥርም ይችላልና የዳኢ ተጫዋች ሁሉንም አካሄዶች ጠንቅቆ ማወቅ ይኖርበታል። አሪዎች በወይሳ ሙዚቃ ጥበባቸው ውስጥ ይህን ሁሉ ረቂቅ የባሕል ሙዚቃ ጨዋታቸው ሕገ ደንብ አድርገው ባያሰፍሩትም፤ ግን ሲከውኑት የምንመለከተው ይህንኑ ነው። የአሪዎች ጥበብና የወይሳ ጨዋታ ከፍታው እዚህ ላይ አይገታም።
ወጣቱ የባሕል ሙዚቃ ተጫዋች፣ ስለ አሪ ወይሳ ሲያጫውተኝ ከሀሳቤ ውስጥ ስትመላለስ የቆየችውን አንዲት ጥያቄ በስተመጨረሻ ሰነዘርኩለት።
“ስለ ደራሼዎቹ ሎላትና ፊላ ታውቃለህ?”
“አዎን አውቃቸዋለሁ” አለኝ።
በመጀመሪያው ጥያቄ ተንደርድሬ “የናንተ ወይሳ እና የደራሼዎቹ ሎላትና ፊላ የሚመሳሰሉ ብዙ ነገሮች አሏቸውና አንድ ናቸው?” አልኩት፤ ምናልባት ሁለቱንም ያስተሳሰረች አንዲት ቀጭን ክር ያለች ትኖር እንደሆን በማለት። “በጭራሽ አንድ አይደሉም። ማሕበረሰቦቹም ሆኑ የሙዚቃ መሣሪያዎቹ የተለያዩ ናቸው። በቁጥር ደረጃ ብንመለከታቸው እንኳን የእኛ ወይሳ ሰባት ሲሆን የእነርሱ ወደ 20 ይደርሳል። የምንጫወትበት መንገድም የተለያየ ነው” የሚል ምላሹን ሰጠኝ። በእርግጥም በአጨዋወታቸው ብቻ ሳይሆን፤ በአሠራራቸውም የተለያዩ ናቸው። ደራሼዎች ፊላና ሎላትን ለማበጀት የሚጠቀሙት የአጋም እንጨት አሊያም የሳለ ቀንድ ነው፤ አሪዎቹ ደግሞ ወይሳን የሚቀርጹት ከሸንበቆ ነው። ሁለቱም ማሕበረሰብ የሙዚቃ መሣሪያዎቻቸውን የቃኙት ከራሳቸው ልማድና የአኗኗር ስልት ውስጥ ቢሆንም፤ በስጋና መንፈስ ኢትዮጵያዊ ናቸውና አብረው የተጋሯቸው ሙዚቃዊ የጥበብ እንክብሎች ስለመኖራቸውም ማጤን እንችላለን።
ለምሳሌ፤ በአሪዎች የወይሳ ጨዋታ ውስጥ ስልትና ማርሽ ቀያሪው፣ ከሰባቱ አንዱ የሆነው ‹ማኢ› ነው። ወደ ደራሼዎቹ የፊላ ጨዋታ ስናመራ ደግሞ ‹ሎላት› በተመሳሳይ መልኩ መውጫና መግቢያውን ቀያሽ ዘዋሪ ነው። ነገር ግን በግብር አንድ ይሁኑ እንጂ፤ በድምጽ የተለያዩ ናቸው። ወይሳ እና ፊላ፣ ሁለቱም በቁጥርና ግዝፈታቸው የየራሳቸውን ባሕሪያት የያዙ ቢሆኑም፤ ሙሉ ስብስባቸውን አሰልፈው አንድ ላይ በሚቆሙበት ጊዜ፣ ሕብር የሙዚቃ ችቦዎቻቸውን ለማብራት የሚጠቀሙት ተመሳሳይ ጥበብ እንዳለ እንገነዘባለን። እኚህንና ሌሎች ስልታዊ አጨዋወቶቻቸውን ስንመለከትም አንድ በውል ያልተረዳነው ነገር እንዳለ የሚያሳይ ነው። ዘመናዊውን የሙዚቃ ዓለም ስንመለከት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሁሉንም አስማምቶ የሚሄድበት ቋንቋ ያለው ነው። ልክ እንደዚሁ፣ ከእያንዳንዱ የባሕል ሙዚቃ ጨዋታዎችን ዘረመል በመውሰድና በብልት ብልቱ በማገጣጠም አንድ ወጥ የሆነን ኢትዮጵያዊ የባሕል ሙዚቃ ዘውግ መፍጠር እንደምንችል ጠቋሚ ነው። እያንዳንዱ ማሕበረሰብ በግል ካለው የሙዚቃ ጥበብ ጎን፤ እንደ ሀገር ሁሉንም የሚወክል አንድ ወጥ ስልትና ቀመር መፍጠር ከቻልን፣ የባእዳኑን ዘመናዊነት በባሕል ዝማኔ ሽረን መልካችንን ባገኘነው ነበር። በአንድነት እንጂ በግለኝነት ውስጥ ላልተጻፈልን ለኛ፣ በዓለም አቀፉ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ከፍ ለማለቱም ቢሆን እየሄድን ካለንበት የተሻለ ፍኖት ነው።
ሰባቱ ጦማሮች አንድ ላይ ሲፈቱ የሚፈጥሯቸው ዓለማት ልዩ ልዩ ናቸው። ከሰባቱ ውህደት ውስጥ ያወጡት ግዙፍ ጥበብ አንድ ብቻ አይደለም። የተለያየ ቅርጽና ቀለም ሰጥተው በጊዜ፣ በቦታ፣ በሁኔታ ከፋፍለውታል። ሰባቱ የሙዚቃ አዕዋፋት በአዘቦትና በክብረ በዓላት የሚዘምሩት ዝማሬ፣ የሚያዜሙት አዛዚያም አንድ ዓይነት አይደለም። አሪዎች የተፈጥሮን ዱካ እየተከተሉ ለእርሻ ወደ ማሳቸው ሲወርዱ፣ ሠርግ ሰርገው ቤተሰብ ወዳጅ ዘመዶቻቸውን ሲድሩ፣ በዓመት አንድ ቀን ብቅ ብለው የሚሄዱትን በዓላትን ሲያስተናግዱ፣ ከሩቅ ሀገር የመጣውን ሲቀበሉ…ለእያንዳንዱ መስተጋብሮቻቸው የራሳቸው የሆነ አጨዋወትና አቀራረብ አላቸው። የባሕል ኪነት ቡድኑ አውራም ጨዋታዊ ጥበብ ነገራውን እዚሁ ላይ አሳረፈው።
ከእነዚሁ ክዋኔዎች ውስጥ አንደኛው ፍጮይሳ (ጎዲሳ) የሚባለው ሥርዓት ሲሆን በዓይነትና መልኩ ‹የቅበላ ወይሳ› ብለን ልንጠራው እንችላለን። በአብዛኛው ማኅበረሰባችን ዘንድ በዋናነት ተጠቃሽ ሊደረጉ የሚችሉ የባሕል ክዋኔዎች ሁለት ናቸው፤ የደስታ ወይንም የሀዘን። የአሪዎቹ ፍጮይሳም በደስታ ጊዜ ብቻ የሚከወን ትውፊታዊ ጨዋታ ነው።
አሪዎች ደስታቸውን እያጣጣሙ ለመዝናናት ብቻ ሳይሆን፤ ሀዘናቸውን ረስተው ለመጽናናትም የወይሳን ሙዚቃዊ ሸማ ይለብሳሉ። “አንድ ሰው ከሞተ በኋላ በዓመቱ እንደ ተስካር ያለ ሥነ ሥርዓት ይፈጸምለታል። የሟች ቤተሰብ አዲስ ልብስ ገዝቶ፣ ጸጉሩን ተላጭቶ… የሞተው ሰው ከእንግዲህ አይመጣምና ቀድሞ የነበረውን ሕይወት እንደ አዲስ ለመጀመር ይዘጋጃል። በዚህ ክዋኔ ላይ ቤተሰቡን ለማጽናናት ከሚደረጉ ነገሮች አንደኛው የወይሳ ጨዋታ ነው። የሚጀምረውም በፍጮይሳ ነው። አስቀድሞ ፍጮይሳ ሳይጫወቱ ሌሎች የወይሳ ጨዋታዎችን ማድረግ አይቻልም” በማለት ስዩም ሁኔታውን ያወጋል።
የአሪዎችን ጥበብ እንድናደንቅ ግድ የሚያስብለን ሌላኛው ነገር የሙዚቃና የጨዋታ ልኬታቸው እኩል መሆኑ ነው። ለሰባቱም የሙዚቃ ስልቶች፣ ሰባት የጨዋታ ዓይነቶች አሏቸው። ሰባቱ የወይሳ ላምባዎች አንድ ላይ በርተው ከሚፈጥሯት አንዲት ጨረቃ ባሻገር፣ እንደክዋክብት በተናጠል እየተወረወሩ የራሳቸውን ሰባት የጨዋታ ዘዬ ፈጥረዋል። አንደኛውም ፍጮይሳ ነው። ሁለተኛው ደግሞ ‹ሃላ› ሲሆን ይህም በእርሻም ሆነ በሌላ ሥራ ውስጥ ሆነው በግልና በደቦ የሚጫወቱት ነው። ቀሪዎቹም ባማይሳክ፣ አንዱላ፣ ሙራ፣ ጉዳሜላ፣ እና ጎጎይሳ ናቸው። የመጨረሻዋ ‹ጎጎይሳ› ግን አንጀት የምትበላ፣ በፍቅርና በስንብት ስሜቶች በልብ ውስጥ የምትንቦራጨቅ ናት። ስዩም ግን “በጉዞም ሆነ በሌላ ምክንያት ተለያይተውና ተራርቀው የሚቆዩበት አጋጣሚ ሲመጣ፣ ለስንብት ጎጎይሳን ይጫወታሉ። ጎጎይሳ ሁሉን ጨርሶ በደህና ቆዩ የማለት መሰነባበቻ ናት” በማለት ነው የሚገልጻት።
‹እኔስ መሄዴ ነው በደህና ሰንብቱ
መለያየት ሞት ነው የእንባ ነው ዥረቱ› ምናልባትም ግጥሙ እንዲህ ነው። ለባሕል ሙዚቀኛው ስዩም ሹዑና አንዲት ጥያቄ፤ በሚሠራበት የአሪ ኪነት ቡድን ውስጥ ባሕላዊውን ወይሳን ብቻ ወይንስ የዘመናዊ ሙዚቃ መሣሪያዎችንም ትጠቀማላችሁ? “ኪቦርድ፣ ጊታርና ሌሎችም ዘመናዊ የሙዚቃ መሣሪያዎችን እንጠቀማለን። ” ታዲያ ግን እንዴት? “በብዛት የምንጠቀመው ዘመናዊውንና ባሕላዊውን አንድ ላይ በማጣመር ነው” አለ። ከዘመናዊው ሳይጎራበጡ፣ ባሕላዊውንም ሳይበርዙ ድንቅ በሆነ መልኩ እያረቁ ይከውኑታል።
አሪዎቹ ግን ‹ሌላም አለን ጨዋታ…› ማለትን አያቋርጡም። ሰዓታት ቀናትን፣ ቀናት ሳምንታትን፣ ሳምንታት ወራትን፣ ወራትም ዓመታትን እየተኩ በሄዱ ቁጥር ሁሉ በአሪዎች ሙዚቃዊ ጨዋታ ውስጥ አንዲት ‹ባር› አለች። የስልት ምቱን ጠብቀው ከፍ ዝቅ፣ አግድም ሰያፍ፣ ዝግዛግ እየመቱ ያቺው ‹ባር› ላይ ያርፋሉ። ኃይላቸውን አድሰው እንደገና ተነስተው ይቀጥላሉ። ያቺ ባር የእነርሱ ‹ዲሽታጊና› ናት። ዲሽታጊናም ከዚያ ከምናውቀው ሙዚቃ ባሻገር የአሪዎች የዘመን መለወጫ ነው። ወይሳዎች አብዮት አፈንድተው፣ ሀገር ምድሩን በሙዚቃ ድብልቅልቁን የሚያወጡት ከየትኛውም ጊዜ ዲሽታጊና ላይ ነው። በ365 ቀናት ምት፣ 360 ዲግሪ አክብቦ የጊዜ ባሩ ዲሽታጊና ላይ ሲያርፍ፣ አሪዎችም የወይሳ ጨዋታቸውን ቴምፖ ጡዘቱ ላይ ያደርሱታል። ጨዋታቸው አያልቅም። እንደገና ባለ አውታሩን ይከረክሩታል። እንደገና ክራር መሳዩን አሽካን ይቀጥላሉ….
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 21 ቀን 2017 ዓ.ም